Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ከዕውቀት እስከ ሕይወት ክህሎት

ዋርካ አካዴሚ ከትምህርት አመራርና ፔዳጎጂ፣ ከሳይኮሎጂ፣ ከዓለም አቀፍ ኪነ ጥበብ፣ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ከባንኪንግና ዓለም አቀፍ ፋይናንስ አመራር ሙያዎች በተውጣጡ ባለሙያዎች የተቋቋመ የትምህርት ተቋም ነው፡፡ በአገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ የትምህርት ተቋማት ጋር ትብብር በመፍጠር ተጨማሪ እሴቶችን መሰብሰብም የዕቅዱ አንድ አካል እንደሆነ ተቋሙ የትምህርት ዘርፉን በይፋ መቀላቀሉን አስመልክቶ ከሳምንት በፊት ባዘጋጀው መድረክ ገልጿል፡፡ አካዴሚው ደቬንቸር ከተሰኘ በስዊዘርላንድ ከሚገኝ ተቋም ጋር ስምምነት ያደረገ ሲሆን፣ ደቬንቸር ለዋርካ መምህራን የበይነመረብ (ኦንላይን) ሥልጠናዎችን ለመስጠት፣ በተፈለገው መስክ አማካሪ ባለሙያዎችን ለማቅረብና ወደፊትም ፈቃደኛ መምህራንን ወደ ዋርካ አካዴሚ ማምጣትና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ተስማምቷል፡፡ ታምራት ሙሉጌታ (ዶ/ር) የዋርካ አካዴሚ የቦርድ ሰብሳቢ ናቸው፡፡ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ትምህርት ቤት በከፈታችሁበት ኮተቤ ካራ አካባቢ በርካታ ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ ምን የተለየ ነገር ይዛችሁ ነው በትምህርቱ ዘርፍ የገባችሁት?

ታምራት (ዶ/ር)፡- የዋርካ አካዴሚን ሐሳብ እንድናነሳ ያደረገን ቁጭት ነው፡፡ በርካታ የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ እኛ ትምህርት ቤት የከፈትንበት ኮተቤ ካራ አካባቢ እንኳን በኪሎ ሜትር ስፋት ውስጥ በርካታ ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ እኛ ዋርካ አካዴሚን የከፈትነው ሁለት ነገሮችን አስበን ነው፡፡ አንደኛው እኛ ልጆቻችንን ስናስተምር፣ እኛም ስንማር፣ እኛም በተለያየ አጋጣሚ ስናስተምር በትምህርት ቤቶች ውስጥ ያየናቸው ክፍተቶች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ክፍተቶቹ ምንድን ናቸው?

ታምራት (ዶ/ር)፡- ሰዎች ትምህርትን ከዕውቀት ጋር ብቻ ያያይዙታል፡፡ ነገር ግን ትምህርት ዕውቀት ብቻ አይደለም፡፡ የትምህርት ፍልስፍና ሦስት ነገሮችን ያካትታል፡፡ የመጀመሪያው ኮግኒቲቭ ዶሜን ከዕውቀት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሁለተኛው ሳይኮሞተር ዶሜን ከክህሎት ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ሦስተኛው አፌክቲቭ ዶሜን ከአመለካከትና ከስሜት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በተጨማሪ የተግባቦት ወይም የሕይወት ክህሎት አለ፡፡ ይህንን ይዘን ልጆቻችን ምን ላይ ነው ያሉት? ስንል ዕውቀት ተኮርና ንድፈ ሐሳብ ተኮር ትምህርት የሚሸመድዱ፣ ገልብጠው የማያስቡ፣ የማይጠይቁ፣ የተሰጣቸውን ነገር ብቻ የሚቀበሉ ሁነዋል፡፡ 14 ትምህርት እያስተማርን ይህንን ብቻ እየያዙ መጨረሻ ላይ ሦስት በመቶ አለፈ ይባላል፡፡ የዚህ መነሻው ከትምህርት አሰጣጥ ጋር ያለ ክፍተትና እንዲሸመድዱ መደረጉ ነው፡፡ ትምህርቱን የራሳቸው እንዲያደርጉ፣ እንዲያሰርፁ፣ ወደ ተግባር እንዲቀይሩ ተደርጎ ባለመሠራቱ ነው፡፡ ይህንን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ እኛም ከዕይታችን ተረድተናል፡፡ ይህ የራሳችንን ትምህርት ቤት ለመክፈታችን እንዱ መነሻችን ነው፡፡ ሁለተኛው የራሳችን ፍልስፍና ነው፡፡ አገርን መቀየር ከፈለግን በትምህርት ነው፡፡ አሁን እየመጣና እያደረገ ያለው ትውልድ እሴቱና መከባበሩ የላላ፣ የአገሩን ትቶ በውጭ ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ ሉዓላዊነት መሆን ችግር ባይሆንም፣ መሠረት የሌለው፣ እግር ያልረገጠ፣ የውጭውን መመኘትና ቴክኖሎጂ ላይ ብቻ ያተኮረ፣ አንድ ሲደመር አንድ ሲባል የሥሌት መሥሪያ የሚይዝ ትውልድ እየመጣ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን እንዴት እንቀይረዋለን?

ታምራት (ዶ/ር)፡- ልጆች ትምህርትን ሲማሩ አንደኛ ዕውቀትን ከተግባር ልምምድ ጋር፣ ሁለተኛ ከአመለካከትና ተግባቦት ጋር እንዲሁም ሦስተኛ መማርን ከመውደድና ዘላቂ ተማሪዎች ከመሆን ጋር የሚለውን ፍልስፍና ማስረጽ አለብን፡፡ እኛም ይህንን ይዘን ነው የተነሳነው፡፡ በአካዴሚው የተሰባሰብነው ከትምህርት ዘርፍ የመጣን ነን፡፡ ብዙ ትኩረታችን ገንዘብ ማግኘቱ ላይ ሳይሆን በትምህርታችን ፍልስፍና ብቁና ጥራት ያለው ትምህርት ያገኘ ትውልድ ማፍራት ነው፡፡ አገሩን የሚወድ፣ የሚቆረቆር፣ ራሱን የሚሆን፣ አካባቢውን የሚያውቅና ጥሩ ማኅበራዊ ተግባቦት ክህሎት አዳብሮ ስብዕናው የተገነባ ትውልድ ማፍራት ነው፡፡ ብዙዎቻችን ልጆቻችን ጎበዝ ተማሪዎች እንዲሆኑ እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን ማኅበራዊ ክህሎት የሌላቸው፣ በቀላሉ አብስለው መብላት የሚቸግራቸው፣ አካባቢያቸውን የማይረዱ ይሆናሉ፡፡ በመሆኑም ዕውቀት ብቻ ሳይሆን የሕይወት ክህሎት ያላቸው እንዲሆኑ የሚያስችል የመማር ፍልስፍና ይዘን ነው የተነሳው፡፡ ይህንን ስንል መነሻችን የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ነው፡፡ እሱን ወደ ተግባር የሚለውጥ ፍልስፍና ይዘን ነው የተነሳነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፍልስፍናውና ጥናቱ በወረቀት ደረጃ አለ፡፡ ነገር ግን ትግበራው ፈታኝ ነው፡፡ በተለይ በዚሁ መንገድ የመጣ መምህር ማግኘት ከባድ ነው፡፡ እናንተ ምን ያህል ብቁ መምህራን አሏችሁ?

ታምራት (ዶ/ር)፡- አዎ! ይህ ሐሳቡ ነው፡፡ ሐሳቡን ወደ ተግባር የሚያወርደው መምህሩና ሠራተኛው ነው፡፡ መሠረተ ልማት ብቻ ትምህርትን ምሉዕ አያደርገውም፡፡ ወደ መሬት የሚያወርደው መምህሩ ነው፡፡ ስለሆነም ልምድ ያላቸው መምህራንን መቅጠር ያስፈልጋል፡፡ ልምድ ብቻውን ግን በቂ አይደለም፡፡ በአገራችን ብዙ ያልተለመደ ነገር ግን ዘላቂ ሙያዊ እድገት (Continuous Professional Development/ CPD) አለ፡፡ ይህንን ስራ ላይ እናውላለን፡፡ መምህራን መሠረታዊ ትምህርቶችን ማወቅ አለባቸው፡፡ ዋርካ አንድ መምህር ማወቅ አለበት የሚለውን ከሚያሟሉና የሚሰጠውን  ተከታታይ ሥልጠና ከሚወስዱ ጋር አብሮ ይሰራል፡፡ ያሉባቸውን ክፈተቶች በጥናትና በምልክታ ለይተን ክፍተቶቹ ላይ ልዩ ሥልጠናም እንሰጣለን፡፡   

ሪፖርተር፡- ሥልጠናውን እንዴት ትሰጣላችሁ?

ታምራት (ዶ/ር)፡- አገር ውስጥ ካሉት ከኮተቤ ዩኒቨርሲቲና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ለመሥራት እናስባለን፡፡ በተቋማችን የድርጊት መርሐ ግብርም ይህን አስቀምጠናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ በትምህርት ዙሪያ ከሚሠሩ ተቋማት ጋር አመራሮቻችን ዓለም አቀፋዊው ዕይታ እንዲኖራቸው እናደርጋለን፡፡ ተማሪው ብቻ ሳይሆን መምህሩ አብሮ የሚበቃበትን አመቻችተን መምህሩን ሥርዓቱ ውስጥ ማቆየት ቀዳሚ ስራችን ነው፡፡ መጀመሪያ መምህሩን ነው ብቁ የምናደርገው፡፡

ሪፖርተር፡- ከመምህር በተጨማሪ ወላጅ ትልቅ ሚና አለውና ምን ዓይነት መስተጋብር ይኖራችኋል?

ታምራት (ዶ/ር)፡- ልጆችን የተለያዩ አካላት ያገኟቸዋል፡፡ ትምህርት ቤት ውስጥ የጥበቃ፣ የፅዳት፣ የትምህርት፣ የአስተዳደር ሠራተኞች ያገኟቸዋል፡፡ ከትምህርት ውጪ የትምህርት ቤቱ አካባቢ ማኅበረሰብ በኋላም ወላጅ ያገኛቸዋል፡፡ በትምህርት ቤት ልጆችን በመያዝና በማስተማር ብቻ የሚፈለገው ውጤት ይመጣል ብለን አናስብም፡፡ ስለሆነም የወላጅም የትምህርት ቤትም ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ከወላጆች ጋር በቅርበት የምንሠራበት አሠራር አለን፡፡ መምህራንን እንደምናሠለጥነው ሁሉ፣ ልጆች አስተዳደግ ላይ የተቸገሩ ወላጆችንም እንደግፋለን፡፡ የምክር አገልግሎት ማዕከል ይኖረናል፡፡ የወላጆች ኅብረትም እንዲሁ፡፡ ወላጆች ስለልጆቻቸው ባህሪ መረጃ የሚለዋወጡበት፣ ልምድ የሚቀስሙበት መድረክ ይኖረናል፡፡ ከመምህራን ጋር ተከታታይ ተግባቦት እንዲኖራቸው እናደርጋለን፡፡ ወላጆችን በሥነ ልቦና እስከመደገፍ ጭምር እንሠራለን፡፡ ትምህርት ቤት ያስጠናውን ቤት ካልተገበረው ምሉዕ አይሆንምና መምህራንና ተማሪዎች ላይ የምንሠራውን ከወላጆች ጋር የምንሠራው ይሆናል፡፡ ከትምህርት ቤቱ አካባቢ ማኅበረሰብ ጋርም አብረን እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- የቀደመው የትምህርት ሥርዓት ተከልሶ አዲስ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ ከዚህ የተጣጣመ አሠራር ትተገብራላችሁ?

ታምራት (ዶ/ር)፡- እኛ የመንግሥትን ሥርዓተ ትምህርት ነው የምንከተለው፡፡ መንግሥት አትቀንሱብን ነው የሚለው እንጂ ለምን ጨመራችሁ አይለንም፡፡ እኛ አጠናክረን ማስተማር ነው የምንፈልገው፡፡ ለአብነት አንድን የሒሳብ ንድፈ ሐሳብ ለልጆቹ በጽሑፍ፣ በተግባር፣ በልምምድ እናስተምራለን፡፡ ይህንን ሥርዓተ ትምህርቱ አይከለክለንም፡፡ በመንግሥት ሥርዓተ ትምህርት ተመርኩዘን ተማሪዎች ትምህርቱን እንዲያሰርፁት ነው የምናደርገው፡፡ ዓለም አቀፍ ልምዶችንም እናመጣለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ገደብና አፈጻጸም የሚሹ የአየር ሙቀት መጠንና የካርቦን ልቀት

የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም የዓለም ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያስተሳስረው ቡድን (ግሩፕ) ሲ-40 (C-40) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከተቋሙ ድረ ገጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የ40ዎቹ ከተሞች...

ሕፃናትን ከመስማት ችግር የሚታደገው የቅድመ ምርመራ ጅማሮ

‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› በጎ አድራጎት ማኅበር በጨቅላ ሕፃናት ደረጃ የመስማት ችግር እንዳይከሰትና በሕክምናውም ዙሪያ በዘመኑ ሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ሕክምና ለመስጠት ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡...

የሳባ መንደር

ሼባ ግሩፕ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሼባ/ሳባ የጉዞ ወኪል በ1960ዎቹ የተመሠረተና በርካታ እህት ኩባንያዎችን ያፈራ ነው፡፡ ሼባ ግሩፕ በቢሾፍቱ ከተማ በ350 ሚሊዮን ብር ወጪ...