Sunday, June 23, 2024

ዲጂታል ቴክኖሎጂው የዜጎችን መብትና ነፃነት ለማስከበር ይዋል!

ባለፈው ሳምንት መገባደጃ አካባቢ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የዲጂታል ሪፎርም ሥራን አስመልክቶ በተዘጋጀ ሥነ ሥርዓት፣ የፌዴራል ፖሊስ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ያደረገውን ሽግግር በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ 500 ያህል ተቋማት የዲጂታል ሥርዓቱን መቀላቀላቸውን ገልጸው፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFP APP) ማስጀመሩን አስታውቀዋል፡፡ የዲጂታል ስትራቴጂ አካል የሆነው ይህ መተግበሪያ የሕዝብ ብዛት እየጨመረ ባለበት ከተማ ጠቃሚ መሆኑንና ዜጎችም መተግበሪያውን ወንጀልን ለመከላከል በፎቶግራፍ፣ በቪዲዮ፣ በድምፅ፣ በሰነድ ወይም በቀጥታ በመደወል ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡ ሁሉም ዜጎች አካባቢያቸውንና ከተሞችን ለመጠበቅ የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡ በፀጥታ አካላት በኩል መኖር ያለበትን ሕግ የማክበርና የማስከበር ጉዳይ ላይ ግን አፅንኦት ሰጥተው ነበር፡፡

‹‹…ዛሬ አደራ ልላችሁ የምፈልገው ነገር ፖሊስ፣ ወታደር፣ የሴኪዩሪቲ ተቋማት ጥሪያችሁ፣ ሕልማችሁ፣ ወዳችሁበትና ፈቅዳችሁበት የገባችሁበት ሥራ ለሕዝብ ጥቅም መስዋዕት መሆን እንጂ ሕዝብን መጉዳት አይደለም፡፡ ፖሊስ ወንጀል የሚከላከል፣ ወታደር ወንጀል የሚከላከል፣ ወንጀል ለመከላከል ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ሲሆን እንጂ፣ ወንጀል ውስጥ ሲሳተፍ እጅግ አደገኛ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ተግባራት በከተማችን ውስጥ መደመጥ ጀምረዋል፡፡ ክትትል እያደረግን ነው፣ ማንም የፖሊስ ወይም የወታደር አባል ባልተገባ መንገድ ዜጎቻችንን እንዲያጎሳቁል፣ ሕግን ባልተከተለ መንገድ የእርምት ዕርምጃ እንዲወስድ አይፈቀድለትም፡፡ ቢፈቀድልን ሕግን ተንተርሰን፣ ሕዝብን ጠብቀን፣ እኛ ተጎድተን ዜጎቻችን በሰላም ወጥተው እንዲገቡ ማድረግ ነው፡፡ ለራስ ጥቅም ሕዝብን የሚጎዳ ተግባር ከወታደሮች በፍፁም አይጠበቅም፡፡ ብዙዎች እየሞቱና እየቆሰሉ ጥቂቶች የተቋማቶቻችንን ስም እንዳያጠፉ፣ ከሕዝባችን ጋር ሆነን ወንጀለኛው በእኛ ውስጥም ይሁን ከእኛ ውጪ በጋራ መከላከል ይኖርብናል፣ ይህንን ለማድረግ የፌዴራል ፖሊስ አመራሮችና አጠቃላይ የሲቪል ተቋማት አመራሮች በትጋት እንድትሠሩ ከአደራ ጭምር ላሳስባችሁ እፈልጋለሁ፤›› ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል መከበር አለበት፡፡ ይህ ቃል መከበር ያለበት ሕግ ባለበት አገር ማንም እንዳሻው መሆን ስለሌለበት ነው፡፡ ሕዝብ ከመንግሥት ጋር ሆድና ጀርባ እንዲሆን ከሚያደርጉት ዋነኛ ችግሮች መካከል አንዱ፣ በፖሊስም ሆነ በተለያዩ የፀጥታ አካላት በዘፈቀደ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ናቸው፡፡ ሕዝብና ፖሊስ ሲተባበሩና ተናበው ሲሠሩ ለወንጀል ምንም ዓይነት መደበቂያ ቦታ እንደማይኖር በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ሕዝባቸውን አክብረው የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ ለመፈጸም ደፋ ቀና የሚሉ ያሉትን ያህል፣ ለወንጀል መስፋፋትና ለሕገወጥነት መበራከት በትልቁ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ መኖራቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ እነዚህን ጉያ ውስጥ አቅፎ ሕግ ማስከበርም ሆነ የአገርን ሰላም ማስከበር እንደማይቻል የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን በየቦታው እንዲህ ዓይነቶቹ እየተበራከቱ ለመሆናቸው ግን ነጋሪ የሚያስፈልግ አይደለም፡፡ ትልቅ ትኩረት ግን ያስፈልጋል፡፡

ከፀጥታ ተቋማት በተጨማሪ ሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የተንሰራፋው ደዌም ከፍተኛ ፍተሻ ያስፈልገዋል፡፡ በየወረዳው፣ በየዞኑ፣ በየክልሉ፣ በከተማ አስተዳደሮችና በክፍላተ ከተሞቻቸው ውስጥ የመሸገው ሕዝብ የሚያሰቃይ ኃይል በሕግ ካልተባለ አገር ከማፍረስ አይመለስም፡፡ ብዙኃኑ ትጉኃን ሠራተኞች በቅንነትና በታማኝነት ሕዝባዊ አደራቸውን ሲወጡ፣ ለአገርም ሆነ ለሕዝብ ደንታ የሌላቸው ግን ተቋማትን የብልሹ አሠራሮች መፈልፈያ አድርገዋቸዋል፡፡ ሕዝባዊ አገልግሎቶችን እንደ ሸቀጥ በጉቦና በምልጃ ካልሆነ ማከናወን የማይፈልጉትን፣ በሕግ ሥርዓት ማስያዝ የግድ መሆን አለበት፡፡ በስብሰባና በሌሎች ሰበቦች ሥራቸው ላይ ሳይገኙ በመሬት ድለላና በኮንትሮባንድ የተሰማሩ ሞልተዋል፡፡ ለሕዝብ አቤቱታና ቅሬታ ጀርባቸውን ሰጥተው ተቋማትን የዝርፊያ ማዕድ ያደረጉ ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ በሕግ አደብ እንዲገዙ ከተፈለገ ከላይ እስከ ታች መዋቅሮች መፅዳት አለባቸው፡፡

የዲጂታል ቴክኖሎጂው ከፀጥታ መዋቅሩ በተጨማሪ የሲቪል ሰርቪሱን የሥራ ከባቢ ማዳረስ አለበት፡፡ በቴክኖሎጂው ሥራዎችንና አገልግሎቶችን ከማዘመን ባሻገር፣ ለብልሹ አሠራር መንስዔ የሆኑ ችግሮችም መፈተሽ ይኖርባቸዋል፡፡ ሕዝብ በመንግሥት ላይ አመኔታ ኖሮት አገልግሎት በአግባቡ ማግኘት የሚችለው፣ ሥራዎች ከሌብነትና ከመንቀርፈፍ መላቀቅ የሚያስችል መደላድል ሲያገኙ ነው፡፡ ብቃት አልባዎች፣ ሥነ ምግባር የሌላቸው፣ ከሌብነትና ከዝርፊያ በስተቀር ምንም የማይታያቸው፣ ለተቀመጡበት ወንበር የሚመጥን ሰብዕና ያላዳበሩና ለአገር ምንም ደንታ የሌላቸው ጭምር መለየት አለባቸው፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች አለቃና ምንዝርን ለመለየት እያዳገተ ነው፡፡ ምክንያቱ ምንድነው ተብሎ ሲፈተሽ ደግሞ የጥቅም ሰንሰለት የፈጠረው ምግባር አልባ ሞራለ ቢስነት ነው፡፡ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሪፎርሙ እነዚህንና መሰል ተግዳሮቶችን ለማስወገድ ማገዝ አለበት፡፡ የሌሎች ትጉኃን ሞራል የሚጠበቀው በዚህ መንገድ ነው፡፡

የአንድ መንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ ነው፡፡ ሕዝብ በሰላም ወጥቶ መግባት፣ በፈለገበት ሥራ የመንቀሳቀስ፣ የመሥራትና የመኖር፣ እንዲሁም በተፈጥሮ የተጎናፀፋቸውና በሕግ ዋስትና ያገኙ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ መከበር አለባቸው፡፡ መንግሥት አሠራሩ ግልጽ፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ሲኖርበት እነዚህ መብቶች በማንም ሊጣሱ አይችሉም፡፡ የመንግሥት ተቋማትም ሆኑ የፀጥታ አካላት በሕግ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ሲወጡ፣ በሕዝብ ላይ በደልም ሆነ ግፍ ሊፈጸም አይችልም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት በሁሉም አካላት ጆሮና አዕምሮ ውስጥ በትክክል ተንቆርቁሮ ከሆነ፣ በየጎዳናውና በየጥጋ ጥጉ በዜጎች መብትና ነፃነት ላይ የሚቀልዱ አይኖሩም ማለት ነው፡፡ የእሳቸው ቃል ካልተከበረ ግን ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት ከመጠን በላይ እተስፋፋ፣ የሕዝባችን በሰላም ወጥቶ የመግባት ሥጋት ተባብሶ ይቀጥላል፡፡ ዘመናዊነትና እንዲህ ዓይነቱ አስከፊ ድርጊት ስላማይጣጣሙ፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂው የዜጎን መብትና ነፃነት ለማስከበር ይዋል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሕግ የማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

የሕግ መሠረታዊ ዓላማ ዜጎችን ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች መጠበቅ፣ ለሕይወታቸውና ለንብረታቸው ከለላ መስጠትና በሥርዓት እንዲኖሩ ማድረግ ማስቻል ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል...

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...