Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልበሙዚቃ ፕሮፌሰሩ አሸናፊ ከበደ ስም የሙዚቃዊ ጥበባት ማዕከል ተመሠረተ

በሙዚቃ ፕሮፌሰሩ አሸናፊ ከበደ ስም የሙዚቃዊ ጥበባት ማዕከል ተመሠረተ

ቀን:

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት መሥራች ዳይሬከተር በነበሩት በሙዚቃ ፕሮፌሰሩ አሸናፊ ከበደ ስም  የሙዚቃዊ ጥበባት ማዕከል መመሥረቱን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡

በሙዚቃ ፕሮፌሰሩ አሸናፊ ከበደ ስም የሙዚቃዊ ጥበባት ማዕከል ተመሠረተ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
አሸናፊ ከበደ የሙዚቃዊ ጥበባት ማዕከል ሲመረቅ ፎቶ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

በኢትዮጵያ የዘመናዊ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ዓይነተኛ አስተዋፅዖ ባበረከቱ፣ ተወዳጅ የሆነውን ‹ባለዋሽንቱ እረኛ› ጨምሮ  ዘመን አይሽሬ ረቂቅ የሙዚቃ ሥራዎችን በቀመሩት፣ ባቀናበሩት አሸናፊ ከበደ (ፕሮፌሰር) ስም ማዕከሉ የተቋቋመው በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ውስጥ ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲው በትስስር ገጹ እንደገለጸው፣ ሙዚቃዊ ጥበባት ማዕከሉን ሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. የመረቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ በዕለቱ ባደረጉት ንግግርም፣ ዩኒቨርሲቲው ማዕከሉን ‹‹ኢትዮጵያን ትናንት እንዲሁም ዛሬን ወደ ነገ በሚያሻግር መልኩ ያደራጀ›› ያሉ ሲሆን፣ አያይዘውም ‹‹ይህን መሰል ድልድይነትና ቀጣይነት በሁሉም ተቋሞቻችን አሠራር መድገም ያስፈልጋል፤›› ብለዋል።

ማዕከሉን  በዳይሬክተርነት የሚመሩትም ታላቁ ዓለም አቀፍ የረቂቅ ሙዚቃ ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ መሆናቸው ታውቋል፡፡

የማዕከሉን ምረቃ ተከትሎ የሙዚቃ ባለሙያው፣ የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት በማኅበራዊ ገጻቸው በሰጡት ሙያዊ አስተያየት ‹‹ለሙዚቃ ‹ፐርፎርማንስ›፣ በተለይም ለረቂቅ ሙዚቃ ‹ፐርፎርማንስ› ምቹ የሆነ፣ የ‹አኩስቲክ› ደረጃው ጥንቅቅ ያለ መድረክ ሲኖረን፣ ይህ ማዕከል የመጀመሪያው በመሆኑ፣ ለሙዚቃ ባለሙያዎች አስደሳች ዜና እና ስጦታ ነው፤›› በማለት አወድሰዋል።

በዳይሬክተሩ ግርማ ይፍራሸዋና በሌሎችም በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የቀረቡት የረቂቅ ሙዚቃ ክዋኔዎች፣ ማዕከሉ ለዚህ ተግባር ምን ያህል ምቹ መሆኑን ያረጋገጡ ሥራዎች ነበሩ ብለዋል።

ከአምስት ዓመት በፊት በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ መታሰቢያ የሳይንስ አካዴሚ’ መድረክ ላይ ስለ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ሕይወትና ሥራ ሙያዊ ዲስኩር ያሰሙት ሠርፀ ፍሬስብሐት ስለሙዚቃው ፕሮፌሰሩ እንዲህ ብለው ነበር፡፡ ‹‹ማናችንም እዚህ መድረክ ላይ የተገኘን ታዳምያን ሁሉ እንደምናውቀው፤ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ትልቅ የሙዚቃ ሰው፣ የሙዚቃ ተመራማሪ፣ እና የኢትዮጵያን ሙዚቃ ‹ረቂቅ› በሚባል ደረጃ ቀምረው ያሳዩ የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡››

ነገር ግን ብለው በወቅቱ ቁጭታቸውንም እንዲህ ገልጸው ነበር፡-

‹‹እኚህን የመሰሉ የሙዚቃ ሊቅ፣ በአገራችን ሙዚቃ ውስጥ በምናደንቃቸው፣ በምንወዳቸው፣ ሥራዎቻቸውንም ዘወትር በምናዳምጥላቸው ‹የፖፒውላር› ሙዚቃ አቀናባሪዎች ወይም ድምፃውያን ልክ፤ ማንነታቸውን እና የሞሉትን ሙዚቃዊ ክፍት ቦታ መረዳት የቻልን አይመስለኝም። በዚህም የተነሳ አርዓያነታቸውን የሚከተል ለመፍጠር፣  ባለውለታነታቸውን ለመዘከር፣ በስማቸው የደከሙለትን የረቂቅ ሙዚቃና የምርምር ውጥን ሊተገብር የሚችል የምርምር ወይም የማስተማሪያ ተቋም ለመመሥረት እንዳንችል ሆነናል (ዳርጎናል) ብዬ አምናለሁ፤›› ሲሉ በኅዳር 2011 ዓ.ም. ያስተጋቡት ምኞት ዘንድሮ ዕውን ሁኗል፡፡

በ1930 ዓ.ም. ተወልደው በ60 ዓመታቸው ያረፉት የሙዚቃው ሊቅ አሸናፊ ከበደ (ዶ/ር) በሀንጋሪ ባቀረቡት በባለ ዋሽንቱ እረኛ ሥራቸው ‹‹ጥቁሩ ኮዳይ›› የሚል ቅጽል ስም አትርፈው ነበር፡፡ የዚህን ስያሜ ምንጭ የትመጣነት አስመልክቶ የሙዚቃ ሕይወታቸውን ያጠኑት ሠርፀ ፍሬስብሐት እንደሚከተለው አቅርበውት ነበር፡፡

‹‹የአሸናፊ ከበደ ‹ባለዋሽንቱ እረኛ› በሀንጋሪ ቡዳፔስት መድረክ ላይ በቀረበበት ጊዜ፤ ብዙዎች ይህንን ተአምር ማመን አልቻሉም፡፡ ኦርኬስትራው ቦታውን ከያዘ በኋላ፣ የኦርኬስታራው መራኄ ሙዚቃ (ኮንዳክተር) ሆኖ የቀረበው ወጣት፤ በፍጹም ሙዚቃውን ይመራል፣ ሙዚቃውንም ጽፎታል ብለው ለማመን ተቸግረው ነበር፡፡ የክላሲካል ሙዚቃ ለአፍሪቃውያን ባህል ሩቅ ነው ብሎ ከማሰብ የመነጨ ነው፡፡ ከመድረኩ ተአምራዊ ክዋኔ በኋላ ግን፤ የሀንጋሪ ጋዜጦች የአሸናፊን ምስል፤ ‹Black Kodaly› (ጥቅሩ ኮዳይ) በሚል ቅጽል ይዘው ወጡ፡፡

‹‹ዞልታን ኮዳይ፤ በሀንጋሪ ሙዚቃ ውስጥ ትልቁ ብሔራዊ ሙዚቀኛቸው ነው፡፡ “ኮዳይ ሥነ ዘዴ” ተብሎ የሚታወቅ ዓለማቀፋዊ ሙዚቃ የማስተማሪያ ዘዴም አለ፡፡ የሀንጋሪን ሙዚቃ ትልቅ ያደረጉት ኮዳይ እና ባርቶክ ናቸው፡፡ የዚህን ትልቅ ሙዚቀኛ ስም በቅጽልነት ለአሸናፊ ከበደ መስጠት እንደ ትልቅ ክብር የሚታይ ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ፤ አፍሪቃውያን ከምዕራባዊ ሳይነጻጸሩ በራሳቸው መደነቅ አይችሉምን? የሚል ጥያቄም የሚያስነሳ ነው፡፡››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...