Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበአገር አቀፍ ከሚገኙ 20 የግብርና ምርምር ማዕከላት አብዛኛዎቹ የይዞታ ማረጋገጫ የላቸውም ተባለ

በአገር አቀፍ ከሚገኙ 20 የግብርና ምርምር ማዕከላት አብዛኛዎቹ የይዞታ ማረጋገጫ የላቸውም ተባለ

ቀን:

  • የምርምር ኢንስቲትዩቱ የበጀት እጥረት እያለበት 196 ሚሊዮን ብር በመመለሱ ተወቀሰ

በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ 20 የምርምር ማዕከላት ውስጥ አብዛኛዎቹ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንደሌላቸው፣ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አስታወቀ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2014/15 በጀት ዓመት፣ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የእንስሳትና መኖ ምርምር የሥራ አፈጻጸም ኢኮኖሚያዊ፣ ቀልጣፋ እንዲሁም ውጤታማ መሆኑን በተመለከተ የተከናወነ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርትን መነሻ በማድረግ፣ ባለፈው ሳምንት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በሥሩ የሚገኙ የምርምር ማዕከላት ይዞታዎችን ከማስከበር አኳያ ከፍተኛ ችግር ውስጥ በመውደቁ፣ ይዞታዎቹ በሕገወጥ መንገድ ተወረው የተለያዩ ግንባታዎች እየተከናወኑባቸው እንደሆነ ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

የሆለታ፣ የቁልምሳ፣ የመልካሳ፣ የጅማ፣ የፓዊ፣ የወረር፣ የደብረ ዘይት፣ የወንዶ ገነትና የቴፒ ብሔራዊ ቅመማ ቅመም ምርምር ማዕከላት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ስለሌላቸውና የወሰን ጥያቄ በመፈጠሩ ምክንያት፣ ለከፍተኛ ኪሳራና ለህልውና አደጋ መጋለጣቸውን በኦዲት ሪፖርቱ መካተቱን አክለው ገልጸዋል፡፡

በተለይ የአዳበርጋ መለስተኛ የምርምር ማዕከል ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ባጋጠመው የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ምክንያት፣ በ2011 ዓ.ም. ብቻ በደረሰ የንብረት ጉዳት አንድ ትራክተር ሙሉ ለሙሉ የተቃጠለ መሆኑን፣ በየዓመቱም ይሰበሰብ የነበረው 50 ሺሕ ቦንዳ የተፈጥሮ ሳር በመቃጠሉ፣ መንግሥት ለእንስሳት መኖ ለሚውል ሳር ግዥ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ለወጪ መደረጉን ዋና ኦዲተሯ አስረድተዋል፡፡

ከጥቅምት 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ 32 ሔክታር የሚሸፍን የታጨደና ያልታጨደ የተፈጥሮ ድርቆሽ ሳር ውስጥ፣ አጎራባች በሆኑ አራት ቀበሌዎች ውስጥ በሚኖሩ የአርሶ አደሮች እንስሳት ዘጠኝ ቦንዳ መበላቱንና በመለስተኛ ማዕከሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አብራርተዋል፡፡

የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የሌላቸው እነዚህ ማዕከላት ‹‹በወቅቱ ሲቋቋሙ በደብዳቤ ብቻ እንደነበር የኦዲት ሪፖርቱ ያሳያል›› ያሉት ዋና ኦዲተሯ፣ በአሁኑ ወቅት በየቦታው ይዞታው የእኔ ነው የሚል ጠያቂ ማኅበረሰብ በመፈጠሩ ዘርፉ በከፍተኛ ሁኔታ እየተጎዳ ነው ብለዋል፡፡

የማዕከላቱ በርካታ ግብዓቶች መወረሳቸውን፣ ተክሎች መሸጣቸውንና በይዞታቸው ላይም ቤቶች እየተሠሩባቸው እንደሆነ በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

ዋና ኦዲተሯ ችግሩ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ብቻ ሳይሆን የግብርና ሚኒስቴርና የቋሚ ኮሚቴው ጭምር እንደሆነ ገልጸው፣ እስካሁን ድረስ የምርምር ማዕከላቱ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ለምን እንደሌላቸው መጠየቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ለምርምር ማዕከልነት የተያዙት መሬቶች ሰፋፊ ከሆኑ ማዕከላቱን የሚመጥን ይዞታ መስጠት እንደሚገባ፣ ለዚህም እንደ ባለቤት የግብርና ሚኒስቴር ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡

የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከዚህ በተጨማሪ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት በኦዲት ሪፖርቱ መታየቱን፣ የአሠራር ክፍተቱ ላይ ለወደፊቱ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡

ዋና ኦዲተሯ ወ/ሮ መሠረት፣ የግብርና ምርምር ማዕከላት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲኖራቸው ተደርጎ ለምን ወሰን ማስከበር አልተቻለም በማለት ለኢንስቲትዩቱ ኃላፊዎች ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ኃላፊዎቹ ጥያቄውን ከመመለስ ተቆጥበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርቱን ካዳመጡ በኋላ፣ ኢንስቲትዩቱ ቀዳሚና ተወዳዳሪ የምርምር ማዕከል ሆኖ እንዲቀጥል ከተፈለገ፣ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት የታዩ ክፍተቶችን ለማረም ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት ብለዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ በአርብቶ አደሮች አካባቢ እየደረሰ ያለውን የድርቅ ተጋላጭነት በእንስሳት ሀብት ልማትና መኖ አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂ የተደገፉ የምርምር ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ እስከ ግንቦት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ለቋሚ ኮሚቴውና ለሚመለከታቸው አካላት የክዋኔ ኦዲት የማስተካከል ዕርምጃ አድርጎ ሪፖርት እንዲያቀርብ፣ ምክትል ሰብሳቢዋ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የእንስሳትና የመኖ ምርምር የበጀት እጥረት ገጥሞኛል እያለ፣ ከ196 ሚሊዮን ብር በላይ ተመላሽ በማድረጉም ወቀሳ ቀርቦበታል፡፡

 የኢንስቲትዩቱ የሥራ አፈጻጸም፣ በአንድ በኩል የበጀት እጥረት አጋጥሞኛል እንደሚልና በሌላ በኩል ደግሞ ከ196 ሚሊዮን ብር በላይ ተመላሽ ማድረጉን ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት አስታውቀዋል፡፡

ለእንስሳት መኖ ምርምር የሚያስፈልግ በቂ በጀት አለመኖሩ በኦዲት ግኝቱ ላይ ማየት እንደተቻለ ገልጸው፣ ተቋሙ ያሉበትን ክፍተቶች አጣጥሞ ከመጠቀም ይልቅ ገንዘብ ተመላሽ ማድረጉ ጤናማነት አይደለም ብለዋል፡፡

የዘር ማባዣና ለላቦራቶሪ ምርምር የሚውሉ ግብዓቶች አለመኖር በኦዲት ግኝቱ ላይ እንደ ክፍተት የታየ መሆኑን፣ እነዚህ ሁሉ ችግሮች እያሉ ተመላሽ የተደረገውን ገንዘብ ከመጠቀም ይልቅ ከግል ባለሀብቶች ድጋፍ መጠየቅ አግባብ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

 በተለይ የኦሆታ የምርምር ማዕከል ላለፉት 30 ዓመታት ምንም ዓይነት ዕድሳት ያልተደረገለትና በውስጡም የሚገኙ ማሽነሪዎች ለምርምር የማይሆኑ፣ ያሉበትን ችግሮች ተመላሽ በሆነው ገንዘብ መፍታት ይቻል ነበር ሲሉ ምሳሌ አቅርበዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ያሉበትን የበጀት እጥረት አጣጥሞ ከመጠቀም ይልቅ ለምን ገንዘብን ተመላሽ እንዳደረገ ቢጠየቅም ምላሹ አጥጋቢ አይደለም ያሉት ዋና ኦዲተሯ፣ የኢንስቲትዩቱ የምርምር ማዕከላት ዓለም አቀፍ ስታንዳርድን ያላሟሉ መሆናቸውን ከሪፖርቱ መረዳት ተችሏል ብለዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተሯ ይህንን ቢሉም ጉዳዩን በተመለከተ ምላሽ የሰጡት የኢንስቲትዩቱ የእንስሳት ምርምር ዋና ዳይሬክተር ፈቀደ ፈይሳ (ዶ/ር)፣ መንግሥት በሚያቀርበው አስፈላጊ ግብዓቶችን በማሟላት በጀት ምርምር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የምርምር ድጋፍን በተመለከተ ግብር ከሚያመነጨው አጠቃላይ ሀብት አገሪቱ ለምርምር የምታውለው 0.2 በመቶ እንደሆነ ገልጸው፣ ይህም ከሌሎች አገሮች ጋር ሲታይ በጣም አነስተኛ ነው ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ በኢንስቲትዩቱ ከመንግሥት ለምርምር ከሚሰጠው በጀት ከሰብል ምርምር ቀጥሎ ሁለተኛውንና ትልቁን የሚያገኘው የእንስሳት ዘርፉ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በተለያዩ ማዕከላት ከ20 ሺሕ በላይ የምርምር እንስሳት እንዳሉ አስረድተዋል፡፡

ከ40 እስከ 50 በመቶ የሚሆነው በጀት እነዚህን እንስሳት ለማቆየት በሚደረገው ጥረት እንደሚውል ጠቅሰው፣ ቀሪው በጀት የተለያዩ ነገሮችን አሟልቶ ተግባራዊ ለማድረግ በጣም ከባድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከመንግሥት ከሚሰጠው በጀት በተጨማሪ ከኢንስቲትዩቱ ጋር በአጋርነት ከሚሠሩ ተቋማት ግንኙነት በመፍጠር ሌላ ሀብት በማግኘት፣ የተለያዩ ግብዓቶችን ለማሟላት ሰፊ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ሪፖርተር ያገኘው ሰነድ እንደሚያመለክተው በ2014 በጀት ዓመት 918 ሚሊዮን ብር ለኢንስቲትዩቱ የተበጀተ ሲሆን፣ 433 ሚሊዮን ብር ለዘር ተኮር የግብርና ምርምር ፕሮግራም ለማዋል ታስቦ ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...