Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊጠብቆ የማቆየት ችግር የገጠመው የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት

ጠብቆ የማቆየት ችግር የገጠመው የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት

ቀን:

በዓለም ዙሪያ እየተከሰቱ ያሉ የጎርፍ መጥለቅለቆች፣ የደን ቃጠሎዎች፣ ድርቅ፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብና የመሳሰሉት አደጋዎች መነሻቸው የተፈጥሮ መዛባት ስለመሆኑ የዘርፉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ፡፡ ተፈጥሮ ተጠብቆ እንዳይቀጥልና ለውስብስብ ችግር እንዲጋለጥ የሚያደርጉትን በርካታ ምክንያቶችም ይጠቅሳሉ፡፡ በዋናነትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የዓለም ሕዝብ ቁጥር ያነሳሉ፡፡

ጠብቆ የማቆየት ችግር የገጠመው የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የጣና ባዮስፊር ሪዘርቭ

የሕዝብ ቁጥር ሲጨምር በዕፅዋት፣ በእንስሳትና በሌሎች ሕይወት ባላቸውና በሌላቸው ፍጥረታት ላይ የጭካኔ ክንዱን ያሳርፋል፡፡ ዕፅዋትን፣ የዱርና የቤት እንስሳትን ለምግብነት፣ ለቤት መሥሪያና ለሌሎች ፍላጎቱ ሲያውል፣ የሰማይ ወፎችንም ሆነ የባህር ዓሳዎችን ዝርያቸው እስኪጠፉ ድረስ ያድናቸዋል፡፡

ከምርትና አገልግሎት የሚወጡ ተረፈ ምርቶች የሰማይ አየሩን ሳይቀር በመበከል ተፈጥሮን ያዛባሉ፡፡ እንደ ቀላል የሚታዩና በየዕለቱ የሰው ልጆች የሚፈጥሯቸው ክስተቶች ተጠረቃቅመው በአሁኑ ወቅት የሚታዩ ችግሮችን ወልደዋል፡፡

- Advertisement -

እነዚህ ችግሮች የዓለምን የብዝኃ ሕይወት ሥርዓት በማዛባት ተፈጥሮ ከመስመር እንድትወጣ ያደርጋሉ፡፡ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋና እየጨመረ በመምጣቱ መንግሥታት፣ ተመራማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጋራ ተወያይተው  ችግሮቹን ለመቀነስ የመፍትሔ መንገድ ይበጅላቸው ዘንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.ኤ.አ. ከ2000 ጀምሮ በየዓመቱ ግንቦት 14 ቀን የዓለም ብዝኃ ሕይወት ቀን ታስቦ እንዲውል የጋራ ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ጠብቆ የማቆየት ችግር የገጠመው የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ማጃንግ

በስምምነቱ መሠረተ፣ የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ግንባት 14 ቀን 2016 ዓ.ም. የብዝኃ ሕይወት ቀንን በተለያዩ መርሐ ግብሮች አስቦ ውሏል፡፡ የዓለም ብዝኃ ሕይወት ቀን ‹‹የዕቅዱ አካል እንሁን›› በሚል መሪ ቃል ከግንቦት 8 ቀን ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ የቆየ ሲሆን፣ ለብዝኃ ሕይወት መጥፋትና መመናመን መንስዔ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታትና ዘላቂነትን ለማምጣት የአመለካከት፣ የፖሊሲ የአሠራሮችና መሠረታዊ የሆኑ የአስተዳደራዊ መዋቅሮች ለውጥ ሊኖር እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

በብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ውስጥ በዋናነት የአካባቢ ማኅበረሰብን ተሳታፊ ማድረግ፣ ባህላዊ ዕውቀቶችን ከቴክኖሎጂው ጋር ማጣመር አገር በቀል ዝርያዎችን ጠብቆ ለማቆየት እንደሚረዳ ተመላክቷል፡፡

በመርሐ ግብሩ ከብዝኃ ሕይወት ጋር የተያያዙ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው  ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፣ ተጨማሪ የብዝኃ ሕይወት ማስጠበቂያ ሥፍራዎችን (ባዮስፊር ሪዘርቮች)  በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ እየተሠራ መሆኑን በኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ግርማ እሸቱ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ግርማ (ዶ/ር)፣ የባዮስፊር ሪዘርቭ ፖሊሲ ረቂቅ ይዘትና ፋይዳ የሚዳስስ ሰነድ አቅርበዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ያስመዘገበቻቸውን አምስቱን የባዮስፊር ሪዘርቭ ቦታዎች ለማስተዳደር ተቋማዊ የሕግ፣ የፖሊሲና የስትራቴጂ ማዕቀፍ ያስፈልጋታልም ብለዋል።

ቦታዎቹን ለማስተዳደር እስካሁን ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም የለም ያሉት ግርማ (ዶ/ር)፣ በብሔራዊ ኮሚቴ እየተመራ እንደሆነ፣ ነገር ግን አሠራሮቹ ዘለቄታዊና ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ ከተፈለገ  በሕግ መደገፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ባዮስፊር ሪዘርቮቹ ለተለያዩ ጉዳቶች እየተጋለጡ ነው የሚሉት ተመራማሪው፣ ለአብነትም የጣና ሐይቅ በመጤ አረም ዝርያ መጠቃቱን አንስተው፣ በሌሎቹም ተመሳሳይ ጉዳቶች እየደረሱ ነው ብለዋል።

የባዮስፊር ሪዘርቮች በቁጥር እንዲጨምሩ፣ ያሉትም ከንክኪ ነፃ እንዲሆኑ፣ እንዲጠበቁና  እየታዩ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ ረቂቅ ፖሊሲው ፀድቆ ወደ ሥራ መግባት እንዳለበት ግርማ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

በረቂቅ ደረጃ ያለው ፖሊሲ ወደ ሥራ እንዲገባ ኢንስቲትዩቱ ተጠሪ ከሆነለት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር ውይይት እያደረገ ሲሆን፣ በቀጣይ የመንግሥትን ይሁንታ አግኝቶ የሕግ ማዕቀፉ ተግባር ላይ ሲውል፣ ኢንስቲትዩቱ ተረክቦ ለማስተዳደር ዝግጁ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የበርካታ ብዝኃ ሕይወት መገኛ ናት የሚሉት ተመራማሪው፣ ነገር ግን ጠብቆ ከማቆየት ጀምሮ ተግዳሮቶች እያጋጠሙ እንደሆነ፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ ደካማ ኢኮኖሚ መኖርና ሌሎችም ሰፊ ችግሮች የመንግሥትን ቁርጠኝነትና የዜጎችን ርብርብ የሚጠይቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወቷን ከማስጠበቅ አንፃር ከሌሎች አገሮች ጋር ስትነፃፀር ያሳካቻቸውና የጠበቀቻቸው ቢኖሩም፣ በርካታ ያልተገበረቻቸው ጉዳዮች ስለመኖራቸው አንስተዋል።

ኢንስቲትዩቱ ላለፉት 50 ዓመታት በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን የገለጹት ግርማ (ዶ/ር)፣ በአሁኑ ወቅት ባለው ብቸኛ ብሔራዊ ጅን ባንክ፣ ለትውልድ የሚተላለፍ በርካታ የግብርና ብዝኃ ሀብት ክምችት ማስቀመጡን ተናግረዋል።

ነገር ግን ዝርያዎችንና አካባቢዎችን ባሉበት ቦታ ጠብቆ ከማቆየት አንፃር ክፍተቶች ስለመኖራቸው፣ ዝርያዎች እንዳይጠፉና ሥነ ምኅዳሩ እንዳይጎዳ ሁሉም ማኅበረሰብ ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ዓለም አቀፉ የብዝኃ ሕይወት ስምምነት የተለያዩ መሠረቶችን የያዘ ነው ሲሉ ለሪፖርተር የተናገሩት ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፈለቀ ወልደየስ (ዶ/ር) ናቸው።

ከስምምነቶቹም የብዝኃ ሕይወትን ማንበር ወይም ጠብቆ ማቆየት፣ የሀብቱን ዘላቂነት አስጠብቆ መቆየት እንዲሁም ከብዝኃ ሕይወት የሚገኘውን ጥቅም ፍትሐዊ በሆነ መልኩ መጋራት  የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።

በስምምነቱ ከ190 በላይ አገሮች የተካተቱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ስምምነቱን ተቀብለው ከሚያስፈጽሙ አገሮች ተጠቃሽ ናት ብለዋል። ኢትዮጵያ “ባዮስፊር ሪዘርቭ” የተባሉ የብዝኃ ሕይወት ማስጠበቂያ ሥፍራዎች መናኸሪያ ናት ያሉት ፈለቀ (ዶ/ር)፣ እስካሁን አምስት የሚደርሱ ቦታዎች ባዮስፊር ሪዘርቭ በመባል በዩኔስኮ ማስመዝገባቸውንና በቀጣይ ደግሞ ሌሎችን ለማስመዝገብ እየሠሩ መሆኑን አክለዋል።

ጥብቅ የባዮስፊር ሪዘርቮች ተብለው ከተለዩት አምስት አካባቢዎች መካከል አራቱ ደንን መሠረት ያደረጉት ሸካ፣ ማጃንግ፣ ከፋና ያዩ መሆናቸውን፣ አንደኛው ደግሞ  ብቸኛው የጣና ባዮስፊር ሪዘርቭ እንደሆነ ፈለቀ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

በቀጣይ በዩኔስኮ ይመዘገባሉ ተብለው ከታሰቡት የባዮስፊር ሪዘርቮች በጋምቤላ ክልል የአኝዋክ ባዮስፊር ሪዘርቭና በትግራይና በአፋር አዋሳኝ አካባቢ የሚገኙት ደሰዓ የተሰኙ ቦታዎች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

የብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ሥራ ብዙ ተግዳሮቶች ያሉበት በመሆኑ በአንድ ተቋም ብቻ ችግሩ ሊፈታ አይችልም ሲሉም ያብራራሉ።

እያንዳንዱ ሰው ለብዝኃ ሕይወት መጠበቅ፣ መስፋፋትና መበልፀግ ምክንያት በመሆኑም፣ ተጠያቂ ነው ሲሉ ፈለቀ (ዶ/ር) አብራርተዋል።

ስለብዝኃ ሕይወት ከተማረው ማኅበረሰብ እስከ መደበኛው ዜጋ ድረስ ከፍተኛ የግንዛቤ እጥረት አለ የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ችግሩ ዓለም አቀፋዊ በመሆኑ ትልቅ ሥራን እንደሚፈልግ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...