Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትየክለቦችን የፋይናንስ አስተዳደር ጤናማ ለማድረግ የወጣው አስገዳጅ መመሪያ

የክለቦችን የፋይናንስ አስተዳደር ጤናማ ለማድረግ የወጣው አስገዳጅ መመሪያ

ቀን:

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የተጫዋቾችና የአሠልጣኞችን አጠቃላይ ዓመታዊ ክፍያ ለመቆጣጠርና የክለቦችን የፋይናንስ አስተዳደር ጤናማ ለማድረግ አስገዳጅ መመሪያ ማውጣቱን አስታውቋል፡፡ የመመሪያውን ተግባራዊነት የሚቆጣጠርና የሚያስፈጽም ከጠበቆች ማኅበርና ከሌሎችም የተለያዩ ተቋማት ልዩ ኮሚቴ ስለመዋቀሩ ጭምር አክሲዮን ማኅበሩ ይፋ አድርጓል፡፡

ከአምስት ዓመታት በፊት አክሲዮን ማኅበሩ ሲመሠረት ዓላማው የነበረው በዘርፉ ሃይባይ አጥቶ የቆየውን የፋይናንስ አስተዳደር ጤናማ በማድረግ የክለቦችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በሚል ነው፡፡ ይህንኑ ዕውን ለማድረግ ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ‹‹ዘልማዳዊ›› የነበረውን የክለቦች አወቃቀር፣ የክለቦች የፋይናንስ ሁኔታ፣ የሊጉን መዋቅራዊ ቁመና፣ አንዲሁም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሸን ከክለቦች ጋር ያለውን ግንኙነትና የክለቦች ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሲያስጠና መቆየቱ ይታወሳል፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ ግንቦት 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሦስት ዓመት በላይ የፈጀውን የጥናቱን ይዘት፣ እንዲሁም ለጥናቱ ተግባራዊነት የሚቆጣጠረውንና የሚያስፈጽመውን አካል ማንነት እንዲሁም የሚኖረውን ኃላፊነት ጭምር ይፋ አድርጓል፡፡

- Advertisement -

የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ፣ ከጥናቱ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል አንዱ ክለቦች ያላቸው የፋይናንስ አስተዳደር አንዲሻሻል ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አገር ክለቦችም በእግር ኳሱ እንዲጠቀሙ ምን መደረግ አለበት? የሚለው ላይ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የሊጉን ክለቦች አቅም እየተፈታተነ የሚገኘውን የክፍያ ሥርዓት አስተዳደር መቆጣጠርና ሥርዓት ማስያዝ የሚችል መመሪያ ማውጣት አስፈልጓል፡፡

መመሪያው የፀደቀው ባለፈው በሚያዝያ አክሲዮን ማኅበሩ ባካሄደው 4ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ መሆኑን የሚናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ በመመሪያው መሠረት ክለቦች በዓመት ለተጨዋችና ለአሠልጣኞች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅምን ጨምሮ ከ57 ሚሊዮን ብር በላይ መክፈል አልያም ወጪ ማድረግ አይችሉም፡፡

መመሪያ ፀድቆ ይፋ ከመደረጉ በፊት ከክለቦችና ሌሎች ይመለከተናል ከሚሉ ወገኖች ቅሬታ ወይም ግልጽ ያልሆነ ነገር አለ እንዳይባል፣ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና ከሁሉም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጋር ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በዚሁ መሠረት የክለቦችን ፋይናንስ ኦዲት የሚያደርገው ድርጅት ከአክሲዮን ማኅበሩና ከክለቦቹ ጋር ውል እንዲፈጽም ይደረጋልም ብለዋል፡፡

የክለቦችን የፋይናንስ ሁኔታ ኦዲት የሚያደርገው ድርጅት የውጪ (ገለልተኛ) ሆኖ የሒሳብ ሥራውን ካጠናቀቀ በኋላ ውጤቱን ለሚመለከተው አካል፣ ማለትም ቀደም ሲል በተገለጸው መሠረት ከጠበቆች ማኅበር የሕግ ሰዎችን ጨምሮ ከተለያዩ ተቋማት ለተውጣጣው ኮሚቴ ያቀርባል፡፡

በኮሚቴው ውስጥ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ፣ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ማኅበር፣ ከኢትዮጵያ ሒሳብ ባለሙያዎች ማኅበር፣ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንና የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የተውጣጣ ባለሙያዎች ይገኙበታል፡፡

ኮሚቴው ክለቦች በተቀመጠላቸው የወጪ ገደብ መሠረት ለተጨዋቾችና ለአሠልጣኞች ዓመታዊ ጥቅል ክፍያ እየከፈሉ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን በሚቀርብለት የኦዲት ሪፖርት መሠረት የሚቆጣጠር አካል ስለመሆኑ ጭምር አቶ ክፍሌ ተናግረዋል፡፡

መመሪያው ለተጨዋችና ለአሠልጣኞች በግል የሚከፈላቸው ክፍያ ላይ ገደብ እንደማያስቀምጥ የሚናገሩት አቶ ክፍሌ፣ ዋነኛ ትኩረቱ ዓመታዊ ጥቅል የክለቦች ክፍያ ጣሪያ ላይ እንደሚሆን፣ ይህ የክፍያ መመሪያ መተግበር የሚጀምረው ከ2017 የውድድር ዓመት ጀምሮ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

መመሪያውን ተግባራዊ የማያደርጉ ክለቦች አልያም ተጫዋቾችና አሠልጣኞች ቢኖሩ፣ ለእያንዳንዱ ተግባርና የዲሲፕሊን ጥሰት የየራሱ የቅጣት ደረጃ እንዳለው አቶ ክፍሌ እንደሚከተለው አስረድተዋል፡፡

የቅጣቱን መጠንም በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ስለተጨዋቾችና አሠልጣኞች ክፍያ መረጃ ያልሰጠ ክለብ 50,000 ብር፣ የማስጠንቀቂያው ቀነ ገደብ ባለፈ ቁጥር የቅጣት መጠኑ እንደሚጨምርና 30 ቀናት ካለፈው ክለቡ ካለው ውጤት ላይ ሦስት ነጥብ የሚቀነስበት ይሆናል፡፡

ሌላው አንድ ክለብ በበጀት ዓመቱ በመመሪያው መሠረት ከጣሪያ በላይ ካወጣና በተቆጣጣሪው አካል ጥፋቱ ከተረጋገጠ ከሊጉ እንዲወርድ ይደረጋል፡፡ በአክሲዮን ማኅበሩ ያለው ወይም ሊከፈለው የሚገባው ገንዘብ ለማኅበሩ ገቢ ይሆናል፡፡ መመሪያው ከዚህ በፊት እንደተለመደው ማለትም ቅድሚያ ክፍያ ወይም የፊርማ ክፍያ የሚባለውን አይፈቅድም፡፡

አንድ ተጨዋች ወይም አሠልጣኝ ይህንኑ ያለ ህጋዊ ውል መፈጸሙ ከተረጋገጠ እስከ ሦስት ሚሊዮን ብር እንደሚቀጣ በመመሪያው ተካቷል፡፡ በተጨማሪም በዚህ ድርጊት ላይ ተሳትፎ የተገኘ ተጨዋች ወይም አሠልጣኝ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ ወይም ፕሬዚዳንቱ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ የሚደርሰው ይሆናል፡፡

ክለቦ በፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማኅበር ካስመዘገቡት የሒሳብ አካውንት ውጭ አስመዝግበው ከተገኙ ወይም አክሲዮን ማኅበሩ ከሚያውቀው አካውንት ውጭ ከፍለው ማረጋገጫ ከተገኘባቸው እስከ ሦስት ሚሊዮን ብር ቅጣት ይጣልባቸዋል፡፡ አንድ ክለብ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት ፈጽሞ ከተገኘ ደግሞ ከሊጉ እንዲወርድ ይደረጋል፣ ከአክሲዮን ማኅበሩ ሊያገኝ የሚገባው የገንዘብ መጠንም ይሰረዝበታል፡፡

ሌላው ተጫዋች ወይም አሠልጣኝ ከሕጋዊ ክለቡ ውጪ ከሦስተኛ ወገን ውል ተዋውሎ፣ ገንዘብ መቀበሉ ከተረጋገጠ እስከ 200,000 ብር ቅጣት ይጣልበታል፡፡ የወሰደው ገንዘብም ለአክሲዮን ማኅበሩ ገቢ ይደረጋል፡፡ በቅጣቱ ሳይታረም ለሁለተኛ ጊዜ ከተገኘ ቅጣቱ 500,000 ብር ከፍ ሊል እንደሚችልም መመሪያው ይደነግጋል፡፡

ከመረጃ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ መመሪያውን እንዲያስፈጽም ኃላፊነት የተቀበለው ኮሚቴ፣ ክለቡ መረጃ እንዲሰጥ የተጠየቀበትን ቀን ያሳለፈው ለመጀመሪያ ጊዜ ከሆነ 20,000 ብር፣ እንዲሁም ምርመራው እስኪጠናቀቅ ምንም ዓይነት ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ ደግሞ ክለቡ ከ15 ነጥብ እስከ ታችኛው ሊግ መውረድ የሚደርስ ቅጣት ሊደርስበት እንደሚችል ይደነግጋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...