Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን ግድ ብሏቸው፣ አሳፋሪዎችም የዕለት እንጀራቸውን የሚቆርሱበት ኑሮአቸው ይኼው ሆነና ፈላጊና ተፈላጊ ተገናኝተዋል። ሠርቶ አደር የሆነ ሕዝብ እኮ ያስታውቃል። ኑሮው ዳገት ሆኖበት በገረጣ ሰውነቱ ሲባዝን በግልጽ ይታያል፡፡ በዝርፊያ የደነደነው ደግሞ ገንዘቡን እንደ ፈንዲሻ ሲበትነው ኃፍረት የለውም፡፡ ‹‹አያ ሆ…ሆ… ማታ ነው ድሌ… የሚለው ጭፈራ የሚታወቀው በኳስ ሜዳ ታዳሚያን ካምቦሎጆ ነበር። አሁን ዘመኑ ተቀይሮ ምድረ ሌባ በዘረፈው የሕዝብና የአገር ሀብት በጎልድና በቡሉ ሌብል እጁን እየታጠበ  ያዜመዋል አሉ። እኛ ምስኪኖች ግን…›› እያለ አንድ ጎልማሳ በሰቀቀን ይናገራል፡፡ ‹‹አያ ሆ…ሆ… ቀሪ ዘመኔን ገባሁ ከርቸሌ እያለ የሚያስላዝን የጠንካራ መንግሥት ጡንቻ ምድረ ሌባን ቢደቁሰው እኮ እኛም ፀሐይና ውርጭ እየተፈራረቁብን ታክሲ በመጠበቅ አናረጅም ነበር…›› ትላለች ከመሀል አንዲት ወይዘሮ። ብሶት የወለደው ጉዞ ሊሆንብን ነው መሰል!

‹‹መቼም የማይባል የለ የማይሰማ የለ፡፡ ዘንድሮ ‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባ› የሚባለው ቀርቶ ‹ጉድ ሳይሰማ መዋል አይታሰብ ማደር አይታለም› መባል ከተጀመረ የቆየ ይመስላል። ይህን የምላችሁ ፊት ለፊቴ የተሰቀለውን ጥቅስ እያነበብኩ ነው። የጥቅስ ነገር መቼም የልብ ያደርሳል ይባላል። አንዳንዶች እንዲህ የሚለው ጥቅስ የሕይወቴን አቅጣጫ ቀየረው ይላሉ። በምንለጥፈው የጥቅስ ብዛት ቢሆን ኖሮማ ተስፋይቱን ኢትዮጵያ በአንድ ሌሊት ሠርተናት ባደርን ነበር። ‹ድህነትን ጉድ ባይ› ካሉት ጀምሮ ‹ድህነትን ተረት እናደርጋለን› እስካሉት ድረስ ብዙ ሰምተናል፡፡ ድህነት በወሬ ቢጠፋ ኖሮ ፖለቲከኞቻችን የዘመኑን ታላቅ ሽልማት ማንም አይወስድባቸውም ነበር፡፡ ወሬ ብቻ ሆኖ ቀረ እንጂ…›› እያለች ወይዘሮዋ ወጉን በስፋት ጀመረች፡፡ ዘንቢል ከያዙት እናት አጠገብ የተቀመጠው ጎልማሳ ደግሞ ስለሸመታቸው ወሬ ይቆሰቁሳል። ‹‹እማማ ከገበያ ነው የሚመጡት?›› ሲላቸው የት አውቆኝ ነው የሚያናግረኝ አላሉም። ለብሶታቸው እንኳን ይኼን መሰል መድረክና የመርፌ ቀዳዳ የምታክል መሹለኪያ እንኳን ቢያገኙ ሾልከው የሚናገሩ ነው የሚመስሉት፡፡ እንኳን ዘንቦብሽ አሉ። ‹‹የምን ገበያ? ገበያ የሚባለው ድሮ ቀረ ልጄ፡፡ ይልቅ ዝርፊያ ቆይተው ነው ወይ የመጡት ብለህ አትጠይቀኝም?›› ሲሉት ሁላችንም ሳንወድ ፈገግ አልን። ‹‹ትልቅ ሰው በነገር አዋቂነት ሲካን ወጣቱ በአሉባልታና በሐሜት ትንተና ተክኖት አርፏል…›› ትላለች ወይዘሮዋ። አልተቻለችም!

‹‹እንዴት?›› አላቸው ጎልማሳው። ‹‹እንዴት እንዴት ትለኛለህ? ዋናው ቴሌቪዥን ጣቢያ ነው እንዴ የምትሠራው?›› አሉ ቆጣ ብለው፡፡ ‹‹አልገባኝም እማማ?›› አላቸው ጎልማሳው ግራ ተጋብቶ። ‹‹ምኑ ነው የማይገባህ? የዛሬን አያድርገውና ድሮ በአሥር ብር አሥር ዓይነት ገዝቼ ዘንቢሌን ሞልቼ ነበር የምገባው። አሁን እኮ አንዲት ቅንጣት ነገር መግዛት ብርቅ ሆኗል፡፡ ለአንድ ሺህ ብር እኮ ይህች ስስ ፌስታል እኮ ትበዛለች፡፡ ታዲያ ይኼ ካልገባህ አገራችን የልማትና የዕድገት ግስጋሴዋን እያፋጠነች ነው ከሚሉት ወሽካቶች ጋር ነህ ማለት ነው…›› ብለውት ፊታቸውን ዞር ሲያደርጉት ጎልማሳው ጭጭ አለ፡፡ ‹‹ኧረ አንተ አምላኬ ኧረ ገላግለኝ፣ ኧረ እባክህ ውሰደኝ…›› እያሉ እማማ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ጀመሩላችሁ። ‹‹ኧረ እማማ እርስዎን የሚያህል ትልቅ ሰው እንዴት እንዲህ ተስፋ ይቆርጣል? እንኳን እርስዎ እኛ ወጣቶቹ እንዲህ ሆድ አልባሰንም…›› አላቸው አንድ ወጣት። ሁሉም እማማን ማረጋጋት ጀመረ። ‹‹ምን ላድርግ ብላችሁ ነው? የምንሰማውና የምንኖረው ለየቅል ሲሆን ጊዜ ምን አድርጊ ትሉኛላችሁ?›› ብለው እንባቸውን ያዘሩት ጀመር። ‹‹እማማ በእርስዎ ብቻ አይደለም በአገር ነው የመጣው እኮ። አይደለም እንዴ ጎበዝ?›› ይላል ጥራዙ ከበድ የሚል መጽሐፍ የያዘ ፂማም ጎልማሳ። ምሁር ይሆን እንዴ!

‹‹ድሮም እኮ ተብሎ ነበር፣ ግን ማንም ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም። ማርክስ እኮ ተናግሮት ነበር። ነገር ግን ምድረ ራስ ወዳድ ሊተገብረው አልቻለም፡፡ ካፒታሊዝም መጨረሻው ላይ እንደሚጠነዛና እንደሚሞት ማርክሲስቶች ተንብየው ነበር…›› እያለ ጎልማሳው የማፅናናቱን ጉዳይ ትቶ የኮሙዩኒስት ማኒፌስቶውን ያነበንብብ ጀመር ጎልማሳው። ‹‹የቀበሮ ባህታዊ በጎች መሀል ገብቶ ይሰግዳል አለ የአገሬ ሰው። አሁን ይህችን ቁንፅል ዕውቀት ይዞ ነው እኛ ላይ የሚያንበለብለው…›› ይላል አንዱ ከፊት በሹክሹክታ። ‹‹ኧረ ጎበዝ የካፒታሊዝምን ስም እያጠፉ ኮሙዩኒስቶቹን እንደገና እንዳያስነሱብን? የኮሙዩኒስቶቹ ርዝራዦች ወደኋላ እንዳይመልሱን አደራ?›› የሚለው ወጣቱ ነው፡፡ ይኼን ጊዜ መጨረሻ ወንበር የተቀመጠች ደህና የምትመስል ነገር ግን ነካ የሚያደርጋት የምትመስል ወጣት ጩኸቷን አቀለጠችው። ለነገሩ በአሁኑ ጊዜ ጤነኛውን ደህና ከሚባለው መለየት አልተቻለም። ሾፌሩ እየተበሳጨ ታክሲዋን አቁሞ ወያላውን፣ ‹‹እባክህ ይኼ የሕዝብ ማመላለሻ እንጂ የዕንባ ጠባቂ ተቋም አይደለም፣ አስወርድልኝ በፍጥነት። ቆይ ጤነኛ ሰው ለይተህ አታስገባም እንዴ? እኔ ወፈፌ ሳይ ይነሳብኛል…›› ሲል የእሱም ጤንነት አጠራጠረን። ይኼኔ ‹‹ምን?›› አለች ወጣቷ። ‹‹እኔ ነኝ ዕብድ? ለነገሩ እንዴት አላብድ? የሞቀ ቤቴን ስለቅ እንዴት አላብድ? ንገሩኝ በአንድ ቀን በረንዳ አዳሪ ስሆን እንዴት አላብድ?›› እያለች ታቀልጠው ጀመር። ‹ታዲያ ታክሲ እንጂ ወረዳ ወይም ክፍለ ከተማ አይደለም። በሕግ አምላክ ውረጂልን…›› አላት ሾፌሩ እሱም እያንዘፈዘፈው። ‹‹በየትኛው ሕግ? ሕግ ካለ አስወርደኝ ስለሌለ ግን አልወርድም…›› ብላው ድርቅ አለች። ‹‹የምን ሕግ…›› እያለች ዓይኗን ስታጉረጠርጥ ፈራን፡፡ ለምን አንፈራ!

ከባለቤቱ ጋር መሀል ወንበር ላይ የተቀመጠ አንድ ጎልማሳ እንድትወርድ ለማግባባት ሊጥር ሲል ባለቤቱ አቋርጣው፣ ‹‹አርፈህ ተቀመጥ፣ ታሞ ያበደና አውቆ ያበደ አንድ አይደለም…›› ስትለው እንሰማለን። አውቆ አበድ የሚያደርግ ብሶት መሆኑ ጠፍቷት ይሆን? መቼም የምንወደውን ነገር ለመከላከል የምንቀምረው ነገር ለኑሮ ግሽበቱም ብንሞክረው ውጤት ሳያመጣልን አይቀርም። በብዙ ጭቅጭቅ ልጅ እግሯ ‹አውቆ አበድ› የተባለችው ወረደች። ወያላው ሒሳብ መቀበሉን ትቶ በድንጋጤ ይቁለጨለጫል። እንኳን እሱ የኮሙዩኒስት ማኒፌስቶ ያነበንብ የነበረውም ዝም እንዳለ ቀርቷል። ሁላችንም ለጥቂት ግዜ በሐሳብ ሰርጥ ውስጥ ፈሰስን። በመንገድ ያሳለፍነው፣ ባለመግባባት ያሳለፍነው፣ በመደናቆር ያሳለፍነው፣ በቂም በቀል የሳለፍነው ሁሉ ትዝ እያለን ጉዟችን ይቀጥላል። ‹ጉዞው ቢቀጥልም መውረጃችን ሩቅ ነው› ብለን እያሰብን ከመንገድ የምንቀርም ሞልተናል፡፡ አሁን ደግሞ ብሶብናል፡፡ ወያላው በሾፌሩ ቁጣ ሒሳቡን መቀበል ጀምሯል። በወረደ ተሳፈሪ ፋንታ የጫነው ቻይና አጠገብ ሲደርስ ‹‹ከዚህ ጋርማ አልዳረቅም ከፈለጋችሁ አግዙኝ…›› አለ ተሳፋሪዎችን እየቃኘ። ይኼን ጊዜ አንድ ወጣት፣ ‹‹እነሱ እንደሆን እንኳን አማርኛ የብሔር ብሔረሰቦችን ቋንቋዎች አቀላጥፈው ይናገራሉ የሚባለው ወሬ ነው፡፡ እስቲ ዝም ብለህ ልከፈው…›› ሲለው ሾፌሩ በበኩሉ፣ ‹‹መቅመስ ካማረህ ከአብሮ አደጎችህ ጋር አትጣላም?›› ሲለው እኛ ሳቅን። ቻይናው እንዳልሰማ ሆኖ ዝም ብሏል፡፡ ዝምታው ያሳስባል!

ቻይናው ኮስተር እንዳለ ወያላው እጁን እየዘረጋ፣ ‹‹እሺ ቢጫዋ ሒሳብ ዱብ አድርጊ…›› ሲለው ሁላችንም አፍጥጠን አየነው። ቻይናው ምንም መደናበር ሳያሳይ፣ ‹‹ስንት ነው?›› አለው በጠራ አማርኛ። ወያላው አመዱ ቡን አለ። ያ ወጣት በመስኮት የዘለለ ይመስል ልናየው አልቻልንም። ቻይናው በተነገረው መሠረት እየሳቀ ሒሳቡን ከፈለ። አይሰሙኝም ብሎ መቀደድ ትርፉ ይኼ ነው። አንዳንዴ ደግሞ ይሰሙናል ብለን ወሬያችንን ቀምመን፣ ጉሮሮአችንን ጠራርግን ስንናገር ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ያልፉናል፣ የውጮቹ  ሳይሆኑ የውስጦቹ ቻይናውያን። ቻይናው መውረጃው ሲደርስ፣ ‹‹እጃችሁን አስራችሁ አፋችሁን ከምትከፍቱ፣ አፋችሁን ሰብሰብ አድርጋችሁ እጃችሁን ፈታችሁ አሠሩት…›› ሲለን በኃፍረት ጭጭ አልን፡፡ ልካችንን የሚነግረን እያጣን እንጂ ስንት ጉድፍ አለብን፡፡ ያስብላል!

ጉዞው እየተገባደደ ነው፡፡ ‹‹እዚህ አገር ግርም የሚለኝ ነገራችን ሁሉ ወደፊት ሳይሆን ወደኋላ ይጎትተናል። ሕይወትን ሳይሆን ሞትን ያደፋፍረናል። ‹ለመኖር የሚያጓጓ ለመሞት የሚያስፈራ ነገር የለም› እያልን በከንቱ መባዘናችን ይገርማል። መደማመጣችን፣ ፍቅራችን፣ መተሳሰባችን ሁሉ ሰው በሚለው መለኪያ መሆን ቀርቷል። ለፍርድ መቻኮል ይነዳናል። ስንታይ የምንመስለውማ ውስጣችን ይለያያል። የሚነገረን ሌላ የምንኖረው ሌላ። ስለአገራችን ጠማማ ፖለቲከኞች የሚነግሩንን በሰማን ቁጥር ካለንበት ጤናማ ሕይወት እንደ ቅዠት ሕልም መባነን እንመኛለን። እውነታችን ላይለቀን በአጉል ተስፋ እንታሻለን። በሚነገረንና በምንኖረው መካከል የተፈጠረው ክፍተትም ይገርማል፡፡ መግረም ብቻ ሳይሆን ያበሳጫል፡፡ እያደር ቁልቁል ብቻ…›› እያለች ወይዘሮዋ በሰፊው ስታብራራ ወያላው ‹‹መጨረሻ…›› ብሎ ሲያስወርደን ሽቅብና ቁልቁል የተምታቱብን እንመስል ነበር፡፡ መልካም ጉዞ!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት