Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊመነቃቃትን ያሳየው የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ

መነቃቃትን ያሳየው የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ

ቀን:

የውጭ ጉዲፈቻ ከተቋረጠበት ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ከፍተኛ የሆነ መነቃቃት ማሳየቱ ይነገራል፡፡

ወደ ተለያዩ አገሮች በጉዲፈቻ ይሄዱ የነበሩ ሕፃናት ለማንነት ቀውስና ለተለያዩ ጉዳቶች እየተጋለጡ ነው በሚልና የሚሄዱበት መንገድም በብዙ ችግሮች የተሞላ በመሆኑ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወሳል፡፡

  የውጭ ጉዲፈቻ መቋረጡን ተከትሎ የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ መነቃቃት ማሳየቱን የሚናገሩት በአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሕፃናት መብት ደኅንነት ማስጠበቂያ ዳይሬክተር አቶ አንዱዓለም ታፈሰ ናቸው፡፡

ካለፉት ጥቂት ዓመታት ጀምሮ 1,546 ሕፃናት በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ቤተሰብ ማግኘታቸውን የተናገሩት አቶ አንዱዓለም፣ ከችግሩ ስፋት አንፃር ሥራው በጣም የሚያኮራ ነው ባይባልም፣ እየታየ ያለው ጅምር ግን በጣም ያበረታታል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ከሦስት ሺሕ በላይ ሕፃናት በተለያዩ የሕፃናት ማሳደጊያ ማዕከላት ተጠልለው ይገኛሉ ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ለእነዚህ ሕፃናት አሳዳጊ ማግኘት እንዳልተቻለ ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጉዲፈቻ ማግኘት ያልቻሉ ሕፃናት የአደራ ቤተሰብ በሚል 50 ሕፃናት ለተለያዩ አሳዳጊዎች ዘንድሮ መሰጠታቸውን ገልጸዋል፡፡

ጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት ከዚህ በበለጠ ቢሠራበትና ሁሉም ሰው ኃላፊነቱን ቢወጣ በጎዳና ላይ ያሉ፣ በችግር ውስጥ የሚገኙና በተለያዩ የማሳደጊያ ማዕከላት ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት በጉዲፈቻ ወይም በአደራ ቤተሰብ በእንክብካቤ የማደግ ዕድሉን እንደሚያገኙ አብራርተዋል፡፡

የሕፃናት ሁለንተናዊ ተሳትፎ፣ ቤተሰባዊና ማኅበረሰባዊ ጥበቃ፣ መብትና ደኅንነታቸውን  ለማስከበር በሚል በየዓመቱ ሰኔ 9 ቀን የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ሕፃናት ቀን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ለማክበር ከወዲሁ መዘጋጀቱን ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡

የሕፃናት መብት ደኅንነት ማስጠበቂያ ዳይሬክተሩ በመግለጫው ላይ የዘንድሮው የአፍሪካ ሕፃናት ቀን፣ በነገ አገር ተረካቢ ትውልድ ቀረፃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ባለው በሕፃናት ትምህርት ተሳትፎና ጥራት ላይ ማተኮሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ሕፃናት ቀን ‹‹የሕፃናትን ትምህርት፣ ተሳትፎና ጥራት ለማሳደግ ጊዜው አሁን ነው፤›› በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር የቢሮው ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ እመቤት ተስፋዬ ተናግረዋል።

‹‹ሕፃናት መብትና ደኅንነታቸው ተጠብቆ፣ ምቹ አካባቢ ተፈጥሮላቸው፣ በዕውቀትና በሥነ ምግባር የታነፁ፣ እንዲሁም ለነገ ጥሩ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል ዛሬ ብዙ ልንሠራ ይገባል፤›› ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ፣ በከተማዋ ለሚገኙ ሕፃናት መብታቸውን ከማስጠበቅና ደኅንነታቸውን ከማረጋገጥ አንፃር በርካታ ሥራዎች እየተተገበሩ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡

ሕፃናት የልደት ምዝገባ ምስክር ወረቀት የማግኘት መብታቸው እንዲረጋገጥ በተሠራ ሥራ ለ155 ሺሕ ሕፃናት የምስክር ወረቀት የተሰጣቸው ሲሆን፣ ለ477 ሺሕ ሕፃናት ደግሞ አስፈላጊ ክትባቶችን ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

  ሕፃናት ከጉልበት ብዝበዛ፣ ካለዕድሜ ጋብቻና መሰል ጥቃቶች ነፃ እንዲሆኑ ሊሠራበት ይገባል ያሉት ወ/ሮ እመቤት፣ ሕፃናት በተሻለ አያያዝና አስተዳደግ በሥነ ምግባር ታንፀው እንዲያድጉ ወላጆችና አሳዳጊዎቻቸውን ማሠልጠንና ግንዛቤ መስጠት እንዲሁም፣ ትምህርት ቤቶች ከሕፃናት ጥቃትና ከአድልኦ ድርጊት ነፃ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ሕፃናት እንደአስፈላጊነቱ የትምህርት ድጋፍ በማድረግ ማስተማር፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትክክለኛው ዕድሜ መጀመራቸውን ማረጋገጥና መሰል የመብት ማስጠበቅ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

የአፍሪካ ሕፃናት ቀን በመባል የሚታወቀው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ሕፃናት ቀን፣ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት አማካይነት በየዓመት ሰኔ 9 ቀን መከበር የጀመረው ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ የመከበሩ ምክንያትም በ1968 ዓ.ም. የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ አገዛዝን በመቃወም በሶዌቶ በተደረገ ዓመፅ የተሳተፉትንና የተገደሉትን ለማክበር እንደሆነ ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...