Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርለአዳዲስ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሐሳቦችና ሞዴሎች ትኩረት ይሰጥ

ለአዳዲስ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሐሳቦችና ሞዴሎች ትኩረት ይሰጥ

ቀን:

በጌታነህ አ.

አሁን ባለው ሁኔታ የዋጋ ንረት የዛሬ ሁለት ዓመት (ግንቦት 2014) ከነበረበት 37.3 በመቶና የዛሬ አንድ ዓመት (ግንቦት 2016) ከነበረበት 33.5 በመቶ፣ ዘንድሮ በሚያዝያ 2016 ዓ.ም. 23.30 በመቶ ደርሷል። ይህ በጣም ፈጣንና ከፍተኛ ሊባል የሚችል ለውጥ ሲሆን፣ ይህ እንዲሆን ያደረገው ደግሞ የማክሮ ኢኮኖሚ ዕርምጃ ነው ። ከዚህ ባሻገር  መሬት ላይ ምን ጥሩ ነገር አመጣ ምንስ ጉዳት አደረሰ የሚለውን ለማወቅ ጥናት የሚያስፈልገው ነው። ነገር ግን ሁኔታዎች እንደሚያሳዩት ከአሁን በኋላም የዋጋ ንረት ምጣኔው በፍጥነት እንደሚቀንስ ነው። ይህ ሲሆን ደግሞ የማክሮና የማይክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ዕርምጃዎች ተናበው መሥራት አለባቸው።

እንደ እኔ እምነት መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚው የፖሊሲ ዕርምጃ መውሰድ ከጀመረ የማይክሮ ኢኮኖሚውን ዕገዛ መፈለግ የለበትም፣ በራሱ ነው መጨረስ ያለበት። ነገር ግን በራሱ የማይተማመን ከሆነና በሚወስደው የፖሊሲ ዕርምጃ ውጤታማነት ጥርጣሬ ካለውና የማይክሮ ኢኮኖሚውን ፖሊሲ ዕገዛ የሚፈልግ ከሆነ የሚወሰዱት ዕርምጃዎች የአጭር ጊዜና ያዝ ለቀቅ እየተደረጉ የማክሮ ኢኮኖሚ የፖሊሲ ዕርምጃው አስተካክሏቸው እንደሆነ ማየት ያስፈልጋል።

እዚህ ላይ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ  አንድ ጥሩ ምሳሌ ልስጥ፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አንድ መኖሪያ ቤት የተከራየው 15,000 ብር ነው እንበል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ  ለሁለት ዓመት የሚቆይ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ዕርምጃ የተወሰደ ቢሆንና በዕርምጃው  መጨረሻ የቤቱን ኪራይ ዋጋ 10,000 ብር የማድረግ አቅም ይኖረዋል ብለን እናስብ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የማይክሮ ኢኮኖሚው ፖሊሲ የከተማው አስተዳደር የቤት ኪራይ ዋጋ በነበረበት 15,000 ብር  መቀጠል አለበት ብሎ ቢወስን፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ውጤቱ ላይ ተፅዕኖ አሳደረበት ማለት ነው። 

ስለዚህ ይህ እንዳይፈጠር ሁለቱም የፖሊሲ ዕርምጃዎች እየተናበቡ መሥራት አለባቸው። ከዚህ ውጪ ከሆነ ግን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ዕርምጃ እየተወሰደ ባለበት ጊዜ ውስጥ፣ የማይክሮ ፖሊሲ ዕርምጃዎች ባይወሰዱ ጥሩ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ዕርምጃ ሲወሰድ የገበያው ዋጋ ትክክለኛ ቦታውን እስኪይዝ ድረስ ኢኮኖሚውን የመበጥበጥና ድርጅቶችን የማስደንገጥ ባህሪ ስላለው፣ የማይክሮ ፖሊሲ ባለሙያዎች  ሥራ መሆን ያለበት ዕርምጃው ሲወሰድ ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦችንም ሆነ ድርጅቶችን ማረጋጋትና መደገፍ መሆን አለበት። 

የማክሮ  ኢኮኖሚ ፖሊሲ ዕርምጃው  በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ውጤት ካመጣ  በቋሚነት ቦታውን መያዝ አለበት። ይህም ማለት የፖሊሲ ወለድ ምጣኔው በቋሚነት መተመን አለበት፣ የቀጥታ ብድር መጠን ቋሚ  ሕግ ሊኖረው ይገባል፣ የባንኮች ብድር መጠን በብድር ቁጠባ ጥምርታ መጠን ልክ መሰጠት አለበት፣ የበጀት ምደባ በኢኮኖሚው አቅም ልክ መበጀት አለበት። ይህ ከሆነ ዘንድ በማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት የተስተካከለው ኢኮኖሚ ፀንቶ እንዲቆይ፣ በቀጣይነት በማይክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ እየደባበሱ የኢኮኖሚውን ዕድገት ጤናማ አድርጎ ማስቀጠል ነው።  ከዚያ በኋላ የፖሊሲ ዕርምጃው ውጤት ካመጣ ኢኮኖሚው መስመር ይዞ በአግባቡ መጓዝ ይችል ይሆናል። በቀጣይ ችግር እንኳን ቢገጥም የዓለም የኢኮኖሚ ችግር ሲገጥመው የሚጠቀምበትን የወለድ ምጣኔ ፖሊሲ ተጠቅሞ ኢኮኖሚውን ማስተካከል ይቻላል  የሚል ነው።

እስኪ ዓለም  የኢኮኖሚ ችግር ሲገጥመው የወለድ ምጣኔን ተጠቅሞ እንዴት እንደሚያስተካክል እንመልከት፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ የኢኮኖሚ ዕክል ገጥሟት የዋጋ ንረት ምጣኔዋ 9.1 በመቶ ደርሶ ነበር። ለእነሱ ይህን የኢኮኖሚ ዕክል ለማስተካከል ቀላሉ መንገድ የወለድ ምጣኔ ፖሊሲን  መጠቀም ነው። ስለዚህ ይህን ለማድረግ የወለድ ምጣኔአቸው ከነበረበት 0.25 በመቶ ቀስ በቀስ ኢኮኖሚው ሳይንገራገጭ  5.5 በመቶ ላይ አድርሶ  የዋጋ ንረቱ ሁለት በመቶ ላይ ሲደርስ፣ በሒደት ወደ ነበረበት 0.25 በመቶ መመለስ ወይም ገበያው ወደ ሚፈልገው የወለድ ምጣኔ ማስቀመጥ ነው።

በዚህ ሒደት ውስጥ ታዲያ የሚፈለገው ውጤት የዋጋ ንረት ምጣኔው እ.ኤ.አ. ሰኔ 2022 ከነበረበት  9.1 በመቶ ግብ ወደ ተደረገው ሁለት በመቶ የተረጋጋ የዋጋ ንረት ምጣኔ ማውረድና ማስፈን ነው። በዚህ ሒደት ውስጥ ምን ችግር ገጠማቸው የሚለውን ስንመለከት ገና ከጅምሩ ጥቂት ባንኮች ላይ ተፅዕኖ አሳድሮ ከገበያ ሲያስወጣቸው፣ ባለሀብቶችን ደግሞ ለሥጋትና ለጭንቀት ሲዳርግ ተመልክተናል። የሆነው ሆኖ አሁን ውጤቱ ምን ላይ ደረሰ የሚለውን ስንመለከት  የፖሊሲ ወለድ ምጣኔው እ.ኤ.አ. ከሐምሌ 2023 ጀምሮ  ከፍተኛ ጣሪያ 5.50 በመቶ ላይ የተቀመጠ ሲሆን፣ የሚያዝያ ወር 2024 የዋጋ ንረት ምጣኔው ደግሞ 3.4 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል። ይህ የሚያሳየው የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት  የተወሰደው የፖሊሲ  ዕርምጃ   በታቀደው ልክ ውጤት እንዳላመጣ ነው።

ስለዚህ ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን የዋጋ ንረት ችግር ለመፍታት ዓለም አሁን እየተጠቀመበት ያለውን  የወለድ ምጣኔ ፖሊሲ እኛ ደካማ ኢኮኖሚ ላይ ስለማይሠራ፣ መደበኛ ባልሆነና ኋላቀር በሆነ ዘዴ ካስተካከልነው በኋላ ወደፊት ለወለድ ምጣኔ ፖሊሲ ታዛዥ የሆነ ኢኮኖሚ  ከፈጠርን፣ በእሱ በመታገዝ የተረጋጋና ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ መገንባት እንችላለን የሚል ሐሳብ በኢትዮጵያ ፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ ሐሳቡ እንዳለ ይሰማል።

እዚህ ጋ ቆም ብለን ልናየው የሚገባው ነገር አንደኛ እየተጠቀምን ያለው የፖሊሲ መሣሪያ መደበኛ ያልሆነና ኋላቀር በመሆኑ፣ ዕቅዳችንን በተፈለገው ልክ ያሳካል ወይ የሚለውና ይህን ለማሳካት በኢኮኖሚው ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በምን እንክሰዋለን የሚል መሆን አለበት።  ጉዳዩ ይህ ከሆነ የፖሊሲ ዕርምጃ መወሰዱ ትክክል ነው ወይ የሚለውን ጥያቄ ስናቀርብ መልሱ አዎ ትክክል ነው።

እጅና እግርን አጣምሮ ከመቀመጥ ባለው ነገር መታገል በጣም ተገቢ ነው። ምክንያቱም የዋጋ ንረት ባለበት ሁኔታ ስለኢኮኖሚ ዕድገት ማሰብ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው።  በአሁኑ ጊዜ የአንድን አገር ኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣትና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ ጥቅም ላይ የሚውለው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ በጣም ወሳኝ ነው። አሁን አሁን ዓለም እየተጠቀመባቸው ያሉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሣሪያዎች እየተዳከሙና አቅም እያነሳቸው መጥተዋል። 

ይህ ባለበት ሁኔታ አዳዲስ የኢኮኖሚ የፖሊሲ ሞዴሎች ሲመጡ አገሮች ትኩረት መስጠትና ፈትሸው ጥቅም ላይ ማዋል ይጠበቅባቸዋል። ስለዚህ ኢትዮጵያ ካደጉ አገሮች ተርታ መሠለፍ የምትችለው፣ በዜጎቿ የሚቀርቡላትን አዳዲስ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሐሳቦችና ሞዴሎችን ትኩረት ሰጥታ ስትቀበልና ጥቅም ላይ ማዋል ስትችል ነው።
      ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የኢኮኖሚና የባንክ ባለሙያ ሲሆኑ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...