Sunday, June 23, 2024

ከግጭት አዙሪት ውስጥ የሚወጣው በሰጥቶ መቀበል መርህ ነው!

የኢትዮጵያን ሰላም፣ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅሞች ማዕከል በማድረግ መነጋገር ሲቻል ለጠብ የሚጋብዙ ምክንያቶች አይኖሩም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚደረጉ ክንውኖች በሙሉ ከጥፋት የዘለለ ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች በእኩልነትና በነፃነት መነጋገር ያለባቸው ዜጎችም ሆኑ ፖለቲከኞች፣ ከሁሉም አቅጣጫ የሚሰነዘሩ ሐሳቦች ዋጋ አግኝተው ለአገር ጠቀሜታ እንዲያስገኙ ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ የሐሳብ ምኅዳሩ ግልጽ፣ ዴሞክራሲያዊና እንከን አልባ ሆኖ እንዲከናወን ደግሞ ከየትኛውም ወገን ጫና ሊፈጥሩ የሚችሉ ንግግሮችም ሆኑ ድርጊቶች ሊታሰብባቸው ይገባል፡፡ የሐሳብ አቀራረቡ በነፃነት እንዲከናወን የሚያስፈልገው የተለያዩ ዕይታዎች ያለ እንቅፋት እንዲንሸራሸሩ ነው፡፡ ለአገር እስከጠቀሙ ድረስ ሁሉም ሐሳቦች ዋጋ አላቸው ተብሎ ስለሚታሰብ፣ በመንግሥት ሆነ በሌላ አካል ዋጋ ቢስ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ከችግር ውስጥ እንድትወጣ ለሁሉም ሐሳቦች እኩል ትኩረት ይሰጥ፡፡

በሐሳብ ገበያው ውስጥ ተስፋ የሚያስቆርጡ ድርጊቶች ሲስተዋሉ ንቁ ሆኖ እርምት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በከፍተኛ ትኩረት የሚከታተለው ኢትዮጵያ ለምን ከግጭት አዙሪት ውስጥ መውጣት እንዳቃታት ነው፡፡ በቅርቡ ይፋ በተደረገ ጥናታዊ መረጃ መሠረት በመቶ ሺዎች አልቀውበት በርካታ ሚሊዮኖች የተፈናቀሉበት፣ እንዲሁም ከፍተኛ የአገር ሀብት የወደመበት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ኪሳራ 44 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህ እሳት ውስጥ የተጣለ ሀብት ለውድመት ተዳርጎ ዜጎችን ለምድራዊ ሲኦል ፈተና ከማጋለጡ በፊት፣ በእርጋታና በስክነት በመነጋገር ያጋጠመውን አለመግባባት መፍታት ይቻል ነበር፡፡ በተጨማሪም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ በሚካሄደው ውጊያ እየደረሰ ያለው ጥፋት ከንግግር በዘለለ ለመጨራረስ የሚያበቃ አልነበረም፡፡ የተለያዩ ሐሳቦችን ወደ መነጋገሪያው መድረክ አምጥቶ በስክነት መወያየት ሲቻል፣ አሁንም ከሰሜኑ ዕልቂትና ውድመት ለመማር ባለመፈለጉ ከባድ ኪሳራ እየደረሰ ነው፡፡

በምግብ ራስን መቻል እጅግ ከባድና አስቸጋሪ በሆነባት አገር ውስጥ ፆሙን እያደረ ያለ ሰፊ የእርሻ መሬት ማልማት፣ በአፍሪካ ግዙፍ የሚባለውን የውኃ ሀብት ለተለያዩ ሥራዎች መጠቀም፣ በዓይነታቸውና በመጠናቸው የበዙ ማዕድናትን ለውጭ ገበያ አውጥቶ መሸጥ፣ ቁጥራቸው የበዛ የቱሪስት መስህቦችን አልምቶ የጎብኚዎችን ቀልብ መሳብ፣ ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ የጥሬ ዕቃ ምንጮችን በብዛት ማምረት፣ ከምንም ነገር በላይ ደግሞ ከ120 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 70 በመቶ ያህል የሆነውን ወጣት ኃይል ለብሔራዊ ሀብት ልማት ለማንቀሳቀስ የሚያስችሉ የፖሊሲ ማዕቀፎችን ማዘጋጀትና የመሳሰሉት ሥራዎች ተወዝፈው ድህነት ተንሰራፍቷል፡፡ ከድህነት ውስጥ በፍጥነት ሊያስወጡ የሚችሉ ሥራዎችን በቅደም ተከተል ለማከናወን የሐሳብ መዋጮ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ አገራቸውን በቅንነት ለማገዝ ከቆረጡ ኢትዮጵያውያን ማግኘት አያቅትም ነበር፡፡

ኢትዮጵያ በዕድገት ወደፊት ለመገስገስ ከምንም ነገር በፊት ሰላም ያስፈልጋታል፡፡ ሰላም በሌለበት እንኳንስ ዕድገትን ማሰብ በሰላም ወጥቶ መግባትም አይቻልም፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ የሕዝባችን ትልቁ ችግር የሰላም ዕጦት ነው፡፡ ሰላም እንዲሰፍን ግን የሁሉንም ወገኖች ትብብር ይፈልጋል፡፡ መንግሥት ከማንም በፊት ግማሽ መንገድ ተጉዞ የሰላሙን ጎዳና ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ በሰላማዊውም ሆነ በአመፅ መንገድ ላይ የተሰማሩ ተቀናቃኞቹ የቀረውን ግማሽ መንገድ መጓዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በመተማመን ላይ የተመሠረተ ግንኙነት መኖር አለበት፡፡ በየትኛውም የፖለቲካ ልዩነት ውስጥ በሥርዓት ተቀምጦ ለመነጋጋር አጀንዳ ያስፈልጋል፡፡ ይህ አጀንዳ የተለያዩ ሐሳቦች የታጨቁበት ሆኖ በእኩልነት የሚያነጋግር መድረክ ይሻል፡፡ አንዱ ሌላውን የሚጫንበት፣ ትከሻውን የሚያሳይበት፣ ወይም ምን ታመጣለህ ብሎ የሚታበይበት ሳይሆን ለዘላቂ ሰላም መስፈን የሚያግዝ ቅንነትና ፈቃደኝነት መኖር አለበት፡፡

በአገራዊ ምክክሩ አማካይነት ለኢትዮጵያ ሰላም ተስፋ ሰጪ ምልክቶች መታየት ሲገባቸው፣ ከወዲሁ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች መስተዋል ሲጀምሩ ለአገራቸው ሲሉ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል የሚፈልጉ ዜጎች ይሳቀቃሉ፡፡ ቀድሞም ለምክክሩ ጀርባቸውን የሰጡ ደግሞ ‹ምን ብለን ነበር› እያሉ ተስፋ መቁረጡን ያባብሳሉ፡፡ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር በሁሉም ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር እንዲደረግና የተሻሉ ሐሳቦች ተጨምቀው እንዲወጡ፣ መሰናክል ከማብዛትና አላስፈላጊ ሰበቦችን ከመደርደር መውጣት ያስፈልጋል፡፡ መንግሥትም ሆነ የሚመራው ገዥ ፓርቲ በአገራዊ ምክክሩ እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ሆኖ መሳተፍ ሲገባው፣ የምክክሩ አቅጣጫ ቀያሽ ወይም መሪ መሆን የለበትም፡፡ ሌሎች ወገኖችም አለን የሚሉትን ሐሳብ አቅርበው ከመደመጥ ውጪ ሒደቱን ማወክ የለባቸውም፡፡ ከዚህ ተቃራኒ የሚኖሩ ድርጊቶች ተስፋን ከማጨለምና የቀውስ አዙሪቱን ከማባባስ የተሻለ ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡

ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ሲሉ ማድረግ ከሚገቧቸው ጉዳዮች መካከል ዋና ዋናዎቹ በተቻለ መጠን ገንቢና ጠቃሚ ሐሳቦችን ማቅረብ፣ የሌሎችን ዕይታ በፀጋ መቀበል፣ ፍላጎቶቻቸውም ሆኑ ጥቅሞቻቸው ከኢትዮጵያ ህልውና በታች እንደሆኑ ማመን፣ ለፀብና ለግጭት ከሚቀሰቅሱ ነውጠኝነቶች መታቀብ፣ በብሔርና በጥቅም ትስስር በመቧደን ከሌብነት፣ ከዘረፋ፣ ከሴራ፣ ከክፋት፣ ከቂም በቀል፣ ከአጓጉል ትርክቶችና ከመሳሰሉት አክሳሪ ድርጊቶች መራቅ ይጠቀሳሉ፡፡ ከሞላ ጎደል ልዩነቶችን ይዘው ለአገራቸው ሲሉ በስክነት ለመነጋገር፣ ለመደራደርና የጋራ አቋም ለመያዝ ጥረት ያድርጉ፡፡ ኢትዮጵያ ከገባችበት ቀውስ ውስጥ ባጠረ ጊዜ መውጣት የምትችለው፣ ሁሉም ልጆቿ በመግባባት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ሲኖራቸው ነው፡፡ በእኩልነት፣ በመፈቃቀድና በመተማመን ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንዲኖር ለሰጥቶ መቀበል መርህ መገዛት ያስፈልጋል፡፡ ከግጭት አዙሪት ውስጥ መወጣት የሚቻለውም በሰጥቶ መቀበል መርህ ብቻ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሕግ የማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

የሕግ መሠረታዊ ዓላማ ዜጎችን ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች መጠበቅ፣ ለሕይወታቸውና ለንብረታቸው ከለላ መስጠትና በሥርዓት እንዲኖሩ ማድረግ ማስቻል ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል...

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...