Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናአዋጆችን ወደ ደንብ ቀይሯል የተባለው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምላሽ እንዲሰጥ ትዕዛዝ ተላለፈ

አዋጆችን ወደ ደንብ ቀይሯል የተባለው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምላሽ እንዲሰጥ ትዕዛዝ ተላለፈ

ቀን:

የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ከኅዳር 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጻሚ እንዲሆን ያፀደቀው ደንብ ቁጥር 4/2016 እንዲሻር፣ አንድ አገር በቀል የሲቪል ማኅበር ባቀረበው የሕገ መንግሥት ትርጉም አቤቱታ ላይ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ምላሽ እንዲሰጥ ትዕዛዝ አስተላለፈ።

አጣሪ ጉባዔው አስተዳደሩ ምላሽ እንዲሰጥ ትዕዛዝ ያስተላለፈው፣ ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ (Human Rights First Ethiopia) በተሰኘው አገር በቀል የሲቪል ማኅበር ድርጅት ታኅሳስ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. እንደተጻፈ የሚገልጽ አቤቱታ ከቀረበለት ከአራት ወራት ቆይታ በኋላ ሐሙስ ግንቦት 8 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ በንዑስ አጣሪ ጉባዔና በአጣሪ ጉባዔ ጽሕፈት ቤቱ ሰፊ ማጣራት ተደርጎባቸው፣ ለውሳኔ ከቀረቡለት አቤቱታዎች መካከል በ32ቱ ላይ ውሳኔና አቅጣጫ በሰጠበት ስብሰባው ወቅት መሆኑን አሳውቋል።

ለአጣሪ ጉባዔው የቀረበው ሰነድ የጉዳዩ መነሻ አድርጎ ያቀረባቸውም የፕሪቶሪያ ስምምነት አንቀጾች ይዘት ላይ የሰፈሩ ድንጋጌዎች፣ በዚሁ ስምምነት መሠረት በትግራይ ክልል የተደረገ ምርጫና ምርጫውን ተከትሎ የተቋቋመው ክልላዊ ምክር ቤት ‹‹ሕገ መንግሥታዊ አይደለም›› ተብሎ እንዲፈርስ መደረጉ፣ ሆኖም ጊዜያዊ አስተዳድደሩ የአገሪቱንም ሆነ የትግራይ ክልል ሕገ መንግሥትን የሚቃረን አዲስ ደንብ አፅድቆ በሥራ ላይ ያዋለ በመሆኑ፣ ደንቡ ኢሕገ መንግሥታዊ ነው ተብሎ እንዲሻር የቀረበ አቤቱታ መሆኑን እንደሚገልጽ፣ ጥር 5 ቀን 2016 ዓ.ም. መዘገባችን አይዘነጋም።

- Advertisement -

ሪፖርተር የተመለከተው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቱ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጠውና እንዲሻር የሚል ጥያቄ ያቀረበበት ሰነድ ዝርዝር አቤቱታ፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ያወጣውና አሁን በሥራ ላይ ያለው፣ ‹‹ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሕጎች ወደ መደበኛ ሕግ ለመመለስ የወጣ የመሸጋገርያ ደንብ ቀጥር 4/2016›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ደንብ፣ ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረኑ አራት ድንጋጌዎችን ያቀፈ መሆኑን በዝርዝር ያስረዳል።

እንዲሻሩ ጥያቄ ከቀረበባቸው አራት ድንጋጌዎች ተቀዳሚው የመሸጋገሪያ ደንቡ፣ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ኢሕገ መንግሥታዊ ተብሎ የፈረሰው፣ የክልሉ ምክር ቤት ያወጣቸው ሕጎች ተፈጻሚነታቸው እንዲቀጥል ያደረገ መሆኑን ይጠቅሳል።

በአቤቱታ ሰነዱ ላይ እንደተገለጸው ሕገወጥ ተብሎ በፈረሰው ምክር ቤት፣ በ2014 ዓ.ም. የትግራይ ክልል የፖሊስ ኮሚሽን ዳግም ለማቋቋም በሚል የወጣ አዋጅ ቁጥር 360/2014 ነባሩን የፖሊስ ኮሚሽንን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 221/2004 በመሻር፣ የፖሊስ ኮሚሽኑን ሙሉ ለሙሉ በማፍረስ እንደ አዲስ እንዲቋቋም ማድረጉን በማስታወስ፣ ይህ አዋጅ በጊዜያዊ አስተዳደሩ በፀደቀው የመሸጋገሪያ ደምብ ላይ ተፈጻሚ ሆኖ እንዲቀጥል መወሰኑን ይገልጻል።

ይህ አዋጅ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽን ሥር ሲሠሩ የነበሩ የፖሊስ አባላት ያለ ምንም ሕጋዊ ምክንያት ወደ ሥራቸው እንዳይመለሱ እንደተደረጉ፣ አቤቱታው እስከቀረበበት ታኅሳስ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ደመወዛቸው እንዳልተሰጣቸውና ከእነ ቤተሰቦቻቸው በከፍተኛ ሥቃይ ውስጥ መሆናቸውን የመብት ጥሰቱ ተጠቂ የሆኑ የትግራይ ፖሊስ አባላት ማሳወቃቸውን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቱ ገልጿል።

‹‹ከአንድ ሺሕ በላይ የሚሆኑና እስከ 30 ዓመት ያገለገሉ የትግራይ ክልል ፖሊስ አባላትን ኮሚሽኑን አፍርሶ በትኗል›› የተባለውን የግጭት ጊዜ አዋጅ፣ የፕሪቶሪያ ስምምነት ሁሉም ነገር ወደ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲመለስና በሕገ መንግሥቱና ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርገው በወጡ አዋጆችና በሌሎች ሕጎች ሁሉም እንዲመራ የሚያስገድድ ቢሆንም፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ግን ይህን ስምምነት በመጣስ በኢትዮጵያና በክልሉ ሕጎች መሠረት የተቀጠሩ፣ የሠለጠኑና ለዓመታት ያገለገሉ የፖሊስ አባላት ‹‹በትጥቅ ትግል አልተሳተፉም›› በሚል ወደ ሥራ ማባረሩ ወይም ከሥራ እንዳይመለሱ መከልከሉ፣ የጡረታና የሌሎች ማኅበራዊ ዋስትና ጥበቃ እንዳያገኙ መከልከሉም ተገልጿል።

‹‹ሕገ መንግሥታዊ አይደለም በተባለ ምክር ቤት የወጣ አዋጅ ሕጋዊ ሆኖ ተፈጻሚነቱ የሚቀጥልበት አግባብ የለም፤›› የሚለው የሲቪል ማኅበረሰቡ የአቤቱታ ሰነድ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የመሸጋገርያ ደንብ ክፍል አንቀጽ 11(2) ላይ ‹‹…አዋጅ ቁጥር 360/2014 ከመደበኛ ሕጎች ጋር ተመዛዝኖ እስከሚሻሻል ድረስ ተፈጻሚነት ይኖረዋል…›› በሚል በግልጽ ተፈጻሚነቱ እንደሚቀጥል ያመላከተ መሆኑን ጠቅሷል።

ይህ ድንጋጌም የአገሪቱን ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9(1) ማለትም፣ ‹‹ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም›› የሚል ድንጋጌ የሚቃረን መሆኑን በመግለጽ እንዲሻር ተጠይቋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የመሸጋገሪያ ደንብ ድንጋጌ በሁለተኝነት ጥሰት ፈጽሟል የሚል አቤቱታ የቀረበበት ደግሞ፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 4 ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ ሕግ አካል ናቸው የሚለውን ድንጋጌ፣ እንዲሁም አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ 5 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ያወጣል እንደሚል፣ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ክልሎች የፌዴራሉ መንግሥት የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በግልጽ ባልተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ሕግ የማውጣት ሥልጣን ይኖራቸዋል የሚለውን ድንጋጌ ጥሰት ፈጽሟል በሚል ነው።

የአስተዳደሩ ደንብ ኢሕገ መንግሥታዊ ተብሎ የፈረሰው የክልሉ ምክር ቤት ‘የአስቸኳይ ጊዜ ሕጎች’ በማለት በጦርነቱ ጊዜ የፌዴራሉ የወንጀል ሕግ የሚሸፍናቸውን ድንጋጌዎች በመዘርዘር፣ ከባድ ቅጣት የሚያስከትሉ፣ የፌዴራሉ የወንጀል ሕግ ተፈጻሚነቱ እንዲቆም ያደረጉ ዝርዝር ድንጋጌዎች የያዙ አዋጆችና ደንቦች አውጥቶ እንደነበር፣ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የቀረበው አቤቱታ ያስታውሳል፡፡

አሁን እንዲሻር የጠየቀበት ደንብ ቁጥር 4/2016 አንቀፅ 9(2) በአስቸኳይ ጊዜ ሕጎች መሠረት በፍርድ ቤት በክስ ወይም ይግባኝ በሒደት የሚገኝ የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ጉዳይ ወይም መዝገብ በተከሰሰበት የአስቸኳይ ጊዜ ሕግና የሥነ ሥርዓት ሕግ መሠረት ቀጥሎ ዕልባት ያገኛል የሚለው፣ እንዲሁም ንዑስ አንቀጽ 3 ከላይ በተጠቀሰው ንዑስ አንቀጽ መሠረት የተወሰነ የወንጀል ጉዳይ ላይ የሚነሳ የይግባኝ ጥያቄ በተከሰሰበት የአስቸኳይ ጊዜ ሕግና የሥነ ሥርዓት ሕግ መሠረት ቀጥሎ ዕልባት ያገኛል፣ የሚል ድንጋጌዎችን በማስፈር የአስቸኳይ ጊዜ ሕጎቹን በመሻር ከማረም ይልቅ፣ የተከሰሱ ሰዎች ጉዳያቸው በእነዚህ በጦርነቱ ወቅት የወጡ ሕጎች መታየቱ እንዲቀጥል ማድረጉ ተነግሯል።

ድንጋጌዎቹ ሕገወጥ በተባለ ምክር ቤት የወጡ ሕጎች ተፈጻሚነታቸው እንዲቀጥሉ ከማድረጉ በተጨማሪ፣ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55(5) በፌዴራሉ ምክር ቤት የወጣ የወንጀል ሕግ ያልሸፈናቸው ካልሆኑ በስተቀር፣ የወንጀል ሕግ በፌዴራል ምክር ቤት ይወጣል የሚል የሕገ መንግሥት ድንጋጌ የሚቃረን እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡

በሦስተኝነት ለሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ የቀረበው የአስተዳደሩ ደንብ አንቀጽ 10፣ በአስቸኳይ ጊዜ ወቅት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ዕልባት ያገኙ የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ እንዳይባልበት ታግዶ ይቆያል በሚል የተደነገገበት ክፍል ነው።

ይህ ደግሞ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 80 ላይ የሰፈረውን የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበትን ማናቸውንም የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም፣ በሰበር ችሎት የማየት ሥልጣን ይኖረዋል የሚለውን እንደሚቃረን ያሳያል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጡ የተባሉ የወንጀል ሕጎች የፌዴራሉ የወንጀል ሕግ የደነገጋቸውን በመድገም የወጡ እንደነበሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቱ በማስረዳት እንዲሻሩ ጠይቋል፡፡

በስተመጨረሻ የቀረበው የሕገ መንግሥት ጥሰት ደግሞ የደንቡ የመሸጋገሪያ ክፍል አንቀጽ 11(3) በግልጽ ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. እስከ ኅዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ያለው ጊዜ፣ የመንግሥት ሠራተኛ፣ የግል ተቋማት ሠራተኛና የግለሰብ ሠራተኛ ውዝፍ ደመወዝ የሚመለከት አዲስ ክስ ጉዳይ ታግዶ ይቆያል በማለት ያሰፈረው ድንጋጌ ነው፡፡

ከዚህ ድንጋጌ ጋር በተመሳሳይ በሒደት ላይ ያሉ የክስ፣ ይግባኝና የአፈጻጸም ጉዳዮች በሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ተጠንቶ መፍትሔ እስከሚደረግበት ባለበት ይቆያል በሚልም ተጽፏል፡፡

በአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 37(1) የተደነገገው ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት አለው የሚል መብት ገደብ ያስቀመጠ ነው፡፡

ይህ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ደንብ አንቀጽ ግን ሥልጣን ባልተሰጠው አካል ለዚያውም በደንብ ዜጎች ባሏቸው የፍትሕ ጥያቄዎች መከልከል፣ ዜጎች መብታቸውን በፍርድ ቤት ወይም ሌሎች የዳኝነት አካላት እየቀረቡ መብታቸውን ለማስከበር ያላቸውን መብት የሚገድብ መሆኑን አቤቱታው ያብራራል፡፡

ዜጎች በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ካላቸው ለፍርድ ቤት በማቅረብ እንደ የጉዳዩ እየታየ መወሰን ሲገባው ገና ለገና ጉዳዮች በፍርድ ቤት እንዳይታዩ ለመከልከል የተደረገው የሕግ ክልከላ ተገቢነት የሌለው፣ ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ ስለሆነ ሊሻር የሚገባው ነው በሚል ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ቀርቧል፡፡

ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ (Human Rights First Ethiopia) በተሰኘው አገር በቀል የሲቪል ማኅበር ድርጅት የቀረበውን አቤቱታ የገመገመው የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔም፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በቀረበበት አቤቱታ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ሪፖርተር ጉዳዩን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡ ለትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ እንዲሁም ለአስተዳደሩ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ኃላፊ አቶ ረዳኢ ሃለፎምን ለማግኘት ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...