Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሲቀር ለሚቀረው…!

ጉዞ ከጎሮ ወደ መብራት ኃይል። በስንት ጥበቃ የተገኘ ሚኒባስ ታክሲ ተሳፍረናል፡፡ ‹‹ተማር ልጄ… ተማር ልጄ… ሀብት ዘመድ የለኝ…›› የሚለው የአለማየሁ እሸቴ ጊዜ የማይሽረው ጥዑመ ዜማ ይንቆረቆራል። ‹‹እንዲህ ተብሎ ተዘፍኖ ለትምህርት የተለመነበት አገር ውስጥ ነው እንዴ፣ በድንጋይ ውርወራ የተጀመረው የተማሪዎች ትግል አብዮት ወልዶ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት የምንባላው?›› ትላለች መሀል ወንበር የተቀመጠች ወይዘሮ።  መንቀሳቀስ ጀምረናል። ጋቢና አባትና ጎረምሳ ልጃቸው ተቀምጠዋል። ለጊዜው ሁለቱ ብቻ ናቸው የሚያወሩት። አባት፣ ‹‹ነግሬሃለሁ ደጋግሜ እኔ የማወርስህ ምንም ነገር የለኝም። በራስህ ጥረት ኑሮህን ለማሸነፍ ዋናው ቁልፍ ትምህርት ነው። አይ ካልክ አንተ ታውቃለህ። ምን አበላው ይሆን፣ ምን አለብሰው ብዬ የምጨነቅበት ምክንያት የሚኖረኝ እንዳይመስልህ ከእንግዲህ ወዲህ። አርፈህ ትምህርትህ ላይ በርታ ብያለሁ…›› ይላሉ፡፡ ጎረምሳው የ12ኛ ክፍል የዘንድሮ ፈተና ተፈታኝ ነው መሰል አቀርቅሮ ያዳምጣቸዋል። ከትምህርቱ ይልቅ አባቱ የሚፈጥሩበትን ጫማ መሸከም የከበደው ነው የሚመለስለው። ጭነቱ ሁሉም ዘንድ ነው እንዴ የከበደው!

ከታክሲው ስፒከር የአለማየሁ እሸቴ ዘፈን ሲያልቅ የድሮው የአያሌው መስፍን ዘፈን ተከተለ፡፡ አያሌው በዚያ መረዋ ድምፁ፣ ‹‹ተው ቻለው ሆዴ… ተው ቻለው ሆዴ… ሲቀር ለሚቀረው ምነው መናደዴ…›› እያለ ትኩረታችንን ሰረቀው፡፡ ‹‹… ሲያልፍ ለሚያልፍ ቀን ምነው መንገብገቤ…›› እያለ ሲያክልበት፣ ‹‹እህህህ… ወይ ጊዜ፣ ‹ነበር እንዲህ ቅርብ ነበር› ያሉት እቴጌ ጣይቱ እውነታቸውን ነው… እህህህ…›› እያሉ አንድ አዛውንት ሲብሰለሰሉ ሰማናቸው፡፡ ያቺ ሐያሲ መሳይ ወይዘሮ፣ ‹‹አባቴ የጊዜን ነገርማ ተውት፡፡ እንኳንስ ያለፉት ሃምሳ ዓመታት ይኸው ያለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ስንት ነገሮች ተከናወኑ… ብቻ ሆድ ይፍጀው…›› እያለች ስትናገር፣ ‹‹አሁንስ አልበዛም እንዴ… እኛን እኮ አላላውስ ብሎ እግራችንን የሚጎትተው ያ ትውልድ የሚባለው የዚያን ዘመን ሰው ከፖለቲካው ውስጥ አልወጣ ብሎ ማስቸገሩ ነው፡፡ ለዚህ ዘመን የሚመጥን ሐሳብ ያላቸው ወጣቶች እያሉ ለምንድነው በእኛ ተስፋ ላይ የበፊቶቹ ለመወሰን የሚንደፋደፉት…›› ብላ አንዲት ጠይም ኮስታራ ወጣት በንዴት ስትናገር ሰማናት፡፡ ወይ ቁጣ!

ወያላው ሒሳብ እየሰበሰበ ነው። መካከለኛው የጥንዶች ረድፍ ላይ አንድ ጎልማሳና ቆንጅዬ ወጣት በቀስታ ይጫወታሉ። ጎልማሳው በትውልዶች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት መካረሩ እያስገረመው፣ ‹‹ይኸውልሽ ይህች ብስጩ ወጣት ያነሳችው ሐሳብ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ልክ እንደ በፊቶቹ ደምፍላታም ወጣቶች እሷም ንዴቷን መቆጣጠር ባለመቻሏ ሁሉንም አንድ ላይ ጨፍልቃ ትራገማለች፡፡ የበፊቱ ለአሁኑ፣ የአሁኑ ደግሞ ከበፊቱ የሚቀባበሉት በርካታ ጥሩ ነገር እያለ የሚተኮረው አይረቤው ትርክት ላይ ነው፡፡ እኔ ከልምዴ የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር የዘመኑን ነገር ለዘመኑ ሰው መተውን አስፈላጊነት ቢሆንም፣ የበፊቱ መልካም ተሞክሮ ሲታከልበት ደግሞ ውጤቱ ከሚጠበቀው በላይ ይሆናል…›› ብሎ ሲያብራራ ሰማነው፡፡ ቆንጅዬዋም፣ ‹‹ጋሼ እውነትህን ነው፣ ትልቁ ችግር ግን ለመነጋገርና ለመደማመጥ የሚያስችል ባህል አለመገንባታችን ይመስለኛል፡፡ መነጋገርን ባህል ስናደርግ እኮ የሐሳብ ልውውጡ በሥርዓት ይመራል፡፡ በሥርዓት የሚመራ ንግግር ደግሞ የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ ያግዛል፡፡ ሥርዓት ሲኖር በእኩልነትና በመተሳሰብ ላይ የተመሠረተ መቀራረብ መፍጠር አያዳግትም…›› ብላ ንግግሯን ስትቋጭ ከውበቷ በላይ ብስለቷ ማረከን፡፡ ምናለበት እንዲህ ማሰብ ብንችልበት!

ጉዟችን ቀጥሏል። ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየሙ ወጣቶች ሥጋት አዘል ጨዋታ ይዘው የተሳፋሪውን የመኖር ተስፋ ያጨልማሉ። ‹‹አንተ ዶናልድ ትራምፕ በ34 ክሶች ጥፋተኛ ነው መባሉ በአሜሪካ ላይ መዓት ሊያመጣ ይችላል እየተባለ ሲነገር ሰማሁ…›› ይላል አንደኛው። ‹‹ዓለም በኑክሌር ቦምብ መጥፊያዋ ተቃርቧል ሲባልም ሰምቻለሁ…›› አለው ሌላው፡፡ ‹‹አይ ጉድ የዛሬ ልጆች የመጣባችሁ ጣጣ። እኛስ በደጉ ጊዜ አየሩ ሳይበረዝና የሰው ባህሪ ሳይቀር ተቻችለን ኖረናል። የዛሬ ልጆች ግን ምን ዓይነት ጉድ ነው የመጣባችሁ?›› ብለው አዛውንቱ አንገታቸውን ወዘወዙ። ‹‹ኧረ በስንቱ እንወዝወዝ እናንተ?›› ከአዛውንቱ አጠገብ የተቀመጡ ትልቅ ሴት ቀጠሉ። ‹‹በቁራሽ እንጀራ ለምትዘጋ አንጀት እንዲህ ላይ ታች ስንል ኖረን ማለፋችን ሳያንስ ደግሞ ሌላ ጣር?›› ሲሉ አጠገባቸው መጽሐፍ የሚያነብ ወጣት፣ ‹‹ለዚህ እኮ ነው የእርስ በርስ ፍትጊያችንን አቁመን ለሰላም መስፈን ጠበቃ መሆን የሚጠበቅብን…›› በማለት እያንዳንዳችንን በዓይኑ ቃኘን፡፡ ከተሳፋሪዎች መሀል  አንዱ፣ ‹‹የፓርላማው አልበቃ ብሎ ደግሞ ወደ ታክሲ ተዞረ? ለነገሩ በአምላክ ፀጋና ቸርነት ለሚኖር ሁሉን አሜን ብሎ መቀበል እንጂ ሌላ ምን ምርጫ አለው?›› ብሎ አረፈው።  ወዲያው ደግሞ፣ ‹‹ታዲያስ ‹ወገኛ ቀበሮ ሙክት ያባርራል› አለ የአገሬ ሰው። አሁን ማን ይሙት እነ አሜሪካ ዓለምን ማተራመስ ባይፈልጉ እንዲህ መከራ እናይ ነበር?›› ሲል ጎልማሳው፣ እርስ በርስ የዶለቱ ይመስል ተሳፋሪዎች በአንድ ቃል፣ ‹‹‘እኛ ምኑን አውቀን?›› አሉ፡፡ አቤት ድንጋጤ? መርበትበት በሉት!

‹‹ትራምፕስ በአንድ በኩል የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት፣ አሁንም ለፕሬዚዳንትነት አሸናፊነት የታጨ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ቢሊየነር ነው፡፡ እሱ በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ ተወስኖ ከአንድ ወር በኋላ ይታሰር አይታሰር አናውቅም፡፡ የሕጋዊውም ሆነ የፖለቲካው ጦስ ለአሜሪካውያን እንጂ ለእኛ ምን ይፈይዳልና ነው ይህ ሁሉ ሥጋት…›› ብላ ያቺ ጠይም ቁጡ ወጣት የረሳነውን ስታስታውስ፣ ‹‹እንዴ አንቺ ልጅ ምን ነክቶሻል ዛሬ… የአሜሪካ ጉዳይማ እንኳን እኛ ዲቪን በታላቅ ጉጉት ለምንጠብቀው ለመላው ዓለም ጭምር ትልቁ አጀንዳ ነው፡፡ በዚያ ላይ አስቢው አሜሪካ የምትባለው የተስፋ ምድራችን ችግር ውስጥ ገባች ማለት እኮ የእኛም ተስፋ ተዳፈነ ማለት ነው…›› ብሎ ከአባቱ ጋር የተቀመጠው ጎረምሳ በከፍተኛ ግለት ሲናገር አባቱ አንገታቸውን ደፍተው ዝም አሉ፡፡ ‹‹አባቱ በርትተህ ተማር ይሉታል አጅሬ የአሜሪካ ዲቪ ሎተሪ ዕጣ ተማምኖ መቀመጡ ለአገራችን ብልፅግና ጠንቅ እንደሆነ ይህ ትንሹ አመላካች ነው…›› የምትለው ያቺው ወጣት ናት፡፡ የአሜሪካ ሰሞነኛ ሁኔታ የሁሉም አጀንዳ ሆኖ ለተወሰኑ ደቂቃዎች የሹክሹክታ ወሬ ደራ፡፡ በአሜሪካ ቀልድ የለም ማለት ነው!

ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። ወደ ሥራ የሚጓዘው ሠራተኛ፣ ወደ ትምህርቱ የሚሮጠው ተማሪ፣ ለእርሻ የወጣ ገበሬ፣ ላቡን አንጠፍጥፎ የሚሠራ ባተሌ እየተርመሰመሰ መንገዱ ተዘጋግቷል። ‹‹እኔን የሚገርመኝ በዚህ እሳት ኑሮ የዚህ ሁሉ ሰው በልቶ ማደር ነው…›› አሉ አዛውንቱ። ‹‹በልቶ ማደሩ ነው የሚገርምዎት ወይስ በቀን ሦስቴ መብላት እየተገባው በአንዲት ጉርሻ  በሕይወት መኖሩ?›› ብለው ሴትየዋ አዛውንቱን ጠየቋቸው። ‹‹ሁለቱም…›› አሉ አዛውንቱ በአጭሩ ለመገላገል ይመስልባቸዋል፡፡ ‹‹አይዞን መንግሥታችን አሁን የበጋ ስንዴ ምርትና የከተማ ግብርና ጀምሮልናል። አይደለም ሦስቴ በቅርቡ ዘጠኝ ጊዜ ባንበላ ቱ ከምላሴ ፀጉር…›› ሲል ያ ባለመጽሐፍ ወጣት ገባበት። ‹‹ኧረ ፀጉር ማብቀሉ ቀርቶ ምላስህ አርፎ በተቀመጠ። ምን ሊለን ነው እናንተ? ይኼ አንድ ፍሬ ልጅ አሁን የአዞ ዕንባቸውን እያፈሰሱ ‹ሕዝባችን በቀን ሦስቴ ሲበላ ማየት ነው የምንፈልገው› ከሚሉ ሻርክ ፖለቲከኞቻችን ሊበልጥ ያምረዋል እንዴ?›› ብላ ወይዘሮዋ ቱግ አለች። ጠይሟ በቁጣ፣ ‹‹በምግብ ራሳችንን መቻላችን ሲነገር አልሰማሁም ለማለት ነው ወይስ የብልፅግና ጉዞአችን አልዋጥ ብሎ ይተናነቅሻል…›› ስትል ሁላችንም ፀጥ እረጭ አልን፡፡ ቁርጡን ንገሪኝ ማለት ይኼኔ ነው!

‹‹ሰንበትን እሑድ ነው ብለን ካላስረዳን እኮ የልማታችን ጉዞ አይታያቸውም ምድረ አደናቃፊ፡፡ በኮሪደር ልማት ቅናት፣ በምግብ ራስን መቻል ቅናት፣ ቆሻሻን አስወግዶ በማሳመር ቅናት…›› እያለ ባለመጽሐፉ ወጣት ንግግሩን ሲያረዝመው ከጀርባው ከተቀመጡ ወጣቶች አንደኛው፣ ‹‹ቆይ ግን መሪ ዕቅዶቻችን የተቀዱት ከሆሊውድ ፊልም ላይ ነው እንዴ?›› ሲል ያኛው መልሶ፣ ‹‹ለአንተና ለመሰሎችህ ሁሉም ነገር ፊልም የሚመስላችሁ ለምን እንደሆነ ታውቃለህ ሥራ ጠል፣ ልማት ጠል፣ ብልፅግና ጠል ስለሆናችሁና ቅዠት ውስጥ ስለምትኖሩ ነው…›› ብሎ ሳይጨርስ፣ ‹‹ይኼ ጉዳይ እኮ አሜሪካኖች ከእኛ በላይ ሆነው ያከበሩልን፣ እኛ ግን ንቀን ትተነው ድራፍት በጃምቦ ስንጋትበት የዋልነው ካሌንደር የዘጋው ግንቦት ሃያ ቀን በሰፊው ብንነጋገርበት መልካም ነበር፡፡ ምን ያደርጋል ሳይሆን ቀረ…›› እያለ ሲመልስለት ታክሲያችን ሥፍራ ይዛ ስትቆም ወያላው ‹‹መጨረሻ…›› አለን፡፡ የአያሌው መስፍን ዘፈን እንደገና ተከፍቶ ኖሮ፣ ‹‹ተው ቻለው ሆዴ…›› እሰማን በየፊናችን መንገዳችንን ስንያያዝ ዘፈኑ በርቀትም ሆኖ ‹‹ሲቀር ለሚቀረው ምነው መናደዴ… ሲያልፍ ለሚያልፍ ቀን ምነው መንገብገቤ…›› እያለ ነበር፡፡ መልካም ጉዞ!    

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት