Saturday, June 15, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

585 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይበተኑ እንድረስላቸው!

በታምራት ደሴ (ዶ/ር)

በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ የሚገኘው አራት አሠርታትን ያስቆጠረው የፈታዘር ትምህርት ቤት በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ እዣ ወረዳ፣ በደቡብ ምዕራብ ውልባረግና ትርትሮ ቀበሌ፣ በሰሜን ምሥራቅ እንጀፎ ቀበሌ፣ እንዲሁም በምዕራብ ቸሀ ወረዳ የሚያዋስኑት ሲሆን በውስጡም ያሞራዘር፣ የዤር፣ የግንድ፣ ከፊል ያንፋር፣ ከባሮ፣ ቃጫ፣ ይርቀተረ፣ ጫጮ፣ ቀጡቻና መደርቾ የሚባሉ 15 ቀበሌዎችን አካትቷል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ትምህርት ቤቱ 585 ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡ በያዝነው ዓመት ከተመዘገቡት ተማሪዎች ውስጥ ሴቶች 275 (47 በመቶ) ናቸው። በተለያዩ ቀበሌዎች ሦስት የመዋለ ሕፃናት ቅርንጫፎች አሉት፡፡

የፈታዘር ትምህርት ቤት የሚገኝበት በጉመር ወረዳ በዞኑ ውስጥ ከሚገኙ አሥር ወረዳዎችና አምስት የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ አንዱ ነው። 29 የመጀመሪያ ደረጃ፣ አራት ከፍተኛ አጠቃላይና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች አሉ።

ፈታዘር ትምህርት ቤትን ለማሻሻል የቀድሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና የአካባቢው ማኅበረሰብ የተጋረጡበት በርካታ ችግሮችን ለመቅረፍ በጋራ እየሠራ ነው፡፡ የትምህርት ቤቱ ችግር ከወረዳው አቅም በላይ በመሆኑ በወረዳው አስተዳደርም ጭምር ይሁንታን ያገኘ ሲሆን፣ በትውልድ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ሁሉ እንደሚያግዙን እምነታችን ነው፡፡

በእያንዳንዱ የሕይወታችን እንቅስቃሴዎች ውስጥ ከተፈጥሮ ዘርፈ ብዙ ነገሮች እንማራለን፡፡ ትውልድ እንደ ጅረት ውኃ ነውና እየተቀባበለ መፍሰሱን ይቀጥላል፡፡ አንደኛው ትውልድ ሲያልፍ ለሌላው ሥፍራውን እየለቀቀ ይሄዳል፡፡ በዚህ የተፈጥሮ ሒደት ውስጥ በተሰጣቸው ዕድሜና ዘመን ለትውልድ መልካም አሻራቸውን ጥለው ያለፉት በተተኪው ትውልድ ሲታወሱና እንደ ማንቂያ ደወል ሌላውን ሲያነቁ ይስተዋላል፡፡

ይህ ትምህርት ቤት የቀለም ትምህርት ባልተስፋፋበት ዘመን ለአካባቢው ማኅበረሰብ ብርሃን ሊፈነጥቅ ተመሥርቷል፡፡ በደርግ ዘመነ መንግሥት በፈታዘር ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያንና በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ አማካይነት እንደተቋቋመ የታሪክ ማኅደሩ ያሳያል፡፡

አቶ ግርማ ገብረ ጻድቅና ግዛው መንጀታ የዚህን ዕውቀት ገላጭ ትምህርት ቤት ፕሮጀክት ፈታዘር ቀበሌ ላይ እንዲሆን መሠረት በመጣላቸው ይታወሳሉ፡፡ እነዚህ ሁለቱ ወንድማማቾች ከጉመር አልፈው የማኅበረሰባቸውን ችግር አንገብጋቢነት በመመልከት በጉራጌ ዞን በሁሉም ቀበሌዎች ያሳረፉት ገና በልጅነት ዕድሜያቸው ነበር፡፡ በ1970ዎቹ በኢትዮጵያ የነበረው ረሃብና የሰላም ዕጦት በአካባቢያቸው ላይም ጉዳቱን አሳርፎ ነበር፡፡ በወቅቱ ምንም እንኳ ለራሳቸው በቂ መተዳደሪያ ቢኖራቸውም ተወልደው ያደጉበትን ማኅበረሰብ ጉዳይ ግን እንቅልፍ አላስተኛቸውም፡፡

በወቅቱ ለሚመለከተው አካል አካባቢው ዕርዳታ እንዲደረግለት ቢጠይቁም፣ በሰዓቱ ዞኑ ላይ የከፋ ነገር የለም ተብሎ ምላሽ ሲሰጣቸው፣ ሌላ ዘዴ በመዘየድና ያላሰለሰ ጥረት በማድረግና ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ጋር በመነጋገር የጉራጌ ማኅበረሰብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚ እንዲሆን ከጥረት አልፎ ወደ ውጤት ተቀይሯል፡፡

በተጨማሪም የጉመር ወንጌል አማኞች ፈታዘር ቤተ ክርስቲያን ከዚሁ ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ጋር በመነጋገር ማኅበረሰቡ ሁለንተናዊ ተጠቃሚ እንዲሆን ማለትም የትምህርት፣ የጤና፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ ተደራሽነት፣ የተለያዩ ሙያዊ ሥልጠናዎች እንዲያገኙ፣ የተለያዩ ምርጥ ዘሮች እንዲሰጡ፣ በየአካባቢው በጄኔሬተር የሚሠራ ወፍጮ እንዲቋቋም፣ የተለያዩ አልሚ ምግብ እንዲከፋፈል፣ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ፣ ዩኒፎርም፣ ደብተርና እስክሪብቶ እንዲያገኙ ያደረጉት እልህ አስጨራሽ ጉዞ ፍሬ አፍርቶ ሁሌም በትውልዱ ሲዘከሩ ይኖራሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በአገር አቀፍ ደረጃ የጉራጌ ባህል በሚገልጽ ሁኔታ ኖርማልና ስፔሻል ክትፎ በኮባ ጥለስ በአሻሻት ቆጮ በማስተዋወቅ ፈር ቀዳጅ በመሆን ለሌላው ምሳሌ የሆኑ ወንድማማቾቹ፣ በተለይም ከጉራጌ አካባቢ ወደ ከተማ የሚመጡ ልጆች ተጋላጭ እንዳይሆኑ ለብዙዎች በከተማ እንዲሁም ገጠር ትልቅ ኢንቨስትመንት ላይ ከሌሎች ጋር በመሆን የሥራ ዕድልን የፈጠሩ ናቸው፡፡ ገና በልጅነታቸው በቦታ ርቀት ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠው የተሰደዱበትን ሁኔታ የእግር እሳት ስለሆነባቸው ኅብረተሰቡ የዕውቀት ብርሃን ሊፈነጥቅለት ይገባል በማለት የአዋቂዎች መሠረተ ትምህርት፣ እንዲሁም በወቅቱ አጠራር ከሀ፣ ሁ እስከ ሦስተኛ ክፍል በ1970ዎቹ መጀመሪያ በፈታዘር ትምህርት ቤት አቋቋሙ፡፡

ከአርባ ዓመት በፊት እንደተመሠረተ ታሪኩ የሚያስረዳው ይህ ትምህርት ቤት፣ እኔን ጨምሮ በርካቶቻችን ለወግ ማዕረግ አብቅቷል፡፡ በተለያዩ ደረጃዎች አንቱታን ያተረፉ ምሁራን ከዚህ ትምህርት ቤት ወጥተዋል፡፡ ከራሳቸው አልፈው አገራቸውን አገልግለዋል፣ እያገለገሉም ይገኛሉ፡፡

የመጀመሪያዎቹ መምህራን ገስግሽ ግዛው፣ መንግሥቱ ብዛ፣ ታደለ ንዳ፣ ፈቀደ ወልደ ማርያም፣ ታደሰ ደሊል፣ ዓለሙ ኃይሌ፣ ክብነሽ ኃይሌ፣ ጀማል ሙጂብ፣ አበበች ኃይለ ማርያምና ደሴ ኃይሌ ሲሆኑ፣ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች ደግሞ ረሺድ ኬራጋ፣ አሰፋ መንጀታ፣ ፈለቀች ገብረ ማርያምና ደግፌ መልስ ከፍተኛውን አበርክቶ የነበራቸው ናቸው፡፡

በ1988 ዓ.ም. መንግሥት ተረክቦት ተጨማሪ የግንብ ክፍሎች ተገንብተው በርካታ ታዋቂ ተማሪዎችን ለውጤት አብቅቷል፡፡ ከተለያዩ አካባቢ የሚመጡ ተማሪዎችንም ተቀብሎ አስተምሯል፡፡

ትምህርት የሁሉም ተግባራት መክፈቻ ቁልፍና ትውልዱ በዕውቀትና በሥነ ምግባር እንዲታነጽ ካለው ጉልህ ድርሻ አንፃር ትምህርት ቤቶች ምቹና ተማሪዎችን የሚስቡ ማድረግ ይገባል፡፡ ካደጉት አገሮች እንደምንረዳው አገሮች የዕድገታቸው ምስጢር ላይ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው፣ እንዲሁም ለአንድ አገር ዕድገትና ለውጥ ብሎም አምራች፣ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለመፍጠር ዋነኛ መሣሪያው ትምህርት ነው፡፡ ከምንጊዜም በላይ ለትምህርት ዕድገት የሁሉንም ሰው ርብርብ ይፈልጋል፡፡ እንደ አገር ሥራ ፈጣሪ፣ ብቁና ተወዳዳሪ የተማረ ዜጋ መፍጠር ያሻል፡፡

ሥራው ሰፊ በመሆኑ አሁን በአገሪቱ ውስጥ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የትምህርት ጥራት ደረጃ በሚደረገው ርብርብ ሁሉ በየደረጃው እንደ አቅሙ የድርሻው ካልተወጣ ‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው› የሚሆነው፡፡ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ከአልባሌ ቦታ ርቆ ትኩረት ሰጥቶ እንዲማር ብቁ መምህራን መመደብ፣ የትምህርት ቤቱ ግቢ አካባቢ ምቹና ሳቢ ማድረግ ይገባል፡፡

የፈታዘር ትምህርት ቤት ያሉበትን የግብዓትና የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ከተፈለገ ከሁሉ በማስቀደም ለመማር ማስተማር ምቹ የሆነ ከባቢን መፍጠር ጊዜ የሚሰጥ ጉዳይ አይደለም፡፡ በትምህርት ቤቱ ውስጥ በርካታ ችግሮች የሚስተዋሉ ሲሆን የመማሪያ ክፍሎች ምቹ ያለመሆን፣ የቤተ መጻሕፍት አለመሟላትና ያሉት መጻሕፍትም ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ጋር የማይዛመዱ መሆናቸው፣ የሳይንስና የምርምር ላቦራቶሪና መሣሪያዎች አለመኖር፣ ስለዲጅታል ቴክኖሎጂ በሚወራበት በዚህ ዘመን የአይሲቲ ክፍልና ኮምፒዩተር፣ የኢንተርኔት ዝርጋታ አለመኖር፣ የመፀዳጃ ቤት ችግር፣ ደረጃውን የጠበቀ የመምህራን ማረፍያ አለመኖር በመማር ማስተማር ሥራው ላይ ተግዳሮት ሆኗል፡፡

ትምህርት ለአንድ አገር ዕድገትና ብልፅግና የሚጫወተው ሚና አይተኬ ሲሆን፣ ዕውን ለማድረግ የትምህርት ቤት ልማት ላይ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል የሚያደርገው በአገር ላይ ያለው አስተዋጽኦ ድርሻው የላቀ ነው፡፡ ትምህርት ያላወቅነውን ነገር ለማጥበብ ይረዳናል፡፡ ለአንድ አገር ዕድገት ቁልፍ ሚና ያለው ሲሆን፣ አንድን አገር ለመግደልም ለማሳደግም ድርሻው አይተኬ ነው፡፡ ትምህርት ምክንያታዊ ትውልድ ከመፍጠር አንፃር ጉልህ አበርክቶት ያለው ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የትምህርት ተቋማት ላይ እየተስተዋለ ያለው ችግር ለዚሁ ማሳያ ነው፡፡ በትምህርት ሰዎች የተለያዩ ሐሳቦችን የሚያፈልቁበት፣ እንዲሁም የሐሳብ የበላይነት ገዥ ሆኖ የሚወጣበት ሲሆን የተለያዩ ጠቃሚ ሐሳቦችን፣ መረጃዎችንና ክህሎትን ይገበያሉ፡፡

እያንዳንዳችን ስለዕርዳታ ወይም ድጋፍ ያለን አረዳድ እንደሚለያይ ዕሙን ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ስለመስጠት ሲወራ ብዙ ገንዘብ ይኖራቸዋል ተብሎ ስለሚታሰቡ ሰዎች እነሱን ብቻ እንደሚመለከታቸው መፈረጅ የተለመደ ሲሆን፣ አንዳንዶች ደግም ራሳቸውን ከሌሎች ጋር ሲያነፃፅሩም እንመለከታለን፡፡ ነገር ግን ትክክለኛ አመለካከቶች ናቸው ብዬ አላምንም፡፡ እንደሚታወቀው በምንኖርባት ዓለም ሰዎች በብዙ ነገር ሊታወሱ እንደሚፈልጉ ሲናገሩ መስማትና ያደረጉትን ደግም ማየት የተለመደ ነው፡፡

የዕውቀት እናት የሆነችው ፈታዘር ትምህርት ቤት ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ሰዎች በምድር ላይ በብዙ ነገር መታወስ እንደሚፈልጉ ሁሉ፣ ዛሬ ሁላችንም በትምህርት ቤቱ አማካይነት በትውልዱ መካከል እንድንታወስ ስለምትፈልግ ልጆቿን አድኑልኝ እያለች እየተጣራች ትገኛለች፡፡

በአንድ ወቅት የገጠመኝን ትምህርት ሊሆን ስለሚችል ላጋራችሁ፡፡ እኔ የተወለድኩበት ሆስፒታል አዲስ አበባ ስታዲየም አጠገብ በሚገኘው የጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ስለነበር፣ መረጃ ፈለግኩና ወደ ቅጥር ግቢው ባቀናሁበት ወቅት አንድ ነገር ተመለከትኩኝ፡፡ ፊት ለፊት በዕድሜ የገፋ ሕንፃ ግድግዳው ላይ በእምነበረድ በደማቅ የተጻፈው ጽሑፍ ዓይኔ አረፈና የተጻፈውን የተለያየ አገር ዜግነት ያላቸውን ሰዎች ስም ዝርዝርና ያደረጉትን የገንዘብ አስተዋጽኦ ተጽፎ ተመለከትኩኝ፡፡ እነዚህ ደጋጎች ኢትዮጵያ የምትባል አገር ማንነቷን እንኳ በውል የማያውቁት ባደረጉት ድጋፍ ይህንን የጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል በመገንባቱ ብዙ የኢትዮጵያ እናቶች እናቴንም ጨምሮ በሰላምና በጤና ልጆቻቸውን አቅፈውበታል፡፡

እነዚህ ደጋግ ሰዎች ሰብዓዊነት ተሰምቷቸው ያደረጉት አስተዋጽኦ ምንም እንኳን ብዙ አሠርት ዓመታት ቢያልፉም እስካሁን፣ እንዲሁም በቀጣይ ትውልድ እየታወሱ ይኖራሉ፡፡

በዚሁ አጋጣሚ ትልቅ አሻራ ለማስቀመጥና በክብር መዝገብ ሁላችንም በትውልድ እንድንታወስ ከእናንተ ጋር አብረን እናሳካቸዋለን ብለን በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ይፈጸማሉ ተብሎ የተነደፉ ዕቅዶች አሥራ ሰባት ሚሊዮን ብር ይፈጃሉ፡፡

የፈታዘር ትምህርት ቤት እኔንም ጨምሮ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ያፈራ ሲሆን በንግድ፣ በግልና በመንግሥት ድርጅት ተሰማርተው ብቁ ዜጋ ሆነው በአገር ውስጥ እንዲሁም በውጭ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

ስለዚህ ይህ ሙሉ በሙሉ የመፍረስ አደጋ ያንዣበበትን ትምህርት ቤት ለመታደግ ብሎም የተማሪዎቹን የትምህርት ጉዞ እንዳይጨልም፣ እንዲሁም ትምህርት ቤቱን ከውድቀት ለመታደግ የመማሪያ ክፍሎች ምቹ ማድረግ፣ የመማርያ መጻሕፍትና ሌሎች ቁሳቁሶች ሟሟላት፣ የላይብረሪና የፈጠራ ማዕከል፣ እንዲሁም የመምህራን መኖርያ ለመገንባት የሚያስችል ዕቅዶቻችን ዕውን እንዲሆኑ የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ እንማፀናለን፡፡ ነገ አገር ተረካቢ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ለማፍራት በሚደረገው እንቅስቃሴ የድርሻችንን አንድ ጠጠር እናስቀምጥ እላለሁ፡፡ ትምህርት ቤቱን ለመደገፍ በንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በተከፈተ አካውንት 7000057223796 ይጠቀሙ።

ከአዘጋጁ:- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል።

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles