Saturday, June 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የወጪ ንግድ ክፍተቶችን ለመቅረፍ አዲስ ፕሮጀክት ለመቅረጽ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር ፕሮዲዩሰር ኤክስፖርተርስ አሶሴሽን

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱ የወጪ ንግድ በሚፈለገው ደረጃ እንዲያድግ የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢኖሩም የወጪ ንግድ ምርቶችን የሚቀበሉ አገሮች በየጊዜው የሚጠይቋቸው የተለያዩ መሥፈርቶች ለዘርፉ ማነቆ መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

በቀረቡም የአውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ የሚገቡ ምርቶች ላይ አዲስ መሥፈርቶችን በማውጣት ተግባራዊ እንደሚያደርግ ማሳወቁ የዘርፉ ተዋንያኖችን እንደሳበ መገለጹ ይታወሳል፡፡

ይህ የአውሮፓ ኅብረት አዲስ መሥፈርት ከተተገበረ ችግር ውስጥ ይገባሉ ተብለው ከተጠቀሱ ዘርፎች ውስጥ አንዱ የሆርቲካልቸር ዘርፍ ሲሆን አዲስ የወጣውን የአውሮፓ ኅብረት መሥፈርት ሊያሟላ ካልቻለ ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለው የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል እስከመግለጽ ደርሷል፡፡

የኢትዮጵያን ምርቶች ከሚቀበሉ አገሮች በተከታታይ የሚወጡ የተለያዩ መሥፈርቶችን አላሟሉም የተባሉ የኢትዮጵያ ምርቶች ገዥ አገሮች ከደረሱ በኋላ እንዲመለሱ የተደረጉበት አጋጣሚዎች መፈጠራቸው ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ይህንን የወጪ ንግድ ማነቆ የሆነ ጉዳይ ዘላቂ መፍትሔ እንዲኖረውና ወደፊትም ሳይጠበቅ የሚመጡ የአገሮች አዳዲስ መሥፈርቶችን በቶሎ አውቆ የተጠየቀውን መሥፈርት ለማሟላት መፍትሔ ይሆናሉ ተብለው ከሚታሰቡ ዕርምጃዎች መካከል አምራችና ላኪዎችን አቅም ማሳደግ ለሚጠየቁት መሥፈርቶች በቶሎ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አሠራር መዘርጋት በቀዳሚነት የሚቀመጥ ሆኗል፡፡

በተደጋጋሚ የተለያዩ መሥፈርቶች እየቀረቡበት ካሉ የወጪ ንግድ ምርቶች መካከል አንዱ የሆነው የሆርቲከልቸር ዘርፍም ይህንን በመረዳት ተለዋዋጭ የሆኑ የገዥዎችን መሥፈርቶች በቶሎ አውቆ መፍትሔ ለማበጀትና በአጠቃላይ ዘርፉ የሚታየውን የዕውቀት ያግዛል ያለውን አዲስ ፕሮጀክት ቀርፆ ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑ ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማኅበር ይህን ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግም ከሁለት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ትናንት ስምምነት አድርጓል፡፡

በአጠቃላይ እስከ 350 ሺሕ ዶላር በጀት የተያዘለት ይህ ፕሮጀክት ዋነኛ ዓላማው በሆርቲካልቸር ዘርፍ የሚያጋጥሙ የወጪ ንግድ ክፍተቶችን በመለየት እነዚህን ክፍተቶች ለመድፈን የሚያስችሉ የዕውቀት ሽግግሮችና ተያያዥ ሥልጠናዎችን በዘመናዊ መንገድ እንዲሄድ ማድረግ ነው፡፡

ስምምነቱ በተደረገበት ወቅት እንደተገለጸውም፣ የወጪ ንግዱን ለማሳደግ እንዲሁም በኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ምርቶች ላይ እየቀረቡ ያሉ ያልተቋረጡ የምርት መሥፈርቶችን ለማሟላት በተቀናጀ መልኩ ሥልጠናዎች በአምራችና ላኪዎች በቂ ዕውቀት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡

ሥልጠናውንም ጊዜው በደረሰበት ቴክኖሎጂ ደረጃ ለመስጠት ጭምር ታሳቢ ተደርጎ የተቀረጸው ፕሮጀክት ለመተግበርና ሲስተሙን ለመዘርጋት ከማኅበሩ ጋር ለመሥራት ስምምነት ያደረገው በዘርፉ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ በወጪና ገቢ ንግድ ሥራዎች እንዲበረታቱ ዕገዛ እያደረገ ያለው ትሬድ ማርክ አፍሪካ የተባለ ኩባንያ እንደሆነ ታውቋል፡፡

ፕሮጀክትን አስመልክቶ የኢትዮጵያ አበባ አትክልልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማኅበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዱ እንደገለጹት የዚህ ፕሮጀክት ትግበራ በርካታ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ነው፡፡

ኢትዮጵያ በሆርቲካልቸር ዘርፍ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ዘርፍ ቢሆንም፣ ካለው እምቅ አቅም አንፃር ግን በበቂ ሁኔታ እየተመረተና ለውጭ ገበያ እየቀረበ እንዳልሆነ የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ ለዚህም አንዱ ተግዳሮት ክህሎት ያለው አምራች ኃይል ባለመኖሩ ነው፡፡

‹‹የሆርቲካል ኢንዱስትሪው ብቃት ያለው አምራች ኃይል ይፈልጋል፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ብቃቱ የሚመጣው ደግሞ ጥራት ያለው ሥልጠና መስጠት ስንችል ነው ለማለት በዕለቱ ያደረጉት ስምምነት ሲተገበር ይህንን አቅም ለመፍጠር ዕገዛ የሚደረግ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ሥራው ሲጀመር በየትኛውም ቦታ ያሉ የአበባ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ካሉበት ቦታ ሥልጠናውንና የዕውቀት ሽግግሩን እንዲያገኙ ከሚያስችሉም በላይ በተለያዩ ወቅቶች ከገዥዎች ለሚቀርቡ መሥፈርቶች መፍትሔ ለመስጠት ያስችላል፡፡

በተለይም ሆርቲካልቸር ዘርፍ መሟላት ያለባቸው የማኅበራዊ፣ የአካባቢዊ የሠራተኞች አያያዝ፣ የፀረ ተባይ አጠቃቀም የውኃ አያያዝና የመሳሰሉ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ሥርዓትና ሒደቶች ስላሉ እነዚህን በአግባቡ ተፈጻሚ ለማድረግ ይህ ከወራት በኋላ ሥራው ተናቆ የሚተገበረው አሠራር ዕገዛ እንደሚያደርግ የአቶ ቴዎድሮስ ማብራሪያ ያመላክታል፡፡

የዚህን ፕሮጀክት ሲስተም በመዘርጋትና ለመሠረተ ልማት ግንባታው የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ነው፡፡ የትሬድ ማርክ አፍሪካ ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ ዕውነቱ ታዬ እንደገለጹትም ተግባራዊ የሚደረገው ሲስተም የሆልቲካልቸር የውጭ ንግድ ጉድለቶችን ለማሟላት የሚያስችል ሥርዓት እንዲዘረጋ የሚያስችል ጭምር ነው፡፡ ስታንዳርድን ለመጠበቅ ያሉ ክፍተቶችን ጭምር ከማገዝ ባለፈ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ክፍተትን የሚሞላ ይሆናል፡፡ በተለይ አዳዲስ የአሠራር ክፍተቶችን ለይቶ በቀላሉ ለአባላት ለማሠራጨትና አባላትም ባሉበት እንዲደርሳቸው ያስችላል፡፡

እስካሁን በማኅበሩ በማንዋል ይሰጥ የነበረውን አሠራርን ወደ ሲስተም መቀየር፣ አባላት ባሉበት ቦታ ሆነው መረጃ እንዲኖራቸው እንዲሁም ሥልጠናዎችን በቀላሉ እንዲያገኙ በማድረግ የወጪ ንግዳቸውን እንዲያሳድጉ ይደረጋልም ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊትም ትልቁ ችግር የአሠራርና የዕውቀት ችግር በመሆኑ ማኅበሩንና አባላቶቹን በተለይ በምርትና ኤክስፖርት ሥራቸው ላይ በተከታታይ የሚደረግ የአቅም ግንባታና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያገኙ ለማድረግ ይህ ሲስተም ለውጥ ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ሌላ እስካሁን ድረስ የሆርቲካልቸር ማኅበር አባላት ምርት ማምረት እንጂ ገበያው ምን ዓይነት ምርት በምን ዓይነት የጥራት ደረጃ ይፈልጋል የሚለው ጉዳይም መፍትሔ የሚሆን ዕውቀት እንዲያገኙም ይረዳቸዋል፡፡

እንደ አቶ እውነቱ ገለጻ የዚህ አሠራር መተግበር ትልቁ ጠቀሜታ ምርት ተቀባይ አገሮች በየጊዜው እያሳደጉ ከሚመጡት ፍላጎታቸው አንጻር የሚጠይቁቸውን መሥፈርቶች አውቆ ወዲያው ማስተካከያዎች እንዲደረጉ ማስቻሉ ነው፡፡ በዚህ ፕላትፎርም አማካይነት ሥራቸው ሳይስተጓጎል መሥፈርቱን እንዲያሟሉ ማድረግ በጣም አንገብጋቢ ጉዳይ በመሆኑ እንዲህ ላለው ችግርም መፍትሔ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ ጊዜ የተለያዩ ምርቶች ወደ አውሮፓ ከተላኩ በኋላ ስታንዳርድ አላሟሉም ተብለው የሚመለሱበት ሁኔታ መኖሩን በማስታወስም እንዲህ ዓይነቱን ችግር ለመቅረፍ ከምርት ጀምሮ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሁን በሚተገበረው ሲስተም መሠረት የሚሰጠው ሥልጠና አጋዥ ይሆናል፡፡

ይኼ ፕሮጀክት ሠርቶ ለመጨረስ ወደ 350 ሺሕ ዶላር በጀት እንደተያዘለት የገለጹት አቶ እውነቱ የእርሳቸው ድርጅት ዋነኛ ሥራው የሚሆነው ሲሲተሙን ዴቨሎፕ ማድረግ፣ ለሲስተሙ ግብዓት የሚሆኑ መሣሪያዎችን ማቅረብና በዚህ ሲስተም አባላት እንዲጠቀሙ የሚያስችላቸውን ሥልጠና መስጠትን ያጠቃልላል፡፡ ይህንን ሥራ በስድስት ወራት ካጠናቀቁ በኋላ ሲሲተሙን የሚመሩ ባለሙያዎችን በማፍራት ሥራው በማኅበሩ በኩል እንዲመራ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ይህ ተስፋ የተደረገበት ፕሮጀክት እንደተባለው በትክክል ለውጥ ያመጣል ወይ? ለሚለው ጥያቄ አቶ እውነቱ ለውጥ እንደሚያመጣ ያምናሉ፡፡

ለዚህም በተለያዩ 14 የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የሠራውና የተገኘውን ውጤት በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡

ድርጅታቸው ትሬድማርክ አፍሪካ ከዚህ አንጻር የሠራውን ሥራ በተመለከተ እንደገለጹትም ድርጅቱ በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ ቦታዎች  የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ጭምር የተሳተፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ የወጪና ገቢ ንግድን ለማሳደግ ከመሠረተ ልማት ዝርጋታው ባሻገር ኢንቨስትመንት ላይ ጭምር ተሳታፊ እንደሆነ የገለጹት አቶ እውነቱ በዚህ ረገድ ተሠራ ያሉትን ምሳሌ ገልጸዋል፡፡

ይህም ከኬንያ ሞምባሳ አድርጎ ወደ ስድስት የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የሚሄደውን ሰሜን ኮሪደርን የዲጂታል የካርካርጎ ትራኪንግ ሲስተም፣ የኤሌክትሪክ ሲስተምና የዋን ስቶፕ ሲስተም ሙሉ በሙሉ በመቀየር በዚህ አካባቢ ለትራንዚት ይወሰድ የነበረውን ጊዜ በ300 ፐርሰንት ማሻሻል ችሏል፡፡

ይህንኑ ሥርዓት በኢትዮጵያና በሶማሌላንድ እንዲሁም በኢትዮጵያና በጂቡቲ መካከል በመፍጠር በተለይ የወጪ ንግድ ሥራው የሎጂስቲክስ ወጪው እንዲቀንስ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ከአቶ እውነቱ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ትሬድማርክ አፍሪካ የመጀመርያ ሥራውን የጀመረው በኬኒያ ሲሆን አሁን 14 አገሮች ላይ እየሠራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

ለዚህ ፕሮጀክት ተፈጻሚነት ከትሬድ ማርክ አፍሪካ ሌላ የአውሮፓ ኅብረትና የፈረንሣይ ልማት ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን ከ8.15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆነውን የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችለውን ስምምነት በዕለቱ ከኢትዮጵያ አበባ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማኅበር ጋር ተፈራርመዋል፡፡

ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ አበባ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ በ2015 በጀት ዓመት ከ658.3 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ያስገኘ ሲሆን ከዚህ ውጭ 566 ሚሊዮን ዶላር የተገኘው ከአበባ ወጪ ንግድ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች