Saturday, June 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከሆርቲካልቸር ዘርፍ ኤክስፖርት የተገኘው ገቢ የ25 በመቶ ቅናሽ አሳየ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ የወጪ ንግድ ገቢ በማስገኘት የሚጠቀሰው የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ በ2016 የበጀት ዓመት ያልተጠበቀ ነው የተባለ የገቢ ቅናሽ እንዳሳየ ተመለከተ፡፡ ሩስያ ከኢትዮጵያ የምትገዛው የአትክልት ምርት በ44 በመቶ ዕድገት አሳየ፡፡ 

የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ከአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች የተገኘው የውጭ ምንዛሪ 368 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን የሆልቲካልቸር አፈጻጸምን የተመለከተው መረጃ ያመለክታል።

ይህ አፈጻጸም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ25 በመቶ በላይ ወይም ከ132 ሚሊዮን ዶላር በላይ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ዘርፉ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቅ ከነበረው አንፃር በበጀት ዓመቱ እየታየ ያለው አፈጻጸም በሙሉ በጀት ዓመቱ የሚጠበቀውን ያህል ገቢ እንደሚያስገኝ አመላክቷል፡፡ 

ከዘርፉ በሙሉ በጀት ዓመቱ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ይገኛል ተብሎ የታሰበው 598.1 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ለማወቅ የተቻለ ሲሆን፣ አፈጻጸሙ ግን ከዕቅዱም ሆነ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸርም ያነሰ መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ከሌሎች ዓመታት የኤክስፖርት ገቢው በተለየ ሁኔታ ቅናሽ የታየበት ይህ የሆልቲካልቸራል ዘርፍ፣ የ2016 በጀት ዓመት ከገባ ጀምሮ በየወሩ የነበረው አፈጻጸም ቅናሽ እየታየበት የመጣ መሆኑም ታውቋል፡፡ በተለይ በመጀመሪያዎቹ ሰባት ወራት የዘርፉ ገቢ ከ101 ሚሊዮን ዶላር በላይ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ የዘርፉን የሰባት ወራት እንቅስቃሴ በዝርዝር የሚመለክተው መረጃ፣ በበጀት ዓመቱ ከሌላው ጊዜ የተለየ የገቢ ማሽቆልቆል እየታየ ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ ነው ተብሏል፡፡ በመረጃው መሠረት፣ በበጀት ዓመቱ በሰባት ወራት ውስጥ 200,659 ቶን የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በመላክ 466.54 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ የነበረ መሆኑን ነው፡፡ 

ይሁን እንጂ የተላከው የምርት መጠን 174,364 ቶን በመሆኑ ከምርት መጠን አንፃር የዕቅዱን 86.9 በመቶ ማሳካት ችሏል፡፡ ሆኖም ከገቢ አንፃር ክንውኑ 66.8 በመቶ ብቻ ሊሆን ችሏል፡፡ ይህ አፈጻጸም በተመሳሳይ በቀጣይ ሁለት ወራት ውስጥ በመቀጠሉ ዘጠኝ ወራት አፈጻጸሙም በተመሳሳይ ቅናሽ እያሳየ የውጭ ምንዛሪ ግኝት የቅናሽ መጠኑ እየሰፋ እንዲሄድ አድርጓል፡፡ በሰባት ወራት ከአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 311.61 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ይህ አፈጻጸሙም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ24.5 በመቶ ዝቅ ማለቱን ይኼው ይፋዊ መረጃ ያሳያል፡፡ በ2105 በጀት ዓመት በሰባት ወራት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ 412.68 ሚሊዮን ዶላር በመሆኑ፣ በሰባት ወራት ብቻ የሆርቲካልቸር ዘርፍ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከ101 ሚሊዮን ዶላር በላይ ቅናሽ ሊያሳይ ችሏል፡፡ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ደግሞ ከዘርፉ የተገኘው ቅናሽ መጠን ከ132 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከፍ ማለቱ በበጀት ዓመት ይገኛል ተብሎ በዕቅድ የተቀመጠውን ግብ ማሳካት እንደማይቻል አመላክቷል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው በሆልቲካልቸር ዘርፍ ላይ የተሳተፉ ባለሀብቶች ከዚህ ቀደም በዘርፉ እንዲህ ያለ የገቢ ቅናሽ እንዳልታየ ጠቁመዋል፡፡ በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዋጋ ላይ የተወሰነ ቅናሽ ማሳየቱ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ገበያውን በማቀዛቀዙ የገቢ መጠኑ ባልተለመደ ሁኔታ እንዲቀንስ በምክንያት ተጠቅሰዋል፡፡

በዘርፉ ውስጥ ከሚካተቱት ምርቶች መካከል አንዱ የሆነው የአትክልት የወጪ ንግድ ከአበባና ከፍራፍሬ የበለጠ ቅናሽ የታየበት ሆኗል፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከፍራፍሬ የተገኘው ገቢ አሥር ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ በሰባት ወራት ውስጥ ይገኛል የተባለውና ታቅዶ የነበረው ግን 22.13 ሚሊዮን ዶላር የነበረ መሆኑ፣ አፈጻጸሙ ግን የዕቅዱን ግማሽ ያህል እንኳን ማሳካት ባለመቻሉ አጠቃላይ የሆርቲካልቸራል ገቢ አፈጻጸም ላይ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡

ከዚሁ አኃዛዊ መረጃ መረዳት እንደሚቻለው ግን በበጀት ዓመቱ የተላከው የፍራፍሬ ምርት መጠን የ124 በመቶ ያደገ መሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን ገበያው በአሥር ሚሊዮን ዶላር ተወስኗል፡፡ በቀዳሚው ዓመት በሰባት ወራት ውስጥ 17,080 ቶን ፍራፍሬ ተልኮ 17.09 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቶ እንደነበረ መረጃው ያሳያል፡፡ በተለይ እንደ ጂቡቲ ያሉ አገሮች በሰባት ወር ውስጥ የገዙት የፍራፍሬ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፡፡ ከመረጃው መረዳት እንደሚቻለው በሰባት ወር ውስጥ ጂቡቲ 21.93 ሚሊዮን ኪሎ ግራም አትልክት የገዛች ሲሆን ከዚህም 5.14 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቶበታል፡፡ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ግን ወደ ጂቡቲ ተልኮ ከነበረው አትክልት 22.3 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቶ የነበረ በመሆኑ በገቢ ደረጃ ከጂቡቲ የተገኘው የውጭ መንዛሪ 76 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ በጥቅል ሲታይ በሰባት ወራት ውስጥ ወደ አትክልት መዳረሻ አገሮች የተላከው የፍራፍሬ ምርት መጠን 26,706 ቶን ሲሆን የ56 በመቶ ብልጫ ቢኖረውም ገቢውን ግን ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ43.6 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱ በበጀት ዓመቱ ምርቱ በዝቅተኛ ዋግ እየተሸጠ መሆኑን የሚያመላክት እንደሆነ ያነጋገርናቸው የዘርፉ ተዋንያን ገልጸዋል፡፡ 

በተመሳሳይ የአበባ ምርት መጠን የ18.4 በመቶ ብልጫ ቢያሳይም ገቢው ግን በ22.4 በመቶ ቀንሷል፡፡ የአትክልትም የተላከው መጠን ከቀዳሚው ዓመት 16.7 በመቶ ብልጫ ያለው ነበር፡፡ ሆኖም የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ የ33.6 በመቶ ቅናሽ በማሳየቱ የዘንድሮው የሆርቲካልቸራል የውጭ ምንዛሪ ገቢ የዕቅዱን ያህል ብቻ ሳይሆን ከቀዳሚው ዓመት ያነሰ አፈጻጸም እየተመዘገበበት ሊሆን ችሏል፡፡ 

ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በየዓመቱ በመጠንም ሆነ በገቢ ደረጃ ዕድገት እያስመዘገበ የመጣው ይህ ዘርፍ፣ በ2016 የታየው አፈጻጸሙ በዚህን ያህል ደረጃ ለመቀነሱ በአንዳንድ የእርሻ ቦታዎች ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የገጠሙ ዕክሎችም የራሳቸው ተፅዕኖ ነበራቸው፡፡ 

በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት ከዘርፉ የተገኘው አጠቃላይ ገቢ 568 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡

የኢትዮጵያን የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርት በመግዛት አሁንም በቀዳሚነት አሁንም ሶማሊያ፣ ጂቡቲ፣ ኔዘርላንድ፣ ቤትናም፣ ሩሲያ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ታይላንድ በዋናነት የሚጠቀሱ ቢሆንም፣ በ2016 በጀት ዓመት ሩሲያ ከኢትዮጵያ የምትገዛውን የአትክልት ምርት በማሳደግ ተጠቃሽ ልትሆን ችላለች፡፡ በተለይ በመጀመሪያዎቹ ሰባት ወራት ሩሲያ ከኢትዮጵያ የገዛችው የአትክልት ምርት መጠን በ44 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ሩሲያ የገዛችው የአትክልት መጠን 137,040 ቶን ነው፡፡ ከዚህም 1.07 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡ 

በቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ላይ ሩሲያ የገዛችው የአትክልት መጠን 95,131 ቶን በመሆኑ የምትገዛውን መጠን በ44.1 በመቶ እንዲሁም ምርቱን የገዛችበትን የገንዘብ መጠን በ12.2 በመቶ ማሳደግ ችላለች፡፡ 

በአንጻሩ ወደ ኔዘርላንድ የተላከው የአትክልት ምርት መጠን በ15.3 በመቶ የቀነሰ ሲሆን በገቢ ደረጃም የ2.5 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ኢትዮጵያ በ2015 በጀት ዓመት ከሆልቲካልቸር ዘርፍ 658.3 ዶላር ማግኘቷ ይታወቃል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች