Wednesday, July 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል?

በሙሉጌታ ቢያዝን

አሐዱ

‹‹ከወደዱስ መውደድ መውደድ ነው አንደኛ፣

አንድም ሙዚቀኛ አንድም ጋዜጠኛ፡፡››

የተባለለት አንድ ጋዜጠኛ አንድን ባለሥልጣን በጥያቄ ይፈትነዋል፡፡ ባለሥልጣኑም “ለጥያቄው እርግጡን ወይስ ኦፊሴሊያዊ /ዲፕሎማሲያዊ/ መልስ?” ይለዋል፡፡ ጋዜጠኛውም “የለም እርግጡን መልስ ይስጡኝ” ይላል፡፡ ባለሥልጣኑም “እንግዲያው መቅረጸ ድምፁን አጥፋ”፡፡ መልእክቱ ‘የኮሪደር ወግና/corridor talk/ የሚዲያ ወግ ለየቅል ነው’ ለማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው ሚዲያ ላይ የሚተላለፉ መልእከቶች ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው፡፡

ይህን ለማለት የገፋኝ እንደቋያ እሳት እየተዛመተ ያለ መፈክር በሚመስል አባባል ምክንያት ነው፡- ‘ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል’፡፡ ይህን የተለምዶ አባባል “ሰው ሲፈጠር ሙሉ አይደለም እንዴ?” የሚል ጥያቄ ያስነሣል፡፡ መልእክቱ ሰውን የተሻለ አሳቢ፣ አገናዛቢ፣ ስንዱ፣ አዋቂ ወዘተ ያደርጋል ለማለት ይመስለኛል፡፡ ይህ አባባል ለኔ የዳርዊንን የዝግመተ ለውጥ /Evolution/ ሐሳብ የተሸከመ ነው፡፡ ማንበብ በተሰኘ የዝግመተ ለውጥ ሂደት ጎደሎው ሰው ሙሉ ኾኗል እንደማለት ያለ…፡፡

እንደ ቮልቴር “በምትለው ባልስማማም ለመናገር መብትህ ዘብ እቆማለሁ” ባልልም ተናጋሪዎች/ጸሐፊዎች ያሻቸውን ቢናገሩ ችግር የለብኝም፡፡ ሰው በፈጣሪው አምሳል ከሁሉ ፍጥረት ከብሮ እንደተፈጠረ መናገሩ ስብከት ስለሚመስልብኝ ብዘለው አደገኛ አባባል መኾኑን ግን መዝለል የሚገባ አይመስለኝም፡፡ ይሄን የምለው ጥሩ አማኝ ኾኜ ነጥብ ለማስቆጠር ወይም ‘ርካሽ ተወዳጅነት’ ለማፈስ በማለም አይደለም፤ሳናውቅ ይሄን አባባል የምንቀባበል ካለን ግን ብናስብበት፡፡ ዳሩ ሰው ፍጹም ነው እያልኩም አይደለም፡፡

“ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል” የሚለውን መፈክር በሰማሁና ባነበብኩ ቁጥር ሳልፈልግ ቡት ጫማውን ተጫምቶ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ የሚለውን አንድ ሰው ከነመፈክሩ ያስታውሰኛል፡፡Death is the solution to all problems. No man, no trouble” በሚለው

መፈክሩ ዐውቀዋለሁ፡፡ ይህ ሰው ዛሬ በሕይዎት ቢኖር ኖሮ ያለፈው ዲሴምበር 18/ የ145 ዓመት አዛውንት ኾኖ እንደሴት ልጁ ስቬትላና ልመንኩስ ካላለ በቀር ወይ እስር ቤት አለያም በሆስፒታል ኦክስጅን እየተቀለበ እናየው ነበር፡፡

ገና በወጣትነቱ ከት/ቤት ሲባረር 18 መጻሕፍትን ሳይመልስ ነበር እብስ በማለት “አንባቢ አይሰርቅም፤ሌባ አያነብም” የሚለው የኢራቃውያን (?) አባባል ፉርሽ አደረገ፡፡ይሄው ዐመሉ ተከትሎት ይመስላል፣ ከ54 ዓመት በኋላ ሕይወቱ ሲያልፍ በግል ቤተ መጻሕፍቱ ሼልፍ ላይ የሌኒን ቤተ መጻሕፍት ንብረት የኾኑ 72 መጻሕፍት ተገኝተዋል፡፡ በየቀኑ ከ300-500 ገጽ ያነባል የሚባልለት ይህ ሰው ሽቁጥቁጥና ፈሪ ደራስያን “አንብብልን” ብለው የሚሰጡትን መጻሕፍት ትተን በየዓመቱ 500 አዳዲስ መጻሕፍት እንዲቀርቡለት ትእዛዝ ይሰጥ ነበር፡፡ መጻሕፍትን ‘ይበላ ነበር’ ማለት ይቻላል፡፡ የጫማ ሰሪው ልጅ ስታሊን በርግጥም አንባቢ ነበር፡፡

የታሪክ ሊቁ ጄፍሪ ሮበርትስ የስታሊን ላይብራሪ /Stalin’s Library: A Dictator & His Books/ በሚለው ጥናቱ ‘ስታሊን 25ሺ መጻሕፍት ነበሩት’ ይለናል፡፡

መጻፍ የማይደክመው ስታሊን በአለቃው በሌኒን ይኹንታ በማርክሲዝምና በብሔር ጥያቄ ላይ የሚያጠነጥን አንድ መጣጥፍ ጻፈ (እነዋለልኝ መኮንን ይህን መጣጥፍ ሳይኾን አይቀርም ያነበቡት)፡፡

ስታሊን ከፖለቲካና ከምጣኔ ሀብት መጻሕፍት በተጨማሪ አያሌ ልብወለዶችን፣ግጥምና ድራማዎችን አንብቧል ይባልለታል:: ጭካኔውን ግን አላስጣለውም፡፡ ቫይታል ሸንተልንስኪ KGB’s Literary Archive በተሰኘው መጽሐፉ በስታሊን የሽብር አገዛዝ ኦሲፕ ማንደልስታምን

የመሰሉ ገጣሚያንን ጨምሮ 1500 ደራስያን እንደተገደሉ አጋልጧል፡፡ ብዕሩ በሩሲያ ወጣቶች ላይ በጎ ተጽእኖ አምጥቷል ብሎ እንደማያምን ሲናገር ተሰምቶ ነበርና ፊዮዶር ዶስቶቨስኪ መትረፉ ከተአምር የሚቆጠር ነበር፡፡ “ማንበብ ይወዳል፣ አንባቢ ነው” የሚባልለት ስታሊን ይሄን ማድረጉ ‘ማን የጻፈውን ሊያነብ ይኾን?’ ያስብላል፡፡

ሚሊዮኖችን ጨፍጭፏል፣ የተቃወሙትን ወይም የተቹትን ከ139 የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል 93ቱን፣ ከ103 የጦር ጄኔራሎችና አድሚራሎች 81ዱን አስገድሏል፡፡ የጦር መኮንኖችን፣ ልሂቃንን፣ እሽኮኮ ብለው የሥልጣን ማማ ላይ ያወጡትን እንኳ እንዳልማረ ቢቢሲ አጋልጧል፡፡

ክልኤቱ

ይህ ሰው ‘ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል’ የሚለው ይገልጠዋል? ርኅራኄን የገደፈ ሰውነት ሙሉ ነው ማለት ይቻላል?

በ2016 በተደረገ የዳሰሳ ጥናት (‘Reading fiction & reading minds’) ‘… ልብ ወለድ የሚያነቡ ሰዎች ከማያነቡቱ ሩኅሩኅና የሌላውን ስሜት የሚረዱ ኾነው ተገኝተዋል፡፡ … በሰው ልቦና ላይ የሚያተኩሩ የሥነ ጽሑፍ ሀብት ያካበቱ አገሮች /ማኅበረሰብ/ የላቀ አዛኝና ሩህሩህ ናቸው’ ይላል፡፡ “…ግን በዚህ ረገድ ስታሊንን ካበቀለችው ከሩሲያ የላቀ አገር አለ? ሂትለርን ያበቀለችው ጀርመንስ ብትኾን? ማኦዜዱንግን ያበቀለችው ቻይናስ ብትኾን በዚህ ይታማሉ?” ሲል ይጠይቃል ቶንኪን፡፡

ዘነበ ወላ ከተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር) ጋር ሲጨዋወት “ማንም ሰው የራሱ የኔ ከሚለው ሙያ ተጨማሪ ሥነ ጽሑፍና ታሪክን እንዲመርቅ ይመክራሉ፡፡ ሥነ ጽሑፍ የነገውን፣ ታሪክ ደግሞ የትናንቱን ያውቅበታል!…” ሲሉ፡፡ “ውሸትን ደጋግመው እውነት ይሆናል” በሚል እኩይ ምክሩ የሚታወቀው የሂትለር አማካሪ /ፕሮፓጋንዳ/ ዋና ሰው ጆሴፍ ጎብልስና ሩሃቸውን ሳይስቱ የመንትያ አይሁድ ሴቶችን ዓይን እየደነቆለ ምርምር ያደርግ የነበረው ጆሴፍ መንጌል ከሙያቸው ተጨማሪ ሥነ ጽሑፍና ታሪክ ስለማንበባቸው እርግጠኛ አይደለሁም፡፡

‘ራስህን ዕወቅ’ (Know thyself) እንዲል ሶቅራጥስ ሰው የነገውንና የትናንቱን ቢያውቅ ራሱን እንዲያውቅ ካልተራዳው? ራሱን አክብሮ፣ ሌላውን ሰው እንዲወድ ካልረዳው ፋይዳው ምንድን ነው?

አንድ ሰው “ሼኩም እኔም ያው አንድ እንጀራ ነው የምንበላው” ሲል የሰማ አንድ ቀልደኛ ሰው “ግዴለም ስለወጡ እናውራ” እንዳለው ስታሊንና መሰሎቹ ስላነበቡት መጻሕፍት ማውራት ትርጉም የለውም፤ ስለወጡ/በት ቤተሰብ እንጂ፡፡

[ወላጆቹ ሦስት ልጆችን ቀብረው ያገኙት ስታሊን ብቸኛ ልጅ ቢኾንም በስስት አላደገም፡፡ በተለይ ጠጪ/ሰካራም ላለማለት ነው/ እንደነበርና መጠጥ ቤት ውስጥ በተፈጠረ አምባጓሮ በሰው እጅ ሕይወቱ እንዳለፈ የሚነገረው አባቱ ቀማምሶ ወደቤት በገባ ቁጥር ብላቴናው ስታሊንን በቡት ጫማው እንደእባብ ይቀጠቅጠው፣ በቃላትም ክፉኛ ያጠቃው እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ስታሊን የአባቱን የሰርክ ዱላ የሚቋቋመው ሁሉንም በመጠራጠር፣ “ከአሁን አሁን መታኝ” በሚል መባባት፣ ከዱላው ለመትረፍ የባጥ የቆጡን ዘባርቆ በማታለል እና ጥርሱን ነክሶ ዱላውን በመቻል ነበር፡፡ ስታሊን ልክ እንደ ሂትለር እጅግ የተገፋና በአባቱ ክፉኛ ያቄመ ሰው ነበር፡፡ አድጎ ጎልምሶ ሚሊዮኖችን ለመፍጀት ያነበባቸው መጻሕፍት ሊገላግሉት ከቶ አቅም አልነበራቸውም፡፡]

ስታሊን ከሞተ በኋላ “እንደምን ሰው በላ ኾነ?” ለሚለው ጥያቄ ለማወቅ ካነበባቸው መጻሕፍት አንዳች ፍንጭ ለማግኘት በብርቱ የተጋውና በስታሊን ላይ መጨከን የማይደፍረው ሮበርትስ /Goefrey Roberts) ዓለምን የሚያይበትን መነጽሩን እንጂ ነፍሱን ማንበብ /ልቡን

ማግኘት/ እንዳልቻለ አልሸሸገም፡፡ ስታሊን “ይህ ነው የሚያስደስተው፣ ይህ ነው የሚያስከፋው” ብሎ ለመደምደም የሚያስችል ቋሚ ጠባይ አልነበረውም፡፡ ለዚህ ነው የስታሊን የቅርብ ረዳቱ የነበረው ላዛር ካጋኖቪች “አምስት ወይም ስድስት ስታሊኖችን አውቃለሁ” ሲል ልቡን ማግኘት አስቸጋሪ መኾኑን ምስክርነቱን የሰጠው፡፡

አንባቢው ስታሊን በስሑት ፖሊሲው “ሆሎዶሞር” በመባል በሚታወቀው እስከ አሥር ሚሊዮን ዩክሬናውያንን በረሃብ የረገፉትን ጨምሮ (ለያውም እንቁልልጭ እያለ ስንዴ ወደ ውጭ አገር እየላከ) በአገዛዙ የሞቱት ንጹሐን ቁጥር ከሃያ እስከ ስድሳ ሚሊዮን እንደሚገመት ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ ሞት፣ እስር፣ ቶርቸር፣ ስደት ወዘተ ሕዝቡን በፍርሃት ጠፍንጎ የገዛበት ስልቶች ነበሩ፡፡ ቶንኪን ምን አለ? “Nothing is more dangerous than a well-read dictator” ዛድያ ‘ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል’ የሚለውን አባባል “ካነበበ አምባገነን ይጠብቀን” በሚል ቢተካ አይሻልምን!!

አሜን! አበቃሁ!

ከአዘጋጁ:- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል።

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles