Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየቴክኒክና የሙያ ትምህርትና ሥልጠና የሚወስዱ ዜጎችን ማማከር የሚያስችል ሰነድ ተዘጋጀ

የቴክኒክና የሙያ ትምህርትና ሥልጠና የሚወስዱ ዜጎችን ማማከር የሚያስችል ሰነድ ተዘጋጀ

ቀን:

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው ወደ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና የሚገቡ ዜጎችን ማማከር የሚያስችል ሰነድ ተዘጋጀ፡፡ ሰነዱ ማኅበረሰቡ ለዘርፉ ያለውን አመለካከት ይቀይራል ተብሏል፡፡

በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጆች የሚገቡ ዜጎች በየደረጃው ውጤታማ እንዲሆኑ የማማከር አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሰነድ በአዲስ አበባ ደረጃ ይፋ መደረጉን፣ ሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በኢሊሌ ሆቴል በተደረገ የባለድርሻ አካላት ውይይት ላይ ተገልጿል፡፡

ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራና ክህሎት ቢሮ፣ ከተለያዩ የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ኮሌጆችና ተቋማት፣ እንዲሁም ከኢንዱስትሪዎች የተውጣጡ ከ80 በላይ ባለድርሻ አካላት መመርያው ያለውን ጠቀሜታ፣ አተገባበርና በሚተገበርበት ወቅት ስለሚኖሩ ችግሮች በስፋት ውይይት ተደርጓል፡፡

በመመርያው መሠረት ወደ ቴክኒክና ሙያ የሚገቡ ዜጎች ዝንባሌያቸው ተለይቶ ሥልጠና እንዲወስዱ በማድረግ፣ ለዚህም የማማከር አገልግሎት መስጠት ተገቢ መሆኑን በመገንዘብ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ለተግባራዊነቱ እየተሠራ መሆኑን በሚኒስቴሩ የሥልጠና ባለሙያ አቶ ይታያቸው ደሊል ገልጸዋል፡፡

ሰነዱን ያቀረቡት አቶ ዓባይነህ መኮንን፣ የተዘጋጀው ሰነድ የቴክኒክና የሙያ ተቋማት የተሻለና ውጤታማ ሥልጠና መስጠት እንዲያስችላቸው፣ ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰው ኃይል ለማፍራትና ሠልጣኞቹም አስፈላጊ ክህሎት ይዘው በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ እንደሚያግዛቸው፣ ሰነዱ የዘርፉን ተፈላጊነት በመጨመርና የሀብት ብክነትን በመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።

ሰነዱ የማማከር ሥራው በዘርፉ ልምድ ባካበቱና በሠለጠኑ ሙያተኞች የሚተገበር በመሆኑ፣ ለሠልጣኞች ከሚሰጠው ሙያዊ ዕውቀት ጎን ለጎን፣ ከኢንዱስትሪው ጋር የሚያስተሳስራቸው መሆኑንም አብራርተዋል። የማማከር አገልግሎቱን ሠልጣኞች ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት፣ ትምህርት ላይ እያሉና ትምህርታቸውን አጠናቀው ሲመረቁ ማግኘት እንዳለባቸው በሰነዱ ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት ወጣቶች ወደ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ ገብተው ሥልጠና የሚሠለጥኑበትን ሙያ ከመምረጣቸው በፊት፣ የሚፈልጉትን እንዲረዱ መረጃ እንዲያገኙ ማገዝ፣ ሥልጠና ካጠናቀቁ በኋላ ሥልጠና ማጠናቀቅና የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ይዘው መቀመጥ ሳይሆን ኢንዱስትሪው በሚፈልገው መንገድ ተወዳዳሪ ሆነው ራሳቸውን እንዲሸጡ ማድረግ የሚያስችል መመርያ መሆኑን አቶ ዓባይነህ አስረድተዋል፡፡

የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና በብዙ ተማሪዎች ዘንድ ያለው አመለካከት ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ፣ የመማር ፍላጎት ባለመኖሩ በዚህ መመርያ መሠረት ሠልጣኞቹ ምን ዓይነት ሥነ ምግባር እንደሚያስፈልጋቸው፣ ከቴክኒክና ሙያ መመረቅ ብቻ ሳይሆን በአግባቡ ሲቪ ማዘጋጀት፣ ራሱን ማበልፀግ፣ በሥነ ምግባር መታነፅና ራስን ለሥራ ዝግጁ ለማድረግ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንና በተለይም ዜጎች ለቴክኒክና ሙያ ያላቸውን አመለካከት መቀየር ያስችላል ሲሉ አቶ ዓባይነህ ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙ ተሳታፊዎችም ሠልጣኞች ሥልጠና አጠናቀው በቅጥር ወደ ሥራ በሚሰማሩበት ወቅት የሚጠብቁትና እንዲከፈላቸው የሚፈልጉት የገንዘብ መጠን ካለው ገበያ ጋር ያልተመጣጠነ መሆንና ፍላጎታቸው እጅግ የተጋነነ መሆን፣ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ላይ ያለው ዝቅተኛ አመለካከት፣ ኢንዱስትሪዎች በትብብር ሥልጠና ወቅት ሥልጠናውን እንዲወስዱ ከማበረታታት ይልቅ ከማይመለከታቸው ሙያ ላይ እንዲውሉ ማድረግ፣ ቴክኖሎጂን ማለማመድ እንደ ሥራ መፍታት መቁጠር፣ ሚዲያው ስለቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ግንዛቤ መፍጠሪያ የአየር ሰዓት አለመኖር፣ የአሠልጣኞች በቂ ልምድ አለመኖርና ሙሉ ጊዜያቸውን በትክክል በመጠቀም ሥልጠና አለመስጠት፣ እንዲሁም ሠልጣኞች በሚመረቁበት ሙያ በቂ የቴክኒክ ልምድ አለማዳበር በዘርፉ ከሚታዩ ችግሮች መካከል ናቸው ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ ማኅበረሰቡ ስለቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ጥሩ አመለካከት እንዲኖረው ለማስቻል፣ 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን የሚጨርሱ ዜጎች ወደ ቴክኒክና ሙያ እንዲገቡ፣ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ገብተው ኢንዱስትሪው በሚፈልገው ሙያ እንዲሠለጥኑ፣ ሥልጠና አጠናቀው በሚሰማሩበት የሥራ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ ይህ የምክር አገልግሎት መስጫ ሰነድ መዘጋጀቱ አስፈላጊ መሆኑ ተወስቷል፡፡

‹‹ኢንዱስትሪው ሥልጠናውን በትብብር ለማገዝ እንዲያስችለውና በሚፈለገው ሙያ የሠለጠነ የሰው ኃይል በቀላሉ ከተቋማት ለማግኘት በመሆኑ፣ ሁላችንም ይህንን ሰነድ ተግባራዊ ማድረግ ይገባናል፤›› ሲሉ የውጤት ተኮር ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ነጋ አራጋው አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...