Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አጀንዳ ነጣቂዎች!

ሰላም! ሰላም! ሳምንት አልፎ ሌላ ሳምንት ሲተካ በሰላም በመገናኘታችን ለፈጣሪያችን ምሥጋና ይድረሰው እላለሁ፡፡ እናንተም እንደ እኔ ምሥጋና እንደምታቀርቡ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እዚህ ምሥጋና ውስጥ የለንበትም የምትሉ ካላችሁ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ለማንኛውም ሁላችሁም እንዴት ሰነበታችሁ? እንደ እምነታችሁ ለሰላምታዬ ምላሽ የመስጠት መብታችሁ የተጠበቀ ነው፡፡ አዛውንቱ ባሻዬ፣ ‹‹ልጅ አንበርብር እንዴት ሰነበታችሁ ሲባል ምላሹ እግዚአብሔር ይመሥገን ነው፡፡ የፈጣሪን ስም ጠርተን ሰላምታ ስንለዋወጥ እሱ ከእኛ አይርቅም፡፡ ለዚህም ነው እግዚአብሔር ይመሥገን የፈጣሪ ምሳና እራቱ ነው የሚባለው…›› እያሉ ሳያስረዱኝ ያለፉበት ጊዜ የለም፡፡ እሳቸው በስተርጅና ዕድሜ ላይ ሆነው ሁሌም ፈጣሪን በከፍተኛ ፍቅርና አክብሮት ስሙን ሲጠሩት ፊታቸው ላይ የሚታየው የአዛውንትነት ፀዳል ያስደምመኛል፡፡ ምሁሩ ልጃቸውም እንደ እሳቸው ጥግ የደረሰ ማብራሪያ ባይሰጥበትም ፈሪኃ ፈጣሪ እንዳለው እመሰክርለታለሁ፡፡ ‹‹አንበርብር ሁሉም ነገራችን የሚከናወነው በፈጣሪ ፈቃድ ስለሆነ ሁሌም እሱን ማስታወስ ይገባናል…›› ይለኛል፡፡ እኔም በደስታ ነው ሐሳቡን የምጋራው፡፡ ደስ ሲል!

በቀደም ዕለት አንድ ደንበኛዬ ቀጥሮኝ ሰዓቱ እስኪደርስ በሐሳብ ተውጬ መንገዱ ላይ ስንጎራደድ፣ ‹‹አቶ አንበርብር ሥራ ፈተህ አንዴ ወደ ላይ አንዴ ወደ ታች ከምትል ለምን የኮሪደር ልማቱን ሄደህ አታግዝም…›› የሚል ድምፅ ሰማሁ፡፡ ድምፁ ለእኔ አዲስ ባይሆንም ሐሳቡ አስገርሞኝ ዞር ስል፣ ከሠፈራችን ትንሽ ምዕራፍ ራቅ ብሎ ያለ አትክልት ቤት ነጋዴ ነበር፡፡ አጠገቤ ደርሶ ሰላምታ ከሰጠኝ በኋላ፣ ‹‹ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ይህ የመንገድ ማስፋትና ማሳመር ሥራ ካልተጠናቀቀ እኮ፣ ሁላችንንም ጎርፍ ይዞን እንዳይሄድ መንግሥት የእኛን ዕገዛ ይፈልግ ይሆን ብዬ ነው…›› እያለ ኮስተር ብሎ ሲያየኝ፣ ‹‹ወንድሜ ሰዎቹ በየወሩ ግምገማ እየተቀመጡ ስለአፈጻጸማቸው ሲነጋገሩ ሐሳብ እንድንሰጥ ቢጋብዙን  የዕገዛው ጉዳይ አይገድም ነበር…›› አልኩት፡፡ ልብ ብለን ካሰብንበት እኮ የአትክልት ነጋዴው ሥጋት ትክክል ነው፡፡ ዘንድሮ ጎርፍ ያስፈራል ተብሎ ብርቱ ማሳሰቢያ ሲነገረን የኮሪደር ልማቱም የጎርፍ ሰለባ ሆኖ ችግር እንዳይፈጠር ለማለት ነው፡፡ ይታሰብበት!

በዚህ መሀል የስልኬ የመልዕክት ማሳወቂያ ጮኸ፡፡ የእንጀራ ነገር ሆኖብኝ በፍጥነት ከካፖርቴ ኪስ ውስጥ መዝዤ አጮልቄ ሳይ፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተሳትፎ ጥሪ ነበር፡፡ ‹‹አጀንዳችን ለነገዋ ኢትዮጵያችን!›› የሚል ርዕስ የያዘው መልዕክት፣ ‹‹የአጀንዳ ሐሳብ በመስጠት በአገራዊ ምክክር ሒደቱ ላይ በንቃት እንሳተፍ›› ይላል፡፡ ጎበዝ እኔ እንዲህ ዓይነት ጥሪ እጅግ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ በሁሉም አገራዊ ጉዳዮቻችን እስቲ እንነጋገር፣ እንከራከር፣ እንደራደር፣ በጋራም ለአገር የሚጠቅም የውሳኔ ሐሳብ ላይ እንድረስ የሚል ነገር አልናፈቃችሁም? ወይስ ተቀምጦ በሰከነ መንገድ ከመነጋገር ይልቅ እንደ ፈረደብን እየተጨራረስን የድህነት መጫወቻ መሆን ይሻለናል? እኔ በበኩሌ ለዚህ አገራዊ ምክክር ዕድል ሰጥተን የሰላም ማምጫውን መንገድ ብንሞክረው እመርጣለሁ፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም ለዚህ ጉዳይ ጀርባቸውን የሚሰጡ ሰዎች ያናድዱኛል፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አንበርብር አትናደድ፣ አንተ የምትላቸው ሰዎች እኮ በራሳቸው አዕምሮ ሳይሆን በሌሎች ነው የሚነዱት…›› ሲለኝ መለስ እላለሁ፡፡ ወገኖቼ ችግሮቻችንን በጠመንጃ እንደማንፈታ ልምዱ ያላቸው ባዕዳን ሲነግሩን፣ እኛ በተቃራኒው ከተጓዝን አገራችንን ለጠላት ቀላል ዒላማ እንደምናደርጋት አትጠራጠሩ፡፡ እንዲያ ነው!

በእግር በፈረስ ፈልጎ ሊያገኘኝ የቀጠረኝ ደንበኛዬ ዘንድ በሰዓቱ ደርሻለሁ፡፡ መሀል ቦሌ ውብ የሆነው ዘመናዊ ሕንፃው ውስጥ የሚገኘው ቢሮው ስደርስ ሲያይዋት የምታሳሳ ቀይ ብስል ቆንጆ ጸሐፊ ተበቀለችኝ፡፡ መቼም በውበቷ ብቻ ሳይሆን በኦፊስ ማኔጅመንት ዕውቀት የተላበሰች እንደሆነች አነጋገሯና ሁኔታዋ ያሳብቃሉ፡፡ ደንበኛዬ ዘንድ ያሉ እንግዶች እስኪጨርሱ ቡና ከውኃ ጋር ቀርቦልኝ በነበረኝ ቆይታ፣ ውቢት አንዴ በእንግሊዝኛ ሌላ ጊዜ በፈረንሣይኛ ልቅም ባለ የንግግር ክህሎት ከሚደውሉ ሰዎች ጋር ስትነጋገር ፈዘዝኩ፡፡ እኔ ብዙ ቦታ ሄጃለሁ እንደ እሷ ዓይነት በውበትም ሆነ በሚገርም ክህሎት ሥራዋን የምታከናውን ጸሐፊ ገጥማኝ አታውቅም፡፡ እርግጥ ነው ብዙ ጎበዞች ይኖራሉ፣ የእዚችኛዋ ግን በቃላት ለመግለጽ የሚያዳግት ነው፡፡ ፍዝዝ ነበር ያደረገችኝ፡፡ አደራችሁን ውዴ ማንጠግቦሽ እንዳትሰማ ይህንን ጉዴን፡፡ እኔማ እንዲህ ዓይነት ጥቂት ሰዎች ሲያጋጥሙኝ ምናለበት ለአገራችን ብዙ ቢሆኑልን እላለሁ፡፡ ምኞት ነው!

ደንበኛዬ እንግዶቹን ሸኝቶ በሞቀ አቀባበል ቢሮው ይዞኝ ገባ፡፡ ይህ ሰው ሁሌም እንዳስገረመኝ ነው፡፡ ቢሮው ቀለል ባሉ የቢሮ ዕቃዎች እንጂ የተንዛዙ ነገሮች አልተሞላም፡፡ ግድግዳው ግን መሳጭ በሆኑ ሥዕሎች የተንቆጠቆጠ ሲሆን፣ የሰውየውን የጥበብ ብቻ ሳይሆን ጥልቅ የሆነ ሰብዓዊነት የሚናገሩ ሥዕሎች ተሰድረዋል፡፡ ተፈጥሮን ከማድነቅ እስከ የተጎሳቆሉ መንደሮችና ሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ገላጭ ናቸው፡፡ እሱ አፍ አውጥቶ አይናገርም እንጂ በርካታ ትምህርት ቤቶችን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ብዙ ሥፍራዎች አስገንብቷል፡፡ ኑሮ የከበዳቸው በርካቶችን ይደጉማል፡፡ ዩኒቨርሲቲ አስገብቶ የሚረዳቸው ብዙ ወጣቶች እንዳሉም ሰምቻለሁ፡፡ ለገጠር ቤተ ክርስቲያናት ግንባታና ለአገልግሎታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ የቅርብ ሰዎቹ ይናገራሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት የተከበረ ሰብዕና ያለው ሰው አንድም ቀን አልባሌ ቦታ ታይቶ አይታወቅም፡፡ ሁሌም ሥራ ላይ፣ ሁሌም የታመሙ ጥየቃ፣ ሁሌም ሰብዓዊ ተግባራት ላይ መገኘቱ ይደንቀኛል፡፡ ብዙዎች ውስኪ እያንቆረቆሩ በስስትና በክፋት ተዘፍቀው አገር ለመዝረፍ ሲያደቡ፣ ይህ የተከበረ ሰው ግን ለፍቶ ከሚያገኘው ላይ ወገኖቹን ለመደገፍ የሚሄድበት ርቀት ያስገርመኛል፡፡ ሰው ከሆኑ አይቀር እንዲህ ነው፡፡ ሺሕ ዓመት አይኖር!

ደንበኛዬ በፍጥነት ለምን እንደፈለገኝ ነገረኝ፡፡ ይኼ ሰው ምን እንዳለኝ ታውቃላችሁ? ‹‹አንድ መቶ ቤተሰቦች የሚኖሩባቸው የአፓርትመንት ሕንፃዎች ገንብቼ በዕጣ ለዕድለኞች ማስተላለፍ ስለምፈልግ፣ ለዚህ የሚሆን የግል ይዞታ በፍጥነት ፈልግልኝ…›› ነበር ያለኝ፡፡ ‹‹በሕልሜ ነው ወይስ በዕውኔ…›› እያልኩ ለራሴ ሳጉተመትም፣ ‹‹አቶ አንበርብር በዕውንህ ነው፣ ይልቁንስ ከአሁኑ ሰዓት ጀምሮ ሥራህን ጀምር…›› ብሎኝ የባንክ አካውንቴን ቁጥር ጠየቀኝ፡፡ አሁንም ቅዠት ላይ ያለሁ ይመስል ስደነባበር፣ ‹‹አቶ አንበርብር ጊዜ የለንም እባክህ የአካውንትህን ቁጠር ንገረኝ…›› ብሎ ከቅዠቴ መሀል ሲቀሰቅሰኝ ነቅቼ እየተንተባተብኩ የአካውንቴን ቁጥር ሰጠሁት፡፡ ለሥራ ማስኬጃ ብሎ አካውንቴ ውስጥ የዶለለኝ በትንሹ አራት ወር ቀብረር አድርጎ የሚያኖረኝ ገንዘብ ነበር፡፡ ወገኖቼ ይህ ሰው የተናገረውን በተግባር የሚሠራ፣ ቃል የገባውን የሚፈጽም፣ ለዋዛ ፈዛዛ ቦታ የሌለው፣ ደግነቱ ከመብዛቱ የተነሳ ለሰው ልጅ አዕምሮ የሚከብድ፣ እንዲያው በደፈናው የፈጣሪን ትዕዛዛት በሚገርም ሁኔታ ሥራ ላይ ያዋለ መሆኑ ይደንቀኛል፡፡ ፈጣኑን ሥራ በአክብሮት ተቀብዬ እንቅስቃሴ ጀምሬያለሁ እላችኋለሁ፡፡ ይቅናህ በሉኝ!

የእዚህን ለየት ያለ ሰው ድርጊት ለምሁሩ ወዳጄ ስነግረው፣ ‹‹መቼም እዚህች አገር ውስጥ ያለን በሙሉ ብንደመር ይህንን ሰው እንመጥናለን ለማለት ይከብደኛል፡፡ የእኛ እንደ ላባ የቀለለ የዘወትር ሥራ የእዚህ ሰው ሥራ ላይ ለመድረስ ከዚህ እንደ ፀሐይ የሚርቅ ጉዞ ይፈልጋል፡፡ በታሪካችን እንደ ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ የመሳሰሉ ከወጣትነት እስከ አዛውንትነት ድረስ አገራቸውን ያለ አንዳች ጥቅም ያገለገሉ ሰዎችን ውለታ ቢስ ሆነን የገደልን፣ እንደ አፄ ምኒልክ የመሳሰሉ በበርካታ መቶ ዓመታት አንዴ መገኘታቸው የሚያጠራጥሩ ሰዎችን የምናናንቅ፣ የራሳችንን ጊዜ ተጠቅመን ታሪክ መሥራት ሲገባን ባልኖርንበት ዘመን ላይ ተመሥርተን የምንጣላና የምንጋደል፣ ሀብት በአቌራጭ ማግበስበስ እንጂ ማካፈል የማናውቅ፣ ግብር ማጭበርበርና መሰወር፣ ሌብነትን ሙያ ማድረግ፣ ለሰው ልጆች ክብር መንፈግ፣ በጉልበት በመመካት አስገድዶ መድፈርና የመሳሰሉት ድርጊቶቻችን ያሳፍሩኛል…›› እያለ ሲንገፈገፍ ከፋኝ፡፡ እህት ወንድሞቼ በመልካም ሰዎች ሚዛን ካልሆነ በስተቀር በመንጋ ድጋፍ ዕብደት እንጂ ጤና አይኖርም፡፡ እንዲያ ነው!

ሰሞኑን ደላላ ወዳጆቼ ጋር የምንገናኝበት የጀበና ቡና መሸጫ ተቀምጠን ወጋችንን እንሰልቃለን፡፡ እንደምታውቁት የደላላ መሰባሰቢያ ማለት የከተማው ኢኮኖሚና ፖለቲካ እንደ ካርታ የሚፐወዝበት ማለት ነው፡፡ አንዱ ድለላም ዲጂታል እንደሚሆን እየነገረን ነው፡፡ አንዱ ነባር ደላላ፣ ‹‹ድላላን በአናሎግም በዲጂታልም ማስኬድ ይቻላል፡፡ ዋናው ቁምነገር ሥርዓት ይዞ መሥራት ብቻ ነው የሚያስፈልገው…›› እያለ ሲያብራራ፣ ‹‹አሁን እኮ ድለላ ከመኖሪያ ቤት እስከ መሥሪያ ቤት ድረስ የሁሉም ሥራ እየሆነ ነው፡፡ ጃኬት፣ ሱሪ፣ ቲሸርት፣ ቀሚስ፣ ጫማ፣ የቤት ቁሳቁስ… በዲጂታል ንግዱ እየተቀላጠፈ እኮ ነው…›› ብሎ ሌላው ወጣት ደላላ ተናገረ፡፡ ‹‹እናንተ ይህንን ትላላችሁ፣ ማታ ማታ እስኪ ወደ ክለቦች ጎራ በሉ፡፡ የሜትር ታክሲ ሾፌሮች ከአንዱ ክለብ ወደ ሌላው ደንበኞችን ሲያንቀሳቅሱ ብቻ የሚያመሹ መሰላችሁ እንዴ፡፡ በዋትስአፕና በቴሌግራም እዚያው ክለብ ውስጥ በዓይን እየተያዩ የተፋፈሩ ወንድና ሴትን የአዳር ሒሳብ እያደራደሩ ይደልላሉ…›› በማለት ሌላው ወጉን አሰፋው፡፡ …ቀን ሥራ ላይ የምናውቃቸው እኮ ማታ አካላቸውን መቸርቸር ሥራቸው ከሆነ በጣም ቆየ…›› ብሎ ዋጋውም እስከ ሃያና ሰላሳ ሺሕ ብር መሆኑን ሲዘረዝርልን ተገረምን፡፡ ጉድ በሉ ማለት አሁን ነው!

በሉ እስቲ እንሰነባበት፡፡ ከቀኑ ፋታ አልባ ድካም በኋላ ያላበው ቢራ እየተጎነጨን ለማውጋት ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር ግሮሰሪ ተቀጣጥረናል፡፡ ቀልጣፋ አስተናጋጅ የምንፈልገውን አቀራርቦልን መጎንጨት ስንጀምር፣ ‹‹ውሎ እንዴት ነበር…›› በማለት አፌን ሳሟሽ ከፊት ለፊታችን መቀመጫ አንዱ፣ ‹‹ውሎ እንደ ግለሰቡ ሁኔታ ሳይሆን እንደ አገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ነው የሚመዘነው…›› ብሎ ጣልቃ ሲገባ፣ ‹‹ወዳጄ አጠገብህ ካለው ጋር ያንጠለጠልከውን ወሬ መጀመሪያ ጨርስ…›› ሲለው ወዳጄ ሳቅ አፈነኝ፡፡ ያኛውም ቀልደኛ ኖሮ፣ ‹‹የኮሪደር ልማቱም ተንጠልጥሎ እንዳይቀር ማሳሰቢያ ሲሰጥ ነበር…›› ብሎ፣ ‹‹እውነት እኮ ነው ለምንድነው እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቶች ሌሎችም በፍጥነት የማይከናወኑት…›› እያለ ያላሰብነውን ካሰብነው ጋር ሲቀላቅለው አስደነገጠን፡፡ ‹‹አንበርብር ሰውዬውን አጠገቡ ለተቀመጠው ሰው ካልተውነው ከአጀንዳችን ውጪ ሌላ ቦታ ስለሚከተን ዝም እንበለው…›› ብሎኝ የራሳችንን ውሎ መነጋገር ጀመርን፡፡ ጎበዝ በሌሎች አጀንዳ እየተጠለፍን እኮ ነው የራሳችንን በወጉ መነጋገር ያልቻልንበት፡፡ አጀንዳ ነጣቂዎች ከያሉበት ብቅ ብቅ ሲሉ እኛ ደግሞ በግራ አሳይተን በቀኝ መታጠፍ መቻል አለብን፡፡ የአጀንዳ ነጣቂዎች ሰለባ ከመሆን በራሳችን አጀንዳ ብንመራ ኖሮ ሰላማችንን አጥተን የድህነትና የኋላቀርነት መፈንጫ አንሆንም ነበር፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት