Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመጪው ዓመት 8.4 በመቶ እንደሚያድግ መተንበዩ ተነገረ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመጪው ዓመት 8.4 በመቶ እንደሚያድግ መተንበዩ ተነገረ

ቀን:

  • የ2017 ዓ.ም. በጀት ጉድለት 358 ቢሊዮን ብር ሆኗል

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ዓመታት ካጋጠሙት ጫናዎች አገግሞ በ2016 በጀት ዓመት የ7.9 በመቶ ማደጉን፣ በ2017 በጀት ዓመት በ8.4 በመቶ ዕድገት እንደሚመዘገብ መተንበዩን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመጪው ዓመት 8.4 በመቶ እንደሚያድግ መተንበዩ ተነገረ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ

በበጀት ዓመቱ ሁለተኛውን አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራን ተከትሎ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖረው ተሳትፎ እያደገ እንደሚሄድ፣ ለዕድገቱም ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ታሳቢ መደረጉን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተናግረዋል፡፡ የገንዘብ ሚኒስትሩ የ2017 ዓ.ም. ረቂቅ በጀት በተመለከተ ማክሰኞ ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሁለተኛውን አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ኢኮኖሚውን ለውጭ ባንኮች ክፍት የማድረግና የካፒታል ገበያን የመጀመር የመሳሰሉ የፖሊሲ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል፡፡

ለ2017 ዓ.ም. በጀት ዓመት 971.2 ቢሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ የተጀመሩ የካፒታል ፕሮጀክቶችም የክፍያ ጊዜያቸውን በማሸጋሸግ የወጪ ቅነሳ በማድረግ ጭምር የተዘጋጀ በጀት መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ በ2017 በጀት ዓመት ጠቅላላ የፌዴራል መንግሥት ገቢ የውጭ ዕርዳታን ጨምሮ 612.7 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በ2016 በጀት ዓመት ከፀደቀው የገቢ በጀት አንፃር የ21.1 በመቶ ዕድገት እንዳለው ሚኒስትሩ አክለው ተናግረዋል፡፡

እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ረዥም የአቅርቦት ሰንሰለት መኖር፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ውስንነት፣ የነዳጅ ዘይትን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታየው የሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መናር፣ እንዲሁም በቀይ ባህር የንግድ መተላለፊያ መስመር ላይ የሚታዩ እክሎች የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት እየተገዳደሩት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በ2017 ዓ.ም. የመንግሥት በጀትን በዘላቂነትና በአስተማማኝነት ተግባራዊ ለማድረግ የመንግሥት ገቢ አሰባሰብን ማሳደግ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ኢኮኖሚው ውስጥ ሊመነጭ የሚችለውን የገቢ አቅም አሟጦ ለመጠቀም የሚያስችሉ የታክስ ፖሊሲና የታክስ አስተዳደር ማሻሻያዎች በተጠናከረ መንገድ ተግባራዊ ይደረጋሉ ብለዋል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት ተግባራዊ ለማድረግ ከታቀዱ የታክስ ፖሊሲ ዕርምጃዎች መካከል የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ማሻሻያና የኤክሳይዝ ቴምብር ቀረጥ ሥርዓት ዋናዎቹ ናቸው። እነዚህንም ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ በመሆናቸው፣ ከቀጣዩ በጀት ዓመት መጀመሪያ አንስቶ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ከታክስ ገቢ በተጨማሪ ታክስ ያልሆኑ ገቢዎችና የልማት አጋሮች የውጭ ሀብትም የ2017 በጀትን ፋይናንስ ለማድረግ እንደሚውሉ ታሳቢ እንደሚደረጉ አስታውቀዋል፡፡ በዚህም አማካይ የዋጋ ንረት በግንቦት 2016 ዓ.ም. መጨረሻ ካለበት 27.4 በመቶ በቀጣዩ በጀት ዓመት ወደ 12 በመቶ ዝቅ እንደሚል ታሳቢ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ከአጠቃላይ የ2017 ዓም የወጪ በጀት ውስጥ 451.3 ቢሊዮን ብር ለመደበኛ፣  283.2 ቢሊዮን ብር ለካፒታል እንዲሁም 236.7 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለክልሎች የተመደበ የበጀት ድጋፍ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 14 ቢሊዮን ብር የሚሆነው የዘላቂ የልማት ግቦችን ለማስፈጸሚያ ለክልሎች የተመደበ ድጋፍ  መሆኑ በበጀት ማብራሪያው ተገልጿል፡፡

ለ2017 ዓ.ም. ከተመደበው ጠቅላላ የካፒታል በጀት ውስጥ ብር 187.1 ቢሊዮን ብር (66.1 በመቶው) የተመደበው ቅድሚያ ትኩረት ለተሰጣቸው ለመንገድ፣ ለትምህርት፣ ለግብርናና መስኖ፣ ለመጠጥ ውኃና ሳኒቴሽን፣ ለጤናና ለገጠርና ከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ልማት ማስፈጸሚያ የተመደበ ነው፡፡ በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ ንብረቶችንና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ወደ ነበሩበት ለመመለስና ለማቋቋም ለተጀመረው ፕሮጀክት ከመንግሥት ትሬዠሪ 20 ቢሊዮን ብር ተመድቧል፡፡ ለክልሎች የተመደበው የበጀት ድጋፍ ዝርዝር እንደሚያሳየው ለትግራይ 13 ቢሊዮን ብር፣ ለአፋር 6.5 ቢሊዮን ብር፣ ለአማራ 46.9 ቢሊዮን ብር፣ ለኦሮሚያ 74.8 ቢሊዮን ብር፣ ለሶማሌ 21.6 ቢሊዮን ብር፣ ለቤንሻንጉል ጉሙዝ 3.9 ቢሊዮን ብር፣ ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ 12.8 ቢሊዮን ብር፣ ለጋምቤላ 2.88 ቢሊዮን ብር፣ ለሐረሪ 1.6 ቢሊዮን ብር፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 5.4 ቢሊዮን ብር፣ ለድሬዳዋ አስተዳደር 1.9 ቢሊዮን ብር፣ ለሲዳማ 8,911,940,002 ቢሊዮን ብር፣ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች 6,746,163,838 ቢሊዮን ብር፣ ለደቡብ ኢትዮጵያ 15 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

የ2017 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ገቢ በዝርዝር ሲታይ ከታክስ 502 ቢሊዮን ብር፣ ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች 60 ቢሊዮን ብር፣ ከካፒታል ገበያ አንድ ቢሊዮን ብር፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ዕርዳታ 37.5 ቢሊዮን ብር፣ ከመንግሥታት ዕርዳታ 4.2 ቢሊዮን ብር፣ ከመሠረታዊ አገልግሎቶች ከለላ 7.2 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም 601 ሚሊዮን ብር ከውጭ አገሮችና ድርጅቶች ብድር ይይዛል፡፡

የፌዴራል መንግሥት መደበኛ ወጪ ዝርዝር ሲታይ ለአስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት 106.8 ቢሊዮን ብር፣ ለኢኮኖሚ አገልግሎት 8.4 ቢሊዮን ብርና ለማኅበራዊ አገልግሎት 68 ቢሊዮን ብር መመደቡ ተገልጿል፡፡

የካፒታል ወጪ ዝርዝር እንደሚያሳየው ደግሞ ለአስተዳደርና ለጠቅላላ አገልግሎት 43.3 ቢሊዮን ብር፣ ለኢኮኖሚ አገልግሎት 163.7 ቢሊዮን ብርና ለማኅበራዊ አገልግሎት 65.9 ቢሊዮን ብር ተመድቧል፡፡

ለሕግ አውጭውና ለአስፈጻሚው አካል 4.5 ቢሊዮን ብር፣ ለፍትሕና ደኅንነት ተቋማት 27.6 ቢሊዮን ብር፣ ለአገር መከላከያ 65 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ለጠቅላላ አገልግሎት 52.3 ቢሊዮን ብር ተመድቧል፡፡ የአገር መከላከያ በ2016 ዓ.ም. ከነበረው በጀት በ15 ቢሊዮን ብር የጨመረ ሲሆን፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ የመከላከያ በጀት መጨመር አገር የማስቀጠል ኃላፊነት ያለበት መንግሥት የውጭም ሆነ የውስጥ ሥጋቶችን መቀነስ ስላለበት ነው ብለዋል፡፡

ለግብርናና ለገጠር ልማት 23 ቢሊዮን ብር፣ ለከተማና ኢንቨስትመንት 104.7 ቢሊዮን ብር፣ ለውኃ ሀብትና ኢነርጂ 25 ቢሊዮን ብር፣ ለትምህርት 79.8 ቢሊዮን ብር፣ ለጤና 33.8 ቢሊዮን ብርና ለአደጋ መከላከል 11.9 ቢሊዮን ብር መደልደሉ ተመላክቷል፡፡

ለክልሎች ከተመደበው በጀት ውስጥ ለአዳዲስ ክልሎች የተመደበው በየትኛው ቀመር ተመደበ የሚል ጥያቄ ከምክር ቤት አባላት ቀርቧል፡፡ የቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ ሕዝበ ውሳኔዎች ወደ አራት ክልሎች መበተኑ ይታወሳል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ሕዝቡን ወደ ግጭት እየጋበዘው ያለው ችግር የመንግሥት ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ አለመዳረሱ እንደሆነ በመጥቀስ በአንዳንድ አካባቢዎች መንግሥት ፈሰስ የሚያደርገው ገንዘብ ከዓመት ዓመት እየቀነሰ መሆኑን፣ ወ/ሮ ሶስና ጌታሁን የተባሉ የምክር ቤቱ አባል ተናግረዋል፡፡

ሌላው የምክር ቤት አባል ባነሱት ጥያቄ አንዳንድ ፕሮጀክቶች ዕርዳታና ብድር ሲገኝ ይሠራሉ እየተባለ ፕሮጀክቶች ሳይጀመሩ ለበርካታ ዓመታት እየተንከባለሉ መሆናቸውን ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አባል አብርሃም በርታ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት የውጭ ምንዛሪ ችግርን ለመፍታት መንግሥት የትይዩ ገበያውን የምንዛሪ ዋጋ ከባንኮች ጋር እኩል ለማድረግ የሚደረጉ ጫናዎች እንዳሉ መስማታቸውን ገልጸው፣ ይህ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ አገሪቱ የማትወጣበት ችግር ውስጥ እንደሚካተትና ሕዝቡን የማያረጋጋ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ከእስር በኋላ ፓርላማ የተገኙት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባል ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በ2016 ዓ.ም. ምክር ቤት በተሳተፉበት የመጀመረያው ስብሰባ ላይ ባነሱት ጥያቄ መንግሥት በቀረበው በጀት በብድር ይገኛል ያለውና በበጀቱ የሚታየው አጠቃላይ  ጉድለት ተደምሮ የበጀቱን 37 በመቶ እንደሚይዝ ጠቅሰው፣ መንግሥት ይህን ያህል ችግር ያለበት በጀት ይዞ መምጣቱ እንዴት ይታያል በማለት ጠይቀዋል፡፡ አክለውም መንግሥት ምርታማ የሆነ ዘርፍ ላይ ሀብት በማፍሰስ የቅድሚያ ቅድሚያ ለማይሰጣቸውና ምርት ለማይሰጡ ፕሮጀክቶች የሚያውለውን በጀት መቀነስ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ በሰጡት ምላሽ በደቡብ ኢትዮጵያ ለሚገኙ አራት ክልሎች በአገር አቀፍ ደረጃ አዲስ ቀመር እስኪወጣ ድረስ፣ የቀድሞው ክልል ይጠቀምበት የነበረውን የበጀት ቀመር መሠረት በማድረግ ይከፋፈላል ብለዋል፡፡

ፍትሐዊ የልማት ጥያቄን በተመለከተም በሁሉም አካባቢዎች የሚነሱ ጥያቄዎች መሆናቸውን ገልጸው፣ ባለፉት ስድስት ዓመታት በርካታ የመንገድና የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች የተያዙት ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡ የት ክልል ምን ዓይነት ፕሮጀክት እንዳለ መዘርዘር ይቻላል ያሉት ሚኒስትሩ፣ ምክር ቤቱ በዚህ ላይ እምነት ሊኖረው ይገባል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በትይዩ ገበያና ባንኮች መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሪ ግብዓት ማጥበብ ግድ እንደሚል ጠቅሰው፣ በቀጣይ በሁለተኛው የአገር በቀል ኢኮኖሚ በጥናት ላይ በመመሥረት የሪፎርሙ አካል ሆኖ ይሠራል እንጂ በመጪው ዓመት ይከናወናል ተብሎ የቀረበ እንደሌለና በነበረው እንደሚቀጥል ተደርጎ ነው የተወሰነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን መንግሥት የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖር አበክሮ ይሠራል በማለት ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ ይህ አገር በከፍተኛ ጥንቃቄ በፊስካል ፖሊሲ እየተመራ ነው ብለዋል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት በኢትዮጵያ የተሻለ ሰላም እንደሚኖር ግምት ውስጥ ገብቷል ሲሉም አክለዋል፡፡

ለ2017 ዓ.ም. ከቀረበው አጠቃላይ 971.2 ቢሊዮን ብር ውስጥ የበጀት ጉድለቱ 358 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ከውጭ ብድር 32.9 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ ብድር ደግሞ 325.5 ቢሊዮን ብር ለመሸፈን መታቀዱ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...