Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የቀሽሞች ድራማ!

ሰላም! ሰላም! ሰላም ለሁላችን ይሁን፡፡ ለተደሰታችሁም ሆነ ለአዘናችሁ ሰላማችሁ ይብዛ፡፡ በዚህ ዘመን ዓለም አቀፋዊነት የነገሠ ይመስል የአርሰናልና የማንቸስተር ሲቲ የዋንጫ ፉክክር ደማችንን ከፍና ዝቅ ሲያደርገው ከረመ፡፡ ውጤቱ ምንም ይሁን እስከ መጨረሻው የውድድሩ መርሐ ግብር ቀን ድረስ ዋንጫውን ማን እንደሚያነሳው አለመታወቁ መሰለኝ፣ ብዙዎችን በደስታ ሲያፍነከንክ የሰነበተው፡፡ እውነት ነው ቀድሞ የተበላ ዕቁብና ዋንጫ ያን ያህል ስሜት ስለማይሰጥ፣ እስከ መጠናቀቂያው ቀን ድረስ አንገት ለአንገት ተያይዘው ቁጭ ብድግ ስላደረጉን ሁለቱም ቡድኖች ምሥጋና ይግባቸው፡፡ ዋንጫውን ማንም ያንሳው ማን የእኔ ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገር ግን ያንን የመሰለ ትንፋሽ የሚያሳጥር ዓውድ መፈጠሩ ነው ዋናው ደስታና ቁምነገር እላለሁ፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅም፣ ‹‹አንበርብር ልክ ሲጀመር መጨረሻው እንደሚታወቅ ቀሽም ድራማ ቢሆንማ ኖሮ ማን ጣፋጭ ሰንበቱን ያባክን ነበር…›› ያለኝ ይህንን እውነታ ያረጋግጥልኛል፡፡ ለዚህም ነው በውጤቱ የተደሰታችሁም ያዘናችሁም ያንን የመሰለ መልካም አጋጣሚ ለከርሞ እንዲደገም መልካም ምኞታችሁ ይሁን፡፡ ምሁሩ ወዳጄ እንዳለው በቀሽም ድራማ ትወና ይሰለቻል፡፡ ኧረ ያቅለሸልሻል!

ወደ መደበኛው ወጋችን መለስ ስንል ለመሆኑ እኛ ለምን ይሆን ቡድን የምንወደው ግን? ስፖርት እንጂ ሐሳብ የቡድን ሥራ ይፈልጋል እንዴ? እኔ እኮ ግራ ገባኝ እናንተ? ‹‹በሸንጎ ቢረታ ሚስቱን ገብቶ መታ…›› አሉኝ አዛውንቱ ባሻዬ፡፡ ‹‹ማን ነው እሱ?›› ስላቸው፣ ‹‹ማንነቱ ምን ይሠራልሃል? ዝም ብለህ ከምሳሌው ተማር። ምነው አንተም በማንነት ስም የሚቀነቀን እኔነት አለብህ?›› ብለው ቆጣ አሉ። እኔነት የሰው ልጆች ሁሉ ደካማ ጎን እንደሆነ እያወቁ ባሻዬ ሲቆጡ ግራ ገባኝ። መቼም ዘንድሮ ተስፋ ቆርጦ ተስፋ የሚያስቆርጠን በዝቷል። ቆይ ለምን ብቻቸውን አይቆርጡም? ለምን ሌላውን ጭምር ከእንጀራ ገመዱና ከመኖር ስስቱ ጋር ያቆራርጡታል? እንጃ ዘንድሮስ። ‹ኮሜንት› በቡድን፣ ‹ላይክ› በቡድን፣ ‹ብሎክ› እንዲሁም ‹ኢግኖር› በቡድን ሆኗል ይላሉ። ከሁሉ ከሁሉ ግን የሚገርመኝ እያንዳንዷ ጥቃቅን ነገር ሳትቀር እንደ ‹ሳውንድ› ትራክ ፖለቲካዊ አጀንዳ መያዟ ነው። ያውም በመንጋ ፖለቲካ ተቀፍድዳ፡፡ ይገርማል!

ምን ልበላችሁ በቃ አንዲት እርግብ ከትናንት ወዲያ ተመርቆ ሥራ ከጀመረው የእከሌ ሕንፃ መስታወት ጋር ተጋጭታ ሕይወቷ አለፈ ሲባል አንዱ ከተፍ ብሎ፣ ‹‹የሰው አልበቃ ብሏችሁ ደግሞ ምንም የማያውቁትን እንስሳት መግደል ጀመራችሁ?›› ብሎ ኮሜንት ይሰጣል። ያዝ እንግዲህ ይባልልኛል። አንዱ በቀደደው መንቆርቆር ነው። ግር ብለን እንነዳዳለን። ‹‹የእከሌ ትርፍ አንጀት ፈንድቶ ወደ ሕክምና ጣቢያ ሳይደርስ ሕይወቱ አለፈ…›› ሲባል፣ ‹‹ይህንን ሁሉ ዓመት ሙሉ ገዝታችሁ አንድ እንኳ በአቅራቢያችን በፍጥነት የምንደርስበት ሆስፒታል የለም…›› ብሎ አንድ መጀመር ብቻ ነው የሚጠበቅበት። ሌሎቻችን መግተልተል ነው። ደላላው አንበርብር ምንተስኖት፣ ‹‹በአዕምሮ ትተን በእግር ማሰብ ጀምረናል…›› አለ ቢባል፣ ለምሳሌ ስንት ምሁር ባለባት አገር በማይም ደላላ እንመከር ማለት ብቻ ነው የሚጠበቅባችሁ። ቡድን ይኑራችሁ እንጂ ተከታዩ ሺሕ ነው፡፡ ማን ነበር ‹የዝንጀሮ መንገድ ቢከተሉት ገደል› ያለው ያኔ በደጉ ዘመን ያስብላል እኮ ይህ ጊዜ፡፡ ወይ ጊዜ!

እናላችሁ የሰሞኑ መብራት መጥፋት ከዝናቡ መጣሁ ቀረሁ ጋር ተደርቦ ይኼ በተነዱበት መነዳትና ያለ ምክንያት ማሰብ በየአቅጣጫው ሲወረኝ፣ እውነቴን ነው የምላችሁ ነገር ሁሉ ይሰለቸኝ ጀምሯል። ለምን የሚሉት ጥያቄ ጠፍቷል፣ ተሰዶብናል። የት? እንዴት? መቼ? ቀብረናቸዋል። አስቡት እስኪ እንደ ደንባራ በቅሎ ቃጭል አንጠልጥሎ ስንሆን። እናማ ተማርኩ አወቅኩ የሚለው ደግሞ ባሰ። በቀደም ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር ቁጭ ብለን አንድ ካፌ ውስጥ ካፊያ እንጠለላለን። አንዱ ድንገት ደርሶ፣ ‹‹ሰው አለው?›› አለን። ወንበሩን መሆኑ ነው። ‹‹የለውም ውሰደው…›› አለው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፡፡ ከዚያ ገና ሳይቀመጥ፣ ‹‹ለነገሩ ዘንድሮ እንኳን ወንበሩ መንበሩስ ምን ሰው አለው ብላችሁ ነው?›› ብሎ ጀመረላችኋ። እንኳን ይህችን የዝንብ ጠንጋራ ቀርቶ የዝንብ ወፈፌም እናውቃለን አልኩና በልቤ፣ ‹‹ቢል ታመጣልን?›› አልኩት አስተናጋጁን። ‹‹ካፊያው ያባራ እንጂ ቆይ…›› ሲለኝ የባሻዬ ልጅ ያ ነገረኛ አሁንም ሳይፈቀድለት፣ ‹‹አዬ እንጃ የዘንድሮ ካፊያስ እንዳያያዙ ከሆነ የሚያባራ አይመስለኝም…›› ብሎ ብቻውን ሳቀ። አሳሳቁ ታዲያ ቲፎዞ ፍለጋ ስለሚመስል ነገረ ሥራው አላማረኝም፡፡ ምን ልበል ታዲያ!

‹‹ሰው ብርቱ ነው በጎርፍ ውስጥ አረማመድ ያሳምራል…›› ያለው ገጣሚ ስንኝ ትዝ ብሎኝ ፈገግ ስል ለእሱ የሳቅኩለት መስሎት፣ ‹‹እኔ ምለው ግድ የለም ዛሬ እኔ ልጋብዛችሁ…›› አለን። ይኼውላችሁ እንግዲህ ገና ለገና ጥርስ ለጥርስ ተለካካን ብለን፣ በአጋጣሚም በስህተትም ብርጭቋችን ተጋጨ ተብሎ እዚህ ደረጃ ደርሰናል። ፆታዊ ጥቃት ያደረሰ ብቻ ይመስላችኋል አይደል ደፋሪ? የክብር፣ የሐሳብ ነፃነት ተጋፊ፣ የልዩነት ፀሮችም እኮ ከዚያ በላይ ናቸው። የሰውዬውን ሁኔታ መልሼ መላልሼ ሳስበው ስለተበሳጨሁ፣ ‹‹እቸኩላለሁ…›› ብዬ በካፊያው ውስጥ መሮጥ ጀመርኩ። ለወትሮው ካፊያና ዶፍ ነበር የምንጠለለው። ይኼውላችሁ ዘንድሮ ከሰው መጠለል ጀምረናል። አንዳንዴ የአንዳንዶችን ነገር ሳስብ የሆነ መዛነፍ ይታየኛል፡፡ ወይ በአካል ተመሳስለን በጭንቅላት ተራርቀናል፣ ካልሆነም እንዳንግባባ ተደርገን ተረግመናል እላለሁ፡፡ አንዳንዱ እኮ አንገቱ የተሸከመው ጭንቅላት ሳይሆን ኮብልስቶን እየመሰለ ነው፡፡ ምን ልበል ታዲያ!

መቼስ አንዳንዴ ስሜታዊ እየሆንኩ ጨዋታዬ እንደ ዘመኑ ተቃዋሚዎችና ደጋፊዎች ድርቅ ይላል አይደል። ምን ላድርግ ቀልድ ጠፋ። ማለቴ ቀልዱ ሁሉ ያው እንደምታዩት የምር የምኖረው ኑሮ ሆኗል። ቀልድ አሯሯጫችን መሆኑ ቀርቷል። እንደ ሳይንስ ፊክሽን ማለቴ ነው። የዛሬን አያድርገውና በቀደሙት ዘመናት አሁን በእጃችን የጨበጥናቸው ኪሳችን የከተትናቸው፣ ቆፍረን የቀበርናቸው ቴክኖሎጂዎችና የጦር መሣሪያዎች ትናንት ተረት ተረት ነበሩ። ቀልድና ሳይንስ ፊክሽን የሚያመሳስላቸው ይኼው ነው። ትናንት ቀልድና ስላቅ እንደ ዛሬው እያንዳንዳችን የሚያጋጥመን የምኖረው ሀቅ አልነበረም። በአብዛኛው ነው የምላችሁ። ዘመኑ የመረጃና የማስረጃ ነውና ማስረጃዬን ላቅርብ። በቀደም አንድ ቪላ ቤት እያሻሻጥኩ ነበር። የማሻሽጠው ቤት የነበረበት አካባቢ የአንድ ዘመናዊ ሥጋ ቤት ምረቃ ስለነበረ ሞቅ ተደርጎ በሁለት ሞንታርቦዎች ሙዚቃ ተከፍቷል። መቼም የዘንድሮ ሥጋ ቤቶች እንደ ኬክ ቤቶች መስፋፋት ያየ ሰው ምን እንደሚል እንጃ። በከተማው አራቱም ማዕዘናት የአንበሳ ልደት በየቀኑ የሚከበር ይመስል ዘመናዊ ሥጋ ቤቶች እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ የሥጋ አመጋገብ ለጥቂቶች ቀላል የሆነበት አገር ውስጥ፣ ‹‹አምስት በመቶ የሚሆኑት ዳቢት ከሻኛ ሲቆርጡ፣ ብዙኃኑ ግን ቁርጡን አውቆ ተቀምጧል…›› ሲባልም ሰምቻለሁ፡፡ እውነት አለው!

ከሚመረቀው ሥጋ ቤት ከተለቀቀው ሙዚቃ፣ ‹‹…ሎሚ ብወረውር ደረቱን መታሁት አወይ ኩላሊቱን ልቡን ባገኘሁት…›› የሚለው ነፍሷን ይማረውና የዘነበች ታደሰ (ጭራ ቀረሽ) ዘመን ተሻጋሪ ዘፈን ሲጀምር በአካባቢው የነበረ ወፈፍ ያደረገው ጎልማሳ በትዊስት ሥልት ሲውረገረግ ቆይቶ፣ ‹‹ዳቢት፣ ሽንጥ፣ ሻኛ፣ ሰብራዳ፣ ዘርፍ፣ ነብሮና ጎድን እየጎመዱና ውስኪ እየገለበጡ ከመጨናነቅ እንዲህ በንፁህ አየር በዳንስ ዕብድ ብሎ ውኃ መጎንጨት ጤና ነው…›› እያለ ሥጋ ቤቱ ውስጥ ያሉትን ታዳሚዎች ሲሸረድድ ሳቄ አመለጠኝ፡፡ ሰውየው የእኔ ሳቅ ተጋብቶበት ነው መሰል እሱም እየሳቀ፣ ‹‹ጋሼ እውነቴን እኮ ነው፡፡ እነዚህን ዘመናዊ መኪኖች ደርድረው ውስጥ ጮማና ብርንዶ በውስኪ የሚያወራርዱ፣ እስኪ አንድ ቀን መቄዶንያ ወይም ሌሎች ዕርዳታ የሚፈልጉ ወገኖች ዘንድ ሄዳችሁ ጎብኙ ብትላቸው አይሰሙህም፡፡ ከጠዋት እስከ ምሽት ብሎም እስከ ውድቅት መብላትና መጠጣት ፅድቅ የሚመስላቸው በዝተዋል…›› ሲለኝ አስደነገጠኝ፡፡ በዚህን ያህል መጠን ትዝብት የሚያቀርብ እሱን መሰል ሰው አጋጥሞኝ ስለማያውቅ ብደነግጥ አይግረማችሁ፡፡ ጎበዝ እስቲ እየተሳሰብን እንጂ፡፡ እንዲህ ዓይነት ጠልቆ ተመልካች ባለበት አገር ውስጥ ራስን መግራትና መልካም ለመሥራት መነሳት ይታሰብበት፡፡ አደራ!

ታዲያላችሁ ኮሚሽኔን በስልኬ ተቀባብዬ ወደ ቤቴ ተጣድፌ ስሄድ ማንጠግቦሽ ቤቱ እንደተዝረከረከ ለጥ ብላ ተኝታለች። ሰዓቴን ሳይ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ይላል። እንግዲህ ተመልከቱ ይኼን እያየ እየሰማ ራሱ የኢትዮጵያን ዕድገት የሚጠራጠር አለ? ለነገሩ የእኛ እንቅልፍ በዕድገት የሚረዝም በረሃብ የሚያጥር አይደለም፡፡ እሱ በጥበቡ ሲሠራን በተፈጥሯችን ተኙ ብሎ ፈጥሮናል። አዛውንቱ ባሻዬ ይኼን አስተሳሰቤን ስለሚጋሩኝ፣ ‹‹የእኛ ጠላታችን ከድህነት ጎን ለጎን የሚቀሰቅሰን ብቻ ነው…›› ይሉኛል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ቀስቃሽ በአየቅጣጫው የዘመተበት ሁኔታ ነው ያለው (ዕድሜ ለአገራችን የሶሻል ሚዲያ ወሬ የሌለ የሌለ አማርኛ ለምደን፣ ይኼው በጥንቱም በአሁን ጊዜ ሰውም መሳቂያ ሆነን ቀረን) ሁኔታ ብል በአንድ ወቅት በቴሌቪዥን ዜና አንድ ሮቦት አይቼ እንደነበር አስታውሳለሁ። ሮቦቷ ሴት ናት። ይገርማል እኮ እናንተ። እንደ ምዕራባውያን ኑሮ ግራ ያጋባን የለ? ተፈጥሮ ፆታ መዳድባ ቦታና ሥፍራ እያቀያየረች ስታዞርብን ከርማ ደግሞ፣ በጎን ሰው ሠራሹን ነገር ሴት ወንድ እያለች ፆታ ታድላለች። ድንቅ ነው!

ቆይ ግን ታዳዩና አዳዩ የሚገናኙበት ዘመን ሳይመጣ እንሞት ይሆን? ብቻ ወደ ጀመርኩት ልመለስና ያቺ እንስት ሮቦት ሥራዋ አዛውንቶችን ማጫወት ነው። አንድ ጋዜጠኛ ቃለ መጠይቅ ሲያደርግላት፣ ‹‹እንዲያውም ሥራዬ ማውራት ነው። በወሬ ዕጦት የተጎዱ ሰዎችን እያነጋገርኩ ማጫወት የሕይወቴ ግብ ነው…›› ስትለው ያለ አስተርጓሚ ገባኝ። ደግሞ ለዚህ አስተርጓሚ ልጥራና ጉድ ልሁን? በቀደም ይኼው እንዲሁ ዓይነት ስለሕይወት ግብ የሚጫወትን ጎልማሳ ቃለ መጠይቅ እያዳመጥኩ አልገባህ ብሎኝ አንድ የሠፈር ልጅ ጠራሁና ምን እንደሚል ንገረኝ እለዋለሁ፣ ‹‹የሕይወቴ ለውጥ የመጣው ሚስቴ የሞተች ቀን ነው ይላል…›› አይለኝ መሰላችሁ? ሰው እንዴት አካሉ ጎድሎ በቀጥታ ስለለውጥ ያስባል? ባንቀብርም እኮ ሕመሙ ይገባናል። የማይገባቸውማ ይኼው ‹ሙቱ እንሙት፣ ተኙ እንተኛ› እያሉ እያሉ በደንታ ቢስ ፉከራቸው የኢትዮጵያን እናቶች የመኖር ጉጉት ያደበዝዛሉ። ሰው ከታሪኩ ባይማር፣ ሲነገረው ባይገባው፣ ሲጨቀጭቁት ቢደክመው እንዴት ከጎረቤቱ መማር ያቅተዋል? እንጃ!

በሉ ልንሰነባበት ነው። የሕይወትን ዘርፈ ብዙ ገጽታ ታዝቤ ሳልጨርስ ማንጠግቦሽ ትዝ አለችኝ። አስተኛኘቷ ደስ አላለኝም። ከመጮኼ በፊት አንዴ ልሞክራት ብዬ ነካ አደርጋታለሁ፣ ‹‹የቀሰቀሷቸውን ደንበኛ አሁን መነሳት አይችሉም። እባክዎ ከሰዓታት በኋላ እንደገና ይሞክሩ…›› ብለኝ ተገላብጣ ተኛች። ደህና ከሆንሽስ ብዬ ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር ተያይዘን ወደ ግሮሰሪያችን አመራን። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ የማንጠግቦሽን ኩመካ ሰምቶ ሲያበቃ፣ ‹‹አንዳንዱ እንቅልፍ እኮ ለበጎ ነው አንበርብር። ባንነቃ ባንቀሰቀስ የሚሻለን ጊዜ  አለ ሰሚ የለም እንጂ…››  ሲለኝ፣ ‹‹አንዳንዴ ሳምንቱ ቅጣቱ ሲከብድ፣ ምንም አይሳካም ከእሑድ እስከ እሑድ…›› ብሎ አንዱ በአንድ ወቅት ያጨደው መከራ ትዝ አለኝ። ምነው የዘንድሮ ባሰ አልኩ። መነካት በማይገባን ጎናችን እየተነካን፣ መቀስቀስ በሌለብን ሰዓት እየቀሰቀሱን እኛም አቤት እያልን ከእሑድ እስከ እሑድ ከትውልድ እስከ ትውልድ፣ ከዓመት እስከ ዓመት፣ ከሚሊኒየም ሚሊኒየም፣ እንዲሁም እስከ ዛሬ የተባላነው አይበቃም ጎበዝ? እስከ መቼ በእንቅልፍ ላይ እንቅልፍ? እስከ መቼ? እስከ መቼ? ከዓመት እስከ ዓመት፣ ከእሑድ እስከ እሑድ መና ይቀራል? ሌላው ቢቀር ለዕድሜ እንዘን፡፡ ሺሕ ዓመት ላይኖር ራሳችንንም አገራችንንም አናሰቃይ፡፡ ባለፈው ሳምንት እንደ ተጠናቀቀው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ፍልሚያ እኛም ጅማሬያችንን በአስደሳች ፍፃሜ እንቋጨው፡፡ የቀሽሞች ድራማ አጃቢ አንሁን፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት