Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሽብርተኝነትን በገንዘብ የረዳ ወንጀለኛን አሳልፎ ለመስጠት ትብብር የሚጠየቅበት ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

ሽብርተኝነትን በገንዘብ የረዳ ወንጀለኛን አሳልፎ ለመስጠት ትብብር የሚጠየቅበት ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

ቀን:

በወንጀል የተገኘን ንብረት ሕጋዊ ማስመሰልና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን በሚመለከት፣ ወንጀለኛን አሳልፎ በመስጠት ረገድ በሌሎች አገሮች አግባብ ያላቸው ባለሥልጣኖች ጋር የሕግ ድጋፍ ትብብር ማድረግ እንደሚገባ ሚደነግግ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቷል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ እንደተገለጸው፣ ረቂቅ አዋጁ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብንና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር፣ ከዚህ ቀደም ሥራ ላይ የነበረው አዋጅ ቁጥር 780/2013 ላይ ማሻሻያዎች በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከተደረጉት ማሻሻያዎች መካከልም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረገውን ትብብር ለማጠናከር ኢ መደበኛ የትብብር ማዕቀፍ እንዲዘረጋለትና ሕጋዊ ዕውቅና እንዲያገኝ የሚያስችል መደረጉ ዋነኛው ነው፡፡ 

ፍትሕ ሚኒስቴር በበላይነት ይመራዋል በተባለው የዓለም አቀፍ ትብብር ማዕቀፍ፣ በወንጀል የተገኘን ንብረት ሕጋዊ ማስመሰልና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን የፈጸመ ግለሰብ አሳልፎ በመስጠት፣ በመመርመርና ለፍርድ በማቅረብ ረገድ ከሌሎች አገሮች ጋር ትብብር እንደሚደረግ ተደንግጓል፡፡

ከዚህ በፊት ሥራ ላይ የነበረው አዋጅ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ በርካታ ጉዳዮችን ይዞ ሲሠራበት የነበር ቢሆንም፣ ግልጽነት የጎደለውና ከሌሎች ሕጎች ጋር የማይጣጣም፣ ወቅታዊ ለሆኑ ችግሮች በቂ ምላሽ የማይሰጥ በመሆኑ የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚንስቴር ዴኤታ ወ/ሮ መሠረት ኃይሌ አብራርተዋል፡፡

በሰባት ክፍሎችና በ55 አንቀጾች የተደራጀው ረቂቅ አዋጁ፣ የወንጀል ጥፋቶችንና ቅጣቶችን፣ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን፣ ወንጀሎችን ለመለየት የሚያስችሉ ምርመራዎችን እንዲሁም ዓለም አቀፍ ትብብርን የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን ማካተቱንም ወ/ሮ መሠረት አክለዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ አሻሽሎ ካካተታቸው ድንጋጌዎች መካከል ሌላኛው የወንጀል ቅጣቶችን የሚመለከተው ክፍል ሲሆን፣ ሥራ ላይ በነበረው አዋጅ የተቀመጠው የገንዘብ ቅጣት መጠን ዝቅተኛ በመሆኑ፣ በተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ አስተማሪ ያለውን የገንዘብ ቅጣት አስቀምጧል፡፡

በዚህም በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ በማስመሰል ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ግለሰብ፣ ከዚህ ቀደም በነበረው አዋጅ ንብረቱ መወረስ እንዳለ ሆኖ፣ ከአሥር እስከ 15 ዓመታት ፅኑ እስራትና ከ100 ሺሕ ብር በማይበልጥ መቀጮ እንዲቀጣ ተደንግጎ የነበር ሲሆን፣ በተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ የገንዘብ መዋጮው ከ500 ሺሕ ብር በማይበልጥ መቀጮ እንዲቀጣ ተደርጎ ተሻሽሏል፡፡ 

የሕጎች አስፈላጊነት እንዳለ ሆኖ ተግባራዊ ሲደረጉ ግን፣ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ለማጥቃት ሲውሉ እንደነበር የአብን ተመራጭና የምክር ቤት አባሉ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)፣ ዓለም አቀፍም ሆነ አገር ውስጥ ያሉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች እነዚህ ዓይነት ሕጎችን በሥጋት እንደሚመለከቷቸው ገልጸዋል፡፡

አክለውም ‹‹ተቃዋሚዎችና መንግሥትን የሚተቹ ተቋማትም የእነዚህ ዓይነት ሕጎች ሰለባ ሆነው ጉዳት ደርሶባቸዋል፤›› ብለዋል፡፡ ስለሆነም አዋጁ የመንግሥት ተቃዋሚዎችን ለማሳደድ እንዳይውል የተደረገ ዝግጅት መኖሩን የጠየቁት ደሳለኝ (ዶ/ር) ረቂቅ አዋጁ የሚመራለት ቋሚ ከሚቴም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ላይ ጥያቄያቸውን ያቀረቡት ሌላኛው የምክር ቤት አባል አቶ አበረ አዳሙ በበኩላቸው፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት የሚለው የረቂቁ ክፍል ከፀረ ሽብር ሕጉ በምን እንደሚለይ ጠይቀው፣ በፀረ ሽብር ሕጉ ላይ የተቀመጡ ተመሳሳይ ድንጋጌዎች መኖራቸውንና ይህም ለአፈጻጸም እንደሚያስቸግር ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይም ‹‹በወንጀል የተገኘ ንብረትን በሚመለከት በረቂቅ አዋጁ ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎች በፀረ ሽብር ሕግ፣ በፋይናንስ ደኅንነት ሕግ እንዲሁም በወንጀል ሕግ የተደነገጉ አንቀጾች አሉ፡፡ እነዚህን የተበታተኑ ሕጎች ለአፈጻጸም አመቺ እንዲሆኑ ወደ አንድ ማካተቱ አይሻልም ወይ?›› በሚል ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡

ምክር ቤቱ ከአባላቱ የተነሱ አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን ጨምሮ በሁለት ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ ለዝርዝር ዕይታ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 23/2016 ሆኖ ለሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...