Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየመንግሥት ሠራተኞች ረቂቅ አዋጅ ለኃላፊዎች የበዛ ሥልጣን በመስጠቱ ትችት ቀረበበት

የመንግሥት ሠራተኞች ረቂቅ አዋጅ ለኃላፊዎች የበዛ ሥልጣን በመስጠቱ ትችት ቀረበበት

ቀን:

  • ለ30 ዓመታት ለሠራተኞች የዋጋ ንረት ማስተካከያ አለመደረጉ ተገልጿል

በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት የሚገኘው የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች ረቂቅ አዋጅ፣ ለመንግሥት መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች የበዛ ሥልጣን የሚሰጥ፣ ለሠራተኞች ችግር ደግሞ መፍትሔ የማያመጣና ተቋማዊ አሠራርና አደረጃጀት ላይ ብቻ ያተኮረ ነው የሚል ትችት ቀረበበት፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ከምክር ቤቱ የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጋር በመሆን በረቂቁ ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ፣ መልስ ይሻሉ ያላቸውን ጥያቄዎች የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ እንዲሰጡ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው ከኮሚሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በረቂቁ ላይ ባዘጋጀው መድረክ በርካት ያሉ ጥያቄዎችን ሰንዝሯል፡፡

ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን በአዋጁ ለምን አልተካተተም? የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች ከልማት ድርጅቶች ጋር ያላቸው ደመወዝ ለምን ተለያዩ? የሜሪትና የደወመዝ ቦርድ እንደሚቋቋም በተጠቀሰው አንቀጽ 17 ላይ የመንግሥት ሠራተኞች ተወካዮች በቦርድ አባልነት ለምን አልተካተተም? የሚሉት ይገኙበታል፡፡

በረቂቁ አንቀጽ 51 ላይ ‹‹የአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የበላይ ኃላፊ አንድ ሠራተኛን ወደ ሌላ የሥራ መደብ አዛውሮ ማሠራት ይችላል›› በሚል የቀረበው ድንጋጌ፣ ለአንድ ኃላፊ ሙሉ ሥልጣን ከመስጠቱ ባለፈ፣ ሠራተኛው ካልተስማማ እንዲያሰናብተው ለኃላፊው ሥልጣን ተሰጠው አይደለም ወይ? የሚል ጥያቄ ቀርቧል፡፡ በዚሁ አንቀጽ ላይ ሠራተኛው ዝውውሩን ካልተቀበለ ሥራውን በገዛ ፈቃዱ እንደለቀቀ ይቆጠራል ተብሎ የተቀመጠ ሲሆን፣ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ይህ ድንጋጌ የሠራተኛውን መብት የሚጥስ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ አስተያየት የሰጡት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ   (ዶ/ር) የአዋጁ ረቂቅ ለበላይ ኃላፊ የተንቦረቀቀ ሥልጣን መስጠቱን ጠቅሰው፣ የሠራተኛውን መብት እንዴት ተመልክታችሁት ነው? የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪ ፖለቲካው በሽተኛ በሆነበት የሚመጣ ኃላፊ በሽተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ምንም እምነት በማይደረግበት ሲስተም ለሚመጣ አመራር የአንድ ሠራተኛንና ዜጋን መብት መጣስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሠራተኞችን በእንዲህ ዓይነት ሰዎች እጅ መጣል ተገቢ ነው ወይ ብለዋል፡፡ ‹‹የተቋም ኃላፊ በሚፈለገው ደረጃ ከፍተኛ የሞራል ልዕልና ቢኖረውና ያለ ብሔር፣ ያለ ሃይማኖትና ያለ ቋንቋ ልዩነት ማስተናገድ የሚቻልበት ደረጃ ገንብተን ከሆነ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ እንደዚያ አይደለም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ሰብሳቢው ረቂቅ አዋጁ ሠራተኛውን በሚያበረታታ፣ ሕይወትና ጥቅሙን በሚያስጠብቅ ሁኔታ አለመዘጋጀቱን ጠቅሰው ረቂቅ አዋጁ የሠራተኛውን ሕይወትና ጥቅም በሚያስከብር መንገድ እንዲዘጋጅ ጠይቀዋል፡፡

ሌላው ጥያቄ በረቂቁ አንቀጽ 59 በሕዝብ በዓላት ቀናት ከሥራ ባህሪያቸው አስገዳጅነት አንፃር በፈረቃ የሚሠሩ ሠራተኞችን ‹‹የሕዝብ በዓል›› አይመለከትም የተባለውን በተመለከተ፣ ለሁሉም ሠራተኞች የሕዝብ በዓላትን የማክበር መብት ለምን አይሰጥም? ለበዓል ለገቡ ሠራተኞች ለምን የትርፍ ሰዓት ክፍያ አይታሰብላቸውም የሚሉ ጥያቄዎች ቀርበው ነበር፡፡

የወሊድ ፈቃድን በተመለከተ በሚያብራራው አንቀጽ 65 ላይ በቀረበ ጥያቄ፣ ለወሊድ ፈቃድ 120 ቀናት በቂ አለመሆኑንና ወደ ስድስት ወራት ለምን አይራዘምም ተብሏል፡፡

 በአንቀጽ 84 ድንጋጌ መሠረት አንድ ሠራተኛ በሥራው ምክንያት ጉዳት ከደረሰበት፣ በአገር ውስጥ ታክሞ መዳን ካልቻለ ውጭ አገር ሄዶ መታከም እንደሚችል ለምን አልተደነገገም? የሚል ጥያቄ ተነስቶበታል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ በረቂቁ አንቀጽ 99 ላይ ከባድ የዲሲፕሊን ጥፋቶችና ቅጣታቸውን በሚያብራራው ድንጋጌ ላይ ባነሳው ጥያቄ፣ ሠራተኛውን እስከ ማባረርና ማሰናበት የሚደርስ ሥልጣን ለተቋሙ የሥራ አመራር ጉባዔ መሰጠቱ አግባብ አለመሆኑን ገልጾ፣ ረቂቁ አስተዳደራዊና መደበኛ ፍርድ ቤት መሄድንና ይግባኝ መጠየቅን የሚከለክል መሆኑን በመጥቀስ ለምን ሲሉ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡ በተጨማሪም በዲሲፕሊን ኮሚቴ የተወሰነን ውሳኔ አንድ የበላይ ኃላፊ ውድቅ ማድረግ እንደሚችል መደንገጉ ለምን እንደሆነ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

በተመሳሳይ የምክር ቤቱ ከፍተኛ የህግ ጉዳዮች ባለሙያ ወ/ሪት ሃይማኖት ደበበ ባቀረቡት ጥያቄ፣ በአንድ መሥሪያ ቤት የሥራ አመራር ጉባዔ አማካይነት የተሰጠን ከሥራ የማሰናበት ውሳኔ፣ በዚህ አዋጅ ወይም በሌላ ሕግ በተቋቋመ ማንኛውም አስተዳደራዊም ሆነ መደበኛ ፍርድ ቤት በይግባኝ ሊታይ እንደማይችል መደንገጉ፣ የበላይ ኃላፊዎች ሥልጣናቸውን በአግባቡ እንዳይጠቀሙና የሕግ የበላይነት እንዲጣስ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አክለውም የመንግሥት ሠራተኛ በሥራ ላይ ሆኖ ለሚደርስበት አደጋ በአገር ውስጥ ሕክምና ማግኘት ካልቻለ፣ በውጭ አገሮች ሕክምና እንዲያገኝ ለምን አይደረግም? የዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ለምን በረቂቅ አዋጅ አልተካተተም? የሚሉ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ (ዶ/ር) በበኩላቸው የይግባኝ ክልከላን በተመለከተ ባነሱት ጥያቄ፣ ‹‹የአስተዳደር ጉባዔ እንዴት ከሕገ መንግሥት በላይ ሆኖ ይግባኝ ይከለክላል፡፡ የአንዳንድ ዜጋ መብት በዚህ ልክ መገደብ የሚቻል ነው ወይ?›› የሚል ጥያቄም አንስተዋል፡፡ አንድ ዜጋ መብቴ አልተከበረልኝም ካለ እስከ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ድረስ ሊሄድ እንደሚቻል ጠቅሰው፣ በዚህ ድንጋጌ በዴሞክራሲ በሚመራ አገር የአንድን ዜጋ ፍትሕ የማግኘት መብት መገደብ የሚቻል ነገር አይደለም ብለዋል፡፡

በተነሱት ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ የሰጡት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የሲቪል ሰርቪስ ሕጎች ዴስክ ኃላፊ አቶ መስፍን ረጋሳ፣ የሜሪትና የደመወዝ ቦርድ ከቀመር አሠራርና ከአስፈጻሚው የመንግሥት ክፍል ጋር የተገናኘ ጉዳይ በመሆኑ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚያው አግባብ የተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም በአንድ መንግሥት መሥሪያ ቤት አንድን ሠራተኛ ለማዘዋወር ኃላፊው በተቋሙ ውስጥ ትልቅ ኃላፊነት አለው የሚል ድንጋጌ እንዳለ ጠቅሰው፣ ነገር ግን አንድ ኃላፊ ያልተገባ ተግባር ላይ ተሰማርቶ ከተገኘ የተጠያቂነት ድንጋጌ በመኖሩ በሕግ እንደሚጠየቅ አስረድተዋል፡፡

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ ስመኝ ውቤ የሕዝብ በዓላትን አከባበር በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፣ ከዚህ በፊትም እየተሠራበት ያለ ድንጋጌ በመሆኑ ይኸው አሠራር መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡ ለአብነትም በሕክምናና እንዲሁም በፀጥታ ተቋማት ለሚሠሩ ሠራተኞች የበዓል ቀናትን መፍቀድ አግባብነት እንደሌለው ገልጸው፣ 24 ሰዓት የሚከናወኑ ሥራዎችን ታሳቢ ተደርጎ የወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የወሊድ ፈቃድን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ አገሪቱ አሁን ያላትን ኢኮኖሚ ታሳቢ ተደርጎ የተሠራ ስለመሆኑ ገልጸው፣ ወደፊት የአገሪቱ ዕድገት እንደ ፈቀደ ታሳቢ ተደርጎ ሊታይ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

በሥራ ቦታ ላይ አደጋ የደረሰባቸውና በአገር ውስጥ መታከም ለማይችሉ የመንግሥት ሠራተኞች፣ በውጭ አገር ሕክምና ለምን አይፈቀድም ተብሎ ለቀረበው የቋሚ ኮሚቴ ጥያቄ፣ መንግሥት ወደፊት እያሰበ ያለውን ትልልቅ ሆስፒታሎች በመገንባት ወደ ውጭ የሚደረገውን ጉዞ በአገር ውስጥ ለማድረግ መታሰቡን ጠቅሰው፣ ይህ ከአገር ኢኮኖሚ ጋር ታስቦ የተደነገገ ስለመሆኑ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ሠራተኞችን ለመደበኛና ለአስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ይግባኝ መጠየቅን መከልከል በተመለከተ የኮሚሽኑ የሲቪል ሰርቪ ሕጎች ዴስክ ኃላፊ በሰጡት ምላሽ፣ በመንግሥት ተቋማት ሙስናን ጨምሮ ከፍተኛና መጠነ ሰፊ የሆኑ በቡድን በመደራጀት ጭምር የሚፈጸሙ ወንጀሎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ ለእንዲህ ዓይነት ጉዳዮች የመሥሪያ ቤት ማኔጅመንት ኮሚቴ ሙሉ ሥልጣንና ኃላፊነት ሊሰጥ ይገባል በሚልና ኃላፊዎች የተሰጣቸው አደራና ኃላፊነት ከባድ በመሆኑ፣ ውሳኔ መስጠት እንዲችሉ ሊታገዙ (Empower) ይገባል ከሚል የመጣ ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም የመሥሪያ ቤትን ህልውና የሚፈታተኑ ጉዳዮችና የሥራ ቦታ በጥብቅ ዲሲፕሊን መመራት ያለባቸው በመሆኑ፣ ለሥራ አመራር ጉባዔ ይህ ኃላፊነት እንደተሰጠ ተናግረዋል፡፡ የዴስክ ኃላፊው በተጨማሪም በመደበኛና በአስተዳደር ፍርድ ቤት ይግባኝ የተከለከለው የሥራ ቦታ እንዳይበደልና ጭቅጭቅን ለማስቀረት ለጥንቃቄ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) ረቂቅ አዋጁ በዋነኛነት ሲቪል ሰርቪሱ ትልቅ ለውጥ እንዲያመጣና የመንግሥት ሠራተኛው የባህሪና የቴክኒክ ብቃቱ እንዲሻሻል የሚያስገድድ መሆኑን፣ ይሁን እንጂ የደመወዝ ጭማሪና የዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ጉዳይ በቀጣይ በአዋጁና በሚወጡ አሠራሮች አማካይነት ይፈታል ብለዋል፡፡

ኮሚሽነሩ እንደገለጹት የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ጊዜ በሄደ ቁጥር ከዋጋ ንረት ጋር ተያይዞ ማስተካከያ መደረግ የነበረበት ቢሆንም፣ ባለፉት 30 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ማስተካከያ አልተደረገም፡፡ የመንግሥት ሠራተኛው ክፍያ በየዓመቱ ተመሳሳይ ቢሆንም የገንዘብ የመግዛት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ መሄዱን ገልጸው፣ ይህም ሊሆን የቻለው፣ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ማስተካከያ ስኬል ባለመፈቀዱ ነው ብለዋል፡፡ ይህ ጉዳይ በዚህ አዋጅ አማካይነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መዘጋትና መቆም አለበት ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የዋጋ ንረትን በሚያጠናው የስታትስቲክስ አገልግሎት ተቋም ምጣኔና ዓመታዊ ሪፖርት መሠረት፣  ኮሚሽኑ በየሁለት ዓመቱ በሠራተኛው መነሻ ደመወዝና አበል ላይ የዋጋ ንረት ማስተካከያ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ሌላው ኮሚሽነሩ የገለጹት ጉዳይ አገራዊ ዕድገቱና ኢኮኖሚው ሲያድግ የመንግሥት ሠራተኛው ከአገሪቱ ዕድገትና መሻሻል ጋር አብሮ መሻሻል ያለበት በመሆኑ፣ የስኬል ማሻሻያ በየአራት ዓመቱ እንደሚደረግ ነው፡፡ ይህ የሕግ አንቀጽ መንግሥትን በየአራት ዓመቱ ማስተካከያ እንዲያደርግ የሚያስገድድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኞች በተለይም በትጋት የሚሠሩ ሠራተኞች በሥራ አፈጻጸምና በማትጊያ፣ እንዲሁም ከዋጋ ንረት ውጪ በሚታሰብ አበል ላይ የሚደረግ የዕድገት ጭማሪ እንደሚኖር  አስረድተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ (ዶ/ር) በማጠቃለያ ሐሳባቸው በአገር አቀፍ ደረጃ አገልጋዩ በሚሰጠው፣ እንዲሁም ተገልጋዩም በሚቀርብለት የመንግሥት አገልግሎት ዕርካታ እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የመንግሥት ሠራተኛውን ሊያኖር የሚችል የደመወዝ ማስተካከያ እንዲኖር አስገዳጅ ረቂቅ አዋጅ እንዲወጣ፣ እንዲሁም የተሻለ ሕይወት የሚመሩ ሠራተኞችና የመንግሥት አገልግሎት ተጠቃሚው ኅብረተሰብም ከምሬት የወጣ አገልግሎት የሚያገኝበት አዋጅ ሆኖ እንዲዘጋጅ ጠይቀዋል፡፡

ቀድሞ ከነበረው ባለ 106 አንቀጽ አዋጅ ወደ 160 አንቀጽ ከፍ ያለው ይህ ረቂቅ አዋጅ፣ ከ2.5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የመንግሥት ሠራተኞችን ችግር ይፈታል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...