Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበሰሜኑ ጦርነት ወቅት በተለያዩ ንግድ ባንኮች ሒሳባቸው የታገደባቸው ግለሰቦች ቅሬታቸውን አሰሙ

በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በተለያዩ ንግድ ባንኮች ሒሳባቸው የታገደባቸው ግለሰቦች ቅሬታቸውን አሰሙ

ቀን:

  • ሕይወቱን ካጣ የሠራዊት አባል የባንክ ሒሳብ ከ100 ሺሕ ብር በላይ ተወስዷል

በአገሪቱ ተከስቶ በነበረውና ለሁለት ዓመታት በቆየው የሰሜኑ ጦርነት ወቅት በተለያዩ የንግድ ባንኮች የሚገኝ ሒሳባቸውን እንዳያንቀሳቅሱ የታገደባቸው ግለሰቦች፣ ‹‹ላለፉት ሁለት ዓመታት በላይ ገንዘባችንን እንዳናንቀሳቅስ መታገዳችን ችግር ላይ ጥሎናል›› ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ የሟች ባለቤቴ የባንክ ሒሳብ በግጭቱ ወቅት ተዘርፎብኛል ያሉ የሦስት ልጆች እናትም ችግር ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ወ/ሮ ራሄል ዓለም የተባሉ ግለሰብ ኮለኔል ገብረሓዋርያ ወልደሩፋኤል የተባሉ በጦርነቱ ወቅት ከትግራይ ጦር ጎን ተሠልፈው ሲዋጉ የቆዩ ባለቤታቸው፣ በውጊያ ወቅት ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ ለተከታታይ ወራት ባልታወቀ ግለሰብ ከሟች የባንክ ሒሳብ ላይ በተለያዩ ኤቲኤም ማሽኖች 102 ሺሕ ብር እንደተዘረፉ ለሪፖርተር ገልጸዋል።

የሟች ኮሎኔል ወንድም አቶ መትከል ወልደሩፋኤል ጉዳዩን በተመለከተ ለሪፖርተር ሲያስረዱ ‹‹ወንድሜ ኮሎኔል ገብረሓዋርያ ወልደሩፋኤል ይባላል። ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ነው። ቤተሰቦቹ ምንም የሚያውቁት አልነበረም። የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በጦርነቱ ወቅት ሕይወታቸው ያለፈ ታጋዮችን ስም ዝርዝር ይፋ በሚያደርግበት ወቅት ኅዳር 14 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደተሰዋ የተነገራቸው። የቤተሰቡ አስተዳዳሪ እሱ ነበር፤›› ብለዋል።

- Advertisement -

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ኮሎኔሉ በውጊያ ወቅት ሕይወታቸው ማለፉን ካሳወቃቸው በኋላ፣ ወራሽነታቸውን አረጋግጠው ከሟች የባንክ ሒሳብ ገንዘብ ለማውጣት በሄዱበት ወቅት፣ የባንክ አካውንቱን የሒሳብ እንቅስቃሴና ያለው የገንዘብ መጠን (Bank Statement) ለማወቅ በሚመለከቱበት ወቅት፣ ከታኅሳስ ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 17 2013 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ 102 ሺሕ ብር በተለያዩ የኤቲኤም ማሽኖች ወጭ መደረጉን መገንዘብ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ መትከል ‹‹ገንዘቡን ወጭ ያደረገው ሰው ማንነት ስለማይታወቅ የኤቲም ካርዱ ባለቤት ደግሞ በሕይወት ስለሌለ፣ ለፖሊስ አመልክተን ጉዳዩ ፍርድ ቤት ቀረበ›› ሲሉ ቤተሰቡ የተፈጸመውን ድርጊት ካወቀ በኋላ የወሰደውን ዕርምጃ አስረድተዋል፡፡

ሪፖርተር የተመለከተው በመቀሌ ከተማ በሰሜን ክፍለ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. የተጻፈ ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመቀሌ ዲስትሪክት የክፍለ ከተማው ፖሊስ ጣቢያ ባቀረበው ማመልከቻ መሠረት፣ ባንኩ በሟቹ ኮሎኔል የባንክ ሒሳብ ደብተር ከኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በተለያዩ ጊዜያት ገንዘብ ወጭ ያደረገውን ማንነቱ ያልተጠቀሰና ያልታወቀ ግለሰብ ምስል የሚያሳይ የካሜራ ቅጅ ከእነሙሉ የግለሰቡ መረጃ ለአመልካች እንዲሰጥ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

በመቀሌ ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኣግዓዚ ጎዳና ቅርንጫፍ ለፍርድ ቤቱ በላከውና መጋቢት 12 ቀን 2016 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ፣ የኮሎኔል ገብረሓዋርያ የባንክ ደብተር በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙ የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች በማይሎሚ ዓብይ-ዓዲ ቅርንጫፍ፣ በመቀሌ መናኼሪያ፣ ማይዳዓጋመ፣ ሓሚዳይ ዓዲ-ሓቂ፣ ሮማናት ዒላላ፣ ኣግዓዚ እንዲሁም ላጪ ቅርንጫፎች ከሰኔ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ጥቅምት 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ የገንዘብ እንቅስቃሴዎች መደረጋቸውን አብራርቷል።

ፍርድ ቤቱ ለአመልካች የክፍለ ከተማው ፖሊስ ዝርዝር መረጃ እንዲቀርብ የጠየቀበት ቀን የተካተተበት፣ ከጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ባለው ጊዜ፣ ከባንክ ሒሳብ ደብተሩ በኤቲኤም ማሽን በኩል ወጭ የተደረገው ገንዘብ ግን ከትግራይ ክልል ውጭ በሚገኙ ፓዌ፣ እንዚ፣ ህዳሴ ግድብና በለስ በሚባሉ የባንኩ የኤቲኤም ማሽኖች በሚገኙባቸው ቅርንጫፎች መሆኑን አብራርቷል።

ከላይ ከተጠቀሱት የባንክ ሒሳብ እንቅስቃሴዎች ውጭ ከሰኔ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ መጋቢት 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ምንም ዓይነት የገንዘብ ወጭና ገቢ እንቅስቃሴ አለመደረጉን ያብራራው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የመቀሌ ኣግዓዚ ጎዳና ቅርንጫፍ ደብዳቤ በገንዘብ ማጭበርበር የተጠረጠረውን ግለሰብ አድራሻ እንደማያውቅና የፎቶግራፍ ማስረጃ ምስልም ማቅረብ እንደማይችል በማብራራት ምላሽ ሰጥቷል።

የሟቹ ወንድም አቶ መትከል ከዚህ የባንኩ ምላሽ በኋላ ቤተሰቡ በድጋሚ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ማመልከቻና ፍርድ ቤቱም ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባህር ዳር ቅርንጫፍ በጻፈው ደብዳቤ፣ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቱ በሰጠው ምላሽ 102 ሺሕ ብር የራሱ ካልሆነ የባንክ ሒሳብ ኤቲኤም ማሽኖችን በመጠቀም ያወጣውን ግለሰብ ማንነትም ሆነ አድራሻ እንደማያውቅ፣ ነገር ግን ግለሰቡ ገንዘቡን ከተለያዩ ማሽኖች ወጭ ባደረገበት ወቅት በኤቲኤም ማሽኖቹ የተነሳውን ፎቶግራፍ አባሪ በማድረግ ልኳል። ሪፖርተርም ፎቶግራፎቹን ተመልክቷል።

የሟች ባለቤት ወ/ሮ ራሄል ‹‹የተፈጸመብንን በደል ለማን ይዘን እንደምንሄድ ግራ ገብቶናል፣ ልጆቼን ለማብላትና ለማልበስ እንኳን ተቸግሬ ነው ያለሁት፤›› ብለዋል።

በጦርነቱ ወቅት የባንክ አካውንታቸው ተዘግቶባቸው እስካሁን ድረስ ሊከፈትላቸው ያልቻሉ ሰዎችን በተመለከተ፣ የፌዴራል የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የሚያከናውናቸው ሥራዎች ስለመኖራቸው ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ እንዳለ አሰፋ ‹‹ይህን በተመለከተ የምንሠራው ነገር የለንም። እኛ የተሰጠን ኃላፊነትም (mandate) አጭር ነው። ከዚህ ውጭ ያለውን የሚመለከተውን መጠየቅ ነው፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ኃላፊው አክለውም ‹‹የእኛ ኃላፊነት ሥር የተካተተው ሕገወጥ ገንዘብን ሕጋዊ ማስመሰል (money laundering) ድርጊት ሲፈጽሙ የተገኙትንና ከሽብርተኝነት ጋር የገንዘብ ግንኙነት ያላቸው የሚመስሉ አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎች ያላቸውን፣ ከእነዚህ ከሁለቱ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ከመረጃና ከሕግ አስፈጻሚ አካላት በጋራ መሥራት ነው፤›› ሲሉ አብራርተዋል።

በሌላ በኩል በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ አመልካችነት አቶ ገብሬ ገብረመድህን በተባሉ አቤቱታ አቅራቢ በተጻፈ አቤቱታ፣ ከግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ የባንክ ሒሳባቸው ወደ አቢሲኒያ ባንክ 200 ሺሕ ብር ገቢ ተደረገ በሚል፣ ገቢ ለመሆኑ ማስረጃ ሳያቀርብ የባንክ ሒሳባቸው በጥቅሉ መታገዱን በመጥቀስ፣ ያለማስረጃ ዕግዱ አግባብነት የለውም፣ ወይም ዕግዱ መነሳት የለበትም ከተባለ እንኳን፣ ገቢ ተደረገ የተባለው 200 ሺሕ ብር ብቻ ታግዶ በሌላው ላይ ዕግዱ ይነሳልኝ በማለት አቤቱታ ባቀረቡ ግለሰብ ጉዳይ ላይ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመጋቢት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ ብይን ሰጥቷል።

በብይኑ እንደተገለጸው፣ አንደኛ ተጠሪ ከግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ መቀሌ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ከሆነው አቶ መልካሙ መንገሻ ጋር በጥቅም በመመሳጠርና 3,501,804.04 ብር በመውሰድ በባንኩ ላይ ጉዳት አድርሷል በሚል በሙስና ተጠርጥረው ተፈላጊ መሆኑን በመግለጽ የተላለፈበት የዕግድ ትዕዛዝ ፀንቶ እንዲቆይ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ መጠየቁ ተገልጿል።

አያይዞም እነ ደረጀ አብርሃም ስለተባሉት ተጠርጣሪዎች ዕግድ እንዲሰጠው በማመልከት ‹‹አቤቱታ አቅራቢ ለግለሰቡ 200 ሺሕ ብር አስተላልፈዋል በማለት የገለጸው በስህተት መሆኑን በመግለጽ ይቅርታ መጠየቁን ብይኑ ያስረዳል።

ሁለተኛ ተጠሪ ሆኖ በቀረበው በፍትሕ ሚኒስትር ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በተጻፈ መልስም የተገለጸው የወንጀል ምርመራ ምን እንደሆነና ዕግዱንም የማያውቀው አስረድቶ ፍርድ ቤቱ ተገቢ ነው ያለውን ትዕዛዝ ቢሰጥ እንደማይቃወም በመጠቆም ምላሽ መስጠቱ ተብራርቷል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዕግድ ዓላማ ተጠርጣሪው ያልተገባ ጥቅም ያገኘውን ወይም በመንግሥትም ሆነ በሕዝብ ጥቅም ላይ ያደረሰውን ጉዳት ለማካካስ እንዲያስችል እንጂ የተጠርጣሪውን ሀብት ሙሉ በሙሉ በማገድ በንብረት የመጠቀም መብቱን የሚያጣብብ መሆን የለበትም። ስለሆነም በተያዘው ጉዳይ አቤቱታ አቅራቢ ባንክ ሒሳብ ቁጥር ላይ ዕግድ ሊሰጥ የቻለው ከአቢሲኒያ ባንክ 200 ሺሕ ብር ገቢ ተደርጎለታል በሚል ምክንያት ስለሆነ፣ ከዚህ ከተጠቀሰው የገንዘብ መጠን በላይ መታገዱ አግባብነት የሌለው ስለሆነ፣ የተጠቀሰውን የገንዘብ መጠን ታግዶ እንዲቆይና ከዚህ መጠን በላይ ገንዘብ ካለ የዕግድ ትዕዛዙ ሊነሳ ይገባል በማለት ብይን ሰጥቷል፡፡ ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያም ትዕዛዙን እንዲያስፈጽም እንዲጻፍለት ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...