Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በዲጂታል የክፍያ ሥርዓት የሚደረግ ግብይትን የሚከለክሉ አገልግሎት ሰጪዎች በሕግ ይገደዱልን!

የክፍያ ሥርዓትን ለማዘመን በመንግሥት እየተወሰዱ የሚገኙ ዕርምጃዎችና የፋይናንስ ተቋማትም ይህንን ተቀብለው እያደረጉት ያለው ጥረት አመርቂ ውጤቶችን እያስገኘ መሆኑ በገሃድ እየታየ ነው። ለዚህም ማስረጃ የሚሆነው በጥሬ ገንዘብ የሚደረግ የገንዘብ ዝውውር እየቀነሰ በአንፃሩ በዲጂታል የክፍያ አማራጮች የመገልገል ልምድ እየዳበረ መምጣቱ ነው፡፡ የብዙ የፋይናንስ ተቋማት መረጃዎች የሚነግሩንም ይህንኑ ነው፡፡ ከይፋዊ መረጃዎች መረዳት እንደሚቻለው የአገሪቱ ባንኮች በአሁኑ ወቅት በአማካይ 40 በመቶ የሚሆነው የገንዘብ ዝውውራቸው በዲጂታል የባንክ አገልግሎት የታገዘ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያሉት ደግሞ የዲጂታል የገንዘብ ዝውውራቸውን ምጣኔ ከ70 በመቶ በላይ ማሻገር ችለዋል፡፡

ይህ የሚያሳየው የገንዘብ ዝውውር በዲጂታል የባንክ አገልግሎት ላይ የተመሠረተ እየሆነ መምጣቱንና ተገልጋዮችም ጠቀሜታውን ተረድተው እየተገበሩት መሆኑን ነው፡፡ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ያሉ የክፍያና የዲጃል ባንክ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ፈቃድ የተሰጣቸው ተቋማት የዲጂታል የባንክ አገልግሎት ፈጠን ብሎ እንዲራመድ አስችለዋል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም፣ አንዳንድ ባንኮችና የባንክ አገልግሎት እንዲሰጡ ፈቃድ ያገኙ ተቋማት የገንዘብ እንቅስቃሴን በዘመናዊ መንገድ እንዲሳለጥ ከማድረግ አልፈው አነስተኛ ብድሮችን እስከማቅረብ መድረሳቸው በራሱ ለአገልግሎቱ መስፋፋት ትልቅ ለውጥ እንዲታይ አስችለዋል፡፡ 

የእጅ ስልክን ብቻ ተጠቅሞ ለሚሰጡ አነስተኛ ብድሮች እየተጠየቀ ያለው የወለድ ምጣኔ የተጋነነና ሊፈተሽ የሚገባው ጉዳይ መሆኑ እንደጠበቀ ሆኖ የአገልግሎቱ መጀመር ግን የዲጂታል የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን አሳድጓል፡፡ የገንዘብ ዝውውር ከጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴ እየተለቀቀ ወደ ዲጂታል የክፍያ አማራጮች እንዲገቡ ማስቻሉንም መገንዘብ ይቻላል፡፡ 

የዲጂታል የክፍያ አገልግሎት እንዲህ ባለ ደረጃ እያደገና እየሰረፀ በመሆኑ ብዙዎች ጥሬ ገንዘብ ከመያዝ እየወጡ ጊዜ አመጣሹን ዘመናዊ የገንዘብ አያያዝ እየተለማመዱ ወደ ባንክ ሲያደርጉ የነበረውን ምልልስ እንዲቀንስ አድርጓል፡፡ 

ከፍያዎችን በተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ባመቻቹት የተለያዩ መተግበሪያዎች ክፍያዎችን መፈጸም መቻሉ የአገልግሎቱን ጠቀሜታ የተረዱ ተቋማትም ለሚሰጡት አገልግሎት ክፍያዎችን በዲጂታል የክፍያ ዘዴዎች እንዲሆን እየመረጡ ነው፡፡ ይህንንም ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት መተግበሪያዎች ጋር ያስተሳሰሩ ጥሬ ገንዘብ ከመቁጠር ለመላቀቅ እየተጣጣሩ ነው፡፡ ወጪና ገቢያቸውንም በቀላሉ ለማወቅም ቢሆን ያግዛቸዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ 

ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚገለገልባቸው እንደ ውኃ፣ መብራትና የሌሎች አገልግሎቶች ክፍያዎች በተለያዩ አማራጮች በዚሁ የዲጂታል ክፍያ መስመር እንዲያልፍ የተደረገ ነው፡፡

ስለዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ የታየው ለውጥ ወደፊትም ሽፋኑ እየሰፋ እንደሚሄድ የሚታመን ቢሆንም ብዙ ተገልጋዮች የሚጠቀምባቸው የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አሁንም ክፍያዎችን በዲጂታል መተግበሪያዎች ላለመቀበል ሲያንገራግሩ መታየታቸው ግን ለምን? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ክፍያ የምንቀበለው በጥሬ ገንዘብ ብቻ ነው በማለት ተገልጋዮች በፈለጉት አማራጭ ክፍያ እንዳይከፍሉ ሲያደርጉ ይታያል፡፡ በትናንሽ ገበያዎች ጭምር ክፍያን በዲጂታል የክፍያ መተግበሪያዎች እየተጠቀሙ ባለበት በዚህ ሰዓት በመሀል ከተማ ትላልቅ ቢዝነስ ያላቸው አንዳንድ ተቋማት ያለ ጥሬ ገንዘብ አንቀበልም ማለታቸው አስገራሚም አሳዛኝም ነው፡፡  ሌላው  አንዳንድ የራይድ አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎች ሳይቀሩ በጥሬ ገንዘብ ካልተከፈለን ብለው የሚሞግቱ አሉ፡፡ 

ዘመናዊ አገልግሎት ይሰጣሉ የሚባሉ ሆቴሎች ሬስቶራንቶች የተለያዩ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች መሸጫ መደብሮች አካባቢም ይህ ሁኔታ እየተስተዋለ ነው፡፡

ከጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴ እንውጣ እየተባለና አገልግሎቱን ለሁሉም ለማዳረስ ጥረት እየተደገ ባለበት በዚህ ወቅት ያለ ጥሬ ገንዘብ ክፍያ አንቀበልም መባሉ ጊዜውን የሚመጥን አይሆንም፡፡ 

ይህ አሠራር እንዲዘረጋ የተፈለገበት አንዱና ዋነኛው ምክንያት አንድ ሸማች ወይም ተገልጋይ ለተሰጠው አገልግሎት ወይም ለሚገባው ዕቃ ክፍያ ለመፈጸም ዲጂታል መተግበሪያዎችን እንዲጠቀም ነው፡፡ ስለዚህ ተገልጋዩ ጊዜው በሚጠይቀው ወይም ይመቸኛል ባለው የክፍያ ዘዴ እንዲፈጽም መብቱ ሊጠበቅ ይገባል፡፡ ሕግም የሚደግፈው እስከሆነ ድረስ ጥሬ ገንዘብ ‹‹ላምጭው እንዲከፈል ሕግ ያስገድዳል›› እንደሚባለው ሁሉ ተገልጋዮች ክፍያዎችን በዲጂታል የክፍያ አማራጮች መክፈል ከፈለጉ ሊከለከሉ መቻል የለባቸውም፡፡ 

በሌላ በኩል ደግሞ የንግድ ተቋማት በዲጂታል የሚደረጉ ክፍያዎችን የሚቀበሉም ቢሆኑ አንዳንድ ጊዜ አግባብ ነው? አይደለም? የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነገር አለ፡፡

ይህም አንድ ተገልጋይ በዲጂታል ክፍያ ዘዴ ክፍያ ሲፈጽም አንዳንዶች በግለሰብ ስም በተመዘገበ አካውንት በቀጥታ እንዲገባ መደረጉስ ትክክል ነው? ሕጋዊ ተቋማት እስከሆኑ ድረስ በኩባንያው ስም አካውንት ይኖረዋልና ክፍያዎች በቀጥታ በኩባንያ አካውንቶች አለመግባታቸውስ ትክክለኛ አሠራር ነው?

ይህ ጉዳይ መልስ የሚያሻው ሆኖ የዲጂታል ክፍያ እየሰፋ ባለበት አገር አገልግሎት ሰጪዎች ክፍያዎቻቸውን በጥሬ ገንዘብ ካልሆነ እንቢኝ ማለት እንደሌለባቸው የሚያስገድድ ሕግ ሊኖረን ይገባል፡፡ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን የበለጠ ለማስፋት ከተፈለገም እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ፈትሾ መፍትሔ የሚሆኑ አሠራሮችን መተግበር ግድ ይላል፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት