Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናመንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

ቀን:

  • የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል
  • አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ አምስት ዩኒቨርሲቲዎች ከባድ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል

ኢትዮጵያ የገጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የማክሮ ፋይናንስ መዛባት ለማስተካከል፣ መንግሥት ከለጋሽ አካላት ጋር የተጀመረውን ድርድርና ስምምነት ሊቀጥል እንደሚገባ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀትና የፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የገንዘብ ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሲገመግም ሰብሳቢው አቶ ደሳለኝ ወዳጆ በሰጡት ማሳሰቢያ፣ ‹‹የድርድሩ ዋናው ባለቤት የገንዘብ ሚኒስቴር በመሆኑ፣ ከልማት አጋሮች ጋር የተጀመረው ድርድር፣ ንግግርና ስምምነት የማይታለፍ በመሆኑ አበክሮ መሥራት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡ እነዚህ አካላት የሚፈልጉትን የኦዲት ሪፖርት፣ የግዥ አዋጅና መሰል ሕጎች በማፅደቅ ቶሎ ወደ ሥራ ማስገባትና የውጭ ሀብት ፍሰቱ የተጠናከረ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቃል ሲሉም አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያለባት የውጭ ብድር ዕዳ ሽግሽግ እንዲደረግላትና ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ለዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና ለፓሪስ ክለብ አበዳሪ አገሮች ጥያቄ አቅርባ ድርድር ከጀመረች ከሁለት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡

- Advertisement -

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ሪፖርታቸውን ሲያቀርቡ፣ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከውጭ ዕርዳታ በበጀት ድጋፍ መልክ ይፈሳል ተብሎ የታቀደው ገቢ እንደተጠበቀው አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአገሪቱ የውጭና የአገር ውስጥ ብድር ዕዳ 64.36 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ከዚህ ውስጥ የውጭ ብድር 28.5 ቢሊዮን እንደሆነና የአገር ውስጥ ብድር ደግሞ 35.8 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አስረድተዋል፡፡

ከአጠቃላይ የውጭ ብድር ውስጥ የፌዴራል መንግሥት ድርሻ 20.1 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን፣ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ድርሻ 8.4 ቢሊዮን ዶላር፣ ከአገር ውስጥ ብድር ደግሞ የፌዴራል መንግሥት ድርሻ 21.9 ቢሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ድርሻ 13.8 ቢሊዮን ዶላር ነው ተብሏል፡፡

የአገሪቱ አጠቃላይ ብድር ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ጋር ሲነፃፀር 39.4 በመቶ መድረሱን፣ የውጭና የአገር ውስጥ ብድር ከአገር ውስጥ ብሔራዊ ጥቅል ምርት አኳያ በቅደም ተከተል 17.5 በመቶና 21.9 በመቶ እንደሆነ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

መንግሥት በ2016 በጀት ዓመት ለውጭና ለአገር ውስጥ ብድር ክፍያ ለመፈጸም በዕቅድ ከያዘው 159.2 ቢሊዮን ብር ዕቅድ ውስጥ፣ በዘጠኝ ወራት 104 ቢሊዮን ብር ክፍያ ለመፈጸም አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ በዘጠኝ ወራት መክፈል የተቻለው 24 ቢሊዮን ብር ለውጭና 40.7 ቢሊዮን ብር ለአገር ውስጥ እንደሆነ በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

የብድር አፈጻጸሙ ዝቅ ያለበት ምክንያት የውጭ ብድር ክፍያ የዕፎይታ ጊዜ በመገኘቱ መሆኑን፣ የአገር ውስጥ ብድር ክፍያ ደግሞ የልማት ባንክ ብድሮች ወደ ረዥም ጊዜ ቦንድ በመቀየራቸው ክፍያው ባለመፈጸሙ ነው ብለዋል፡፡

ከቻይና ኤክዚም ባንክ ጋር በተደረገ ድርድር የሁለት ዓመታት የብድር አገልግሎት ክፍያ ማራዘሚያ ስምምነት በመፈጸሙ፣ እ.ኤ.አ. በ2023 እና 2024 መከፈል የነበረበት 1.3 ቢሊዮን ዶላር ያህል የዋና ብድርና የወለድ አገልግሎት ክፍያ እንዲራዘም በመደረጉ፣ ወቅታዊ የብድር ክፍያ ጫና ዕፎይታ ማስገኘቱን አክለው ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ከቻይና ልማት ባንክ ጋር በተደረገ ስምምነት በቀጣይ ሦስት ዓመታት መከፈል የነበረበት 400 ሚሊዮን ዶላር የዋና ብድርና ወለድ አገልግሎት ክፍያ እንዲራዘም በመደረጉ፣ ወቅታዊው የብድር ክፍያ ጫና ክፍያ መራዘሙን ገልጸዋል፡፡

መንግሥት በ2016 በጀት ዓመት ለመሰብሰብ ካቀደው 485.8 ቢሊዮን ብር ገቢ ውስጥ፣ በዘጠኝ ወራት ብር 337.9 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ሚኒስትሩ አስረድተዋ፡፡

በአገሪቱ የተወሰኑ አካባቢዎች በሚታየው አለመረጋጋት ለሰብዓዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋም የሚጠይቀው ወጪ ከፍተኛ መሆን በመንግሥት በጀት ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ፣ በተለያዩ ፕሮጀክቶች የውጭ ምንዛሪ የሚጠየቁ ሥራዎችን ለማከናወን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ማጋጠሙ የፕሮጀክቶችን ትግበራ እያጓተተ መሆኑን አቶ አህመድ ገልጸዋል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ከበጀት ውጪ የተፈጸሙ ክፍያዎችን በተለይም ግሬስ ፔሬድ፣ የአደራ ተመላሽ፣ የክልል ብድርና ሌሎችን ጨምሮ ያጋጠመው የበጀት ጉድለት 145.7 ቢሊዮን ብር መድረሱን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ የበጀት ጉድለቱን ከብሔራዊ ባንክ ቀጥታ ብድር በተገኘ 57 ቢሊዮን ብር፣ ከግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ ብር 57.8 ቢሊዮን ብር ከቦንድ ሽያጭ 30 ቢሊዮን ብር መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡

በፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በተሠራው የተቋማት ኦዲት ሪፖርት የ2014 በጀት ዓመት ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት ከተሰጣቸው 24 መሥሪያ ቤቶች ውስጥ 13 ተቋማት ላይ በመመርያው መሠረት አስተደደራዊ ዕርምጃ መወሰዱን ሚኒስትሩ ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሠረት የወላይታ፣ የጋምቤላና የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱና በዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር፣ በአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የፋይናንስ ኃላፊ ላይ የገንዘብ ቅጣትና ለተቋሙ ከባድ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው፣ በኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን የፋይናንስ ኃላፊ ላይ የገንዘብና ከባድ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

ለአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ ለደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ፣ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ለጂንካ ዩኒቨርሲቲና ለቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ከባድ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የበላይ አመራሮች፣ የፋይናንስ ኃላፊዎችና ለኢትዮጵያ ስታትቲስቲክስ አገልግሎት ከባድ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...