Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን የምግብ ጨው ማምረት ተጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ባሌ ዞን ከአዲስ አበባ 783 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ዳዌ ሠረር ወረዳ፣ ጎላኩርማ ቀበሌ የምግብ ጨው እየተመረተ መሆኑ ታወቀ።

የምሥራቅ ባሌ ዞን የንግድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሚን አልዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በባህላዊ መንገድ የሚመረተው ጨው፣ የተለያዩ የጥራት ጥናቶች ከተደረጉና አዋጭነት ያለው ምርት መሆን ከተረጋገጠ በኋላ እየተመረተ ነው።

‹‹ለወደፊቱ መንግሥት የተሻሉ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎችን አመቻችቶ ማሳደግ እንደሚቻል ታምኖበት ነው የተጀመረው›› ያሉት ኃላፊው፣ የጨው ምርት የሚገኝበት ሥፍራ፣ በባለሙያዎች ተጠንቶ ምርት መጀመር እንደሚቻል የተረጋገጠውና ወደ ሥራ የተገባው ከሁለት ዓመት በመስከረም ወር 2014 ዓ.ም. እንደሆነ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ጨው የማምረት ሥራውን እያከናወነ የሚገኘው አንድ ማኅበር መሆኑን፣ በሥሩም አንድ መቶ አባላት እንዳሉት ታውቋል። ማኅበሩ ከመስከረም 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በዓመት 200 ሺሕ ኩንታል የምግብ ጨው እያመረተ እንደሚገኝም ተገልጿል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ከወጪ ቀሪ ሁለት ሚሊዮን ብር ማግኘት የቻለው ማኅበሩ፣ ከጤና ሚኒስቴር ፈቃድና አዮዲን በመውሰድ የሚያመርተውን ጨው የሚያወጣው በባህላዊ መንገድ መሆኑን አቶ አሚን ተናግረዋል።

ጨው እየወጣ ያለው መሬቱን ወደ ታች በመቆፈር በጉድጓድ ውስጥ ጨዋማው ውኃ እንዲከማች በማድረግ፣ ከጉድጓዱ አጠገብ ሌላ አነስተኛ ጉድጓድ በመቆፈር ጨዋማው ውኃ ተገልብጦ እንዲረጋ በማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ጤናማነቱ በባለሙያዎች ተፈትሾ ተረጋግጧል ሲሉ ኃላፊው አስረድተዋል።

አምራቾቹ ጨው ከረጋ በኋላ ከጉድጓድ አውጥተው ፀሐይ ላይ በማስጣትና እንዲደርቅ በማድረግ አዮዲን ጨምረው ለጥቅም እንደሚያዘጋጁትም ተናግረዋል።

የንግድ ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ፣ ‹‹ከአዲስ አበባም፣ ከኦሮሚያም፣ ከምሥራቅ ባሌ ዞንም የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ተገናኝተውና ጥናት አድርገው፣ በአካባቢው በተገኘው ጨው ላይ ምርመራ ተደርጎ መመረት እንደሚችል ዕውቅና ተሰጥቶታል፤›› ብለዋል።

አሁን በሥራ ላይ ያለው ማኅበር አባላቱን በመጨመርና ሌሎችንም በማካተት የምርት መጠኑን እንዲያሳድግ ከዞኑ በኩል ፍላጎት ቢኖርም፣ የገበያ ትስስር ችግር ግን ማነቆ እንደሆነባቸው ገልጸዋል።

‹‹በሥራ ላይ ያለው ማኅበር በየጊዜው ከዞኑ ንግድ ጽሕፈት ቤት የሚጠይቀው የገበያ ትስስር እንድንፈጥርለት ነው፤›› ያሉት አቶ አሚን፣ በአሁኑ ወቅት ግን ከቆላማ የኦሮሚያ አካባቢ የሚመጡ አከፋፋዮች ብቻ ምርቱን እንደሚወስዱ ጠቁመዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች