Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየሃምሳኛው የቡድን ሰባት አገሮች ጉባዔ አጀንዳዎች

የሃምሳኛው የቡድን ሰባት አገሮች ጉባዔ አጀንዳዎች

ቀን:

በዓለም በኢኮኖሚያቸው የበለፀጉት ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝና ካናዳ የተጣመሩበት ቡድን ሰባት (ጂ7)፣ 50ኛ ጉባዔውን በጣሊያን አፑሊያ ከሰኔ 6 እስከ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. ያካሂዳል፡፡

በጉባዔም 12 የዓለም አገሮች እንዲሳተፉ ጥሪ የተደረገላቸው ሲሆን፣ ከአፍሪካ ኬንያ፣ አልጄሪያ፣ ግብፅ፣ ደቡብ አፍሪካና ቱኒዝያ ይሳተፋሉ፡፡ አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ህንድ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ቱርክ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶችና፣ ዩክሬን ግብዣ የተደረገላቸው አገሮች ሲሆኑ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሰብሳቢ ሙሳ ፋኪ እንዲሁም ፖፕ ፍራንሲም የሚሳተፉ ይሆናል፡፡

የሃምሳኛው የቡድን ሰባት አገሮች ጉባዔ አጀንዳዎች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የዩክሬን ሩሲያ ጦርነትና ለዩክሬን የሚሰጥ ድጋፍ የጂ7 አንዱ አጀንዳ ነው

እ.ኤ.አ. በ2014 ሩሲያ ክራይሚያን ማጠቃለሏን ተከትሎ፣ ሩሲያን ከቡድኑ በማግለል ከጂ8ነት ወደ ጂ7ነት የተዋቀሩት የድርጅቱ ሰባት አባል አገሮች፣ የዓለምን ጠቅላላ ምርት 30 በመቶ፣ ከዓለም ሕዝብ አንድ አሥረኛውን የሚሸፍኑ መሆናቸውን የቢቢሲ መረጃ ያሳያል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት በቋሚነት የሚሳተፉበት ጉባዔ፣ ከአባላት ውጪ ያሉ አገሮችን የሚጋብዘው፣ አገሮቹ በሚያሳዩት የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀልበስ ባላቸው አስተዋጽኦና ለዓለም ደኅንነት በሚኖራቸው ሚና ላይ ተመርኩዞ ነው፡፡

የዓለም ሁለተኛ ኢኮኖሚ ያላት ቻይና አባል ያልሆነችበት ቡድን ሰባት፣ በ2024 የጣሊያን ጉባዔው፣ አምስት መሠረታዊ አጀንዳዎች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አሜሪካንፕሮግረስ በድረገጹ እንዳሰፈረው፣ በዩክሬንና በሩሲያ ጦርነት ምክንያት፣ በዓለም ወደ 300 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሀብቷ እንዳይንቀሳቀስ ከተደረገባት ሩሲያ፣ በዩክሬን እያጋጠመ ላለው ችግር ማቅለያ ያጋጠመውን የፈንድ እጥረት ለመሙላት ጥቅም ላይ ይዋል የሚል አጀንዳ ይገኝበታል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት ከሩሲያ የማይንቀሳቀስ ንብረት በዓመት ሦስት ቢሊዮን ዶላር ለማመንጨት ያቀደ ቢሆንም፣ የጂ7 አባላቱ ጀርመንና ጃፓን ዕቅዱ ላይ ያላቸውን ቁጥብነት ገልጸዋል፡፡ አገሮቹ በራሳቸው ውሳኔ ይህንን ለማድረግ ፈቃደኛ እንዳልሆኑ፣ ሌላ የሕግ መዘዝ እንደሚያስከትልና ገበያው ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድርም ተናግረዋል፡፡

ፈረንሣይ፣ ጣሊያንና የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ደግሞ የአገርን ተቀማጭ ገንዘብ መያዝ በዩሮ ላይ ያለውን መተማመን እንደሚሸረሽርና የአንድ ገንዘብ ተቀማጭ ሀብት ብቻ እንዲኖር ሊያደርግ እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

በቡድን ሰባት የፋይናንስ ሚኒስትሮች ስብሰባ፣ አሜሪካ ዩክሬንን ለመደገፍ የ50 ቢሊዮን ዶላር ብድር ለማግኘት ከሩሲያ የማይንቀሳቀስ ሀብት የሚገኘውን ወለድ እንደ ማስያዥያ ለመጠቀም ሐሳብ ያቀረበች ሲሆን፣ ይህም የራሱ ፈተናዎች አሉትና ከዚህ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በጉባዔው የሚነሱ መሆኑን አሜሪካንፕሮግረስ አስፍሯል፡፡

የምግብ ዋስትና ችግሮችን ለመቅረፍ ትኩረት መስጠትና መተባበር ሌላው የጂ7 አጀንዳ ነው፡፡ የሩሲያና በዩክሬን ጦርነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው ፈተናና በየአገሮች ውስጥ ያሉ ግጭቶች በዓለም የምግብ ዋስትና ቀውስ አስከትለዋል፡፡

በ2023፣ በ59 የዓለም አገሮች ውስጥ የሚገኙ በተለይ ሕፃናትና ሴቶችን ጨምሮ 282 ሚሊዮን ሕዝቦች ለከፋ የምግብ ዋስትና ችግር ተጋልጠዋል፡፡ ለአብነት በሱዳን ብቻ ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ሕፃናት ለከፋ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል፡፡ በመሆኑም የጂ7 አገሮች ለዓለም ምግብ ፕሮግራም ከሚለግሱት ገንዘብ በተጨማሪ በችግሩ በጣም ለተጎዱት ዛምቢያ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ አፍጋኒስታን፣ የመንና ሌሎች አገሮች የቀጥታ የሁለትዮሽ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህንን ታች ለማውረድ አባል አገሮቹ አሁን እየተተገበሩ ካሉ ፕሮግራሞች ጋር መጣመርና በመተባበር ፕሮግራሞቹ ተግባራዊ እንዲሆኑ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የእስራኤልና ፍልስጤምን ደኅንነትና ሰላም ለማስፈን መንገድ መቀየስም የዚህ ጉባዔ አጀንዳ ነው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ግጭት በተለይም ፍልስጤም ሐማስ በእስራኤል ላይ የሰነዘረውን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ እየወሰደች ያለው ወታደራዊ ዕርምጃ የሰብዓዊ ቀውሱን አባብሶታል፡፡ በእስራኤልና በኢራን መካከል የተፈጠረው ግጭት በተወሰነ መልኩ ቢረግብም፣ የኢራንን የውክልና ጦርነት ያስፈጽማሉ በሚባሉት ሒዝቦላህና ሁቲ ምክንያት ቀጣናው መረጋጋት አልቻለም፡፡

በመሆኑም የጂ7 ጉባዔ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከሳምንት በፊት አገሮቹ ተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ያቀረቡትን ምክረ ሐሳብ እንዲያፀድቅ ይጠበቃል፡፡ ጉባዔው ስለፍልስጤም የወደፊት ህልውና ግልጽ አቋም ለማስቀመጥ ዕድል እንደሚፈጥርም ታምኗል፡፡

በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተቋቋሙና የተለያዩ አገሮች የሚሳተፉባቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እየተከሰቱ ያሉትን ችግሮች መፍታት ተስኗቸዋል፡፡ ለዚህ አንዱ ምክንያት ደግሞ ውሳኔ ሰጪ አገሮች ጥቂት መሆናቸው ነው፡፡ ይህንን መከለስና መልሶ ማደራጀት ተጠያቂነትና እምነትን ከማጎልበት ባሻገር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ውሳኔ መስጠት እንዲችሉ የሚያደርግ በመሆኑ፣ አባል አገሮቹ ዋና ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከአበዳሪ ተቋማት ጋር ስምምነት በማድረግ ወለድ የሚቀነስበት፣ የመክፈያ ጊዜ የሚራዘምበትና የብድር ክለሳና ስረዛ አገሮቹ ሊወያዩበት ይገባል በሚል የቀረበ ሐሳብ መሆኑን የአሜሪካንፕሮግረስ መረጃ ያሳያል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...