Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሰጠው ብድር ምጣኔ 26 በመቶ መድረሱንና እነዚህ ተበዳሪዎች ከጠቅላላው የባንኩ ተበዳሪዎች ውስጥ 92 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው ገለጸ፡፡ 

ባንኩ በሥራ ዕድል ፈጠራ እያካሄዳቸው ያሉ እንቅስቃሴዎችንና የ15 ዓመታት ጉዞውን በተመለከተ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተፈሪ መኮንን እንደገለጹት፣ ባንኩ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ተበዳሪዎች የሚያቀርበውን የብድር መጠን በማሳደግና የብድር ተደራሽነቱን በማስፋት በአገር ደረጃ ያለውን ለተወሰኑ ዘርፎች ብቻ ብድር የማቅረብ ዝንባሌና ክፍተት ለማሻሻል የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት እየተንቀሳቀሰ ነው።

በዚህ ተግባሩ ባንኩ እስከ 2016 ዓ.ም. ሦስተኛ ሩብ ዓመት መጨረሻ ድረስ ከሰጠው አጠቃላይ የ44 ቢሊዮን ብር ብድር ውስጥ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች 26 በመቶ የሚሆነውን እንደወሰዱ ተናግረዋል፡፡ ይህም ባንኩ እስከዛሬ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ተበዳሪዎች ከ14.5 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር እንዳቀረበ ተናግረዋል።

ከቁጥር አንፃር ሲታይም ከባንኩ ጠቅላላ ተበዳሪ ደንበኞች ውስጥ 92 በመቶው ወይም 7,757 የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ተበዳሪዎች መሆናቸውን የባንኩ መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህ የብድር ሥርጭትና ምጣኔ ከፍተኛ የሚባል እንደሆነ የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ባንኩ የብድር ስብጥሩን ሚዛናዊ በማድረግ ረገድ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ለአነስተኛና ለመካከለኛ፣ እንዲሁም ለጀማሪ ቢዝነሶች የሚሰጠው ብድር ከመጠን አኳያ ሲታይም ከፍተኛ መሆኑን፣ ይህም ባንኩን ለታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ የተያዘው ተልዕኮና ግብ እየተሳካ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡ 

ለ7,757 የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ተበዳሪዎች የተሰጠው የ14.5 ቢሊዮን ብር ብድር በተናጠል ሲታይ፣ በአማካይ ለእንዳንዳቸው 1.5 ሚሊዮን ብር ብድር መቅረቡን ያመላክታል ተብሏል፡፡

ባንኩ ባደረገው ፋይናንስ ባለፉት 15 ዓመታት በአገር ደረጃ ካሳረፋቸው መልካም አሻራዎች መካከል ቀጥሯቸው ከሚያሠራቸው ከ11 ሺሕ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች በተጨማሪ በሚከተለው የብድር መሪ ዕቅድ፣ በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉም ተጠቅሷል፡፡  

በተለይም የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ለሆነው ለግብርናው ዘርፍ በተለየ መልኩ ፋይናንስ በማቅረብ፣ ለግብርናው ዘርፍ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አስታውቋል። እስካሁንም በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ አነስተኛና መካከለኛ ተበዳሪዎች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ማቅረቡን አስታውቋል፡፡ 

ሥራ አስፈጻሚው ባንኩ ባለፉት አሥራ አምስት ዓመታት ለኢንዱስትሪው የተለያዩ አበርክቶዎች ማድረጉን በተመለከተ፣ በሰጡት ማብራሪያ በቅድሚያ የጠቀሱት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን ቀድሞ መጀመሩን ነው፡፡

ከባንኩ የምሥረታ ዋና ዓላማዎች መካከል ከባንክ አገልግሎት ተደራሽነት ውጪ የሚገኙትን የኅብረተሰብ ክፍሎች አካታችነት ማረጋገጥ አንዱ በመሆኑ፣ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ኦሮበረካን በማስተዋወቅ ባንኩ ፋና ወጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

ከዚሁ አንፃር በአሁኑ ወቅት ከ95 በመቶ በላይ ቅርንጫፎቹ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ 45 ቅርንጫፎች አሉት፡፡ 

ከዚህም ሌላ ባንኩ በኢንዱስትሪው በተለየ የሚታወቅበት ነው ተብሎ በዋና ሥራ አስፈጻሚው የተጠቀሰው ከምሥረታው ጀምሮ የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በመጀመሪያው የባንኩ የምሥረታ ዓመት 26 ቅርንጫፎችን በስምንት ወራት ሥራ ያስጀመረ መሆኑን ነው፡፡ ከ26ቱ ቅርንጫፎች 22ቱ የአርሶ አደሩን ማኅበረሰብ ተደራሽ ባደረጉ አካባቢዎች መሆናቸው ልዩ ያደርገዋልም ብለዋል፡፡ ከቅርንጫፍ ከፈታ አንፃር በወቅቱ ባልተለመደ ሁኔታ በዓመት ውስጥ እስከ 100 የሚደርሱ ቅርንጫፎችን በመክፈት ጭምር የተለየ አካሄድ ነበረው ያሉት የኦሮሚያ ባንክ፣ ይህም ባንኮች በቅርንጫፍ ከፈታ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አስችሏል ብለው ያምናሉ፡፡ የዛሬ 15 ዓመታት አካባቢ ሁሉም ባንኮች የነበራቸው ቅርንጫፍ 634 ስለነበር ይህንን ቁጥር በአጭር ጊዜ ከፍ በማድረጉ ረገድ አስተዋጽኦ ነበረንም ይላሉ፡፡ 

ከ15 ዓመት በፊት ቅርንጫፍ በመክፈት በፍጥነት ተደራሽነታቸውን ማስፋት ያስቻላቸው ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ይህንን ስትራቴጂያቸውን እየቀየሩ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት ኦሮሚያ ባንክ ከ570 በላይ ቅርንጫፎች ቢደርስም፣ ከዚህ በኋላ ግን የቅርንጫፍ ከፈታውን ገታ በማድረግ ደንበኞችን ለመድረስ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀሙ ስለመሆናቸው ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡ ለዚህም በበቂ ደረጃ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ትግበራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡  

ቅርንጫፎቹን ወደ ዲጂታል ለመተካትም ምቹ የሆነ ዲጂታል የባንክ አገልግሎት መተግበሪያ ከአራት ወራት በፊት አገልግሎት ጀምሯል፡፡ ኦሮ ዲጂታል የተባለው ይህ መተግበሪያ ወደ ሰባት መተግበሪያዎች ያሉት ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ 

የኦሮሚያ ባንክ ከብድር አመላለስና ከተበላሸ ብድር ምጣኔ አንፃር ያለውን አፈጻጸም በተመለከተ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ ባንካቸው ብድር በማስመለስ ረገድ ጠንካራ አፈጻጸም ያለው መሆኑን ነው፡፡ በሌላው ዓለም ተበዳሪዎች ከባንክ ብድር ወስደው የሚመልሱበት አሠራር ከኢትዮጵያ ጋር ሲነፃፀር ልዩነት እንዳለው የጠቆሙት ኃላፊው፣ በሌላው አገር ያሉ ተበዳሪዎች ብድራቸውን በወቅቱ ካልከፈሉ ሲስተሙ ራሱ ከአጠቃላይ አገልግሎት ስለሚያስወጣቸው ብድር መልሱ ተብሎ እንደማይጠየቅ አስተረድተዋል፡፡ እርሳቸው የሚመሩት ባንክ ግን ጠንካራ የሆነ ብድር አስመላሽ ቡድን ያለው በመሆኑ፣ ብድር አመላለስ ላይ ውጤታማ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የባንኩ የተበላሸ ብድር ምጣኔ ወይም ታማሚ ብድራቸው ከኢንዱስትሪው አንፃር ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ባለፉት 15 ዓመታትም የተበላሹ ብድሮች መጠን ከ1.6 እስከ 2 በመቶ ብቻ ሆኖ መዝለቁንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የባንኮች አማካይ የታማሚ ብድር ምጣኔ 3.4 በመቶ መሆኑ በመጥቀስም ኦሮሚያ ባንክ ዝቅተኛ ታማሚ ብድር ካላቸው ሁለት ወይም ሦስት የአገሪቱ ባንኮች መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህ ጥራት ያለው ብድር እያቀረቡ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የባንኮች የሚሰጡት ብድር ገደብ ያለበት በመሆኑ፣ ይህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ14 በመቶ የብድር ገደብ ጫና አልፈጠረም ወይ? በሚል ከሪፖርተር ለቀረበ ጥያቄ፣ በአሁኑ ወቅት የብድር አቅርቦት እንደቀነሰ አቶ ተፈሪ ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ይህ የሆነው ብሔራዊ ባንክ ጣሪያ ስላስቀመጠ ብቻ ሳይሆን የገንዘብ እንቅስቃሴ አቅርቦት ስለቀነሰ የዲፖዚት እጥረት አለ፡፡ የብድር አቅርቦትም ቀንሷል፡፡ ይህም ቢሆን ግን ኦሮሚያ ባንክ ጤናማነቱን ጠብቀን ከእኛ ጥሩ የሚሠሩ ደንበኞች ስላለን በዚያ መሠረት እየሠሩ መሆኑን፣ እንዲሁም የአነስተኛና የመካከለኛ ተበዳሪዎች ደግሞ የመጪው ጊዜ የኢትዮጵያ ተስፋዎች ስለሆኑ በተቻለ እነዚህን የሚያግዝ ሥራ መሥራታቸው በተወሰነ ደረጃ ጫናውን እንደቀነሰላቸው ጠቁመዋል፡፡

ኦሮሚያ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ቀድሞ በመጀመር የሚጠቀስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አገልግሎቱን ቀድሞ እንደመጀመሩ ከወለድ ነፃ ያሰባሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠንና ፋይናንስ ያደረገው (የሰጠው ብድር) ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱ ቀድሞ የመጀመሩን ያህል ያለመሆኑ ምክንያት ምንድነው? ለሚለው ከሪፖርተር ለቀረበ ጥያቄ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡ 

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከወለድ ነፃ አገልግሎት እንደ ጀማሪነታቸው ከተቀማጭ ገንዘብም ሆነ ፋይናንስ ከማድረግ አንፃር የሚጠበቅበትን ያህል አይደለም በሚለው ጥቅል ሐሳብ ላይ ይስማማሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተለየ መርህ ያለው በመሆኑ፣ በጥንቃቄ አገልግሎቱን ለመስጠት ባንኩ ካለው ጠንካራ እምነት አንፃር የተፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል፡፡  

‹‹ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የራሱ የተለየ መርህ አለው፡፡ በሸሪዓ መርህ ነው የሚመራው በዘፈቀደ የሚሰጥ አይደለም፤›› ያሉት አቶ ተፈሪ፣ ምክንያቱም የባንኩ የሸሪዓ አማካሪዎች የአገሪቱን የእስልምና ጉዳዮች የሚመሩ ከመሆናቸው አንፃር ከሸሪዓ መርህ ካፈነገጠ አገልግሎቱ የመቀጨት ዕድል ሊያጋጥመው ስለሚችል እኛ ፋይናንስ የምንሰጠው (ብድር) በጥንቃቄ ስለሆነ ተቀማጭ አሰባሰብም ሆነ ከፋይናንስ አንፃር በቂ አይደለም የሚል ዕድል ሰጥቶ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ 

ባንኩ ከተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ አንፃር እስከ ዘጠኝ ወራት መጨረሻ ድረስ ከ54 ቢሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ ችሏል፡፡ እንደ ባንኩ መረጃ ከሆነ በአስቀማጮች ቁጥር በአምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ባንክ ነው፡፡ ከመሠረተ ልማት ግንባታው አንፃርም ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እያካሄደ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል የመሸጋገሪያውን ዋና መሥሪያ ቤትና በ20 ሔክታር መሬት ላይ ከሚገነባው በምሥራቅ አፍሪካ በዓይነቱ ለየት ያለው የገላን የልህቀትና የኮንቬንሽን ማዕከል ግንባታ ሥራዎች በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ 

ኦሮሚያ ባንክ በአሁኑ ጊዜ ከ15 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖች አሉት፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች