Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ የጣለውን ዕግድ ቢያነሳም ንግድ ባንክ አላነሳም በማለቱ ተከሰሰ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ብሔራዊ ባንክ አሳልፎት የነበረውን መመርያ መነሻ በማድረግ የአንድ ግለሰብን የባንክ ሒሳብ አግደው የቆዩ አምስት የንግድ ባንኮች በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተላልፎ የነበረውን ዕግድ ሲያነሱ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሳያነሳ በመቅረቱ ክስ ቀረበበት፡፡

ክሱ የተመሠረተው አቶ ገብሩ አሰፋ ሐጎስ በተባሉ ግለሰብ ሲሆን፣ የክሱ ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥር 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ (3)ን በመጥቀስ፣ በቁጥር የተጠቀሱ ግለሰቦች የባንክ አገልግሎት ደንበኝነታቸው እንዲያቋረጥ፣ ለሁሉም ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ባንኮች ትዕዛዝ ከማስተላለፉ ጋር በተያያዘ መሆኑን የክስ አቤቱታው ያስረዳል።

ሪፖርተር የተመለከተው በብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰሎሞን ደስታ ጥር 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ባንኮች ደንበኝነት እንዲያቋርጡ ትዕዛዝ የተላለፈባቸውን 65 ሰዎች ስም ዝርዝር የያዘ ሲሆን፣ የከሳሽን ስምም በመጥቀስ በሕገወጥ የውጭ አገር የገንዘብ ዝውውር ተሰማርተዋል በሚል መጠርጠራቸውን፣ እንዲሁም ከሕግ ውጪ አንቀሳቅሰዋል ተብለው የተጠረጠሩበት የገንዘብ መጠን 35,646,314 ዶላር እንደሆነ ይገልጻል።

ሰኔ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ብሔራዊ ባንክ ለፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የጻፈው ሌላ ደብዳቤ ደግሞ፣ አቶ ገብሩ ግንቦት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ለብሔራዊ ባንክ በጻፉትና በጠበቃቸው በኩል ተፈርሞ በቀረበለት ደብዳቤ፣ ብሔራዊ ባንክ የሰጠውን ትዕዛዝ ተከትሎ የባንክ ሒሳብ እንዳይጠቀሙ መደረጋቸውን በመግለጽ፣ ትዕዛዙ የሕግ መሠረት የሌለው በመሆኑ፣ በሰባት ቀናት ውስጥ እንዲነሳላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን፣ ይህ ካልሆነ ግን መብታቸውን በሕግ ለማስከበር እንደሚገደዱና ለዚህም ወጪያቸውን ለማስከፈል በባንኩ ላይ ክስ እንደሚመሠርቱ ማስጠንቀቃቸውን ያብራራል።

ደብዳቤው አክሎም ግንቦት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ለፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በተጻፈ ደብዳቤ፣ ከዚህ ቀደም ግለሰቡን በተመለከተ በተቋሙ በኩል የመነጨውን መረጃ መሠረት በማድረግ፣ ለሁሉም ባንኮች ትዕዛዝ መስጠቱን በማስታወስ፣ የግለሰቡ የወንጀል ተሳትፎን በሚመለከት የተደረገ ምርመራ ስለመኖሩ ወይም አለመኖሩ፣ እንዲሁም የግለሰቡ ስም ከዕግድ ትዕዛዙ የሚወጣበት ሁኔታ ስለመኖሩ ወይም አለመኖሩ ምላሽ እንዲሰጠው ባንኩ ጥያቄ ማቅረቡን ይገልጻል።

ግንቦት 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ለብሔራዊ ባንክ በተሰጠ ምላሽ ‹‹አቶ ገብሩ በሕገወጥ የውጭ አገር የገንዘብ ዝውውር ተሰማርተዋል›› በሚል ጥቆማ የቀረበባቸው በመሆኑ በተደረገ ማጣራት ግለሰቡ 110,442,007.99 ብር ስለማንቀሳቀሳቸውና በወንጀል ድርጊት ስለመሰማራታቸው አመላካች መረጃ በመገኘቱ፣ ፍተሻና ትንተና ተሠርቶበት ለተጨማሪ ምርመራ ወደ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ መላኩን አገልግሎቱ መጥቀሱንም ያብራራል።

የከሳሽ ጠበቃ አቶ ተስፋለም በርሔ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከሳሽ ብሔራዊ ባንክና ከአምስቱ የንግድ ባንኮች ጋር የባንክ ሒሳቦቻቸውን የማንቀሳቀስ መብታቸው እንዲከበርላቸው ቢያመለክቱም ምላሽ በማጣታቸው ጉዳያቸውን ወደ ፍርድ ቤት ወስደዋል።

በብሔራዋ ባንክና በአምስቱ የንግድ ባንኮች ላይ የተመሠረተው ክስ እንደሚያስረዳው፣ ‹‹ብሔራዊ ባንክ ትልልቅ የገንዘብ ፖሊሲዎችን የሚያወጣ፣ አጠቃላይ የፋይናንስ ተቋማትን የሚቆጣጠር እንጂ አንድ ግለሰብ ባንክ እንዳይጠቀም ወይም የባንክ አገልግሎት እንዳያገኝ ማገድ በሕግ የተሰጠው ሥልጣን አይደለም። ነገር ግን በሌለው ሥልጣን የባንክ ሒሳቦቼ ላይ ሁከት በመፍጠር የባንክ አገልግሎት እንዳላገኝ ትዕዛዝ በማስተላለፍ የዜግነት መብቴ እንዲነፈግ አድርጎኛል፤›› በማለት ክስ መሥርተዋል።

ከሳሽ ያቀረቡት የክስ ሰነድ እንደሚያትተው ብሔራዊ ባንክ ለይግባኝ ባይ መፍትሔ እንዲሰጥ በተደጋጋሚ የተጠየቀ ቢሆንም፣ የደብዳቤውን ሕጋዊነት ራሱ መዝኖ መፍትሔ መስጠት ሲገባው፣ ዛሬ ነገ እያለ ለወራት ካንከራተታቸው በኋላ ሰኔ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ለፋይናንስ ደኅንነትና ሌሎች የፍትሕ ተቋማት ደብዳቤ በመጻፍ፣ ‹‹የከሳሽ የባንክ ሒሳብ እንዲታገድ ያስተላለፍኩት ዕግድ ሕጋዊ ምክንያት ካለው እንድታረጋግጡልኝ ካልሆነ ግን ከሰባት ቀናት በኋላ ዕግዱን አነሳዋለሁ›› ያለ ሲሆን፣ ከሳሽ ምንም ዓይነት በወንጀል የሚያስጠረጥር ነገር ስለሌላቸው ከተቋማቱ የተሰጠ ምላሽ ባይኖርም ሕገወጥ ደብዳቤውን ሊያነሳው አለመቻሉን ክሱ ያስረዳል።

በብሔራዊ ባንክ ከተላለፈው ትዕዛዝ ባሻገር ሙሉ ስማቸው፣ የተጠረጠሩበት ወንጀልና የገንዘብ መጠን ተጠቅሶ ሲገለጽ፣ በደብዳቤው የተገለጸው የገንዘብ መጠንም በብዙ ዓመታት በባንክ ሒሳባቸው ወጪና ገቢ ያደረጉትን ሁሉ ደምሮ ያስቀመጠው ድምር እንጂ፣ የተጠቀሰው ገንዘብም ሆነ ሀብት እንደሌላቸው ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ገልጸዋል።

ከብሔራዊ ባንክ ባሻገር በተከሳሾቹ ንግድ ባንኮች ማለትም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በአዋሽ ባንክ፣ በዓባይ ባንክ፣ በአቢሲኒያ ባንክና በቡና ባንክ የቀረበው ክስ ደግሞ በከሳሽ አቶ ገብሩ የባንክ ሒሳቦች ውስጥ የሚገኝ ገንዘብ ለማውጣትም ሆነ ገንዘብ ለማስገባት የሚከለክል፣ ከሚመለከተው አካል ምንም ዓይነት ሕጋዊነት ያለው ዕግድ ሳይተላለፍ፣ ገንዘባቸውን ለማውጣት የማይከለክል መሆኑ ግልጽ ሆኖ ሳለ፣ ከጥር 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ገንዘብ ለማውጣት ተከልክለው እንደሚገኙ ማብራራታቸውን ሪፖርተር የተመለከተው ሰነድ ያሳያል።

የተዘረዘሩትን ፍሬ ነገሮች ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 16ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ያቀረቡት ከሳሽ፣ በችሎቱ የካቲት 4 ቀን 2016 ዓ.ም. የተሰጣቸውን ብይን የሚገልጸው ሰነድ እንደሚያሳየው፣ ፍርድ ቤቱ ብሔራዊ ባንክ ጥር 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የጻፈውን ደብዳቤ ያነሳ መሆኑን የሚገልጽ ደብዳቤ በመጻፍ፣ በባንክ ሒሳቦቹ ላይ የተፈጠረ ሁከት እንዲቆም ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ተከሳሾቹ የንግድ ባንኮች በየቅርንጫፎቻቸው የተከፈቱ የባንክ ሒሳቦቻቸውን እንዳይጠቀሙና ገንዘባቸውን እንዳያወጡ በማድረግ የፈጠሩትን ሁከት እንዲያቆሙ ትዕዛዝ እንዲሰጥ፣ እንዲሁም ከሳሽ በተከሳሾች ድርጊት ምክንያት ክስ ለማቅረብ ስለተገደዱ የጠበቃ አበል፣ የዳኝነት ክፍያና ሌሎች ወጪና ኪሳራ እንዲተኩላቸው እንዲወሰንላቸውም ለችሎቱ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ተከሳሾች ክሱ ከደረሳቸው በኋላ፣ ብሔራዊ ባንክ ሐምሌ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው ምላሽ፣ ‹‹ግለሰቡ ከባንክ ገንዘቡን እንዳያወጣ አልከለከልኩም፣ የባንክ ደንበኝነት አገልግሎት እንዲቋረጥ ብቻ ነው ያዘዝኩት፣ ስለዚህ ተከሳሾች ለከሳሽ ገንዘባቸውን በመክፈል ደንበኝነት ማቋረጥ ይችሉ ነበር›› በማለት መልስ መስጠቱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና አዋሽ ባንክ መስከረም 11 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ እንዲሁም ዓባይ ባንክና ቡና ባንክ ደግሞ ጥቅምት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. መቃወሚያን ጨምሮ የፍሬ ነገር ክርክሮችንም በማቅረብ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ከሳሽ ገንዘባቸውን እንዳያወጡ አልከለከልኩም የሚል መልስ ስለሰጠ፣ ወደ ክርክር ሳይገባ ከተከሳሽነት እንዲወጣ መደረጉንም ጠበቃቸው አቶ ተስፋለም ለሪፖርተር ገልጸዋል።

አዋሽ፣ ዓባይ፣ አቢሲኒያና ቡና ባንኮችም ‹‹ለይግባኝ ባይ ገንዘባቸውን ለመክፈል ፈቃደኞች ነን›› በማለት ለከሳሽ ገንዘባቸውን ወጪ አድርገው ስለከፈሉ ከክርክሩ እንዲወጡ መደረጉን አክለዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኅዳር 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 43 መሠረት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በመዝገቡ ውስጥ ጣልቃ ገብቶ እንዲከራከር በቃለ መሃላ የተደገፈ አቤቱታ አቅርቧል።

በአቤቱታውም የከሳሽ አቶ ገብሩ የክስ መዝገብ ሲከፈት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አንደኛ ተከሳሽ የነበረ መሆኑን በመጥቀስ፣ ነገር ግን ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በዋለው ችሎት፣ ከሳሽ አንደኛ ተከሳሽ ከክርክሩ እንዲወጣ ጠይቀው ፍርድ ቤቱ በዕለቱ በዋለው ችሎት ከመዝገቡ እንዲወጣ ማድረጉን አስታውሷል።

ከሳሽ ብሔራዊ ባንክ ከመዝገቡ ይውጣ የሚሉበት ምክንያት ግልጽ ካለመሆኑም ባሻገር፣ ብሔራዊ ባንክ ጥር 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት፣ የከሳሽን ስም ከሌሎች ግለሰቦች ስም ጋር በመግለጽ ከንግድ ባንክ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲያቋርጥ ግልጽ ትዕዛዝ የሰጠ በመሆኑና ክሱም የቀረበበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሰጠው ትዕዛዝ አማካይነት ስለሆነ ብሔራዊ ባንክ በዚህ መዝገብ ገብቶ እንዲከራከር አቤቱታ ማቅረቡን ሪፖርተር የተመለከተው ሰነድ ያስረዳል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በከሳሽ አቶ ገብሩ ለተመሠረተበት ክስ ያቀረበው መቃወሚያ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 592/2000 እና የማቋቋሚያ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1159/14 እንዲሁም የባንክ ሥራ አዋጅ 592/2000 መሠረት፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ በአገራችን ውስጥ ያሉ ባንኮችን በሙሉ ይቆጣጠራል፣ መመርያ ያወጣል፣ እንዲሁም ትዕዛዝ ይሰጣል ስለማለቱም አስታውሷል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ጥር 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ለባንኮች በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ‹‹ከከሳሽ ሒሳብ ጋር ያለን የንግድ ግንኙነት እንድናቋርጥ በሰጠው ጥብቅ ትዕዛዝ መሠረት ከመፈጸም ውጪ፣ የከሳሽን መብት ከሕግና ከአሠራር ውጪ ተላልፈን የፈጠርነው ምንም ዓይነት ሁከት የለም›› በማለትም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መቃወሚያውን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተላለፈው መብት ወይም በከሳሽ ይዞታ ላይ የፈጠረው ሁከት በሌለበት ሁኔታ የቀረበበት ክስ በነገሩ የማያገባው በመሆኑ፣ በቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ መሠረት በነፃ እንዲሰናበት ጠይቋል።

ንግድ ባንክ ሌላው ያቀረበው መከራከሪያ ደግሞ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 1149(2) ድንጋጌ መሠረት ‹‹ሁከት ይወገድልኝ›› በሚል የቀረበውን አቤቱታ በሚመለከት ሲሆን፣ አቤቱታ የሚቀርበው በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሆነ እንደሚደነግግ አስረድቷል፡፡ ከሳሽ ገንዘበቸው ከጥር 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የታገደበት ቀን ጀምሮ ክስ እስከቀረበበት ድረስ ሲታይ ከሁለት ዓመት በላይ ስለሆነው፣ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 244(2(ሠ) መሠረት በይርጋ የሚታገድ በመሆኑ፣ ባቀረበው መቃወሚያም መሠረት በክሱ ምክንያት ያወጣውን ወጪ ከሳሽ እንዲከፍሉ ታዞለት በነፃ እንዲሰናበት ጠይቋል።

በክስ መስማት ወቅት ከሳሽ ለመቃወሚያዎቹ በሰጡት ምላሽ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ገንዘቡን እንዲከፍላቸው የጠየቁት ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ታኅሳስ 2015 ዓ.ም. በመሆኑ፣ ገና ዓመት አልሞላውም ብለዋል። እንዲሁም ሁከቱ እስካሁን የቀጠለ ስለሆነ የይርጋ ጊዜው አላለፈበትም በማለት ተከራክረዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ ከሳሽ ትግራይ ክልል ስለነበሩና የቀረበ ማስረጃ ባለመኖሩ፣ እንዲሁም ታኅሳስ 2015 ዓ.ም. ክፍያ ስለመጠየቃቸው ያቀረቡት ማስረጃ ስለሌለ፣ ለባንኩ ደብዳቤ ከተጻፈበት ቀን ጀምሮ ሲታሰብ ክሱ በይርጋ ቀሪ የሚሆን ነው በማለት ተከራክሯል።

ፍርድ ቤቱ የቀረቡትን መቃወሚያዎች መርምሮ ከይርጋ ጋር ተያይዞ የተነሳውን መቃወሚያ ዕልባት ለመስጠት ምስክር መስማት አስፈላጊ በመሆኑ፣ ከሳሽ ምስክሮቻቸውን አቅርበው እንዲያሰሙ አድርጓል።

መዝገቡ ሲመረመር ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍርድ ቤቱ የሥረ ነገር ሥልጣን ጋር በተያያዘ ያቀረበው መቃወሚያ ባይኖርም፣ የሥረ ነገር ሥልጣን ጥያቄ በየትኛውም የክርክር ደረጃ በፍርድ ቤቱ በራሱም ቢሆን ሊነሳ የሚችል ጉዳይ በመሆኑ፣ በፍርድ ቤት ሥነ ሥርዓት ሕግና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በበርካታ መዝገቦች በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የተረጋገጠ ስለሆነ፣ የቀረበው ክስ በዚህ ፍርድ ቤት ሊታይ የሚገባው ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ሊመረመር የሚገባው ይሆናል የሚል ውሳኔ ላይ መድረሱ ተገልጿል።

ፍርድ ቤቱ ተገቢውን ምርመራ ካደረገ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ፣ ከሳሽ አቶ ገብሩ አሰፋ ያቀረቡት ክስ በብሔራዊ ባንክ የተሰጠን አስተዳደራዊ ውሳኔ መሠረት ያደረገ በመሆኑ፣ በአዋጅ 1183/2012 መሠረት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍትሐ ብሔር ችሎት ጉዳዩን በቀጥታ ተቀብሎ ለማየት የሥረ ነገር ሥልጣን የለውም በማለት ክሱን ውድቅ አድርጎታል።

ከሳሽ ባቀረቡት ክስ ሥረ ነገር ሥልጣን ምክንያት የተዘጋ ስለሆነ በፍርድ ቤት ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 245/4 መሠረት ለዳኝነት ከከፈሉት ገንዘብ ተገቢው ተቀንሶ ቀሪው ተመላሽ እንዲደረግ፣ የይግባኝ መብት እንዲጠበቅ ትዕዛዝ በማስተላለፍ መዝገቡን ዘግቶ ተመላሽ አድርጓል።

የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን ብይን ተከትሎ ከሳሽ የተሰጠውን ብይን በመቃወም ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ፍትሐ ብሔር ችሎት የይግባኝ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

ከሳሽ ያቀረቡት ይግባኝ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ብሔራዊ ባንክ ‹‹ከሳሽ ገንዘባቸውን እንዲያወጡ አልከለከልኩም፣ የጻፍኩት ደብዳቤም ደንበኝነትን በተመለከተ እንጂ ገንዘባቸውን እንዲያወጡ አይከለክልም›› ብሎ ለፍርድ ቤት መልስ ሰጥቶ እያለ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስካሁን የከሳሽን ገንዘብ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለም ሲል ይገልጻል።

የሥር ፍርድ ቤትም ጉዳዩን ከሐምሌ 11 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ብይን እስከተሰጠበት ድረስ ሲያከራክረን ከቆየ በኋላ፣ በመጨረሻ በአስተዳደር የሚታይ ስለሆነ የሥረ ነገር ሥልጣን የለኝም በማለት መዝገቡን እንደዘጋው በመጥቀስ፣ ፈጽሟቸዋል ያሏቸውን ሁለት ስህተቶች አቅርበዋል።

የሥር ፍርድ ቤት ሥልጣን የለኝም ለማለት የጠቀሰው አዋጅ ቁጥር 1183/2012 የተፈጻሚነት ወሰኑ በአስተዳደር ተቋማት ብቻ መሆኑን የአዋጁ አንቀጽ 3 በግልጽ ይደነግጋል ብሏል።

ከዚህ ጋር አያይዞም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ሌሎች በሥር ፍርድ ቤት ተከሳሽ የነበሩ ባንኮች ደግሞ፣ የግል ወይም የንግድ ድርጅቶች እንጂ የአስተዳደር አካላት አይደሉምና በአዋጁም የሚሸፈኑ አይደሉም፡፡ የሥር ፍርድ ቤት ግን ‹‹ብሔራዊ ባንክ ያሳገድኩት ገንዘብ የለም›› እያለ ይግባኝ ባይም ‹‹ከብሔራዊ ባንክ ጋር ክርክር የለኝም›› እያሉ፣ በአስተዳደር ጨርስ ማለቱ ስህተት ነው፣ መልስ ሰጪ በራሱ ፍላጎት የከሳሽን ገንዘብ ከለከለ እንጂ፣ ብሔራዊ ባንክ የግለሰቡ ገንዘብ እንዳይሰጥ የጻፈው ደብዳቤ የለም፣ የግል ባንኮችን በተመለከተ ደግሞ የሥር ፍርድ ቤት በጠቀሰው አዋጅ መሠረት በቅሬታና ይግባኝ የሚስተናገድ አይደለም ብለዋል።

በሁለተኝነት የሥር ፍርድ ቤት ስህተት ነው በሚል በይግባኝ አቤቱታው ላይ የቀረበው ማብራሪያ ደግሞ፣ ከሳሽ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውጪ ለሥር ፍርድ ቤት በቀረበው ክስ ላይ ተካትተው የነበሩ የግል ባንኮች ገንዘባቸውን ስለለቀቁላቸው ከክስ እንዲወጡ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግን ገንዘባቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኑን ይጠቅሳል።

በዚህ የይግባኝ ክፍል ብሔራዊ ባንክ ገንዘብ እንዳይወጣ የሰጠሁት መመርያ የለም እያለ፣ የጻፈው ደብዳቤም ስለገንዘብ መከልከል የሚጠቅስ ነገር በሌለበት መልስ ሰጪ በራሱ ተነሳሽነት የግለሰቡን ገንዘብ መከልከሉ ቅንነት የጎደለውና አግባብነት የሌለው መሆኑ ግልጽ ነው በማለት፣ የሥር ፍርድ ቤት ለመልስ ሰጪ የማይመለከት አዋጅ ጠቅሶ መከልከሉ ስህተት ስለሆነ፣ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔን በመሻር፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁከት በማቆም የከሳሽን ገንዘብ እንዲለቅ ውሳኔ እንዲሰጥ አቤቱታቸውን ማቅረባቸውን ሪፖርተር ለፍርድ ቤቱ ከቀረበው ሰነድ ማረጋገጥ ችሏል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች