Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአየር ብክለት በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ ያደረሰው የጤና ጫና

የአየር ብክለት በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ ያደረሰው የጤና ጫና

ቀን:

ተፈጥሮ በበርካታ ውስብስብ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈች ትገኛለች፡፡ ከእነዚህ ፈተናዎች መካከል የአየር ብክለት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት የሚመደብ ነው፡፡ ለከባቢ አየር ብክለት በዋናነት ምንጩ የሰው ልጅ ሲሆን፣ ቀዳሚ የችግሩ ሰለባም ራሱ የሰው ልጅ ነው፡፡

የሰው ልጅ አኗኗሩን ለማዘመን የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን በመመሥረቱና ትራንስፖርትና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋቱ ምክንያት፣ የተለያዩ በካይ ንጥረ ነገሮች ወደ ከባቢ አየር እንዲሠራጩ ሆነዋል፡፡

ከበካይ ንጥረ ነገሮች መካከልም ሠልፈርዳይኦክሳይድ፣ ናይትሮጅን ዳይኦክሳይድና ካርቦንሞኖኦክሳይድ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡

እነዚህ በካይ ንጥረ ነገሮች በተለያየ ደረጃ በሰው የጤና ሥርዓት አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳረፍ ለተለያዩ ችግሮች እየዳረጉ ይገኛሉ፡፡ ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያያዙት የሳንባ ምች፣ የሳንባ ካንሰር፣ አስም እንዲሁም የልብ ጉዳትና ሞትን እያስከተሉ ናቸው፡፡ በእንስሳ፣ በዕፅዋትና በውኃ አካላት የሚያደርሱት የጉዳት መጠንም ከፍ ያለ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የአየር ንብረትና የአማራጭ ኢነርጂ ዳይሬክተር አቶ ሰይድ አብደላ እንደተናገሩት፣ ለአየር ብክለት መንስዔ የሆኑ በካይ ነገሮች የሚለቀቁት ከተሽከርካሪ ጭስ፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከኮንስትራክሽን ሥራዎች፣ ከማዕድን ማውጣት፣ ኢነርጂ ለማመንጨት አገልግሎት ከሚውለው ድንጋይ ከሰል መቀጣጠል፣ ከቆሻሻ መቃጠል፣ ከቤት ውስጥ ኢነርጂ የሚጠቀሰው ማገዶ ማቀጣጠልና ከመሳሰሉት ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2018 የወጣ ዓለም አቀፍ ሪፖርት፣ ከአየር ብክለት ጋር በተያያዘ በየዓመቱ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች እንደሚሞቱ፣ የሰዎች ሞት ከሚያስከትሉ ምክንያቶች የአየር ብክለት አራተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና የአየር ብክለት በጤና ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመመከት በየዓመቱ 225 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚሆን ያሳያል፡፡

እንደ አቶ ሰይድ፣ በዓለማችን ከአሥር ሰዎች ዘጠኝ ያህሉ ንፁህ ያልሆነ አየር ይተነፍሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በተደረገው ዳሰሳ በአየር ብክለት ምክንያት የ1.2 ሚሊዮን (ከጠቅላላው አምስት በመቶ) ሰዎች በላይኛው የመተንፈሻ አካል የታየ ሕመም፣ አምስት በመቶ ያህሉ ደግሞ ለሳንባ ምች ሕመም ተጋልጠዋል፡፡

በሳምባ ምች ሕመም ምክንያት ወደ ሆስፒታል የመጡ ታማሚዎች ቁጥር የመጀመሪያውን ደረጃ ሲይዝ፣ በሟች ቁጥር ደግሞ ሁለተኛውን ደረጃ ይዞ ይገኛል፡፡

ዳይሬክተሩ የአዲስ አበባ ከተማ ብክለት ሁኔታን በተመለከተ እንደተናገሩት፣ ተሽከርካሪዎች 28 በመቶ የኦርጋኒክ ካርቦን፣ 18.3 በመቶ የባዮማስ ነዳጅ እንዲሁም 17.4 በመቶ የአፈር አቧራ ምንጭ በመሆን ለከተማዋ የአየር ብክለት አስተዋጽኦ አላቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ በመሄዱ ብክለቱም በዚያው ልክ በመጨመር ላይ ይገኛል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ያረጁ ተሽከርካሪዎች በትራንስፖርት ሥምሪቱ ውስጥ መገኘታቸው ደግሞ ለብክለቱ መባባስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የነዳጅ ጥራት፣ የመንገድ መረብ በቂ አለመሆንና መጨናነቅ፣ የመንገድ ብልሽትና በወቅቱ አለመጠገን ለብክለቱ መባባስ ድርሻ እንዳላቸው አክለዋል፡፡

በአየር ብክለት የተነሳ በከተማዋ የደረሱ ተፅዕኖዎችን በተመለከተ አቶ ሰይድ እንደገለጹት፣ እ.ኤ.አ. በ2019 የዓለም ባንክ ባደረገው ጥናት፣ ከአየር ብክለት ጋር በተያያዘ በተጠቀሰው ዓመት በከተማዋ 1,600 ያህል ሰዎች ሞተዋል፡፡ በብክለቱ ምክንያት ከሚፈጠር ሕመምና ሞት በከተማዋ በዓመት እስከ 78 ሚሊዮን ዶላር ጉዳት ይደርሳል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውንና እየጨመረ የሚገኘውን አየር ብክለት በጊዜው መከላከልና መቆጣጠር ካልተቻለ፣ በ2017 ዓ.ም. እስከ 2,700 የሚያደርሱ ሰዎች ሊሞቱ እንደሚችሉና ይህ ቁጥር በ2025 ዓ.ም. እስከ 6,000 ሊያሻቅብ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ፣ የከተማዋን የአየር ብክለት ለመቀነስና የአየር ጥራትን ለማሻሻል በመንግሥት የተያዙና እየተሠራባቸው የሚገኙ አቅጣጫዎች አሉ፡፡ ንፁህ የኃይል ምንጮችን ማስተዋወቅ፣ የተሽከርካሪ ልቀት ደረጃዎችን ማስፈጸም፣ ዓመታዊ የተሽከርካሪዎች ቁጥጥር ማድረግና የትራፊክ ፍሰትን ለማሻሻል የትራፊክ መረቦችን ማሻሻል የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ኃይል ቆጣቢ ተሽከርካሪዎችን ማበረታታት፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እንዲስፋፋ ማድረግ፣ የተሻሻሉ ባህላዊ ምድጃዎችን ማስተዋወቅ፣ የቆሻሻ አያያዝን ማሻሻልና የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻዎችን ማከናወን እንደ መፍትሔ ከተቀመጡ አቅጣጫዎች ይጠቀሳሉ፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...