Wednesday, July 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የአካባቢ ቀውስ እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ

በሽብሩ ተድላ /ፕሮፌሰር ኤሜሪተስ/                              

ክፍል ፪

በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም (ዕፀዋት እና አዝርዕት)፡ ጉዳዩን የበለጠ እንድንገነዘብ የኢትዮጵያን የገጠር ኑሮ መቃኘት ይኖርብናል፡፡ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ኑሮ ምን ይመስላል? በድህነት ምክንያት የአገሪቱ  የኃይል ምንጭ- እንጨት፣ የኩበት ማገዶ፣ የመድኃኒት መደብሩ- ዱር፣ ጫካ፣ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት- ከወንዝ፣ ከምንጭ የሚቀዳ፣ ጎጆ ከጫካ በተቆረጠ ዛፍ፣ ከሜዳ በታጨደ ሳር የሚቀለስ፣ በጭቃ የተመረገች፣ አልባሱ ከጥጥ ከቆዳ፣ የእርሻ መሣሪያው ከደን የተቆረጠ፣ ለእርሻም ሆነ ለምግብነት የሚገለገልባቸው እንስሳት ራሳቸው ጥረው ግረው በሚግጡት፣ በሚለቅሙት ምግብ ያደጉ፣ እንክብካቤ የማይደረግላቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ፣ ሕዝባችን በድህነት ምክንያት በቀጥታ ተፈጥሮ በምታበረክተው አቅርቦት ተጠቃሚ የሆነ  ነው፡፡

እስኪ ጥቂት ችግሮችን ዘርዘር አድርገን እንመልከት፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ አርሶ አደር  የሚገኘው በደጋና ወይና ደጋ አካባቢዎች ነው፡፡ የሚያመርታቸው የእህል ዓይነቶች የማሳን አፈር ለጎርፍ፣ ለነፋስ ያጋልጣሉ፡፡ በዚህ መንገድ ከየማሳው የወጣው ውኃ አፈር ለብሶ፣ አፈር ጎርሶ ጅረት፣ ወንዝ እየሆነ ይተማል፡፡ አፈር በጎርፍ ውኃ ታጥቦ ሲወሰድ የሚጠፋው አፈሩ ብቻ ሳይሆን፣ አፈር ውስጥ የሚገኙት ጥቃቅን ጠቃሚ አፈር-አልሚ ሕያው አካላትም (ዘአካላት) ናቸው፡፡ ከመሬት መጣበብ የተነሳ ተዳፋት መሬቶችም ስለሚታረሱ፣ ችግሩ ይባባሳል፡፡ ዛፎች መተኪያ ሳይደረግላቸው ለማገዶ፣ ለቤት መሥሪያ፣ ለእርሻ መሣሪያዎች ማዘጋጃ፣ ወዘተ. ይቆረጣሉ፡፡ ይህም በሕዝብ ብዛት መጨመር (ከተሰማራባት የሕይወት አለኝታ ጋር ተጣምሮ)  ምክንያት ተባብሷል፡፡

የሕዝብ ብዛት ብቻውን የአካባቢ ቀውስን አያስከትልም፡፡ ነገር ግን ያ  በድህነት የታሰረ ከሆነ በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያደርጋል፡፡ ሕዝብ ሲበዛ፣ ተጨማሪ ማሳ፣ ተጨማሪ ጎጆ፣ ተጨማሪ ምግብ ማብሰያ ማገዶ ያስፈልጋል፡፡ ይህም ሒደት በአካባቢው ያለውን የሥነ ሕይወታዊ ሀብት ያመናምነዋል፡፡ አብዛኛው ኑሮውን በቀጥታ ከመሬት በሚገኝ የተፈጥሮ ሀብት ላይ ከመሠረተ፣ የሕዝቡ ብዛት በጨመረው መጠን በየቤቱ የሚሰማው ሮሮ፣ ምግብ ሳያልፍበት የሚውለው/ የሚያድረው ጉሮሮ ይበረክታል፡፡

ይህን በበለጠ ለመገንዘብ እስኪ የገጠሩን ኑሮ ጠለቅ አድርገን እንመልከት፡፡ በየመንደሩ የሕዝብ ብዛት ሲጨምር ከገጠር ወደ ከተማ ለገበያ የሚቀርበው በእህል ፋንታ ማገዶ ይሆናል፡፡ ገበሬዎች የሚያመርቱት እህል ለራሳቸው ፍጆታም አልበቃ ይላል፡፡ ገጠሩ ለገበያ የሚያቀርበው ማገዶ (ከሰል) ራሱ የተከለው ዛፍ ውጤት ሳይሆን፣ እንዲሁ በተፈጥሮ ከበቀለ ጫካ የተሰበሰበ፣ የተመነጠረ ነው፡፡ ለገጠሩ ሕዝብ የጥሬ ገንዘብ ምንጭ ጥሻና ዱር ይሆናሉ፡፡ የአራሹ የራሱ ምግብ ማብሰያ ኩበት ፍግ፣ የዘንጋዳና የበቆሎ አገዳ፣ የገብስና የስንዴ ብርዕ ይሆናል፡፡ ወደ ማሳ መመለስ የነበረበት አገዳ፣ ኩበት፣ ፍግ፣ እና ብርዕ፣ ለምግብ ማብሰያነት ከዋለ፣ የየማሳው የአፈር ልምላሜ እየመነመነ ይሄዳል፣ የማሳውም ምርታማነት ያሽቆለቁላል፡፡ ማሳዎች ምርታማ እንዲሆኑ ኬሚካላዊ ማዳበሪያዎች ይጨመሩባቸዋል፣ ይህም ሌላ የጎላ ችግር ያስከትላል- አካባቢን በኬሚካል መበረዝ፡፡

ሰው በበዛ መጠን ለእርሻ የሚውለው መሬት ስፋት ይጨምራል፡፡ መታረስ የማይገባው ተዳፋት መሬት ተመንጥሮ ለከብት መዋያ ያገለግል የነበረው ወንዝ አጠገብ ያለው ውኃ-አዘል መሬት ሁሉ ወደ ማሳነት/ወደ እርሻ መሬትነት ይቀየራል፡፡ ከብት የሚሰማራበት ቦታም እየጠበበ ይሄዳል፡፡ ባለንበት ወቅት፣ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ወይና ደጋና ደጋማ ቦታዎች የሚገኙ የከብት ማሰማሪያ ቦታዎች በብዙ እጅ ቀንሰዋል፡፡ ስለሆነም፣ የቤት እንስሳት በቂ መኖ አያገኙም፣ በቂ ምግብ ካላገኙ ምርታማነታቸውም ሆነ ጉልበታቸው ይቀንሳል፡፡

ለምግብ ማብሰያነት የምንጠቀምበት ማገዶ እያንዳንዱ ጎጆ ውስጥ ያለውን አየር ይመርዘዋል፡፡ በዚህም በእንጨትና በኩበት ጢስ በተበከለ አየር ምክንያት ብዙ ሕፃናት የሳምባ በሽታዎች ሰለባዎች ሆነዋል/ይሆናሉ፡፡ ሰገራ እና ሽንት የትም ቦታ ሲጣሉ አካባቢውን ስለሚበክሉ  ለብዙ ተላላፊ በሽታዎች መሰራጨት ዋና ምክንያት ይሆናሉ፡፡ በተለይ ሽንትና ሰገራ ለመጠጥ የምንገለገልበትን ውኃ ስለሚበክሉ፣ ሕፃናት ለተቅማጥ በሽታ ይጋለጣሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ከሌሎች ጋር ተዳምሮ፣ ብዙ ሕፃናት አምስት ዓመታቸውን ሳያከብሩ ይቀሰፋሉ፡፡

ከላይ የተደረደሩት ችግሮች ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በመጠኑም ቢሆን ቀንሰዋል፣ ግን ያ ማለት ከችግሩ ተላቀናል ማለት እንዳልሆነ መገንዘብ ያሻል፣ ከችግር የመላቀቅ ጥረቱ ኅብረተሰቡን በጠቅላላ ባሳተፈ መልኩ ነገ ዛሬ ሳይባል መቀጠል ይኖርበታል፡፡

የመሬት አጠቃቀም ሥርዓት (Land Use)፡ ሰሞኑን ስለ መሬት አስተዳደር የወጣውን አዋጅ ገና አልተመለከትኩትም፡፡ በሚዲያ ከተሰጠው ገለጻ እንደተገነዘብኩት፣ ስለ ሥነ ምኅዳር አያያዝ የሰጠው ትኩረት እንዳለ አልተረዳሁም፣ ከተሰጠው የሚዲያ ማብራሪያ እንደሰማሁት ካለም ውስን ይመስላል፡፡ በመሬት አጠቃቀም ሥርዓት ተዳፋት ቦታዎች እንዳይታረሱ፣ በአንፃሩ በዛፍ እንዲሸፈኑ አለመደረጉ፣ ማሳዎች የተሻለ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ይህ ነው የሚባል ጥረት  አለመኖሩ፣ የት ምን መመረት፣ መዘራት እንዳለበት (የሰብል እህል፣ የደጋ ፍራፍሬ፣ የቆላ ፍራፍሬ፣ ወዘተ) ሥነ ሥርዓት አለመኖሩ፣ የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ የመጠቀም ሁኔታን አዛብቶታል፡፡

ይህ ጉዳይ በአሁኑ ወቅት በተለይ የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ምክንያቱም አገራችን ብክለት የማያመነጭ ኃይልን ተጠቅማ የማደግ ዕቅድ ስላላት ነው፡፡ ይህንን ተገቢ አቅጣጫ ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ፣ የወንዞቻችን ተፋሰሶች ሁሉ፣ ቅደም ተከተሉ ከልማት ዕቅዱ ጋር ተቀናጅቶ፣ (ቅድሚያ በመጠናቀቅ ላይ ላለው ለህዳሴ ግድብ/ ለዓባይ ተፋሰስ)፣ ከአፈር እጥበት መላቀቅ አለባቸው፡፡ ይህንንም ለማድረግ ቀላሉ አማራጭ የመሬት ሀብትን በአግባቡ መጠቀም ነው፡፡

የተፈጥሮ ፀጋ (ቅርስ) እይታ፡  አንድ ያስደነገጠን ድርጊት ላውሳ፣ ባሌ ተራራ ከፍተኛው ቦታ ላይ ነው የቴሌፎን/ ድምጽ ቅብብሎሽ ምሰሶ የተተከለው፡፡ እዚያው አከባቢ ትንሽ ዝቅ ብሎ (ጥቂት ሜትሮች) ሊተከል ሲችል፣ ቁንጮው የተመረጠበት ምክንያት ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ምሰሶው አሁን ከተተከለበት ቦታ ትንሽ ዝቅ ብሎ ቢተከል፣ ከተፈለገው አገልግሎት አንፃር ለውጥ ያመጣ ነበር ብሎ ለመገመት ያዳግታል፣ ከሆነም የቅርስነት ክብሩና የልማት ተግባሩ ተመዛዝነው መታየት ነበረባቸው፡፡

በአሁኑ ይዘት አንዱ ጎን በጠቅላላ ክብሩን ተገፈፈ፣ ሌላው ገፋፊው ቁንጮው ላይ ተንቀረፈፈ፣ የአካባቢው ድባብ ተቃወሰ፡፡ ይህም ለአገር “አድባር” ትኩረት አለመስጠትን፣ ያለንን ግንዛቤ ውስንነትም ጭምር ያመለክታል፡፡ ይህን ዓይነት ድርጊት፣ ጥፋት፣ በሌሎችም የተራራ ቁንጮዎች ላይ ተፈጽሞ ሊሆን ይችላል፡፡ የተራራዎች ቁንጮ/አምባ የተፈጥሮ ቅርሶቻችን ናቸው፣ አሁን ባሉበት ሁኔታ፣ ሳይነካኩ መጠበቅ አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ቅርስ ታሪካዊ፣ ሰበ-ነክ፣ ብቻ አይደለም፣ ተፈጥሮዓዊም ነው! ለቅርፅ አሰጣጥ ደግሞ ተፈጥሮዓዊው ሥልት፣ ይዘት፣ ከሰበ-ነኩ ጋር ሲነፃፀር በጣም የላቀ፣ የተዋበ ነው፡፡

የአካባቢ ቀውሶችን ለመግታት የተወሰዱ ተግባሮች

ከዓመታት በፊት ተዳፋት ቦታዎች ያሉ ማሳዎች የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል፣ እርከኖች ይገነቡባቸው ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ከጠፈር (ሳታላይት) ከሚታዩት የምድር ገጽታዎች አንዱ የምዕራብ ሐረርጌ (በድሮው አጠራር) አፈር እጥበት መከላከያ እርከኖች ነበሩ ይባላል፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት በጀት፣ እንዲሁም በስዊስ መንግሥት ዕርዳታ፣ በአፈር እጥበት ላይ ፈርጀ ሰፊ ምርምር፣ ጥናት ይደረግ ነበር፡፡

የመሬት ሽፋን የሆኑ ዕፀዋት ጥበቃም ይደረግ ነበር፡፡ እንዲሁም ብዙ አካባቢዎችን በዛፍ ለመሸፈንም ውስን የሆኑ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ በተለይ የመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣ በዛፍ ተከላ የመሬት አልባስን መልሶ ለመገንባት፣ ዛፍ መትከልን መንከባከብን ለማሰፋፋት ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ ብዙ ሕዝብን ያሳተፉ የችግኝ ተከላ ዘመቻዎች ተካሂደዋል፣ እየተካሄዱም ናቸው፡፡ በብዙ ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞች ተተክለዋል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የማኅበረሱ አባላት በተግባሩ ተሳትፈዋል፡፡ ይህ የሚደገፍ ተግባር ነው፣ ሁሉም የማኅበረሰብ አባል ለዚህ ተግባር ተሳትፎ ማበርከት ይገባዋል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡

የአካባቢ የተፈጥሮ ሀብት መልሶ ለማገገም ለማስቻል የሚረዱ የድርጊት አሳቦች

በትምህርት ቤቶች ማዕከልነት በተፈጥሮ እንክብካቤ የባህል ለውጥ ማምጣት ይቻላል

ከላይ እንደተወሳው፣ የአገራችን ዓበይት ችግሮች ናቸው ተብለው ከሚወሰኑት ጉዳዮች መኻከል፣ አገሪቱ ያላት የተፈጥሮ ሀብት በከፍተኛ የውድመት ሒደት ላይ ያለ መሆኑ ነው፡፡ የዚህ ውድመት መከሰቻው የለም አፈር መታጠብ፣ የመሬት የዕፀዋት አልባስ መመናመን፣ በአንዳንድ ቦታዎች የምድር አልባስ ጨርሶ መጥፋቱ፣ ምንጮች ብሎም ወንዞች መድረቃቸው፣ ወዘተ ናቸው፡፡ ከላይ እንደተወሳው ችግሮች ውስብስብ ተመጋጋቢ የሆኑ ብሎም የርስ በርስ ግንኙነቶችም ያሏቸው ናቸው፡፡ እነዚህና እነዚህን የመሰሉ ችግሮች ተደራርበው ከፍተኛ የሰው ምግብና የከብት መኖ እጥረት (እጦት)፣ የመጠጥ (ውኃ) መጥፋት፣ የማገዶ ችግርና ተመሳሳይ ሌሎች ችግሮች እንዲከሰቱ አድርገዋል፡፡

የተፈጥሮ ሀብት መመናመኑ እንዳይቀጥል ለማድረግ፣ በብዙ አካባቢዎች የእርከን ግንባታና የዕፀዋት ተከላ ቢከናወንም፣ የተደረጉት ጥረቶች ተገቢውን (የሚጠበቀውን) ውጤት አልሰጡም፡፡ የሒደቱ አንዱ እንቅፋት፣ ጥረቱ/ ሙከራው በባህል/ ልማድ ላይ የተመሠረተ አለመሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም ችግሩን ለመፍታት ግን መጀመሪያ በተፈጥሮ ሀብት ክብካቤ ዙሪያ ባህላዊ ለውጥን ማምጣት ያሻል፡፡ መጥፎ ልማድን ለማስጣልና በምትኩ ጥሩ ልማድን ለመተካት፣ የለውጥ መሠረታዊ ግብዓቶች (አንቀሳቃሾች/ ሞተሮች) ትምህርት ብሎም ዕውቀትና/ ክህሎት ናቸው፡፡ ጉዞውም ረዥም ነው፣- አርቆ ማየት ያሻል፡፡

ከዚህ በፊት በመጽሐፍ (ሽብሩ ተድላ የሕያው ፈለግ 2009  ዓ.ም.፣ የኢትዮጵያ አካዴሚ ፕሬስ) ያሰፈርኩትን እይታ ላቅርብ፡፡ የባህልን ለውጥ ለማምጣት ከሚያገለግሉ መድረኮች ዋነኛው ትምህርት ቤት ነው፡፡ በትምህርት ቤት ውስጥ፣ ከትምህርት ጋር አቀናጅቶ ጥሩ ጥሩ ልማዶችን/ ባህሎችን መመሥረት ብሎም ማዳበር ይቻላል፡፡ በብዙ አገሮች የተፈጥሮ ክብካቤ ባህል የሚዳብረው በክለሰቦች አማካይነት ነው፡፡ ስለሆነም፣ በየትምህርት ቤቱ አንዳንድ የተፈጥሮ ክብካቤ ክለቦች፣ በብቸኝነትም ሆነ፣ ከሳይንስ ክለቦች ጋር ተቀናጅተው በጣምራ እንዲመሠረቱ ጥረት ማድረግ ያሻል፡፡ የተመሠረቱም ካሉ እንዲጎለብቱ ማድረጉ ይበጃል፡፡

የተፈጥሮ ሀብት ክብካቤን ዋና ዓላማው ያደረገ አንድ ምዕራፍ፣ በአገሪቱ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ማካተት ያሻል፡፡ ወጣት ተማሪዎች ስለ ተፈጥሮ ሀብት መጠነኛ ግንዛቤ አንግበው፣ በወደፊት ሕይወታቸው ለተፈጥሮ ሀብት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ እንዲንከባከቡ፣ መጠነኛ ዕውቀትን፣ ክህሎትን ለማስጨበጥ ነው- ጥረት መደረግ ያለበት፡፡ በዚህ ስልት/ ዘዴ/ ዕቅድ (Strategy) አሁን በሚያሰጋ ደረጃ እየመነመነ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ውድመት በከፊልም ቢሆን ለመግታት ይቻላል፡፡

የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል ባህል ማዳበር ዋና ዓላማው የሆነ ፕሮግራም፣ የሚከተሉትን ዝርዝር ዓላማዎች ያካተተ ሊሆን ይችላል– (ሀ) የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ አለመጠቀም ስለሚያስከትለው ችግር ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ (ለ) በየትምህርት ቤቶች የሳይንስና የተፈጥሮ ክብካቤ ክበቦችን ማቋቋም/ማጎልበት፣ (ሐ) አጠቃላይ ስለተፈጥሮ ሀብት ያለውን ግንዛቤ ማጠናከር፡፡

የሥራው/ሒደት በሳይንስ ክለቦች ወይም ተመሳሳይ ክለቦች ሊመራ ይችላል፣ የተመሠረቱ ክለቦች ከሌሉ አዳዲስ ክለቦችን ማቋቋም ይቻላል፡፡ የተፈለገውን ውጤት ለማግኘት የሚከተሉትን መተግበር ያስፈልጋል፡፡ ተግባሮችም እንደየአካባቢው፣ ከአካባቢው ባህል፣ ማኅበራዊ ኑሮ ጋር እየተዛመዱ፣ አመችነታቸው እየተቃኘ፣ ተስማሚነታቸው እየተመረመረ፣ እየጠለለ ሥራ ላይ ሊውሉ (ሊተገበሩ) ይገባል፡፡

ትምህርት ቤቶች ቅርበት ያላቸው የማይታረሱ ቦታዎችን፣ ለተፈጥሮ ሀብት ክብካቤ ግንዛቤ ማዳበሪያነት ማዋል፣ ብሎም የዕፀዋት አደባባዮች መመሥረት፡፡ ይህም ከዓመታት በፊት  በየመንደሩ/ በቀበሌው ከተቋቋሙ “ሚሌኒየም ፓርኮች” ጋር ወይም በመቋቋም ላይ ካሉ ሊቀናጅ ይችላል፡፡ በአካባቢው በዛፍ የተሸፈነ ቦታ ካለም፣ ቦታው ለተፈጥሮ ሀብት ግንዛቤ ማዳበሪያነት ሊያገለግል ይችላል፡፡ በግብርና ከተሰማሩ ባለሙያዎች ጋር በመመካከር/ በመወያየት የትምህርት ቤት ግቢዎች በአገር በቀል ዛፎች እንዲሸፈኑ/ እንዲበለፅጉ ብሎም ይሀንንም የትምህርት አካል ማድረግ ያሻል፡፡ የአገር በቀል ዛፎችን ዕድገት/መጠን መጨመር ሳይንሳዊ በሆነ ዘዴ ተማሪዎች  እንዲከታተሉ ማድረግ (ቁመት፣ ውፍረት፣ የቅርንጫፍ ቅጠል ብዛት፣ ቅርፅ፣ ሌሎች ሕዋሳትን መመዝገብ፣ ወዘተ)፡፡

በሚመሠረቱ የዕፀዋት አደባባዮች አካባቢ፡ ምን ምን ዓይነት እንስሳት እንደሚኖሩ፣ በዛፎች ላይ ጎጆ የሚሠሩ ወፎች፣ ግንዶችና ቅጠሎች ላይ የሚታዩ ባለ አከርካሪና አከርካሪ-አልባ እንስሳት (እንሽላሊት፣ ጉንዳን፣ ትንኝ፣ ወዘተ)፣ የዛፎችን ሁኔታ በተለያዩ ጊዜያት (ቀን፣ ማታ፣ በበጋ፣ በክረምት፣ ወዘተ) እና ሌሎችን ሁኔታዎች ማስተዋል፣ ማጥናት፣ መመዝገብ፣ አንዱ የዕውቀት ማካማቻው ስልት ይሆናል፡፡ ክበቦች በተፈጥሮ ክብካቤ ዙሪያ የየራሳቸውን ትንሽ ወቅታዊ መጽሔት በየጊዜው ማዘጋጀት  (ከአራት ገጽ ያልበለጠች)፣ የመጽሔት ስምም ሲመረጥ፣ ባህላዊ/ አካባቢን ያገናዘበ መሆን ይገባዋል፡፡

በላቦራቶሪ፣ በእንስሳትና ዕፀዋት መዘክር ዕገዛ ይህ ነው የሚባል ዕውቀትን/ ክህሎትን ለማግኘት በማይቻልባቸው ትምህርት ቤቶቻችን፣ የእነዚህ ዓይነት የተፈጥሮ ሀብትን ማስገንዘቢያ ማዕከሎች መኖራቸው ፈርጀ-ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብዬ እገምታለሁ፡፡

የዕፀዋት አደባባዮችን ለመመሥረት፣ በዛፍ/ቁጥቋጦ የተሸፈነች የማትታረስ ቦታን ከልሎ ለትምህርት ቤቱ የተፈጥሮ ክብካቤ መማሪያነት እንድታገለግል ማድረግ፣ በቀላሉ ሊከናወን የሚችል ተግባር ነው፡፡ የቦታው መጠን ከአምስት ሺሕ ሜትር ካሬ መብለጥ አያስፈልገውም፣ በእርግጥ ባዶ ቦታ ካለ ግን ሰፋ ቢል ይመረጣል፡፡ ቦታዎች ሲመረጡ ከእምነት ቦታዎች አጠገብ ቢሆኑ (ቤተ ክርስቲያን/ መስጊድ ወዘተ)፣ ለጥበቃው የበለጠ ያመቻሉ፡፡ ጉዳዬ ነው ተብሎ ከተያዘ ጥበቃ አያዳግትም- የተለመደ ተግባር ነውና!

በየዓመቱ ለተወሰኑ በአካባቢ ጥበቃ ጥረት ብልጫ ላሳዩ ትምህርት ቤቶች፣ ለምሳሌ ዛፎችን ለተንከባከቡ፣ ጥሩ ይዘት ያለው መጽሔት ለሚያዘጋጁ  (የውድድር ሚዛን ያስፈልጋል) ሽልማት መስጠትና እነዚህንና እነዚህን ለመሰሉ ሥራዎች መደጎሚያ የሚሆን ገንዘብ ማሰባሰብ የፕሮግራሙ አንዱ አካል ሆኖ መቀረፅ ይኖርበታል፡፡

ከላይ የተዘረዘሩት ፕሮግራም-መሰል ተግባራትን ለማከናወን ቅድመ ዝግጅት ያሻዋል፡፡ ከእነሱም ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው (አስተሳሰቡ ስላልተመከረበት፣ ግርድፍ ሐሳብ መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ መካተት አለበት)፡፡ ለጉዳዩ ቀጥተኛ አግባብነት ካላቸው የክልል መንግሥታት መሥሪያ ቤቶችና የወረዳ ኃላፊዎች ጋር በጉዳዩ ላይ መግባባት ብሎም በፕሮጀክት አፈጻጸም መስማማት ያሻል፡፡ የክልል መንግሥት ኃላፊዎች ይህንን ጉዳይ በክልሉ ውስጥ ለሚገኙ የወረዳ መሪዎች ማስረዳት፣ ብሎም የፕሮጀክቱን ጠቃሚነት ማሳመን፣ የወረዳው አስተዳደር በወረዳው ክልል ውስጥ የሚገኙ ለፕሮጀክቱ አፈፃፀም ምቹ የሆኑ ቦታዎችን ለይቶ ለትምህርት ቤቶች መስጠት፣ በየትምህርት ቤቶች በሚገኙ የሳይንስ መምህራን አስተባባሪነት ከግብርና ባለሙያዎች ጋር በመወያየት፣ በመደጋገፍ፣ በመተባበር፣ በተመረጠው ቦታ ላይ ስለሚተከሉ አገር በቀል ዛፎች ዓይነት መወሰን፣ የተፈጥሮ ሀብት ክብካቤ ክለቦችን ማቋቋም፣ የተቋቋሙም ካሉ እነሱን ማጠናከር፡፡ ከሳይንስ መምህራን መካከል (የሥነ-ሕይወት አስተማሪ ቢሆን ይመረጣል) አንድ የፕሮጀክቱ ተጠሪ የሚሆኑ መምህርን መሰየም (የፕሮጀክት መሪ)፣ ተጠሪውም ለዚሁ ተግባር ከሚመሠረት ኮሚቴ ጋር በመወያየት፣ የክለቦችን ዓላማ ተፈጻሚነት ማረጋገጥ፣ ለፕሮጀክቱ እንቅስቃሴ/ክንውን የተሰየሙ መምህራን የፕሮጀክቱን ፅንሰ ሐሳብና ጠቀሜታ ተማሪዎች በደንብ እንዲረዱት ማድረግ፣ ማሳመን፡ ወዘተ ያካትታል፡፡ ለዚህም ተግባር በየአካባቢዎች የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች መሳተፍ ይገባቸዋል የሚል እይታ አለኝ፡፡ 

በዚህ ሒደት ውስጥ ክለቦች የገቢ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ ድርጊቶችን ሁሉ መዳሰስ አለባቸው፣ ይህም ሲደረግ አካባቢውን ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ይገባል፡፡ የየክልሉ መንግሥት ብልጫ ላሳዩ ለተወሰኑ ትምህርት ቤቶች በየዓመቱ ሽልማት መስጠት ይገባዋል፣ ለዚህ ተግባር ማስፈጸሚያ የሚሆን መንግሥት መጠነኛ በጀት መመደብ ይኖርበታል፡፡

በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት መልሶ ማቋቋም

የብሔራዊ አገልግሎት አካል ሆኖ በኢትዮጵያ ለውትድርና ሥልጠናና ለተፈጥሮ ሀብት መልሶ ማቋቋም ብሔራዊ ፕሮግራም ተመሥርቶ ቢስተናገድ “የዜጋ አስተያት” እና ያገር ጥገና በአመርቂ ደረጃ ሊቃና/ ሊታረቅ ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የብሔራዊ አገልግሎት በሦስት ምዕራፎች የተከፈለ ሆኖ፣ በመጀመሪያ ለመሰናዶ/ ለዝግጅት፣ ሁለተኛው ለውትድርና ሥልጠናና ሦስተኛው ለአካባቢ ጥበቃ/ ክብካቤ ተሳትፎ ቢውል ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል የሚል እይታ አለኝ፡፡

በግርድፉ ፕሮግራሙ እንደሚከተለው ሆኖ ሊታቀድ/ ሊቀረፅ ይችላል፡፡ ወጣቶች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መልቀቂያ ፈተናን ባጠናቀቁ ከወር ገደማ በኋላ (ያም በግንቦት መቋጫ ወይም በሰኔ መባቻ ቢሆን ይመረጣል) እስከ መስከረም አጋማሽ (ለሦስት ወራት ገደማ) በአጠቃላይ ለብሔራዊ አገልግሎት መሰናዶ ቢውል ይመረጣል፡፡ በዚህን ወቅት ለአካባቢ መልሶ ማገገሚያ ለሚወሰድ ተግባር ተሳታፊዎች (ችግኝ ማፍላት፣ ችግኝ መትከል፣ ወዘተ) በቂ ግንዛቤ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ለፕሮግራሙ አመራሮች ደግሞ የድርጅት ማዋቀሪያ ጊዜ ይሆናል፡፡

ከዚያም ለሁለት ሳምንታት (እስከ ጥቅምት መጀመሪያ) ዕረፍት ከተወሰደ በኋላ፣ ከጥቅምት መጀመሪያ እስከ ነሐሴ መቋጫ (ለአሥራ አንድ ወራት ገደማ)፣ በመጀመሪያ ሰባት ወራት የውትድርና ሥልጠና፣ ለሚከተሉት አራት ወራት ለአካባቢ ማገገሚያ ተግባራት ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲውልና ይህም ፕሮግራም ቋሚ ሆኖ እንዲዘልቅ እመኛለሁ፡፡

ይህን መሰል ፕሮግራም የህልውና ጥያቄ፣ ብዙ ጊዜም የግጭት መንስዔ የሆነውን የአካባቢ መጎሳቆል፣ በሒደት ጋብ ሊያደርግ ብሎም ሊገታ ይችላል፡፡ ወጣቶች በውትድርና ሥልጠና ያገኙት የዲሲፕሊን ሥርዓት፣ ወጣቶቹን ከመንደራዊ አስተሳሰብ አላቆ፣ ከሁሉም በላይ የአገር ፍቅር ስሜትን ኮትኩቶ፣ አገር ወዳድነት አዳብሮ፣ በአገር ደረጃ ኃላፊነት የሚሰማቸው ወጣቶችን ያበረክታል የሚል ምኞት ብሎም እምነት አለኝ፡፡ በተጨማሪም የውትድርና ሥልጠና ለአካባቢ መልሶ መቋቋም ተሳትፎ አመለካከታቸውንም ሆነ ተግባራቸውን እንደሚያዳብር ይገመታል፡፡ የከተማ ወጣቶች ስለ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ የተሻለ ግንዛቤም እንደሚያጎናጽፍ አያጠራጥርም፡፡

ከዚህ ተግባር በተጓዳኝ፣ ምሁራን በሙያቸው ተሳትፎ እንዲያደርጉ እመኛለሁ፡፡ ለምሳሌ አርክቴክቶች መሐንዲሶችና፣ ሌሎችም ምሁራን ተረባርበው መጠነኛ ገቢ ያለው የገጠር ቤተሰብ (ደሃ ከተሜንም ሊጨምር ይችላል) ቤት ሊሠራበት የሚያስችለውን ቁስ/ “ማቴሪያል”፣ የሚሠራውን  ቤት ፕላን፣ ወዘተ. በጥናትና በምርምር ላይ ተመርኩዘው እንዲያበረክቱ እመኛለሁ፡፡ እንዲሁም የጤና አጠባበቅ፣ የግብርና ተግባር ለማሻሻል፣ የትምህርተ ስልት ለመቀየስ አመቺ ጊዜ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ በዚህም ሒደት ውስጥ መንግሥት ለምርምር/ለጥናት በቂ ድጋፍ መስጠት አለበት፡፡ በተጨማሪም ሌሎች ማበረታቻ ስልቶችንም መንደፍ ይገባል፡፡ ለምሳሌ እንደ ሽልማት ወዘተ፡፡ ይህንን ማድረግ አሁንም ካለን ችሎታ ውጪ አይደለም፡፡ ይህም ሰፋ ባለ መልክ ሲታይ በተፈጥሮ ሀብት በአግባብ መጠቀምን ያካትታል፡፡

ለዚህም ፕሮግራም አገር አቀፍ የሆነ ብሔራዊ የገንዘብ መዋጮ ቢደረግ፣ በተጨማሪም የመንግሥት መጠነኛ በጀት መመደብ ይገባል የሚል እይታ አለኝ፡፡ በኢትዮጵያ በአገር አቀፍ ደረጃ፣ ገንዘብ መዋጮ ማድረግ የተለመደ ነው፡፡

ቀደም ሲል በጽሑፍ ያቀረብኳቸው ምኞቶች

ከላይ ከተወሱት ምኞቶች ተጨማሪ፣ “በተፈጥሮ ሀብታችን በአግባቡ ለመጠቀም ምን ምን ብናደርግ ይበጃል?” በሚለው ጥያቄ ቀደም ሲል ያቀረብኳቸውን ምኞቶች ላቅርብ፡፡ ይህም በእኔ አዘጋጅነት ርዕይ 2020 በኢትዮጵያ “የኢትዮጵያ ኤንቫይሮመንት /አካባቢ ምን ይዘት አለው? የዛሬ 25 ዓመት ገደማስ ምን ሊመስል ይችላል በሚል ርዕስ ከታተመ (Economic Focus-Bulletin of the Ethiopian Economic Association -EEA Vol 5 No.5 August 2003) ቀጥታ የተዘረፉ ናቸው፡፡ ከታች የሰፈሩት ከዚህ ጽሑፍ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያሉዋቸው ምኞቶቼ ብቻ ናቸው፡፡

‹‹በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ በሆኑ የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ የተመሠረቱ የቱሪስት መስህቦች ተስፋፍተው፣ ከአካባቢው ጋር የሚጣጣሙና አካባቢውን መስለው የተመሠረቱ ሆቴሎችና ሞቴሎች ተሠርተው፣ ቀልጣፋ አገልግሎት ሲሰጡ የተፈጥሮ ሀብታችንን የደስታና የገንዘብ ምንጭ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህንን ብዙ ልምድ ካላቸው የውጭ ኩባንያዎች ጋር በጋራ ሠርቶ እውን ማድረግ ይቻላል፡፡ በዚህ ሒደት የአካባቢ ሙሉ ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡ የተሳትፎውም የጎላ ጎን ከባህል ቅርስ ተቆርቋሪነት ቢመነጭ ይመረጣል፡፡ የአካባቢው ኗሪዎች የሚያገኙትም ጥቅም መረሳት የለበትም፡፡›› ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ ይህም ምኞቴ፣ በከፊልም ቢሆን እየተሳካ ነው፡፡

ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት ከተመኘሁዋቸው አንዱ፣ ‹‹በከተሞች አካባቢ (አዲስ አበባን ያካትታል)  የመፀዳጃ ቦታዎች ተዘጋጅተው›› ማየት ነበር፡፡ ከሳምንት ገደማ በፊት ይህን ተግባር በአዲስ አበባ ከተማ ለማስተናገድ፣ የሕዝብ ድጋፍ መጠየቁ በጣም አስደስቶኛል፡፡

‹‹በአዲስ አበባ የሚገኙትን አምስት መለስተኛ ጅረቶችን (ወንዞች) አጽድቶ፣ ግራና ቀኝ ከ50 ሜትር ያላነሰ ክፍት ቦታ ሰጥቶ፣ ንፁሕ ውኃ እንዲፈስባቸው ሲደረግ ማየት ይቻላል፡፡ የመሠረተ ልማት (ቤት ወዘተ…) ግንባታ ከአረፈባቸው ቦታዎች ላይ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ቢያዳግትም፣ ለወደፊት ተመሳሳይ የቦታ አጠቃቀም ግድፈቶች እንዳይከሰቱ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡›› ይህ ምኞቴ በከፊልም ቢሆን እየተሳካ ነው፡፡

‹‹በተጨማሪም አመቺ ሥፍራዎች ላይ፣ በተለይም ብዙዎች ጅረቶች ተገናኝተው ከሚፈሱባቸው አካባቢዎች (ለምሳሌ በቦሌ፣ በቀበና፣ በቃሊቲ፣ ወዘተ..) ግድቦች ተገንብተው፣ የመዝናኛ ትናንሽ ሐይቆች ተመሥርተው ማየት ይቻላል፡፡ ይህም ለከተማዋ ልዩ ውበት እንደሚሰጣት አያጠራጥርም፣ ብሎም አዲስ አበባም ለሌሎች ለአገራችን ከተሞች ፋና ወጊ ሆና፣ ሌሎች ከተሞች ከእርሷ ልምድ/ ተሞክሮ በቂ ግንዛቤ አንግበው እነሱም ውበት በመጎናጸፍ ሒደት ተሰማርተው፣ ብሎም ሲዋቡ ማየት ይቻላል፡፡›› ይህን ለመተግበር መታሰቡን ገና አልተገነዘብኩም፡፡

ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት ከተመኘሁዋቸው ተግባር ያልተሳኩ ብዙ ናቸው፣ ጥቂቶቹ እነሆ፡፡ ‹‹ለተፈጥሮ ሀብት ግንዛቤ ከአሁኑ በተሻለ ትኩረት የሚሰጡ ፕሮግራሞች በሁሉም ትምህርት ቤቶች፣ በየኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ተቀርፀው፣ ተገቢውን የትምህርት መረጃ ሲያበረክቱ. የትምህርት ሒደት ውጤቱ፣ ስለ ተፈጥሮ ሀብት አያያዝ፣ አጠቃቀም፣ እንክብካቤ፣ ስለተፈጥሮ ሚዛን ግንዛቤን የሚያስጨብጡ ሆኖ ማየት እመኛለሁ፡፡ ይህንም ማድረግ ይቻላል፡፡››

‹‹በየከተሞች አካባቢ ባገር በቀል ዛፎች የተጌጡ (በከፊል የተሸፈኑ)፣ አገራዊ ደኖች/ ፓርኮች፣ አገር ወለድ የዱር እንስሳት የሰፈሩባቸው ቦታዎች ተመሥርተው ማየት ያሻል፡፡››

 በዛፎች የተሸፈኑ የመዝናኛ የከተማ አካባቢዎች፣ በሳምባ ሊመሰሉ ይችላሉ፡፡ ሳምባ በሕያው አካል ውስጥ የተከማቸን ቆሻሻ ሳምባ እንደሚያስወግድ ሁሉ፣ ዛፎች በአካባቢ ያለን በካይ አየር ያስወግዳሉ፣ ብሎም አካባቢው የጥሩ አየር መገኛ ያደርጋሉ፡፡

‹‹እነዚህም ቦታዎች ስለ አገር ግንዛቤ የሚያስጨብጡ፣ ለልጅ ልጅ የሚተላለፉ ቅርሶች ይሆናሉ፣ ይቻላልም፡፡ እያንዳንዱ ከአምሳ ሺሕ  በላይ ነዋሪዎች ያለው ከተማ፣ የእኔ ነው የሚለው የአገር በቀል ዛፎች ክምችት/ ስብስብ የሆነ ደን ፓርክ ያስፈልገዋል፡፡ በተጨማሪ፣ የማገዶን ፍጆታ ሙሉ በሙሉ የሚሸፍኑ ደኖችም፣ በከተሞች አካባቢ መደነን ይገባል፡፡ ይህንን ማድረግ አሁን ካለን አቅም ውጭ አይደለም፡፡ ሆኖም ከተሞች ማገዶን መጠቀም መቀጠል የለባቸውም፣ ሌሎች አማራጮች መፈለግ ይኖርባቸዋል- ለምሳሌ አገሪቱ በቂ ኃይል ማመነጨት በምትችልበት ጊዜ ማገዶ በኤሌክትሪክ ኃይል መተካት አለበት፡፡››

‹‹የመዝናኛ፣ የባህልና የስፖርት ማዕከላትን ማስፋፋት ያሻል፣ በተለይም ወጣቱ የሚዝናናባቸው፣ ስፖርት የሚሠራባቸው ሥፍራዎች በሰፊው መመሥረት አለባቸው፡፡ እንደነዚህ ዓይነት አገልግሎቶች በየአካባቢው ተደራጅተው ቢገኙ፣ ወጣቱ ትውልድ ራሱን በጫትና በአረቄ ከማደንዘዝ ፈንታ፣ በስፖርት በሙዚቃ በቴአትር ወዘተ… አዝናኝና ተዝናኝ እንዲሆን ያስችሉት ነበር ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ እያንዳንዱ ቀበሌ መጠነኛ የመዝናኛና/የስፖርት ቦታዎችን ክፍለ ከተማዎች ደግሞ፣ የተሟሉ የመዝናኛ/ስፖርት ማዕከላት ማደራጀት አለባቸው፡፡››

‹‹በትላልቅ ከተማዎች፣ በተለይም በአዲስ አበባ የሚከፈቱ አዳዲስ የትምህርት ማዕከላት ሰፋ ሰፋ ያሉ ቦታዎች ላይ ተመሥርተው፣ የእግር ኳስ፣ የመረብ ኳስ (የቮሊቦል)፣ የቅርጫት ኳስ፣ የቴኒስ መጫዎቻዎች ያሏቸው ሆነው፣ አዲሱ ትውልድ አሁን ካለበት የእስር ቤት መሰል አስተሳሰብ እንዲወጣ የሚያስችሉ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ለዚህ ዓይነቱ አገልግሎት የሚውሉ በቂ ክፍት ቦታዎች የትም አካባቢ (አዲስ አበባም ጭምር) ይገኛሉ፡፡ ይህ ነገውኑ ጀምሮ መሠራት የማይቻልበት ምክንያት የለም፡፡ ሕዝብ እንዲደሰት፣ እንዲዝናና ማስቻል፣ ማብቃት፣ የልማት ዋና ዓላማ መሆን ይገባዋል- ሕንፃ ብቻውን ልማት አይሆንም፡፡›› ለዚህም መጠነኛ ጥረት እየተደረገ ይመስላል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ፣ እንዳስፈላጊነቱም በየአካባቢው ‹‹አየሁህ/አየሁሽ›› የምትል ከአንድ ገጽ ያልበለጠች ጋዜጣ ማየት እመኛለሁ፡፡ በየሰፈሩ የምትታተመዋ ጋዜጣ፣ በየዕለቱ የምታሠራጨው ዜና፣ ሰሌዳ ቁጥር—-የሆነ፣ ይህን ዓይነት መኪና፣ በዚህ ሰዓት—እና አካባቢ፣ መንገድ ላይ/ ዳር (ሰፈር ጠቅሶ) የሙዝ ልጣጭ፣ የበቆሎ ቆረቆንዳ ወረወረ/ወረወረች፣ የመናፈጫ ቆሻሻ ወረቀት ጣለ/ጣለች፣ ተፋ/ተፋች፣ ወዘተ የሚል ይሆናል፣ ሌላም አካባቢ በካይ ተግባራት ሊታከልበት ይችላል፡፡

መደምደሚያ

ከአካባቢ ክብካቤና የተፈጥረሮ ሀብትን በአግባቡ ከመጠቀም አንፃር የሰነዘርኩዋቸው ብሎም የተመኘሁዋቸው ተግባራት ሁሉ እውን እንዲሆኑ እመኛለሁ፡፡ የአካባቢ ክብካቤ የአገር መውደድ/ ፍቅር አካል መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ እንዲሁም በሳይንሳዊ አስተሳሰብ መዳበር መንስዔ ምክንያታዊ ማኅበረሰብ እንዲመሠረት መፃር ያስፈልጋል፣ ያም እውን እንዲሆን ከፍተኛ ምኞቴ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ በአገር ደረጃ ኃላፊነት የሚሰማው ትውልድ ኮትኩቶ መገንባት እንደሚያስፈልግ አምናለሁ፣ ብሎም ምኞቴ እውን እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ ተስፋ ምኞትን ይጭራል፣ ካለተስፋ  መኖር ደግሞ ያዳግታል፡፡

ማስታወሻ፣ ማጣቀሻ የተደረገውን ዋና ጽሑፍ [ርዕይ 2020 በኢትዮጵያ ‹የኢትዮጵያ ኤንቫይርመንት/ አካባቢ ምን ይዘት አለው? የዛሬ 25 ዓመት ገደማስ ምን ሊመስል ይችላል በሚል ርዕስ የታተመውን (Economic Focus-Bulletin of the Ethiopian Economic Association -EEA Vol 5 No.5 August 2003)] ለማግኘት የምትሹ ሁሉ፣ የኤሌክትሮኒክ ኮፒ በኢሜይል ([email protected]) ልልክላችሁ እንደምችል እገልጣለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡ሐፊው  ሽብሩ  ተድላ  (ፒኤችዲ)  የአዲስ  አበባ  ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕይወት (ባዮሎጂ) ኢመረተስ ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ በርካታ የጥናትና ምርምር ሥራዎቻቸውን አሳትመዋል፡፡ ካሳተሟቸው መጻሕፍት መካከል ማኅበራዊና ሰብዓዊ (ሶሺያል ኤንድ ሂዩማኒስት) ጉዳዮችን  በጥልቀት ያቀረቡበት  ከጉሬዛም ማርያም እስከ  አዲስ አበባ  የሕይወት ጉዞ እና ትዝታዬ፣ የህያው ፈለግ፣ ከየት ወደ የት፣ ወረርሽኝ ይገኙበታል፡፡  ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles