Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናፌዴራል ፖሊስ ከሥራ ተገልለው ለቆዩ የትግራይ ተወላጅ አባላቱ የተሃድሶ ሥልጠና ጥሪ አቀረበ

ፌዴራል ፖሊስ ከሥራ ተገልለው ለቆዩ የትግራይ ተወላጅ አባላቱ የተሃድሶ ሥልጠና ጥሪ አቀረበ

ቀን:

  • ላለፉት ሦስት ዓመታት ደመወዝ እየተከፈላቸው መሆኑ ተጠቁሟል

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት፣ በተቋሙ የሚገኙ ከሦስት ዓመታት በላይ ደመወዝ እየተከፈላቸው በሥራ ላይ ሳይሆኑ የቆዩ የትግራይ ተወላጅ አመራርና አባላት፣ ለተሃድሶ ስልጠና እንዲገቡ ጥሪ አቀረበ።

ሪፖርተር የተመለከተው ሚያዚያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ተጽፎ በምክትል ኮሚሽነር ደርዜ ገቢሳ ተፈርሞ የወጣ ደብዳቤ እንደሚገልጸው፣ ላለፉት ሦስት ዓመታት ከሥራ ውጭ ሆነው በየሳምንቱ እየፈረሙ ደመወዝ እየተከፈላቸው የቆዩ የትግራይ ተወላጅ አመራርና አባላት በተቋሙ እንደሚገኙ ይገልጻል።

እነዚህ የኮሚሽኑ አባላት መደበኛ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት አጠቃላይ የተቋሙን ሪፎርምና ልዩ ልዩ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንዲወስዱና መደበኛ ሥራቸውን እንዲጀምሩ መወሰኑም ተገልጿል።

- Advertisement -

ነገር ግን ወደ ሥራቸው ከመመለሳቸው አስቀድሞ ሚያዚያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 08:00 ሰዓት ጀምሮ በሰሜን ሸዋ አሌልቱ በሚገኘው የፌዴራል ማረሚያ ፖሊስ ተቋም፣ የተሃድሶ ሥልጠና እንዲወስዱ ጥሪ የቀረበላቸው ሲሆን፣ የሚመለከታቸው የኮሚሽኑ የሥራ ክፍሎችም በሒደቱ የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው በረዳት ኮሚሽነሩ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ ያስረዳል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ኃላፊ አቶ ጄይላን አብዲ አመራርና አባላቱ ጥሪ እንደቀረበላቸው ያረጋገጡ ቢሆንም፣ ሪፖርተር ለተሃድሶና የአቅም ግንባታ የተጠሩትና ጥሪውን ተቀብለው ለሥልጠና ወደ ተቋሙ የገቡት የፖሊስ አባላት ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ላቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹ይህ ጉዳይ የኮሚሽኑ የውስጥ ጉዳይ እንደመሆኑ በውስጥ የሚያዝ መረጃ ነው›› የሚል ምላሽ በመስጠት ብዛታቸውን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

በተያያዘም ከዚህ ቀደም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽን ሥር ሲሠሩ የነበሩና በጦርነቱ ወቅት በወጣ ክልላዊ አዋጅ ‹‹በትጥቅ ትግል አልተሳተፉም” በሚል ምክንያት ያለደመወዝና ጡረታ ከሥራ ውጭ የተደረጉ የትግራይ ክልል ፖሊስ አባላት ጉዳይ፣ እስካሁን ያለምንም መፍትሔ መቀጠላቸውን ሪፖርተር ከምንጮቹ መረዳት ችሏል።

በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ (Human Rights First Ethiopia) በተሰኘ አገር በቀል የሲቪል ማኅበር ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተስፋለም በርሀ ‹‹የፖሊስ አባላቱን ከሥራ ውጭ ያደረገው በ2014 ዓ.ም. በሥራ ላይ የነበረው የክልሉ ምክር ቤት ይህን ዕርምጃ የወሰደበት ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ፖለቲካዊ ነበር›› ብለዋል።

የሰሜኑ ግጭት በፕሪቶሪያው ስምምነት ከተቋጨ በኋላ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደርም፣ የቀድሞ ፖሊስ አባላቱ የሚገኙበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ተረድቶ መፍትሔ እንዳላበጀላቸውም ገልጸዋል።

አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኃላፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የክልል ፖሊስ አባላት ጉዳይ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንን እንደማይመለከተውና በዚህ ላይ ውሳኔ መስጠትም እንደማይችል ገልጸው ‹‹ይህ መታየት ያለበት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ነው፤›› ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...