Wednesday, July 24, 2024

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር ጠቃሚ እስከሆኑ ድረስ በበርካታ መስኮች ከተለያዩ አገሮች ልምዶችን መቅሰም ተገቢ ነው፡፡ የሚገኙት ልምዶች ለአገር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ፋይዳ እስካላቸው ድረስ መልካም አቀባበል ሊደረግላቸውም ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ ማንኛውም ዜጋ ለአገሩ የሚጠቅሙ ልምዶችን ማቋደስም ይጠበቅበታል፡፡ በተለይ በተለያዩ አገሮች ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ብዙ ይጠበቃል፡፡ ለአገር ከሚያስገኙት የውጭ ምንዛሪ በተጨማሪ በዕውቀት ሽግግርና በቴክኖሎጂ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረግ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ልምዶች በየአቅጣጫው ሲገኙ ለአገር የሚኖራቸው አበርክቶ ከሚታሰበው በላይ ነው፡፡ ልምዶቹ ሲመጡ ግን ከአገራዊ እሴቶችና መስተጋብሮች ጋር እንዲጣጣሙ በጥናት መደገፍ ይኖርባቸዋል፡፡

የመንግሥት ባለሥልጣናቱ ውይይት በአብዛኛው ያተኮረው፣ በተለያዩ መስኮችና ዘርፎች የተቀሰሙ ልምዶችን እንዴት ወደ መሬት ማውረድ እንደሚቻል ግንዛቤ ለመስጠት ነው፡፡ በውይይቱ ወቅት የተነሱ በርካታ ሐሳቦች ሲሆኑ መነሻ ያደረጉት ከሲንጋፖር ምን ይቀሰም ነው፡፡ ከሲንጋፖር ምን ይቀሰም ሲባል ኢትዮጵያ ከዚያች አገር ጋር የሚያመሳስላትንና የሚለያያትን ከማጤን ይጀመራል፡፡ ሲንጋፖር በደቡብ እስያ ትልቅ ወደብና ስምንት መቶ ዓመት ያስቆጠረች አገርም ከተማም ስትሆን፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ዕድሜ ባለፀጋ ናት፡፡ ሲንጋፖር ለበርካታ አገሮች ሞዴል ለመሆን የሚያስችላት ሥልጣኔ ያላት ለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡ በዓለም አሉ ከሚባሉ ምርጥ ወደቦችም አንደኛዋ ናት፡፡ ከአጠቃላይ ነዋሪዎቿ 29 በመቶ ያህሉ ከተለያዩ አገሮች የተሰባሰቡባት፣ ለኑሮና ለሥራም ምቹ ማዕከል ናት፡፡ የተረጋጋ የፖለቲካ ከባቢ፣ ዝቅተኛ የወንጀል ምጣኔና ሙስና፣ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርትና የአየር ንብረት እንዳላት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ጠንካራ አገረ መንግሥት ያላትና በአንድ ወቅት ከአራቱ የእስያ ነብሮች ከሚባሉት አገሮች አንዷ የነበረችው ውቧ ሲንጋፖር፣ አሁን ያለችበት ደረጃ ለመድረስ በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፋለች፡፡ የሲንጋፖር ልምድ በዘመናዊ ሕንፃዎች፣ በጎዳናዎች፣ በሰው ሠራሽ ሐይቆች፣ በመኖሪያ ቤት አቅርቦት፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በትራንስፖርት ሲስተምና በመሳሰሉት ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ አገሮች የመጡ የውጭ ዜጎችን በማካተት እንዴት አብሮ እንደተኖረ ጭምር መሆን ይገባዋል፡፡ በአንድ ወቅት በእንግዳ ተቀባይነት ስሟ በስፋት ይነሳ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ አሁን ከገባችበት የእርስ በርስ መገፋፋት አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ወጥታ፣ እንኳንስ ለዜጎች ለውጮችም ጭምር አስተማማኝ መኖሪያ እንድትሆን የሚያስችል ምኅዳር ያስፈልጋል፡፡ ልምዱ ከተማ ማሳመርና ማስዋብ ላይ ብቻ አተኩሮ ሌላው ከተረሳ ፋይዳው እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም፡፡ በእኩልነትና በፍትሐዊነት ሊያኖር የሚያስችለው መሠረታዊ ጉዳይ ፈፅሞ አይዘንጋ፡፡

በሌላ በኩል ከባለሥልጣናቱ ውይይት በተደጋጋሚ ሲጠቀስ የነበረው ዜጎች ለአገራቸው ማደግ ሲሉ ይዞታቸውን ማበርከታቸው ነው፡፡ በኢትዮጵያም ለልማት የሚፈለግ ይዞታ ሲኖር ዜጎችን ማስነሳት ልምድ ከሆነ ቆይቷል፡፡ ማንም ዜጋ አገሩ ስታድግና ስትመነደግ የማየት ከፍተኛ ጉጉት ስላለው፣ ለልማት ተነስ ሲባል ያቅማማበት ጊዜ ታይቶ አይታወቅም፡፡ ለልማት የሚነሳ ዜጋ መኖሪያና መሥሪያ ቦታ ማግኘት ስላለበት፣ ከሞላ ጎደል ይኸው እየተደረገ ሰዎች ይዞታቸውን ለቀው አስረክበዋል፡፡ ወደፊትም ይህ አሠራር እንደሚቀጥል ታሳቢ ተደርጎ ዜጎች ተራቸውን እየጠበቁ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ‹‹መረር ያለ ውሳኔ ላይ ተደርሶ›› የሚል አገላለጽ ሲኖር በቂ ማብራሪያ ቢሰጥበት መልካም ነው፡፡ ሌላ ቦታ የተወሰደ ‹‹መራር ዕርምጃ›› እዚህ ሲደገም ውጤቱ ከበድ ሊል ስለሚችል ጥንቃቄ ቢደረግ መልካም ነው፡፡ ዜጎች ፈቃደኛ የሚሆኑትም በዚህ መንገድ ነው፡፡

ልምድ ሲቀሰም በአንድ ጉብኝት በተደረገ ምልከታ ላይ መወሰን የለበትም፡፡ ልምድ የቀሰሙ ወገኖች ሐሳባቸውን አደራጅተው አቅርበው ባለሙያዎች ሲመክሩበት፣ ከዚያም ተጨማሪ የጉብኝት ልውውጦች እየተደረጉ በደረጁ ጥናቶች ሲታገዝ ውጤቱ ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ መንግሥት አንድን ልምድ እንደ ወረደ ተቀብሎ ተግባራዊ አደርጋለሁ ሲል፣ በንድፈ ሐሳብና በተግባር መካከል ከፍተኛ ተቃርኖ ሊፈጠር ስለሚችል ጥድፊያ ገታ መደረግ አለበት፡፡ ልምድ ከአፍሪካም፣ ከመካከለኛው ምሥራቅም፣ ከአውሮፓም፣ ከእስያም ሆነ ከአሜሪካ በስፋት ይገኛል፡፡ ዋናው ቁምነገር ግን ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ፣ ከሕዝቡ ባህሎች፣ እምነቶች፣ እሴቶችና መስተጋብሮች ጋር መጣጣሙ ነው፡፡ ባለሥልጣናቱ ያደረጉት የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት እንደ አለቀለት ጉዳይ ታይቶ ወደ ተግባር ከመግባት በፊት፣ ቢያንስ በየመስኩ ዕውቀቱና ልምዱ ካላቸው ባለሙያዎች ጋር በግልጽ ቢመከርበት የተሻለ ውጤት ይገኛል፡፡

ከሲንጋፖር ጉዞ የተገኘው ልምድም ሆነ ሌሎች ጠቃሚ ተብለው የሚታሰቡ ጉዳዮች ውጤታማ መሆን የሚችሉት በጥናት ሲደገፉ ነው፡፡ ጥናት የበርካታ ባለሙያዎች ተሳትፎ ውጤት ስለሆነ፣ ልምዶችም ሆኑ ሌሎች ተሞክሮዎች በዚህ መንገድ ቢቃኙ ይጠቅማሉ፡፡ በግንዛቤ ማስጨበጫው ወቅት የተነሱ ጉዳዮች እንደ ወረደ መሬት ላይ ይዋሉ መባል እንደሌለበት ሁሉ፣ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አብረው ሊሄዱ የሚችሉ አስፈላጊ ነገሮች እንዲታዩ ማድረግም ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የተለያዩ ሕጎች ሲረቀቁ ከበርካታ አገሮች ልምዶች መቀሰማቸው ቢነገርም፣ በሥራ ላይ ቆይተው የተሻሩ አብዛኞቹ ሕጎች በአገር ላይ ያደረሱት ችግር አይዘነጋም፡፡ አንዳንዶቹ ሕጎች የአገሪቱንና የአጠቃላይ ሕዝቡን ታሪካዊ ዳራዎች ባለማጤናቸው፣ ካልተራገፈ አቧራቸው ጋር የብዙዎችን ሕይወት ፈትነዋል፡፡ ብዙዎችንም ለሥቃይ ዳርገዋል፡፡ ለዚህም ነው ጥናት ማድረግ የሚያስፈልገው፡፡ ባለሥልጣናቱ ከሲንጋፖር የቀሰሙት ልምድም በጥናት ይታገዝ!      

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...

የአገሪቱን የፖለቲካ ዕብደት ለማርገብ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ሚና ምን ይሁን?

በያሲን ባህሩ   የኦሮሚያ ብልፅግና      በአገር ደረጃ የብሔር ፖለቲካ በሥራ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከእንቆቅልሽ ጨዋታ ውስጥ ውጡ!

በወርኃ ሚያዝያ ተካሂዶ የነበረው ውይይት ቀጣይ ነው የተባለው መድረክ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንደገና ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. አገናኝቶ ነበር፡፡ መንግሥትን የሚመራው...

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...