Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትየምርጫ 97 ትውስታ

የምርጫ 97 ትውስታ

ቀን:

(የመጨረሻ ክፍል)

ቅጥቀጣ

በበቀለ ሹሜ

- Advertisement -

የመለስ ዜናዊ መንግሥት ባወጀውና በፓርላማ ባላስፀደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ተጠልሎ ባለ ብዙ አቅጣጫ ዘመቻ ተያያዘ፡፡

ከምርጫ ማግሥት ጀምሮ ተቃዋሚዎቹን ከመንግሥት መገናኛ ዘዴዎች አግዶ በምርጫ አሸናፊነቱን በሌባ ዓይነ ደረቅንት እውነት ማስመሰሉን ተለቀቀበት፡፡ የሚቀርብበትን ማጋለጫ እየካደና ጆሮ እየነሳ፣ ሥልጣን ከእንግዲህ በምርጫ ብቻ እንጂ በእነ ኦነግ ዓይነት የሽብር መንገድ መያዝ እንደማይቻል ተረጋገጠ እያለ አወራ፡፡ ተቃዋሚዎች ፊትም የምርጫውን ውጤት ለመቀበል ዝግጁ አልነበሩም፣ ዓላማቸው ተጭበረበረ ብሎ አመፅ ማስነሳት ነው እያለ ሰበከ፡፡ በእኛ በኩል በተሸነፍንባቸው ቦታዎች ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር አድርጎ ወደ ልማት መግባት ነው ፍላጎታችን እያለ ሊያቄልም ሞከረ፡፡ የመንግሥት ሥራ በደነዘዘበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ስለመጪው አምስት ዓመታት የሥራ ዕቅድና ስለበጀት አወራ፡፡ ተቀጥላ ምሁራኑም በጆርጂያና በዩክሬን የምርጫን ውጤት ያስቀየረው አመፅ ሳይሆን የፍርድ ቤት ውሳኔ ነው፣ ተቃዋሚዎችም ተጭበረበረ ካሉ በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ መጓዝ ነው ያለባቸው፣ ሠልፍና ስብሰባ በተከለከለበት ሁኔታ አመፅ ቢሞከር ኢሕአዴግ ከልምድ እንደታየው አይምርም እያሉ አርፎ መቀመጥን አስተማሩ፡፡ ሕግን ተከትሎ ደጅ መጥናትና ውሳኔን በፀጋ መቀበል ከዴሞክራሲያዊነት ጋር አንድ ተደረገ፡፡ በሰላማዊ ሠልፍ ስርቆትን ማጋለጥ አገርን ለአደጋ ከመዳረግ፣ ልማትን ከማደናቀፍና ድህነትን ከማባበስ ተቆጠረ፡፡ ተቃዋሚዎች ከ‹‹አመፅ›› ርቀው የምርጫውን ውጤት እንዲቀበሉ በየዕለቱ ተወተወቱ፡፡ የምርጫ ቦርድ ዛሬ ይህን ያህል ጊዜያዊ ውጤት ደረሰኝ፣ ኢሕአዴግ በዚህን ያህል ይመራል፣ ቅንጅትና ኅብረት በሁለተኛነትና በሦስተኛነት ይከተላሉ እያለ (ለተቃዋሚዎችም ጭማሪ ጣል የሚደረግበት) የድምፅ ውጤት ከቀን ቀን ሲገልጽ (ወደፊት የተጣራው ውጤት ይፋ ሲሆን ሕዝብ ዱብ ዕዳ ሆኖበት እንዳይቆጣ ከወዲሁ የኢሕአዴግን ማሸነፍ የማለማመድና ስሜት የማብረድ አገልግሎት ሲሰጥ) ቆየ፡፡

በፀረ ትግሬ ስሜትና የጥቃት አደጋ የትግራይ ልጆችን ከተቃዋሚዎች ጋር ለማቃረን፣ በዚህም አማካይነት በወያኔነትና በትግራዊነት መሃል የተፈጠረውን ክፍተት ለመጠገን ውስጥ ውስጡን ብዙ ተባለ፡፡

በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ቡድናዊ ቁጥጥርን ለማጥበቅ፣ ሠራዊቱን ከኢሕአዴግ ተጋድሎና ከግንቦት 20 ድል ጋር የማቆራኘት ፖለቲካዊ ሥራ ተሠራ፡፡ በተቃዋሚ በኩል ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በአመፅ የመቀልበስ (የመንግሥት ግልበጣ የማከናወን) አደጋ አለ በሚል እምነት ሠራዊቱ ኢሕአዴግን ለማትረፍ ተግባር እንዲቆም ተለፋ፡፡ የማዕረግ ዕድገትም ታከለበት፡፡

ከምርጫ 97 ቅስቀሳና ሠልፎች ጀምሮ ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ የታዩ የተቃዋሚዎችን ሰዎች (ደጋፊዎችን፣ አባላትን፣ ታዛቢዎችንና ተመራጮችን) በማስፈራራት፣ ባልታወቁ ሰዎች ድብደባ በማካሄድ፣ ንብረት በማቃጠል፣ በዚህ በኩል መንገድ ይመጣል እያሉ ቤት በማፍረስ በእስራትና በግድያ ጭምር እያዋከቡ የማኮላሸት ዘመቻ ጦፈ፡፡ የዚሁ ሒደት አካል የሆነውና ከግንቦት 28 እስከ 29 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደው የተማሪዎች ለቀማ ቁጣን ጫረ፡፡ ቁጣው ወደ ሌሎች የትምህርት ተቋማትም ተላለፈ፡፡ ‹‹በቅንጅቶች የተቀሰቀሰን ብጥብጥ፣ የዘረፋንና እስረኞችን የማስፈታት ሙከራ ለመግታት›› እየተባለ ጭካኔ የተሞላበት ድብደባ፣ አፈሳና ግድያ ተካሄደ፡፡ መንግሥት 26 ቢልም በአርባ ቤት የሚቆጠሩ ተገደሉ፣ በርካቶች ቆሰሉ፣ ሺዎች ታሰሩ፡፡ ቁጣውን መንገድ የሚያስትና የሚያቆሽሽ የትግራይ ልጆችን የጥቃት ዒላማ ያደረገ ወረቀትም ተረጨ፡፡ በአውሮፓና በአሜሪካ ውስጥ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የፀረ መለስ ውግዘቱና የፍትሕ ያለህ ጩኸቱ ጦፈ፡፡ የመለስ መንግሥትም፣ የንግድ ቤቶችና የታክሲዎች ሥራ ማቆም የተካተተበት የአዲስ አበባ ቅዋሜ ወደ ሌሎች ሥፍራዎች እንዳይዛመት ለማድረግና ለማሟሸሽ ከዛቻ፣ ከቁጥጥርና ከጭፍን አፈሳ በላይ ሁሉም ወደ ነበረበት እየተመለሰ ነው በማለት በተወሰኑ ቀናት ውስጥ (ከሰኔ 1 እስከ 4) ብዙ የውሸት ጋራ ከመረ፡፡ ተቃዋሚዎች እጃችን የለበትም እያሉ ቢጮሁም ቅንጅቶችንና ተቃዋሚዎችን በ‹‹አመፅ›› አነሳሽነት ማውገዙና የቅንጅቶችን አባላትና ደጋፊዎች በየክልሉ መልቀሙ በረታ፡፡

ሰኔ 3 ቀን በአውሮፓ ኅብረት አምባሳደርና በሌሎች አደረዳሪዎች አማካይነት መንግሥትና ሁለቱ ዋና ተቃዋሚዎች አቤቱታ የቀረበባቸው የምርጫ ውጤቶች (የውጭና የድርጅቶቹ ታዛቢዎች በተገኙበት) ተመርምርው (በሒደት ተጨማሪ መረጃ የማምጣት ዕድላቸውም ተጠብቆ) ውሳኔ እንዲያገኙ፣ የምርጫ ቦርድ ውሳኔን ባይቀበሉ የፍርድ ቤት ውሳኔ የመጨረሻ ሊሆን ተስማሙ፡፡ ሆኖም ተቃዋሚዎቹ እየተካሄደ የነበረው መዋከብና እስከ ማስራብ የሄደ የቁም እስር እንዲቆም፣ የታሰሩት እንዲፈቱና የግድያዎች ተጠያቂ እንዲጣራ ለሚሉ ጥያቄዎች አብረው በፅናት መቆምና ተፅዕኖ ማሳረፍ አልቻሉም ነበር፡፡ ቅንጅቶች እነዚህን ጥያቄዎች ማንሳታቸውን መንግሥት ያለ ኃፍረት እንደ ኃጢያት አድርጎ ሲኮንን ነበር፡፡ እነሱን ነጥሎ ለማወራረድም ቋምጦ ነበር፡፡

በኋላ ሦስቱ ፓርቲዎች በመስማማታቸውና ሰላምና መረጋጋት በመገኘቱ ተደስተናል ከማለት ጋር፣ በአዲስ አበባና በአንዳንድ አካባቢዎች የታየው ‹‹ብጥብጥና አመፅ›› ሕገ መንግሥት የጣሰና የፌዴራል ሥርዓቱ በኃይል ለማፍረስ የተደረገ ሙከራ ነበር የሚል የአጠባ ጎርፍ ተለቀቀ፡፡ እውነቱ ግን ሌላ ነበር፡፡ ሰላማዊ ሠልፍ ፍላጎትን/ብሶትን መግለጫና ተፅዕኖ (Influence) ማሳደሪያ መንገድ ነው፡፡ በተቋማዊ መንገዶች አቤቱታን ከማቅረብ ባሻገር በሠልፍ ጥያቄን ማሰማት የትም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ያለ መብት ነው፡፡ ይህ መብት ገዥ ቡድን ግዙፍ ሠልፍ ሊመጣ ነው ብሎ በፈራ ቁጥር የሚታገድ አይደለም፡፡ የገዥ ቡድን መራድና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን በኃይል የመቀየር አደጋ በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ በጊዜው በኃይል ሥርዓቱን ለማፍረስ የተንቀሳቀሰ ፓርቲም አመፅም ፈፅሞ አልነበረም፡፡ ሕገ መንግሥቱን ጥሶ (የድምፅ መጭበርበር ቅሬታ በአደባባይ እንዳይተምበት የመቃወምና የመሰብሰብ መብቶችን ያገደው መንግሥት ነበር፡፡ አግዶም በማሳደድና በማሰር የቁጣ መነሻ የሆነው ራሱ፡፡ እየተሳደዱና እየታሰሩ አርፎ መቀመጥ ተገቢ ሊሆን ነው? አትሰሩን/ልጆቻችንን ፍቱልን ብሎ መንገድ መውጣትና መጮህ ተገቢ ላይሆን ነው? ተቃውሞውም ጎማ ከማቃጠልና ድንጋይ ከመወርወር ያላለፈና በመሠረቱ ሰላማዊነትን ያልለቀቀ ቅዋሜ ነበር፡፡ ብጥብጥና አመፅ አልነበረም፤ [(ብጥብጥ ከቁጥጥር የወጣ ድብልቅልቅ ሁከት ነው፡፡ የአመፅም ትርጉም መሣሪያ ላነሳ እንቢታ ያደላ ነው፡፡ አንድ የሕወሓት ሁነኛ ሰው በአንድ ስብሰባ ላይ የተረተውን ላለታውስ፡፡ሁለት ልጆች አንዲት እንስሳ ከርቀት ዓይተው ክርክር ይገጥማሉ፡፡ አንዱ ወፍ ነች ሲል ሌላው ፍየል ነች ይላል፡፡ ወፍ ነች ባዩ ለማረጋገጥ ቀርበን እንያት፣ ስንጠጋት ትበራለች ይላል፡፡ ተሟጋቹ ግን ብትበርም ፍየል ነች ብሎ ድርቅ ይላል፡፡ የኢሕአዴግ እውነተኛነት እንዲዚያ ሆኗል፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት በፕሮፓጋንዳው እነዚህን ቃላት ያጠበቀው፣ ዴሞክራሲያዊና ሕጋዊ መሆን ቅሬታን አመልክቶ ውሳኔ መጠበቅና የተሰጠን ውሳኔ በፀጋ መቀበል ነው፣ ከዚህ አልፎ ቅዋሜን በዴሞክራሲያዊ መብቶች (በሰብሰባ፤ በሠልፍና በሥራ ማቆም) መግለጽ አመፅ ነው፣ ሰላምን ማናጋትና ሁከት መፍጠር ነው የሚል ‹‹እምነት›› በኅብረተሰቡ አዕምሮ ላይ መጋገር ስለሚፈለግ ነው)]፡፡

የኃይል ጥቃት (Violence) ፈፃሚም ራሱ መንግሥት ነበር፡፡ በየመንገድ የተገኘውን ሁሉ በዱላ ሲቀጠቅጥ፣ ሲያፍስና ሬሳ ሊያነሳ የሮጠንና ከቤቱ ብቅ ያለን ሁሉ በጥይት ሲቀነደብ የነበረው ራሱ ነበር፡፡

ግድያ የተካሄደው ‹‹አደገኛ የዘረፋና እስረኛ የማስለቀቅ›› ሁኔታ ስለመጣ ወይም ‹‹ከፖሊስ አቅም በላይ ሆኖ ለአድማ ብተና ያልሠለጠነ ኃይል መጠቀም ግድ ስለሆነ›› (የፖሊስ ኮሚሽነሩ እንደተናገረው) የሚባለው ሁሉ ሙልጭ ያለ ውሽት ነው፡፡ መከላከያ ሠራዊትን ድረስልኝ የሚያሰኝ የፀጥታ ችግር አልነበረም፡፡ ለነበረው ብጥስጣሽ ቅዋሜ የሚበቃ የፖሊስ ኃይል ነበር፡፡ ከሚያዝያ 1993 ዓ.ም. በኋላ የፖሊስ ኃይልን የማጠንክር ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከምርጫው በፊትም የአድማ በታኝ ፖሊስ ሥልጠናና ምረቃ ነበር፡፡ ቅጥቀጣና ግድያ የተፈጸመውም ሆነ ተብሎ ዳግም ቅዋሜ ብትሞክር አልምርህም የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ተፈልጎ ነው፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ ተሞከረ የተባለውም ከተጠያቂነት ለማምለጥና አደጋው ያለ አስመስሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማርዘም የተካሄደ ማጭበርበር ነበር፡፡ ባልታጠቀ ተቃውሞ ላይ ጥይት እንዲተኮስ አዛዥና አስገዳይ ሆኖ ወይም ይህን ያደረገውን ደብቆ ሠልፉን ያነሳሱት ለግድያው ተጠያቂዎች ናቸው የሚል ልፍላፎም ሹፈት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይጣራል፣ ሌላ ሁከት ከእንግዲህ ቢሞከር እሳቱ አቀጣጣዩን የሚያቃጥል ስለመሆኑ ማስጠንቀቁ በግድያው ከተላለፈው መልዕክት የተለየ አይደለም፡፡ ሠልፉ የተደረገው ሠልፍ በታገደበት ጊዜ መሆኑም የግድያ ድርጊቱን ተገቢ አያደርገውም፡፡

እንደተፈለገውና እንደተጠበቀው አስተማማኝ ሰላም እስኪፈጠር ተብሎ የመብት ዕገዳው ተራዘመ፡፡ የምርጫ ቦርድ ውጤት መግለጫ ጊዜም ከሰኔ ወደ ሐምሌ ተንፏቀቀ፡፡ የ‹‹ማጣራቱ›› ሒደት የኢሕአዴግንና የመንግሥቱን ‹‹ንፅህና›› ለማሳየት እንዲችል ለማድረግ፣ በድጋሚ ምርጫዎች ለማሸነፍም ሆነ በሚፀድቁለት ውጤቶች ላይ ተቃዋሚ እንዳይበዛ ከወዲሁ እያታገለ ነው፡፡ ድምፅ ተጭበረበረ የሚል ቅሬታ እንዲጠወልግና ሕዝብ ተቃዋሚዎችን እንዲጠራጠርና እንዲያወግዝ በድጋሚ ምርጫ ላይ የድምፅ ካርዱን ለኢሕአዴግ እንዲገብር ለማድረግ ቅጥቀጣውን በየፈርጁ ያካሂዳል፡፡ የተቃዋሚ ደጋፊዎች የሚላቸውን በልዩ ልዩ ሥልት በማጎሳቆል ሌላው ከእነሱ አበሳ ተምሮ ከቅዋሜና ተቃዋሚን ከመምረጥ እንዲርቅ ለማድረግ ይሠራል፡፡ ተቃዋሚዎች ድምፅ ተሰረቀ ያሉት ሐሰት ነው፣ ፍላጎታቸው በኃይል ሥርዓቱን ለማፍረስ ነው፣ ምርጫው ነፃና ትክክለኛ ነበር እያለ በስብሰባዎች ይነዘንዛል፣ በመንግሥት መገናኛ ዘዴዎች ከጠዋት እስከ ማታ በየዕለቱ ህሊናን ይደበድባል፡፡

በአዲስ አበባ አልመች ብሎ እንጂ ማጭበርበር ያልተሞከረ ይመስል በአዲስ አበባ ሙሉ ለሙሉ መሸነፉን ለምርጫው ንፁህነት ማስረጃ ሊያደርግ ይጥራል፡፡ ፀረ ድምፅ ማጭበርበር ቅዋሜ በሌሎች አካባቢዎችም መሞከሩ እየታወቀ ከአዲስ አበባ ወጣ ሲባል አፈናው እንደሚባጥጥና የገጠሩ የተበታተነ አኗኗርም ለተሰባሰበ ቅዋሜ እንደማያመች ልቡ እየተረዳ፣ በአዲስ አበባ ‹‹ሁከት የተከሰተው ድምፅ ስለተጭበረበረ ሳይሆን የጥፋት ኃይሎች ስለሚበረክቱ ነው›› ብሎ ይላል፡፡ ‹‹ጭራሽስ አዲስ አበባ ከራሱ አልፎ ስለሌላው ክልል ምን አገባው? ክልሎች ስለራሳቸው አያውቁም?›› በሚሉ ሥልት ለመነጣጠልም ተሞከረ፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ተቃዋሚዎች ድጋፍ ያገኙባቸውን ጥያቄዎች እየመለሰ ቅሬታ የመበተን ትግል ያካሂዳል፡፡ የኦሮሚያ አስተዳደር ከተማ እንደገና አዲስ አበባ እንድትሆን የኦሕዴድ መወሰን፣ ለልማት ለሚወሰዱ መሬቶች የካሳ ማስተካከያ ለማድረግ መሞከር፣ በቢሮክራሲና በሹማምንት ላይ እየላከኩ አስተዳደራዊ በደሎችን ለማቅለል መሞከር፣ የግብር ማቅለያ ዕርምጃዎች መውሰድ፣ የገበሬውን የምርት ግብዓት ዋጋ፣ የመዋጮና የሥራ ጫና ለማቃለል መራወጥ፣ በ8ኛና በ10ኛ ክፍል የትምህርት ደረጃ ላይ ለሚወድቁ ተማሪዎች በግል ደጋግሞ ከመፈተን ባሻገር አንዴ የመድገም ዕድልን መክፈት፣ አሥራ ሁለተኛን አልፈው ኮሌጅ መግባት ያልቻሉ ሌሎች አማራጮች እንዲያገኙ መፍቀድ፣ ለመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ለማስተካከል መራወጥ ሁሉ የዚህ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ሌላም ነገር ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ ሕዝብን ለማስቀየሙ የእምነት ቃል የሰጠባቸው (የሕዝብ ድምፅ እንደከዳውና እንዳጭበረበረም ሳያውቀው የተናገረባቸውና ሕዝብ እባክህ ማረኝ በድያለሁ የሚል ልመና ያቀረበባቸው፣ ለሕዝብና ለተቃዋሚዎችም የትግላችው መኩሪያ የሆኑ) ውሳኔዎች ናቸው፡፡

የኃይልና የአወናባጅ ፕሮፓጋንዳ ቅጥቀጣው ከመሸንገያ ጋር ተብሎ ተብሎ ምርጫውን የሚመለከቱ አቤቱታዎችን የማጣራቱ ሒደት ቀጠለ፡፡ እንደ ተቃዋሚዎቹ ሁሉ ኢሕአዴግም ተበዳይ ሆኖ ቀረበ፡፡ ምርጫ ቦርድን የሚያህል ነገር ይቅርና የማኅበራትን አመራር እንኳ ካልተቆጣጠረ እንቅልፍ የማይወስደው ገዥ ፓርቲ ተቃዋሚዎች በምርጫ አጭበረበሩኝ በማለት ራሱ ለራሱ አቤት ያለበት ታሪክ፣ ኢትዮጵያ ለዓለም ካበረከተቻቸው ብርቅዬ ነገሮች አንዱ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በማጣራቱ አካሄድ ውስጥ ፓርቲዎችና የውጭ ታዛቢዎች እንዲሳተፉና አቤቱታዎች በመረጃ ተጠናክረው ድጋሚ እንዲታዩ ዕድል መከፈቱ ውብ ነበር፡፡ በአጣሪ ቡድን ቅንብር ውስጥ የኢሕአዴግና የምርጫ ቦርድ ተወካይ የድምፅ ብልጫ ዕድል ቢኖራቸውም፣ ውሳኔ ሰጪነት ዞሮ ዞሮ የምርጫ ቦርድ ቢሆንም ንፁህ ሥራ የሠሩ ለማስመሰል በሚያስችል ቅንብር አሸብርቋል፡፡ የማጣራቱን ሥራ ዕርባና ቢስ ያደረገው ዋና የአፈና ሁኔታ መገኛ ግን መረጃን እየተቀበሉ ከመመርመር ኮሚቴያዊ መድረክ በስተጓሮ ነበር፡፡ ሕዝብ በድቆሳ ፍርኃትና በሐሳዊ ፕሮፓጋንዳ ተሰንጓል፣ በተቃዋሚዎች ጎን ሆኖ መመስከርን የመሸሽና ምስክርነትን የማለባበስ፣ እንዲያም ሲል የመካድ ሁኔታ መታየቱም ለዚህ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ደግሞ እንኳን ሲሆን ያዩትን ይቅርና ራስን በራስ ለማስካድም የሚቻለው ነው (በታምራት ላይኔ ላይ እንዳየነው)፡፡

በማጣራቱ ውጤትም ኢሕአዴግ ያሸነፈባቸውን የምርጫ ውጤቶች በማስጠበቅም ሆነ ድጋሚ ምርጫን በማስወሰን በኩል ድል በድል ሆኗል፡፡ ድጋሚ ምርጫ ከመደረጉም በፊት የፌዴራል መንግሥትን ለመምራት የሚያበቃና በድጋሚ ምርጫዎች ውጤት የማይረበሽ አብላጫ ድምፅ ማግኘቱን፣ የክልላዊ የሥልጣን ይዞታም አለመለወጡን (ከአዲስ አበባ በቀር) ምርጫ ቦርድ (ነሐሴ 3 ቀን 1997) ይፋ አደረገ፡፡ በአፋኝ ሁኔታ ውስጥ በተካሄደው ድጋሚ ምርጫ ደግሞ ድሉ እጥፍ ሆነ፡፡ በተቃዋሚዎች ‹‹ማጭበርበር›› እንዳይሆኑ ሆነው የተሸነፉት እንደ አባዱላ ገመዳ ያሉ የኢሕአዴግ ሰዎች ከመጀመሪያው ጊዜ ተቀራራቢ የሆነ ድምፅ ሰጪ የተሳተፈበት በተባለ ‹‹እንከን የለሽ ምርጫ›› በአሸናፊነት ድምፅ ተጥለቀለቁ፡፡ አሁንስ ታሪክ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሕይወት ላይ ማሽሟጠጧን በእጅጉ አላበዛቸውም?

በአጠቃላይ ምንም ሆነ ምን የግንቦት 97 ምርጫ በኢትዮጵያ ሕዝብ የዴሞክራሲ ትግል ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላትና ልትዘከር የሚገባት ነች፣ ብዙ ቁምነገርም አስጨብጣለች፡፡

  • የምርጫ አስፈጻሚዎች ከፓርቲ ተልዕኮ ያልፀዱ መሆናቸውንና ያለው መዋቅር ነፃ ምርጫም ሆነ እርማት የማካሄድ ብቃት እንዲሚጎድለው አጋልጣ የተሻለ ነፃነት የሚኖረው (የአባላቱም ስብስብና የሥራ ቆይታ የፓርቲዎችንና የሕዝብን አመኔታ የሚያንፀባርቅ)፣ አዲስ የምርጫ አስፈጻሚ አካል የማደራጀትን አስፈላጊነት ቁልጭ አድርጋለች፡፡
  • የፍትሕ፣ የነፃነትና የዴሞክራሲ ጥማት በሲቪልነት፤ በፖሊስነት፣ በወታደርነትና በብሔር ቆዳ የማይገደብ የመላ ሕዝብ ጥማት መሆኑን (የወያኔ ኢሕአዴግን አመራርና አባላቱን እንኳ አንድ አድርጎ ማየት በማያስችል አኳኋን) ገልጻለች፡፡ ኢሕአዴግን አለመምረጥን በ‹‹ነፍጠኝነት›› እና በ‹‹ብሔር ጥላቻ›› ማብራራት ድሮ የቀረ ጉዳይ ሆነ፡፡
  • በባዶ ኩራት ሲቀሸርና የሕዝብ ድጋፍ አለኝ እያለ ራሱንም ረጂዎቹንም ሲያጭበረብር ለኖረው ኢሕአዴግ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከተቃዋሚዎች ጋር ውለታ ዋሉ፡፡ በግዳጅ፣ በቅጥፈትና በፖለቲካ ጉቦ እያወነባበደ፣ በሰላም ማጣትና በጦርነት እያስፈራራ መግዛት እንደማይችል ያንን ሁሉ የስብሰባና የሠልፍ ቴአትር ባዶ አስቀርተው እውነቱን አፈረጡለት፡፡ የቱንም ያህል የወንበር ብልጫ አገኘሁ ቢባል ዋንጫው እስኪወልቅ ሽንፈቱን አሳዩት፡፡
  • የፈሪ ምራቅ ሕዝብ ላይ ለሚተፉና አርቆ ማየት ለጎደላቸው ፖለቲከኛ ነን ባዮች፣ ፖለቲካዊ ብልህነትና መታገል እንዴት እንዴት እንደሆነ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትምህርት ሰጧቸው፡፡ ወቅታዊ ሁኔታንና የገዥዎቹን ባህርይ አጢኖ በአጉል መናከስ ችግርን ሳያወሳስቡ (አውሬያዊ ዝንባሌን ከእንቅልፍ ሳይቀሰቅሱ)፣ በሠልፍና በድጋፍ አቂሎ እንዘጭ ማድረግ እንዴት እንደሆነ አሳዩ፡፡ ተቀናቃኞቻቸውን አካይስት አድርገው ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚገፉ ዓይናቸውን ከፍተው ከሕዝብ ቢማሩ ይበጃቸዋል፡፡
  • የኢትዮጵያ ሕዝብ በአላኳሽና በከፋፋይ ቅስቀሳዎች መናቆርና መሸማቀቅ ምን ያህል እንዳንገፈገው፣ መጪዋን ጊዜ ምን ያህል የተሻለና ነፃ ሕይወት ተስፋ እንዳደረገባት ለዓለም አሳይቷል፡፡ በወደፊቱ ጉዞ ነፍስና ሥጋ የሚጨርስ ከባድ ዕዳ መሸከማቸው ያልገባቸው ፖለቲካኞች ካሉ፣ በምላስ ብልጠትና በስርቆት ችሎታ ወንበር አሰባሰብን ብለው የሚያስቡ ካሉ፣ ሕዝብ እያቃሰተ ድምፅ የሰጣቸውና በእስራትና በሞቱ ቆርጦ የተዋደቀው ለምን እንደሆነ ያልገባቸው (በደመወዝና በዝና ምራቃቸው የሞላ ወይም ተንኮል እየሠሩ ተቀናቃኝን በማሳጣት ሥልጣናቸውን ለማስፋት የሚያልሙ) ውዮላቸው!! አገሪቱንና ሕዝቦቿን በተባበረ ፖለቲካ ጠቅልሎ የሚመራ ኃይል በሌለበት፣ ብልጣ ብልጥነት፣ ሸፍጥና የአጋጣሚ አድፋጭነት ሁሉ በሚላወስበት ሁኔታ ውስጥ ታሪክ ኢሕአዴግንና ተቃዋሚዎቹን በአንድ ምክር ቤት ውስጥ ከትታ ለፈተና አቀረበቻቸው – ጉድ ልታይ፡፡

[የሰሚ ያለህ የኢትዮጵያ ሕዝቦች እሪታ ከበቀለ ሹሜ 1999 መጽሐፍ የተወሰደ]

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...