Sunday, June 23, 2024

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ በጣም መሠረታዊ ከሚባሉ ነገሮች መካከል አንዱና ዋናው ሰላም ነው፡፡ ሰላም ግን በምኞት ብቻ የሚገኝ ሳይሆን የሁሉንም ወገኖች ትብብር የሚጠይቅ ነው፡፡ ሰላም እንዲሰፍን ሰላማዊ ሐሳብና ድርጊት ያስፈልጋሉ፡፡ ከሰላም ቀጥሎ የሚመጣው ድህነትን በጋራ እንዴት ተባብሮ መቅረፍ ይቻላል የሚለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ድህነት በሁሉም መስኮች ከተንሰራፋ በርካታ ዓመታት ነጉደዋል፡፡ ድህነት እጅግ ጎልቶ ከሚጠቀስባቸው መካከል የምግብ፣ የመጠለያ፣ የአልባሳት፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የትራንስፖርትና ሌሎች መሰል አስፈላጊ አቅርቦቶች እጥረት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከላይ በተጠቀሱት ችግሮችና ሌሎች ጭምር ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች አሁንም በዝቅተኛው ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው፡፡

እጅግ ፈጣን በሆነ ቴክኖሎጂ እየተለወጠ ባለ ዓለም ውስጥ ኢትዮጵያም የለውጡን ባቡር ተሳፍራ መስፈንጠር ሲገባት፣ የወትሮውን ድህነት የበለጠ የሚያባብሱ ችግሮች በየቀኑ ይፈለፈሉባታል፡፡ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ተገናኝቶ በመምከር የጋራ አቋም ለመያዝ የሚያስችል መድረክ ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት፣ በአንዱ ወገን ውዳሴ ሲቸረው በሌላው ወገን እርግማን ይወርድበታል፡፡ የጠመንጃ ልሳኖችን ዘግቶና ይቅር ተባብሎ ወደ ንግግር መድረክ ከመምጣት ይልቅ፣ አንዱ ሌላውን አሸንፎ ሥልጣኑ ላይ የሚደላደልበትን ዘዴ እያውጠነጠነ ግጭት ተባብሶ ይቀጥላል፡፡ ከግጭት ወይም ከጦርነት በመለስ ያሉ አማራጮች ችላ እየተባሉ፣ ነገሮችን አለባብሶና አድበስብሶ ለማለፍ የሚደረገው ጥድፊያ አስከፊ ውጤቱ አይታሰብም፡፡ በዚህ መሀል ግን የዜጎች ሰላም ይናጋል፣ ዕልቂትና ውድመት ይበራከታል፣ ለአገር ልማት መዋል ያለበት ሀብት እንደ ቆሻሻ እሳት ውስጥ ይጣላል፡፡

የዜጎች ገቢና ወጪ ሊመጣጠን ባልቻለባት ኢትዮጵያ ውስጥ በቀን አንዴ ምግብ ማግኘት ለበርካታ ሚሊዮኖች ሰቆቃ እየሆነባቸው ነው፡፡ ለይቶላቸው ለምፅዋት እጃቸውን ከሚዘረጉ ወገኖች በላይ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በሥውር ረሃብ እየተቆሉ ነው፡፡ ወጣቶች ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው ሥራ ቢይዙም የሚያገኙት ደመወዝ ለቤት ኪራይ እንኳ ሊበቃቸው አልቻለም፡፡ ምን በልተው ወሩን ይገፉታል ተብሎ ሲጠየቅ መልሱ ግራ ያጋባል፡፡ ቀን በመንግሥት ወይም በግል ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ብዙዎች ሌሊት ለመግለጽ በሚያዳግቱ ‹‹ሥራዎች›› እንደሚሰማሩ ይታወቃል፡፡ እነዚህ የከፍተኛ ትምህርት ምሩቃን ብቻ ሳይሆኑ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ወገኖች የኑሮ ውድነቱን መቋቋም ተስኗቸዋል፡፡ ብዙዎቹ ትዳር ይዘው ወልደው ለማሳደግ አቅም እንደማይኖራቸው ተገንዝበው የላጤ ሕይወት ይገፋሉ፡፡ በጦርነት፣ በተለያዩ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ችግሮች የተፈናቀሉ ዜጎች ያሉበት የመከራ ሕይወት የሚታወቅ ነው፡፡

ዘመኑ ይዟቸው የመጡ በርካታ ወርቃማ ዕድሎችን ተጠቅሞ ከሰላም ዕጦትና ከድህነት ማጥ ውስጥ መውጣት ይቻላል፡፡ ለዚህ ግን አገርን ከምንም ነገር በላይ የማስቀደም ወኔ ያስፈልጋል፡፡ አገር ከምንም ዓይነት ጥቅምና ፍላጎት በላይ እንደሆነች እምነት እስከሌለ ድረስ፣ ግጭቱም ሆነ የድህነት አዙሪቱ እስከ ለየለት መፈራረስ ድረስ ይዞ ይጓዛል፡፡ ለመሥራት የሚያስችሉ በርካታ አማራጮች ያሉባት አገር ውስጥ እንደ ልብ ተዘዋውሮ መሥራት፣ ሀብት ማፍራትና ማደግ ካልተቻለ የመጨረሻው መዳረሻ ተያይዞ መጥፋት ነው፡፡ አገር እየመራ ያለው መንግሥት የሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች በተጨባጭ ድህነትን ለማስወገድ በሚያስችሉ ጥናቶች መመራት አለባቸው፡፡ የግብርና፣ የኢንዱስትሪ፣ የቱሪዝም፣ የቴክኖሎጂ፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የትራንስፖርት፣ የማዕድንና የሌሎች ዘርፎች ኢንቨስትመንቶች ለወጣቶች በስፋት ሥራ ፈጣሪ መሆን ካልቻሉ ፋይዳቸው ጥያቄ ይነሳበታል፡፡

በቅርቡ በወጣ መረጃ መሠረት ዘጠኝ ሚሊዮን ሕፃናት የትምህርት ገበታቸው ላይ አይገኙም፡፡ ይህ አኃዝ አስደንጋጭ ከመሆኑ የተነሳ የሚናገረው መራር እውነት አለው፡፡ በዚህ ያህል መጠን ኢትዮጵያውያን ሕፃናት ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለውና ተስፋቸው ጨልሞ፣ ከዚህ የበለጠ ምን ዓይነት አንገብጋቢ ዓላማ ኖሮ ነው ችግሩ በቸልታ የሚታለፈው? የነገዋ ኢትዮጵያ ሚሊዮን ተስፋዎች ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለው ለየትኛው ፍላጎትና ጥቅም ነው መከራ የሚታየው? በተለያዩ ምክንያቶች ከከባድ ጉዳት ጋር ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ወገኖች የሚበሉትና የሚጠለሉበት ተቸግረው ባዕዳን እርጥባን እየተለመኑ፣ ምን በሚሉት ፍላጎት ነው በተለያዩ አካባቢዎች ውጊያዎች እየተካሄዱ ንፁኃን ሰለባ የሚደረጉት? ለ21ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ በማይመጥኑ ቅራኔዎችና በቀሎች ምክንያት ሕዝብ እየተጎዳና አገር እየደማች እስከ መቼ ነው መቀጠል የሚቻለው? የመውጫ መንገዱን በጋራ አለመፈለግ ዋጋ ያስከፍላል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቅኝ ያልተገዛች አገር ሆና ለብዙዎች ምሳሌ መሆኗ ብዙ የተባለለት እውነት ነው፡፡ ነገር ግን በእንግሊዝ ቅኝ የተገዛችው ጎረቤት ኬንያ ለረጅም ጊዜ ሰላም ስለሆነች እኮ ነው፣ ከብዙዎቹ የአካባቢው አገሮች እጅግ በተሻለ ሁኔታ ላይ የምትገኘው፡፡ በቅርቡ ፕሬዚዳንቷ በአሜሪካ ጉብኝት ሲያደርጉ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አጋር መደረጓ፣ በቡድን ሰባት አገሮች አፍሪካን ወክላ እንድትገኝ መመረጧና በሌሎች ጉዳዮችም ስሟ በመልካም መነሳቱ በራሱ የሚናገረው አለው፡፡ ኢትዮጵያን የመሰለች ታላቅ ክብር፣ ዝና፣ ታሪክና ስም ያላት አገር ግን በግማሽ ክፍለ ዘመን ውስጥ የተደረጉ አሳዛኝ ነገሮች አልበቃ ብለው፣ የጦርነት መናኸሪያና የድህነት መፈንጫ መሆኗ ካላሳፈረ ሌላ ምን ያሳፍራል? የዘመኑ ትውልድ ኢትዮጵያን ከቀውስ አዙሪት ውስጥ ማውጣት ካልቻለ ፋይዳውን ይመርምር!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሕግ የማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

የሕግ መሠረታዊ ዓላማ ዜጎችን ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች መጠበቅ፣ ለሕይወታቸውና ለንብረታቸው ከለላ መስጠትና በሥርዓት እንዲኖሩ ማድረግ ማስቻል ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል...

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...