Saturday, June 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች በጥቅሉ 222.8 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ሰበሰቡ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 51.2 በመቶ ድርሻ ይዟል

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በአሥር ወራት ውስጥ ከ222.8 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉንና ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድርሻ 51.2 በመቶ መሆኑ ተመለከተ፡፡

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ወቅታዊ አፈጻጸምን የሚያመለከተው መረጃ እንደሚያሳው፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በየዓመቱ በአማካይ ከ24 በመቶ እያደገ መምጣቱን ነው፡፡ በተመሳሳይ ፋይናንስ የሚደረገው (የሚሰጠው ብድር) ምጣኔም በተለይ በ2016 የሒሳብ ዓመት ከቀዳሚዎቹ ዓመታት የተሻለ ዕድገት ማሳየት መጀመሩ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት (የሲቢኢ ኑር) ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኑር ሁሴን ለሪፖርተር እንደገለጹትም፣ በ2016 የሒሳብ ዓመት ከወለድ ነፃ አገልግሎት አፈጻጸም በሁሉም ረገድ ዕድገት እያሳየ ነው፡፡ በተለይ ከተቀማጭ ገንዘብ አንፃር እየታየ ያለው ዕድገት ለውጡን የሚያሳይ ቢሆንም፣ ፋይናንስ (ብድር ከመስጠት) አንፃር ግን አሁንም ክፍተት ስለመኖሩ ጠቁመዋል፡፡ ይህም ቢሆን ግን በአጠቃላይ በኢንዱስትሪው ከወለድ ነፃ አገልግሎት ዘርፍ በ2016 የሒሳብ ዓመት የተሰጠው ብድር ዕድገት አሳይቷል።

በተለይ በዚህ ዘርፍ ትልቁን የገበያ ድርሻ የያዘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሥር ወራት ያሳየው አፈጻጸም ይህንኑ የሚያመላክት ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስከ 2016 የሒሳብ ዓመት አሥር ወራት ማሰባሰብ የቻለው አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ 114.8 ቢሊዮን ብር መሆኑን አቶ ኑር ሁሴን ገልጸዋል፡፡ ይህም በአሥር ወራት ውስጥ ብቻ ከ24 ቢሊዮን ብር በላይ አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉን የሚያመለክት ነው፡፡ 

የአስቀማጭ ደንበኞችን ቁጥር በተመለከተም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ እያስቀመጡ ያሉ ደንበኞች ቁጥር 7.2 ሚሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን ይህም የወለድ ነፃ ተገልጋዮች ቁጥር በየጊዜው እያደገ ስለመምጣቱ አመላካች ነው፡፡ በአሥር ወራት ውስጥ እንኳን የአስቀማጭ ደንበኞች ቁጥር ከ20 በመቶ በላይ ዕድገት ማሳየቱ ምሳሌ ሊሆን እንደሚችልም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ከፋይናንስ (ብድር) አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ያቀረበው ብድር ከሌሎች ዓመታት በተለየ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ 

እንደ አቶ ኑር ገለጻ፣ በ2016 በአሥር ወራት ውስጥ ብቻ ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰጠው የብድር ክምችት 40.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

ሰኔ 2015 መጨረሻ ላይ ባንኩ አጠቃላይ የብድር ክምችቱ 23.3 ቢሊዮን ብር እንደነበር ያስታወሱት አቶ ኑር አሁን የብድር ክምችቱ የደረሰበት ደረጃ በሒሳብ ዓመቱ  በአሥር ወራት ውስጥ ብቻ ወደ 18 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር መሰጠቱን ያመለክታል፡፡ በቀሪዎቹ የሒሳብ ዓመቱ ሁለት ወራት ውስጥ የሚሰጠው ብድር ሲታሰብ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከቀዳሚው ዓመት ከእጥፍ በላይ ዕድገት ሊያሳይ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ይህም ቢሆን ግን ከተሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ አንፃር እየተሰጠ ያለው ብድር አነስተኛ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ አቶ ኑርም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት እየተሰበሰበ ካለው የተቀማጭ ገንዘብ አንፃር ከወለድ ነፃ የባንክ እየተለቀቀ ያለው ብድር አነስተኛ ነው፡፡ ነገር ግን መሻሻሎች እየታዩበት ስለመሆኑ ግን ያስገነዝባሉ፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከሚሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብ አንፃር የሚሰጠው ብድር የሚጠበቀውን ያህል ላለመሆኑ አንዱ ምክንያት ከወለድ ነፃ ብድር ለመስጠት ለሚያስችሉ የተለያዩ አገልግሎቶች አሁንም ተስማሚ የሆኑ መመርያዎችና አሠራሮች ባለመኖራቸው እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራ ባንክ መመርያም የሚገድብበት ሁኔታ መኖሩን እንዲሁም የብድሩ አሰጣጥ የሸሪዓ ሕግን የጠበቀ መሆን ስለሚገባው ይህንን ሁሉ አሟልቶ ብድሩን ለመፍቀድ የሚያጋጥሙ ችግሮች መኖራቸውም የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

ይህም ቢሆን ግን ባንካቸውም ሆነ አጠቃላይ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የፋይናንስ አቅርቦት ከቀዳሚዎቹ ዓመታት አንፃር ሲታይ እያደገ ነው፡፡ 

በ2016 የሒሳብ ዓመት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሻለ አፈጻጸም እንዳሳየ ማሳያ ያደረጉት ደግሞ በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በኩል እየተገኘ ያለው የውጭ ምንዛሪ ከፍ ማለቱ ነው፡፡ በብዙዎቹ ባንኮች በኩል ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ዕድገት ማሳየቱንም ጠቁመዋል፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሲቢኢ ኑር በኩል የተገኘው የውጭ ምንዛሪ የዕድገት ምጣኔ ከፍተኛ መሆን ችሏል፡፡

ዘርፉ ከውጭ ምንዛሪ ግኝት አንፃር ዘንድሮ የተለየ አፈጻጸም የታየበት መሆኑንና ወደፊትም ቢሆን ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ መሆን የሚችል መሆኑን እንዳመላከተ ተናግረዋል፡፡ 

ባንኩ በአሥር ወራት ውስጥ ብቻ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከ76 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት የሙሉ ዓመት አፈጻጸም ጋር ሲታይ እንኳን ከ15 እጥፍ በላይ ዕድገት መታየቱ ነው፡፡ በቀዳሚው ዓመት ባንኩ በሙሉ የሒሳብ ዓመቱ ያገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 5.4 ሚሊዮን ብር በመሆኑ ዘንድሮ በአሥር ወራት የተገኘው ገቢ ከፍተኛ ጭማሪ እንዳለው ያመለክታል፡፡ እስከ ዛሬ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ እንኳን የዚህን ያህል የውጭ ምንዛሪ ገቢ ያልተገኘ መሆኑም ይጠቀሳል፡፡ 

ዘንድሮ በአሥር ወራት ውስጥ ከ76 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሊገኝ የቻለበት ዋነኛ ምክንያት ባንኩ ኤክስፖርተሮች ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ተጠቅመው ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ ሰፊ ሥራ በመሠራቱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ዘርፍ የሚሰጠው ብድር በዜሮ ወለድ የመስጠት ያህል የሚቆጠር በመሆኑ፣ በዚህ በዚህ መስመር የሚገለገሉ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ኤክስፖርተሮች ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እየተጠቀሙ መምጣት የውጭ ምንዛሪ ገቢውን ሊያሳድገው ስለመቻሉም ከሰጡት ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ 

አሁንም ምርቶቻቸውን ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ምርቶቻቸውን የሚልኩ ኤክስፖርቶችን ቁጥር ማሳደግ እንደሚሹ የገለጹት አቶ ኑር እስካሁን የቡና፣ የሥጋና የፍራፍሬ መሰል ላኪዎች አገልግሎት በሰጠው ባንኩ ባመቻቸላቸው ዕድል ተጠቃሚዎች ሆነዋል፡፡ 

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ግን አሁንም ለተለያዩ አገልግሎቶቹ የሚሆኑ የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልጋቸዋል የሚሉት አቶ ኑር ከሥር ከሥር አስቻይ የሚሆኑ ሕግጋት በብሔራዊ ባንክ ብኩል ሊወጡ ይገባልም ብለዋል፡፡

አንድ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ፋይናንስ ለመስጠት የሚያስችል አሠራር ተቀርፆ ለዚያ የሚሆን ሕግ ማዕቀፍ ከሌለ አዳዲስ አገልግሎቶችን ለገበያው ማቅረብ አስቸጋሪ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡  

አገልግሎቱን ለማስፋት አጋዥ ይሆናል የተባሉ የሕግ ማዕቀፎችን በተመለከተ ብሔራዊ ባንክ ከአጠቃላይ የባንክ አሠራር አዋጅ ማሻሻያዎች ጋር ሥራዎች እየተሠራ ስለመሆኑ ግን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

አሠራሩን ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ የሕግ ማሻሻያዎች ከወጡ ባንኮች ከወለድ ነፃ የሚሰጡትን የብድር መጠን ማሳደግና ብድር የሚሰጡበትንም የአገልግሎት ዘርፎች እያሰፋ ይሄዳል የሚል እምነት አላቸው፡፡

በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በመስኮት ደረጃ የሚሰጡ ከሃያ በላይ ባንኮች ሲኖሩ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ አራት ባንኮች በኢንዱስትሪው ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች