Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአዲሷ የወባ በሽታ አስተላላፊ ትንኝ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ሥጋት መሆኗ ተነገረ

አዲሷ የወባ በሽታ አስተላላፊ ትንኝ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ሥጋት መሆኗ ተነገረ

ቀን:

  • በኩባያ ውኃ ውስጥ መራባት ትችላለች

መነሻዋን ከጂቡቲ እንዳደረገች የሚነገርላት አዲሷ የወባ አስተላላፊ ትንኝ ወደ ኢትዮጵያ መግባቷ በሽታውን በፍጥነት ታዛምታለች የሚል ሥጋት መደቀኑ ተገለጸ፡፡ ዓርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት (አህሪ) የተመሠረተበትን 54ኛ ዓመት በማስመልከት በአዳማ ያስገነባውን የወባና ትኩረት የሚሹ በሽታዎች የምርምርና የሥልጠና ማዕከል ለሚዲያ አካላት ባስጎበኘበት ወቅት እንደተገለጸው፣ አዲሷ የወባ ትንኝ በኢትዮጵያ መከሰት ያለውን ችግር የሚያባብስ ይሆናል፡፡

አዲሷ የወባ በሽታ አስተላላፊ ትንኝ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ሥጋት መሆኗ ተነገረ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
አፈወርቅ ካሱ (ፕሮፌሰር)

የማዕከሉ አስተባባሪና የወባ በሽታ ተመራማሪ አቶ ታደለ እምሩ እንደሚሉትም፣  የወባ በሽታን ለመከላከል ላለፉት 50 ዓመታት ቢሠራም፣ ገዳይነቱን ማስቆም አልተቻለም፡፡ በቅርቡ የተከሰተችው አዲሷ የወባ በሽታ አስተላላፊ ትንኝ ደግሞ ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ እያደረገችው ትገኛለች፡፡

‹‹አኖፊለስ ፊተሲንስ›› የምትባለው አዲሷ የወባ ትንኝ ጂቡቲ ውስጥ በ2012 ዓ.ም የተገኘች ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያ የገባችው በቀብሪ ደሃር አካባቢ ነው፡፡ በተሠራው የቅኝት ሥራ ደግሞ አሁን ላይ በ52 የኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ መታየቷን ተመራማሪው ይገልጻሉ፡፡

እንደ አቶ ታደለ፣ ትንኟ ከቀድሞዎቹ በሽታ አስተላላፊ የምትለይበት በርካታ ባህሪዎች ያሏት ሲሆን፣ ከእነዚህ በማንኛውም ክፍት ውኃ ውስጥ መራባቷ፣ በከተሞች አካባቢ መራባቷ፣ ቀድመው ከነበሩት ሁለት ዓይነት የወባ በሽታ አስተላላፊ ትንኞች በመውሰድ ማስተላለፍ መቻሏ ይጠቅሳሉ፡፡

ትልቁ ለየት የሚያደርጋት ባህሪዋ ከዚህ ቀደም ለወባ በሽታ ይሰጡ ከነበሩ ሕክምናዎችና የመከላከያ ሥራዎች ሁሉ ማምለጥ መቻሏ ነው፡፡ የማስተላለፍ መጠኗም ቀድሞ ከነበረው የጨመረ ነው፡፡ የትንኟ ሌላው አስደንጋጭ ባህሪዋ ከዓመት ዓመት በየትኛውም የአየር ፀባይ በመራባት በሽታ ማስተላለፍ መቻሏ ነው፡፡

አዲሷ የወባ በሽታ አስተላላፊ ትንኝ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ሥጋት መሆኗ ተነገረ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
አቶ ታደለ እምሩ

ድሬዳዋን ጨምሮ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረገ ጥናት ከ10 ሺሕ በላይ አዳዲስ የወባ በሽታ ተጠቂዎች መገኘታቸውንና የበሽታው በከፍተኛ መጠን መዛመት አሳሳቢ እንደሆነ ተመራማሪው ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

አዲሷ ወባ አስተላላፊ ትንኝ ምንድነው የምትበላው? በየትኛው ጊዜዋ ነው  የምትሞተው? ምን ዓይነት መድኃኒት ሊያጠፋት ይችላል? የሚሉትን ጨምሮ በርካታ ምርምሮች እየተደረገባት እንደሆነ ተናግረው፣ ከሥር ከሥር የተገኙ ውጤቶች ለጤና ሚኒስቴር እየተላኩ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡

የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አፈወርቅ ካሱ (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ ኢንስቲትዩቱ በስፋት ከሚሠራቸው የምርምር ሥራዎች አንዱ በወባ ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የወባ በሽታ አዲስ ፖሊሲ፣ አዲስ የሕክምናና የመከላከያ ሥራዎች እንደሚያስፈልገው በጥናት መረጋገጡን፣ አስተላላፊ ትንኞቹ ባህሪያቸውን ሙሉ በሙሉ መቀየራቸው በላቦራቶሪ መታየቱን፣ የሚሰጡ መድኃኒቶች እንደማያሽሉ፣ አጎበሮቹ በኬሚካል የተነከሩ ቢሆኑም ትንኞቹ ወደ ሰው እንዳይገቡ ይከላከላል እንጂ ኬሚካሉ እንደማይገድላቸው፣ እነዚህና ሌሎችም በርካታ የምርምር ውጤቶች መግደል አቁሞ የነበረው የወባ በሽታ፣ ዛሬ ገዳይ መሆኑን ማሳየታቸውን አክለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተገኘችው አዲስ የወባ በሽታ አስተላላፊ ትንኝ ዙሪያ ኢንስቲትዩቱ የቅርብ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥም ጂቡቲ ታይታ አገራችንን አቋርጣ ዑጋንዳ ውስጥ መገኘቷ ትንኟ የትኛውንም አካባቢና አየር በመላመድ በፍጥነት እየተራባችና በሽታን እያተላለፈች እንደምትገኝ አመላካች መሆኑን አሳውቀዋል፡፡

በተለይ የትንኟ መራቢያ በማንኛውም ትንሽና በተጠራቀመ ውኃ ውስጥ መሆኑና በከተሞች ውስጥ መስፋፋት መቻሏ፣ ኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና እንደሚጠብቃት እንደሚያሳይ፣ የአዲሷን ትንኝ ጨምሮ በወባ ዙሪያ የሚደረጉ ምርምሮች መቀጠላቸውን፣ የተገኙ አዳዲስ ውጤቶች ለጤና ሚኒስቴር እንደሚቀርቡና አሮጌውን የወባ መመርያ ኪት በአዲስ የመቀየር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የምርምር ውጤቱ ወጥቶ ወደ መከላከሉ እንደሚገባ ያላቸውን ተስፋ የገለጹት አፈወርቅ (ፕሮፈሰር)፣ ማዕከላቸው በዘመናዊ መሣሪያዎች የተገነባ መሆኑን አመልክተው፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ ከ50 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች አብረዋቸው እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ቀድሞ ናዝሬት የወባ ምርምር ጣቢያ በመባል ይታወቅ የነበረው፣ አሁን ላይ እድሳትና ግንባታ ተደርጎለት የወባና ትኩረት የሚሹ በሽታዎች የምርምርና የሥልጠና ማዕከል የተባለ ሲሆን፣ በአርማወር የምርምር ኢንስቲትዩት ሥር የሚገኝ ነው፡፡ ምሥራቅ ሸዋን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ ከወባ ጋር የተያያዙ ዘመናዊ ምርምሮች የሚደረጉበትም ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...