Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊ20/80 እና 40/60 ያልደረሳቸው ለግንባታ የተሰጣቸው ቦታ በችግር የተተበተበ በመሆኑ መቸገራቸውን ተናገሩ

20/80 እና 40/60 ያልደረሳቸው ለግንባታ የተሰጣቸው ቦታ በችግር የተተበተበ በመሆኑ መቸገራቸውን ተናገሩ

ቀን:

  • ያዋጡት 4.5 ቢሊዮን ብር በዝግ አካውንት ከተቀመጠ ዓመት አልፎታል

በአዲስ አበባ በ2005 ዓ.ም. የ20/80 እና የ40/60 የቤት ፕሮግራሞች ተመዝግበው ዕጣ ያልወጣላቸው ነዋሪዎች፣ በከተማ አስተዳደሩ አማካይነት በ54 ማኅበራት ቢደራጁም፣ ግንባታ መጀመር አለመቻላቸውን ተናገሩ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የቤቶች አስተዳደር ቢሮ በአቃቂ ቃሊቲና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍላተ ከተሞች በተመረጡ ስድስት ሳይቶች ማለትም በአቃቂ ወረዳ በሰባት የተለያዩ  ሳይቶች ውኃ ልማት፣ ማረሚያ ቤት ጀርባ፣ ሃና ማርያምና ወይራ ሠፈር በተሰኙ አካባቢዎች ግንባታውን ለማካሄድ ከ4,500 በላይ ነዋሪዎች የተደራጁት በ54 ማኅበራት ነበር ብለዋል፡፡ ያዋጡት 4.5 ቢሊዮን ብር በዝግ አካውንት ከተቀመጠም ዓመት እንዳለፈው ተናግረዋል፡፡

ማኅበራቱ ግንባታ እንዲያካሂዱበት የተሰጣቸው ቦታ የካሳ ክፍያ ያልተጠናቀቀበትና ተጨማሪ ካሳ የተጠየቀበት፣ መንገድ የሌለው፣ በሃይማኖት ተቋም የታጠረና የተያዘ፣ ለግንባታ የማይመች፣ ወንዝ ያለበት፣ መሬቱ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦና መሰል ችግሮች ያሉበት በመሆኑ ወደ ግንባታ መግባት አልቻልንም ያሉ ማኅበራት ቅሬታቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ጨፌ ሳይት በሚባለው የግንባታ ቦታ ለ17 ማኅበራት ታስቦ የተዘጋጀ ቢሆንም፣ 15 ማኅበራት  ግንባታውን ለማካሄድ ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ከከፈሉ ከዓመት በላይ እንደሆናቸው የሳይቱ አስተባባሪ አቶ መዝገበ ዓለሙ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

አቶ መዝገብ አክለውም የኮንዶሚኒየም ቤት ልማት ፕሮግራም ተመዝጋቢዎችን በማደራጀት፣ በጋራ ሆነው ሕንፃ በመገንባት ተጠቃሚ ለማድረግ ተብሎ የወጣውን መመሪያ መሠረት በማድረግ ግንባታውን ለማካሄድ መነሳታቸውን ይገልጻሉ፡፡ በ2005 ዓ.ም. የ20/80 እና የ40/60 የቤት ፕሮግራሞች ተመዝጋቢዎች በጋራ ሕንፃ መኖሪያ ቤት የኅብረት ሥራ ማኅበር ተጠቃሚ ለማድረግ የወጣው መመርያ ላይ እንደተብራራው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ቢሮ የለማ መሬትና የቤት ዲዛይን ያቀርባል፡፡

ይሁን እንጂ ከሳይቶቹ መካካል ጨፌ የተሰኘው ሳይትና 2,000 አባላት ላሏቸው 15 ማኅበራት የተሰጠው ቦታ፣ ተሽከርካሪና ማሽን ቀርቶ እግረኛ የማያስገባ መሆኑን አቶ መዝገበ አስረድተዋል፡፡  

ቦታው ከመደልደሉ በፊት በቂ ጥናት ያልተደረገበት መሆኑ ማሳያው በሳይቱ አካባቢ ካሉ ሠፈሮች የሚወጣውን ፍሳሽ ወደ አቃቂ ባዮጋዝ ጣቢያ የሚወስድ የተቀበረ ቱቦ መኖሩ፣ ሰፊ የሚሆነው የግንባታው ቦታ በመስጊድ መታጠሩና መሬቱ ወንዝ እንደሚያልፍበት፣ ከጅምሩ የዲዛይን ችግር ያለበት መሆኑንና ያልተጠና ነው ብለዋል፡፡

በዚህም የተነሳ መስጊዱ ብዙ ቦታ በመያዙ፣ ለግንባታ ይሆናል የተባለው ቦታ ላይ ወንዝ በመኖሩና ቱቦ ያለበት በመሆኑ ወደ ግንባታ ለመግባት አልቻልንም ብለዋል፡፡ ወደ ግንባታ ለመግባት 70 በመቶ የሚሆነውን ራሳቸው፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ 30 በመቶ የሚሆነውን እንደሚሸፍን ታስቦ ማኅበራቱ 4.5 ቢሊዮን ብር በዝግ አካውንት ማስቀመጣቸውን አክለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ በመጓተቱ ምክንያት የግንባታ ዋጋ በመናር ቀድሞ ከነበረው በላይ ተጨማሪ ዋጋ ማጋጠሙ ማኅበራቱን ቅሬታ ውስጥ ያስገባ ጉዳይ መሆኑን የተናገሩት አቶ መዝገበ፣ የዋጋው መናር እንዳለ ሆኖ ወደ ግንባታ መግባት ቢቻል እንኳ አንድ መፍትሔ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

ለግንበታ ብሎ ለማኅበራቱ የተደለደለው ቦታ ተጠንቶ ያልተሠራ በመሆኑ፣ የከተማ አስተዳደሩ እንኳን ወደ ሥራ ግቡ ብሎ ደፍሮ ለመናገር መልስ መስጠት እንዳልቻለ ገልጸዋል፡፡

በማኅበራት ተደራጅቶ ለመገንባት የመጀመሪያው የሆነው ሙከራ በሞዴልነት ታስቦ ቢያዝም መጨረሻው ይህ መሆኑ አሳዛኝ ነው ይላሉ፡፡

በተመሳሳይ አቶ የኋላሸት ዓለማየሁ የተባሉ የማኅበር ሥራ አስፈጻሚ  አባል ከሁለት ዓመት በፊት ተደራጅተው ገንዘብ ከቆጠቡ አንድ ዓመት መቆጠሩን ይናገራሉ፡፡ ወደ መደራጀት ሲገባ መሠረተ ልማት የተሟላለት ቦታ እንደሚቀርብና ግንባታ እንደሚጀምር መንግሥትን በማመን ገንዘብ በዝግ ሒሳብ ማስቀመጣቸውን ያስረዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ የተስተካከለ ቦታ ከዛሬ ነገ ይሰጠናል በሚል በተስፋ እየጠበቁ መሆኑን ጠቅሰው፣ አሁን ያለበት ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ ግን በመጪው ዓመትም ወደ ሥራ እንገባለን የሚል ተስፋ የለንም ይላሉ፡፡

ግንባታውን ለመጀመር በ2013 ዓ.ም. ተደራጅተው ወደ ሥራ ሲገቡ ለባለሦስት መኝታ ዋጋ 1.5 ሚሊዮን ብር አካባቢ የነበረው አሁን ወደ አምስት ሚሊዮን ብር ከፍ ማቱን የዋጋ ንረት ጉዳይ ሌላኛው ችግር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባወጣው መመርያ ላይ እንደተብራራው፣ የኅብረት ሥራ ማኅበር አባል ሆኖ ለመደራጀት እንደ ምዝገባው ዓይነት ባለ ሦስት፣ ባለሁለትና ባለአንድ መኝታ ቤቶች ተለይተው ዋጋቸው ተቀምጧል፡፡

በዚህ መመርያ ከተጠቀሱት የቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊነትና ተግባራት መካከል ለጋራ መኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበር አገልግሎት የሚውል የለማ መሬት ከመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ጠይቆ ይረከባል ይላል፡፡ ቢሮው የተረከበውን የለማ መሬት ለአንድ ማኅበር የሚውለውን ልዩ ስም ወይም ኮድ በመስጠት ለእያንዳንዱ ማኅበር በዕጣ እንዲተላለፍ ያደርጋል ሲልም ያስረዳል፡፡

በመመርያው እንደተቀመጠው  የቤቶች የግንባታ ዋጋ ግምት ባለአንድ ምድር ቤትና ዘጠኝ ወለል፣ እንዲሁም ባለ ሁለት ምድር ቤትና 13 ወለል ያሏቸው ሕንፃዎች ይገኙበታል፡፡ በዚህ መመርያ መሠረት የሕንፃዎቹ ዋጋ ባለአንድ መኝታ ትንሹ ዋጋ 882 ሺሕ ብር ሲሆን፣ ለባለ ሦስት መኝታ ቤት አጠቃላይ ዋጋ እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር ድረስ የሚደርስ ዋጋ ተተምኗል፡፡

የማኅበሩ አባላት ከነበሩበት የ2005 ዓ.ም. የኮንዶሚኒየም ምዝገባ እንዲወጡ ተደርጎ ወደ ማኅበር መደራጀት ሲመጡ በድጋሚ ወደ ኮንዶሚኒየም ዕጣ መመለስ እንደማይችሉ ተነግሯቸውና አምነውበት እንደነበር አቶ የኋላሸት ያስረዳሉ፡፡ በ2005 ዓ.ም. ለ40/60 እና ለ20/80 የቤት ፕሮግራም ውስጥ የነበረና ወደ ማኅበር መደራጀት የገባ ተመዝጋቢ ተመልሶ ወደ ኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣና ቋት መመለስ እንደማይችል በመመርያው አንቀጽ 15 ተጠቅሷል፡፡

የቤቶች ልማት ጉዳዩን በዋነኝነት ይፈታዋል ብለው እንደሚጠብቁ የሚናገሩት አቶ የኋላሸት፣ ጉዳዩን ወደ ከንቲባ ቢሮ ለመውሰድ ቢታሰብም ቢሮው አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡ በደብዳቤ እንዲገልጽ ቢጠየቅም ጉዳዩ ከአቅሙ በላይ እንዳልሆነና መፍትሔ ለመስጠት ጠብቁ ስለመባላቸው ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በየጊዜው አዳዲስ አጀንዳ እየመጣ በመጠበቅ ጊዜው ስለመሄዱ ደግሞ ያስረዳሉ፡፡

አቶ ትንሳዔ ነብይ የተባሉ ሌላው የማኅበር ሥራ አስፈጻሚ አባል የቀረበው መሬት መመርያው ከሚለው ውጪ የለማና ለጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውል ሳይሆን፣ ለምንም ዓይነት ለግንባታ አመቺ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ ቢሮው ዲዛይን እንደሚያቀርብ በመመርያው የተጠቀሰ ቢሆንም፣ ዲዛይኑ ቀርቶ ቦታው ለግንባታ አመቺ መሆን አለመሆኑ እንኳ በውል ሳይረጋገጥ የተወሰነ ውሳኔ ስለመሆኑ አክለው ገልጸዋል፡፡

በማኅበር ተደራጅቶ ይከናወናል የተባለው ግንባታ የመጀመሪያ ሞዴል ፕሮግራም መሆኑን፣ ወይራ ሠፈር የሚባለው ሳይት ላይ ግንባታ ለማስጀመር በከተማዋ ከንቲባ አማካይነት የመሠረተ ድንጋይ የተጣለ ቢሆንም ቦታው ሁለት ካርታ ያለው በመሆኑ ወደ ግንባታ ሳይገባ አንድ ዓመት እንዳለፈው ያብራራሉ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ መኮንን በጅና (ኢንጂነር) በጉዳዩ ላይ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ ከአጠቃላይ ስድስት ሳይቶች ውስጥ የመስጊድ፣ የወንዝ ወይም ቱቦ፣ እንዲሁም የካሳ ክፍያና የመንገድ ችግር ያለው በአንድ ሳይት ብቻ መሆኑንና ቀሪዎቹ አማካሪ ቀጥረው ወደ አፈር ምርመራና የዲዛይን ሥራ ሥራ ገብተዋል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ችግር የገጠማቸውን ማኅበራት በቶሎ ወደ ሥራ ለማስገባት፣ ከከንቲባ ጽሕፈት ቤትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው በተለይም ከመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ጋር እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የግንባታ ሒደቱ መዘግየቱ ትክክል ቢሆንም የተወሰኑ ሳይቶች ውስጥ በተለይም አንዱ የፍርድ ቤት ጉዳይ ያለበት መሆኑንና ለሰኔ 2016 ዓ.ም. መቀጠሩን፣ ሌሎች የፍርድ ቤት ጉዳይ የነበረባቸው ጉዳዮች መፍትሔ አግኝተው ይግባኝም ሳይኖር ጉዳዩ መዘጋቱን አስረድተዋል፡፡

መስጊዱ አስፋፍቶ የያዘውን ቦታ ያጠረው መሬት ለማኅበራቱ ከተሰጠ በኋላ መሆኑን፣ ነገር ግን መስጊዱ አስፋፍቶ መያዙ ሲታወቅ የያዘውን ቦታ ቆርጦ በማውጣት ለግንባታው የሚሆን ቦታ ተለይቶ ካርታ ከተሠራ በኋላ በድጋሚ ለሁለተኛ ጊዜ ለማኅበሩ የተሰጠውን ቦታ አጥሮ የያዘው ቦታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት በአስተዳደራዊ አካሄድ እየተጠየቀ መሆኑን ጠቅሰው፣ መስጊዱ የያዘውን ቦታ እንዲለቅ የከተማ አስተዳደሩ ከመጅሊስ ጋር ተጋግሮ እንደሚለቁ ቃል ስለመገባቱ አስረድተዋል፡፡

ባለቤት ያለው ቦታ ላይ ሕገወጥ ማስፋፊያ የማይፈቀድ በመሆኑ፣ የመጨረሻ መፍትሔ ለመስጠት የክፍለ ከተማውን አፈጻጸም እየጠበቁ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ መሬቱ ላይ ወንዝ አለ ስለተባለው ጉዳይ እንደገና ዲዛይኑ ታይቶ ለከተማ አስተዳደሩ ፕላን ቢሮ ቦታው እንዲቀየር ደብዳቤ ተጽፎ ምላሽ እየተጠበቀ ስለመሆኑ ገልጸው፣ መሬቱ ላይ ወንዙ ያረፈባቸው ተመዝጋቢዎች አዲስ ዕጣ እንደሚያወጡ ተናግረዋል፡፡

ወደ ሳይት ለመግባት የሚረዳውን መንገድ የሚገነቡ ተቋራጮች ዲዛይን ጨርሰው ሥራ ለመጀመር ዝግጅት ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ምክትል ኃላፊው፣ በአጠቃላይ ማኅበራት ከተመሠረቱ በኋላ በካቢኔ የፀደቀ ከሊዝ ነፃ መሬት ምደባ ተሰጥቶ መሬቱ ሲተላለፍ የይገባኛል ጥያቄዎችና ክርክሮች እንደመጡባቸው ያብራራሉ፡፡

የቤቶች ቢሮ ጉዳዩን ከአቅሜ በላይ አይደለም የሚል ምላሽ እንደሚሰጥ ሪፖርተር የጠየቃቸው ምክትል የቢሮ ኃላፊው፣ የካቢኔ አባል በመሆናቸው የሆነ ጉዳይ ቢገጥማቸው ለካቢኔ አቅርበው ማስወሰን ስለሚችሉ ከአቅም በላይ የሚባል ነገር የለም ብለዋል፡፡

አጠቃላይ ካሉት ማኅበራት ሁለት ሕንፃዎች መስጊዱ አስፋፍቶ በያዘው ቦታ፣ ሁለት ሕንፃዎች የሚያርፉበት በፍርድ ቤት ክርክር ላይ መሆናቸውን አምስት ሕንፃዎች ደግሞ ወንዝ ላይ ያረፉ ሲሆኑ በአጭር ጊዜ ችግሩ ይፈታል ብለዋል፡፡

የካሳ ክፍያ ለተጠየቀባቸው የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሚከፈል በጀት መያዙን፣ ወረዳው የሰዎችን ስም ዝርዝር ለክፍለ ከተማ አሳውቆ በጀቱ እስኪለቀቅ እየተጠበቀ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...