Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ማራቶን ሞተር በመጪው ዓመት በአገር ውስጥ የተመረቱ ተሽከርካሪዎችን ለገበያ እንደሚያቀርብ አስታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ማራቶን ሞተር ኢንጂነሪንግ በመጪው ዓመት መጨረሻ ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ የተመረቱ ተሽከርካሪዎችን፣ ለገበያ ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በተሽከርካሪዎች ንግድ በ2001 ዓ.ም. ሥራ የጀመረው ማራቶን ሞተር ኢንጂነሪንግ ከተቋቋመ በኋላ ለአራት ዓመታት ያህል በዚህ ሥራ ተሰማርቶ የቆየ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የተለያዩ የሐንዳይ ተሽከርካሪዎችን በ2011 ዓ.ም. በአገር ውስጥ መገጣጠም መጀመሩ ይታወሳል፡፡

የተሽከርካሪ መገጣጠሚያው ከምሥራቅ አፍሪካ ብቸኛው መሆኑንና በአሁኑ ጊዜ በዓመት እስከ 20 ሺሕ ተሽከርካሪዎችን እንደሚገጣጥም፣ የማራቶን ሞተር ኢንጂነሪንግ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መልካሙ አሰፋ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በ2017 ዓ.ም. በኩባንያው የሚገጣጠሙ አብዛኛዎቹ ተሽከርካሪዎች የኤሌክትሪክ እንደሚሆኑ የገለጹት አቶ መልካሙ፣ ከተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ባለፈም፣ በዓመቱ መጨረሻ ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ የተመረቱ ተሽከርካሪዎችን ለገበያ ለማቅረብ እየሠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ የማምረት ውጥኑ 99 በመቶ የተሠራበት መሆኑንና አሁን ካለው ኢንቨስትመንት አንድ በመቶ የሚሆኑ ሥራዎችን ብቻ በመጨመር ወደ ማምረት መግባት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ ባለፉት አሥራ አምስት ዓመታት ኩባንያው የሠለጠነ የሰው ኃይል ማግኘት ፈተና ሆኖበት እንደነበርና ይህንንም ለመፍታት አሁን ላይ አምስት የሥልጠና ማዕከላትን በመገንባት ከዩኒቨርሲቲ የሚወጡ ተማሪዎችን በማሠልጠን ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡

የፋይናንስ አቅርቦት ችግር በተለይም የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሌላኛው ችግር እንደሆነና ይህን ችግር በተቻለ መጠን ለመፍታትም ከመድኃኒት፣ ከነዳጅና ከማዳበሪያ በመቀጠል ለአገር ውስጥ አምራቾች የተሻለ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት መኖሩን በመረዳት ወደ ሥራው መግባታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ አሁን ኩባንያው አምስት ቢሊዮን ብር ኖሚናል ካፒታል እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ መንግሥት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት በመከልከል አዳዲስ መኪኖች ብቻ እንዲገቡ ማድረጉን አስታውሰው፣ የነዳጅ ተሽከርካሪዎች ቀስ በቀስ በኤሌክትሪክ የመተካት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

አክለውም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ስታንዳርድ መዘጋጀቱንና በአሥር ዓመቱ የመንግሥት የልማት መሪ ዕቅድ 4,800 የኤሌክትሪክ አውቶብሶችና 148 ሺሕ አውቶሞቢሎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ማራቶን ሞተር ኢንጂነሪንግ የተመሠረተበትን 15ኛ ዓመት ግንቦት 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች በኃይሌ ግራንድ ሆቴል አክብሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች