Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ተፈናቃዮች የደኅንነት ሥጋት ውስጥ እንደሚገኙ ኢሰመኮ አስታወቀ

የደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ተፈናቃዮች የደኅንነት ሥጋት ውስጥ እንደሚገኙ ኢሰመኮ አስታወቀ

ቀን:

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ከ79 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች፣ ከአርብቶ አደሮች ጋር በሚፈጠር ግጭት ሥጋት ላይ መሆናቸውን መናገራቸውን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰማኮ) አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በወረዳው የሚገኙ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ አስመልክቶ ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት፣ ተፈናቃዮች የግጦሽ መሬት ፍለጋ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ አርብቶ አደሮች ጋር ግጭት ውስጥ እየገቡ በመሆናቸው የደኅንነት ሥጋት እንዳለባቸው ገልጸውልኛል ብሏል፡፡

በኦሞ ወንዝ ሙላት ምክንያት አካባቢው በውኃ በመሸፈኑ የግጦሽ መሬት እጥረት መፈጠሩን የገለጸው ኢሰመኮ፣ ተፈናቃዮች የግጦሽ መሬት ፍለጋ ሲንቀሳቀሱ ከሀመር አርብቶ አደሮች ጋር አልፎ አልፎ የሚከሰተው ግጭት ለተፈናቃዮቹ የሥጋት ምንጭ መሆኑን አስታውቋል፡፡

- Advertisement -

የዳሰነች ወረዳ አስተዳዳሪ በዳሰነችና በኬንያ ቱርካና አርብቶ አደሮች መካከል ዕርቀ ሰላም የተፈጸመ መሆኑን ለኮሚሽኑ እንዳስረዱ በሪፖርቱ የተገለጸ ሲሆን፣ መነሻቸውን ከአካባቢው ያደረጉ አርብቶ አደሮች ግን ከተፈናቃዮች ጋር አልፎ አልፎ ግጭት ውስጥ እንደሚገቡና ይህም በአካባቢው የፀጥታ ሁኔታ ላይ ተፅዕኖ እንዳለው ነግረውኛል ሲል ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

በየክረምቱ በአካባቢው በሚከሰት ከፍተኛ ዝናብ ወንዙ ስለሚሞላ ነዋሪዎች ወደ ሌላ ቦታ በመፈናቀል ክረምቱን አሳልፈው ይመለሱ እንደነበር ለሪፖርተር የገለጹት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ወ/ሮ ራኬብ መለሰ፣ ተፈናቃዮች ለአራት ዓመታት ዘላቂ መፍትሔ ላለማግኘታቸውና አሁን ላሉባቸው ችግሮች የተዳረጉባቸውን ምክንያቶችን በሦስት ከፍለው አስረድተዋል፡፡

በ2012 ዓ.ም. በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ኃይለኛ ዝናብ በመዝነቡ ወንዙ ከበፊቱ በባሰ ሁኔታ መሙላቱና ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ዋነኛው መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፣ በዝናቡ ምክንያት በአካባቢው የሚገኘው የግልገል ጊቤ 3 ግድብ ማስተንፈሱ ሌላኛው ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በ2013 ዓ.ም. በኬንያ በኩል የሚገኘው ቱርካና ወንዝ ከመጠን በላይ በመሙላቱና ወደኋላ በመመለሱ፣ በአካባቢው ላይ ያስከተለው ጉዳትም አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶችም የአካባቢው ነዋሪዎች ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ቀዬአቸው መመለስ አለመቻላቸውን አስታውቀዋል፡፡

በሪፖርቱ እንደተገለጸውና ምክትል ዋና ኮሚሽነሯም እንዳብራሩት የግልገል ጊቤ 3 ግድብ እንዲተነፍስ ሲደረግ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጥናት ቢገልጽም፣ የአየር ንብረት ለውጡን መሠረት ያደረገ እንዳልነበር ተመላክቷል፡፡ ችግሩ ከተከሰተ በኋላም ለአራት ዓመታት ያህል መፍትሔ አለማግኘታቸው ትኩረት የሚሻ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለተፈናቃዮች በክልሉ መንግሥት፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ እንዲሁም በተለያዩ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች ለማድረግ ቢሞከርም በቂና ተከታታይነት ያለው አለመሆኑን ወ/ሮ ራኬብ ገልጸዋል፡፡ 

በተከሰተው የጎርፍ አደጋ መሠረተ ልማቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸው፣ በአካባቢው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ብቻ መኖሩ፣ አካባቢው ረግረጋማ በመሆኑ በሚከሰት የወባ ወረርሽኝ ችግር ላይ መውደቃቸውንም አስታውቀዋል፡፡ የሚመለከታቸው አካላት በጋራ በመሥራት ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጡ ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

የክልሉ መንግሥት ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ኮሚቴ አቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በበኩሉ እያስጠና ያለው ጥናት በሰኔ ወር የዕቅድ ዝግጅቱ ተጠናቆ  ከነሐሴ ወር ጀምሮ ወደ ተግባር እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...