Sunday, June 23, 2024

በፖለቲካ ቁርሾ ሰበብ የአገርን ተስፋ ማጨለም አይገባም!

የአገራዊ ምክክር አጀንዳ የማሰባሰብ ሒደት ትልቁ የአገር ዜና ሆኖ ነው የሰነበተው፡፡ በርካታ ችግሮች የተቆለሉባት አገር ውስጥ በእኩልነትና በመከባበር ስሜት ለመነጋገር የሚያስችል አሳታፊ መድረክ ቢገኝ ማንም አይጠላም፡፡ ለምን ቢባል ጉዳይ አለን የሚሉ በሙሉ ለንግግር የሚሆኑ አጀንዳዎች ከመጠን በላይ ስላሏቸው ነው፡፡ ከሕገ መንግሥቱ ጀምሮ በርካታ የሚያነጋግሩ ጉዳዮች አሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ከምንም ነገር በላይ የሰላም ዕጦት የብዙኃኑ ሕዝብ ራስ ምታት ነው፡፡ ለሰላም ዕጦት ዋነኛ የሚባሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አገራዊ ምክክሩ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ኖሮት ሒደቱ ያማረ እንዲሆን በኢትዮጵያ ምድር የጠመንጃ ልሳን መዘጋት አለበት፡፡ ለዚህም ሲባል የተኩስ አቁም ማድረግ የሚያስችል ውሳኔ ላይ ቢደረስ፣ በፖለቲካ ምክንያት እስር ላይ ያሉ ወገኖች እንዲፈቱ ቢታሰብበት፣ የታጠቁ ኃይሎች አስተማማኝ ዋስትና አግኝተው የሚሳተፉበትና ሌሎች አዎንታዊ ዕርምጃዎች ቢወሰዱ ለአገራዊ ምክክሩ ወሳኝ ጅማሮ መሆን ይችላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዓመታት ሲንከባለሉ የኖሩ በርካታ ችግሮች አሉት፡፡ እነዚህ የተከማቹ ችግሮች በቅደም ተከተል የሚፈቱት በምክክር እንጂ በጦር እንዳልሆነ በቂ ልምዶች አሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን ለመከራ እየዳረጉ ካሉት ችግሮች መካከል ዋናው የሰላም ዕጦት ነው፡፡ በተጨማሪም ሕዝብ በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ነው፡፡ ገቢና ወጪ አልጣጣም ብለው በኪነ ጥበቡ የሚኖርባት አገር ብትኖር ኢትዮጵያ ትመስላለች፡፡ በፖሊሲ ደረጃ ትኩረት የሚሹ በርካታ ታላላቅ ጉዳዮችም አሉ፡፡ ከሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጋር ሊታሰብባቸው ከሚታሰቡ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የፌዴራል ሥርዓቱ ዓይነትና አወቃቀር ይገኝበታል፡፡ ይህ በተለይ ዜጎች በገዛ አገራቸው ተዘዋውረው የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት መብትን የሚመለከት ነው፡፡ የንብረት ይዞታን የሚመለከተው የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ሌላው ርዕስ ነው፡፡ ከታክስ ሥርዓቱ ጋር የሚያያዝ ጉዳይም አለ፡፡ እነዚህና ሌሎችም ንግግር ይፈልጋሉ፡፡

በትንሹ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የዘለቀው የቁርሾ ፖለቲካ ያመረቀዘ ቁስል እንዲጠግና ሰላማዊ ድባብ እንዲኖር፣ በአንድ በኩል መንግሥት ከማንም የበለጠ ታሪካዊ ኃላፊነት ሲኖርበት ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችም የሚፈለግባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ አገራዊ ምክክሩ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ባለቤትነት ማግኘት የሚችለው ከአሳታፊነቱ በተጨማሪ፣ የአገር አንገብጋቢ ጉዳዮች እንዲስተናገዱበት ቅንነትና በጎ ፈቃደኝነት ሲኖር ነው፡፡ ለይስሙላ ያህል የምክክሩን ጅማሮና ሒደት ከመደገፍ ባለፈ በተግባር የሚረጋገጥ እንቅስቃሴ መታየት አለበት፡፡ ለአገራዊ ምክክሩ ከተስፋ ይልቅ ጨለምተኝነት የሚጫነው ሥጋት የተፈጠረባቸው ዜጎች፣ ከጅማሬው እስካሁን ያለውን ሒደት በከፍተኛ ጥርጣሬ ነው የሚያዩት፡፡ እንደተለመደው ችግሮችን በማድበስበስ ለስሙ ምክክር ተካሄደ ከሚለው አጉል አስተሳሰብ መላቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ለኢትዮጵያ የሚበጀው ከገባችበት የቀውስ አዙሪት የሚያወጣት መፍትሔ አመንጪ መድረክ ነው፡፡

ፖለቲከኞች ለንግግርም ሆነ ለድርድር ከመቀመጣቸው በፊት ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጣቸው የተለመደ ነው፡፡ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ የሚቻለውም አስቻይ ሁኔታና እኩል አቅም ሲኖር ነው፡፡ ፖለቲከኞች እርስ በርሳቸውም ሆነ ከገዥው ፓርቲ ጋር ሲነጋገሩ በዚህ መንገድ መድረካቸውን ማመቻቸት የእነሱ ሥራ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲም ከሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር የሚኖረው ንግግርም ሆነ ድርድር በዚህ መሠረት ነው፡፡ በአገራዊ የምክክር ኮሚሽን አማካይነት እየተዘጋጀ ያለው መድረክ ግን የፖለቲከኞች ብቻ አይደለም፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጭምር የሚሳተፉበት ስለሆነ፣ ማኅበረሰቦችን በቀጥታ ከሚወክሉ በስተቀር የሌሎች ጣልቃ ገብነት አያስፈልግም፡፡ ዋናው ቁምነገር ማኅበረሰቦች ተሳትፏቸው በትክክል ውክልና አግኝቷል ወይ የሚለው ነው፡፡ የአገራዊ ምክክሩ ጉዳይ ሲነሳ የፖለቲከኞች ደምፅ ከማኅበረሰቦች በላይ እየሆነ አየሩን አይበክለው፡፡ ለአገር የሚያስቡ ወገኖችም ድምፅ ይስተጋባ፡፡

እዚህ ላይ በብርቱ ሊታሰብበት የሚገባው የገዥው ፓርቲ ብልፅግና ጉዳይ ነው፡፡ የአገራዊ ምክክሩ ሰሞነኛ የአጀንዳ ጥሪ ሲስተጋባ አብሮ የሚሰማ ሥጋት አለ፡፡ ይህ ሥጋት የምክክሩ መድረክ በካድሬዎች እንዳይወረር ነው፡፡ ብልፅግና ፓርቲ በሚኖረው የተሳትፎ ድርሻ ተገድቦ የምክክሩ ሒደት የማይመራ ከሆነ ትልቅ ቀውስ መፈጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ በክልሎችም ሆነ  በከተማ አስተዳደሮች አጀንዳ ማሳሰባሰቡም ሆነ ምክክሩ በይፋ ሲጀመር ከካድሬ ድምፅ ይልቅ፣ የመላ አገሪቱ ሕዝብ የሚፈልጋቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡ በተለያዩ አደረጃጀቶች ስም መድረኩን በማገት የአንድ ወገን ድምፅ ብቻ እንዲንቆረቆር ማድረግ፣ ለቅራኔና ለአመፅ ከማነሳሳት በላይ ምንም ፋይዳ እንደሌለው ያለፉት ዓመታት ተሞክሮዎች ያሳያሉ፡፡ አገራዊ ምክክር ማለት ሁሉም ፍላጎቶች በእኩልነት የሚስተናገዱበት መድረክ መፍጠር ብቻ እንደሆነ የጋራ ግንዛቤ ይኑር፡፡

ተወደደም ተጠላም ኢትዮጵያን ከጥፋትና ከውድመት ቤተ ሙከራነት ማላቀቅ የግድ መሆን አለበት፡፡ ይህ ሊሳካ የሚችለው ግን እየነደደ ካለው እሳት በመራቅ ምክክሩን በማጥላላት፣ ወይም የምክክሩ ተዋናይ በመምሰል ትርፍ ብቻ በማስላት አይደለም፡፡ ከትናንት ስህተቶችና ውድቀቶች የተገኙ ልምዶችን በመቀመር በእኩልነትና በመከባበር ስሜት አገራዊ ምክክሩ እንዲከናወን መፍትሔ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ ዳር ተቀምጦ የአገር ጉዳይን እንደ ተውኔት ማየት አይቻልም፡፡ የራስንና የአገርን መፃኢ ዕድል ሌሎች እንዲወስኑ መፍቀድ አይገባም፡፡ ኢትዮጵያ ጠንካራ አገር ሆና መውጣት የምትችለው አቅምን በሚያዳክመውና ተስፋን በሚያጨልመው ግጭት ሳይሆን፣ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ልክ እንደ ታላቁ የዓድዋ ጦርነት በጋራ ክተት በማለት ነው፡፡ ይልቁንም በአገር ጉዳይ የሚባክን ሐሳብ እንዳይኖር ጥረት ይደረግ፡፡ በፖለቲካ ቁርሾ ምክንያት በሚፈጠር ጥላቻ፣ እልህ፣ ቂም፣ ግትርነትና በቀል ሰበብ የአገርን ተስፋ ማጨለም ተገቢ አይደለም!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሕግ የማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

የሕግ መሠረታዊ ዓላማ ዜጎችን ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች መጠበቅ፣ ለሕይወታቸውና ለንብረታቸው ከለላ መስጠትና በሥርዓት እንዲኖሩ ማድረግ ማስቻል ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል...

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...