Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየ‹‹ክብር ዶክትሬት›› ዲግሪ ጉዳይ

የ‹‹ክብር ዶክትሬት›› ዲግሪ ጉዳይ

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

‹‹የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ግልጽ የሆነ መመርያ እስኪወጣ ድረስ እንዳይሰጥ በጊዜያዊነት ታገደ›› የሚል መረጃ ከትምህርት ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ከተነገረ አንድ ወር አልፎታል፡፡ እንደ መግለጫው ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬት ዲግሪ አሰጣጥን፣ አሰያየምንና አጠቃቀምን በተመለከተ የተሟላ የአካሄድ መረጃ የሚሰጥ መመርያ ማዘጋጀት እንዳለባቸውም መነገሩ ይታወሳል።

ይህ የተባለው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ ‹‹የክብር ዶክትሬት ሽልማትና የዶክትሬት ትምህርት በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ የክብር ዶክትሬት ሽልማትን በተመለከተ  ማስረሻ ፈጠነ (ፕሮፌሰር) ባቀረቡት ሰፊ የጥናት ጽሑፍ የክብር ዶክትሬት ሽልማት እንጂ ለመጠሪያነት እንደማይውል ያስረዱ ሲሆን፣ እንዲሁም ረዳት ፕሮፌሰር ወይም ተባባሪ ፕሮፌሰር የሚለውም ስያሜም ለመጠሪያነት አይውልም በማለት መናገራቸውም የሚታወስ ነው፡፡

በወቅቱ የትምህርት ሚኒስቴር የክብር ዶክትሬት ዲግሪ አሰጣጥን በተመለከተ መመርያ ማውጣት እንደሚገባው በማስረሻ (ፕሮፌሰር) እና ሌሎች ምሁራን የተነገረው ምክረ ሐሳብ ሰሚ አግኝቶ መሰለኝ፣ ደመ ነፍሳዊው የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ በጊዜያዊነት እንዲታገድ የተደረገው የሚል ግምት አለኝ (ቀደም ብሎ ታስቦበትም ሊሆን ይችላል)፡፡

በመሠረቱ ‹‹የክብር ዶክትሬት ዲግሪ›› የሚባለው አንዳችም አካዴሚያዊ መሠረት ሳይኖር፣ ከዩኒቨርሲቲው የትምህርት ሥርዓት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ሳይኖረው ማለትም የማትሪክ ውጤት ሳይኖረው፣ የመግቢያ ፈተና ሳይወሰድ፣ ክፍል ገብቶ ሳይማር፣ ሳይፈተን፣ ማለፊያ ነጥብ ሳይጠየቅ፣ የመጀመሪያ ዲግሪ ሳያገኝ፣ የምርምር ሥራ ሳይሠራና ዩኒቨርሲቲዎች ባላቸው ቻርተር መሠረት ለታዋቂ ሰዎች የሚሰጡት የክብር ሽልማት ነው፡፡

ተማሪዎች ትምህርታቸውን ተከታትለው ጊዜያቸውን ቀን በክፍል ውስጥ፣ ማታ በጥናት ደክመው የመመረቂያ ጽሑፍ አቅርበው ተፈትነው ያገኙት ዲግሪ በሥራ የተገኘ ዲግሪ (Earned Degree) ሲሆን፣ የትምህርት መሥፈርት ሳይኖረው በመደበኛ ሥራው ወይም በማኅበራዊ ተሳትፎው ባገኘው መልካም ስም ብቻ የሚሰጠው ደግሞ ‹‹የክብር ዲግሪ›› (Honoris Causa) ይባላል፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዓለም ታሪክ የተመዘገበውን የመጀመሪያ የክብር ዲግሪ የሰጠው ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ተሸላሚም ሊዮኔል ውድቪሌ ይባላል፡፡ ዘመኑ እ.ኤ.አ. በ1470ዎቹ ዓመታት መገባደጃ ላይ ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ የክብር ዲግሪ ሽልማት በየአገሩና በዩኒቨርሲቲው ሁሉ በሽበሽ ሆኗል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2018 ብቻ በእንግሊዝ የሚገኙ 117 ዩኒቨርሲቲዎች በአጠቃላይ ለ957 ታዋቂ ሰዎች የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሽልማት ሰጥተዋል፡፡ እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ በአማካይ ስምንት የክብር ዲግሪዎችን ሰጥቷል ማለት ነው፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት ዴቪድ አቴንበርግ 32 የክብር ዲግሪ በማግኘት ቀዳሚ ነው፡፡ የኢንዶኔዥያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሱሃርቶ 26 የክብር ዲግሪዎች አሏቸው፡፡

ኢትዮጵያውያን በደንብ የሚያውቋቸው ሰር ቦብ ጌልዶፍ አሥር የክብር ዲግሪዎች ሲሸለሙ፣ ዕውቁ የእግር ኳስ አሠልጣኝ (ማኔጀር) ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ስምንት የክብር ዲግሪዎች ተሸልመዋል የሚል መረጃ ሰምቻለሁ፡፡ ሪያን ጊግስ የተባለው የኳስ ጥበበኛም የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተሸልሟል፡፡

በየዘርፉ ማለትም በዘፋኝነት፣ በዲጄነት፣ በኮሜዲያንነት፣ በፋሽን፣ በተዋናይነት፣ በእግር ኳስ፣ በአትሌቲክስ፣ ወዘተ በርካቶች ተሸልመዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሽልማት የሚሰጠው ዩኒቨርሲቲዎች የገንዘብ ድጎማ (ፈንድ) ለማግኘት ወይም በዝነኛ ሰዎች መልካም ስም ለመጠቀምና ተማሪዎችንም ያተጋሉ፣ ያበረታታሉና አርዓያ ይሆናሉ በሚሉ ምክንያቶች ነው፡፡

አሁን ግን ይህ የክብር ዶክትሬት ሽልማት ትልቅ ጥያቄና ተቃውሞ እያስነሳ ነው፡፡ የመጀመሪያው ጥያቄ እነዚህ በየራሳቸው ዘርፍ ‹ስመ ገናና› የሆኑ ዝነኛና ታዋቂ ሰዎች የክብር ዶክትሬት ዲግሪ መሸለም አለባቸው ወይ? ይገባቸዋል ወይ? (Do Celebs Deserve Honorary Degrees?) የሚለው ጥያቄ ነው፡፡

በእኛ አገር ሁኔታም በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየታየ ያለው መሸላለም ቅጣ አምባር የሌለው፣ በአብዛኛው ከብሔር ተኮሩ ፌዴራሊዝም ጋር በተያያዘ ከአገራዊ አስተዋጽኦና ክብር ይልቅ፣ ለአካባቢያዊ ተዛምዶ የሚያደላ በመሆኑ በበርካቶች ሲተች ቆይቷል፡፡

ይህንን አስመልክተው አንድ የድሬ ቲዩብ ጦማሪ እንደገለጹት፣ በሥራቸው እጅግም አስተዋጽኦቸው ሳይታወቅ በየክልሉ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች እስካለፈው ዓመት ድረስ በገፍ የክብር ዶክትሬት ሲሰጥ፣ እዚህ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እንኳን የሰው ብሔር የሚለይበት ዘዴ የክብር ዶክትሬቱ አሰጣጥ ነው የሚል ስላቅ እስክንመለከት ከቁምነገርነት የፌዝ ምክንያት ሆኗል ብለው ነበር።

በቅርቡ ነገሩ በጥሞና እንዲፈተሽ የሚያስገድድ አገር አቀፍ መመርያ እስከሚወጣ እስከታገደበት ጊዜ ድረስ፣ በየዓመቱ የክብር ዶክትሬት ጉዳይ መነጋገሪያ ሆኖም ነበር የቀጠለው። ዩኒቨርሲቲዎች የሚወቀሱበትም፣ የሚወደሱበትም መንገድ ስለሆነ ትልቅ አጀንዳ ሆኗል። ብዙ ሰዎች ለጉዳዩ የሚሰጡት ቦታ መላቁ፣ የክብር ዶክትሬት ለብዙ ሰው መሰጠቱን እንደ መርከስ ለማየት ምክንያት ሆኗል። ግን አንድ ሰው ደጋግሞ የሚወስደው የላቀ አበርክቶ አንድ የዕውቅና መንገድ መሆኑ በመረሳቱም ይመስለኛል።

ብዙዎቹ የአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች በተለየ መንገድ ‹‹ፖፑሊስት››ነት ያለው ጠቀሜታ የማረካቸው የሚመስል ከበርካታ ዘርፎች አበርክቶዎች ለኪነ ጥበብ፣ ከኪነ ጥበብ ደግሞ ለሙዚቃ ማመዘን ሲታይባቸውም ታዝበናል የሚሉት ጦማሪው፣ እንደ ቴአትርና ሥነ ጽሑፍ ያሉ ዘውጎች ተረስተዋል። ታላላቆቹ ሠዓሊያን ጭራሽ ለዚህ ክብር አይታጩም። ቴክኖሎጂና ምርምር፣ ማኅበራዊ ኃላፊነትና ዲፕሎማሲ ቦታ አለማግኘታቸውም ያስተዛዝባል ብለው ነበር።

በጸሐፊው አባባል እየከበደ የመጣው ጉዳይ ደግሞ ዩኒቨርሲቲ የሚለውን ስም ይዞ ዩኒቨርሳል ያለመሆኑ ነገር ነው። በአካባቢ የታጠረ ዕይታ ሕዝቡን እየረበሸ ዩኒቨርሲቲዎችን እየማረከ መምጣቱ መቋጫ ሊበጅለት ይገባል።

በእርግጥ አንዳንዴ ለምን ዩኒቨርሲቲዎች ለአካባቢያቸው ለላቀ ባለውለታ ዕውቅና ሰጡ ብሎ የክብር ዶክትሬቱን በደፈናው ማጣጣል ልክ ላይሆን ይችላል። ለአብነት ያህል ቀነኒሳ በቀለን ሌሎች የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስላልሸለሙት የራሱ ጉዳይ ብሎ ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች እንደ አንዱ የሚቆጠረው አርሲ ዩኒቨርሲቲ ሲሸልመው መሽኮርመም የለበትም። ቀነኒሳን ማንም ቢሸልመው የአገር ጀግናና ተከባሪ ነውና፡፡

በጸሐፊው ትዝብት መሠረት የወቅቱ ብሔር ተኮር የፌዴራሊዝም ፈተናና ጫና አበርክቶን ዘውጋዊ መድረጉ የማይሸሸግ መሆኑ ነው። ለምሳሌ ደበበ እሸቱ (በፖለቲካ ተቃርኖውም ሊሆን ይችላል) መቀሌ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክተር ሊያገኝ የሚችልበት ሁኔታ አይኖርም። አንዱ የላቀ የሚለው በሌላው አካባቢ እጅግ አደገኛ የሚባል ሊሆን ይችላል። ይኼ ደግሞ የዩኒቨርሲቲዎችን አካባቢያዊ ቅቡልነት ገደል ከከተተ ለተቋማዊ ጉዞው ጤንነት ሥጋት ይሆናል የሚለው ሒስ የሚጣል አይደልም፡፡

በነገራችን ላይ ሽልማቱ አገራዊ መሥፈርት ኖሮት አካባቢያዊ አስተዋጽኦንም ከግምት ማስገባት ብቻ ሳይሆን፣ ከፖለቲካ አድልኦ ነፃ በሆነ መንገድ በሕይወት የሌሉ ሰዎችን ጭምር እንደሚያካትት የዓለም ተሞክሮ ያሳያል፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን አሁን አሁን ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎች ታዋቂ ሰዎችን ስለመሸለም ያላቸውን ፍላጎት ያቁሙ የሚል መከራከሪያም እየተደመጠ ነው፡፡ ቢያንስ በሦስት ምክንያቶች፡፡

አንደኛው ሐሳብ ዩኒቨርሲቲዎች የተቋቋሙት ለአካዴሚያዊ የትምህርት ተግባር ነው፡፡ ዋነኛ ተልዕኳቸውም የመማር ማስተማሩን ሒደት አጠናክሮ ማስቀጠል፣ ብቁ ምሁራንን ማፍራት፣ ብሔራዊ አቅም ያላቸውን ተማሪዎች ጥራት ባለው ትምህርትና ሥልጠና መፍጠርና ችግር ፈቺ የሆኑ የምርምር ሥራዎችን ማከናወን፣ ወዘተ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ነገር ሁሉ የእነሱን ጣልቃ ገብነት የሚፈልግ አይደለም፡፡ ‹‹ትምህርትና ከትምህርት ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ ትኩረት ያድርጉ›› የሚል አንደምታ ያለው ነው፡፡

ሁለተኛው ሐሳብ ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዲግሪዎችን መስጠት ግድ የሚላቸው ከሆነ ለማን እንደሚሰጡ በቻርተራቸው ግልጽ ያድርጉ፡፡ መደበኛ ሥራውን ብቻ ሠርቶ ዝነኛ ለሆነ ሰው መስጠት ተገቢም አስፈላጊም አይደለም፡፡ ይህ ማለት ለምሳሌ ጆ ብራንድ የተባለችው ኮሜዲያን እ.ኤ.አ. በ2018 ከካንተርበሪ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ያገኘችው በኮሜዲ ሥራዎቿ ዝነኛ ስለሆነች ብቻ አይደለም፡፡

ይልቅ ብራንድ ኮሜዲያን ከመሆኗ በፊት የአዕምሮ ሕክምና (ሳይካትሪ) ነርስ በመሆን አሥር ዓመት ሠርታለች፡፡ ኮሜዲያንም ሆና የአዕምሮ ጤና ችግሮች ላይ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማስተካከልና ለማሳደግ በተጫወተችው ሚና ከፍተኛ ውጤት አሳይታለች፡፡ የሕክምና ትምህርትና ሥራ ከዩኒቨርሲቲ አካዴሚያዊ ጉዳዮች አንዱ በመሆኑ ሽልማቱ ይገባታል ተብሎላታል፡፡

ሌላ የውጭ ተሞክሮ ብንጠቅስ ስቴፈን ሱተን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ከኮቬኒተሪ ዩኒቨርሲቲ አግኝቷል፡፡ ሱተን ለሕፃናት ካንሰር መድኃኒት ለመፈለግ ለሚደረጉ የምርምራ ሥራዎችና ለተደራሽነታቸው ጭምር የሚሆን ከፍተኛ ገንዘብ (ፈንድ) አሰባስቦ በማበርከቱ ሽልማቱ ይገባዋል፡፡ ደሪን ሎረንስ ሕፃን ልጇ ስቴፈን ሎረንስ በወንጀለኞች ጥቃት የተገደለባት በመሆኗ፣ በእሷ ልጅ ላይ የደረሰው በሌሎች ሕፃናት እንዳይደርስ የሕፃናት መብት ተቆርቋሪ አንቀሳቃሽ ሆና ወንጀል እንዲቀንስ ላደረገችው አስተዋጽኦ በዝነኛነቷ ብቻ ሳይሆን፣ ከዘርፏ ውጪ ለሰው ልጆች መብት የቆመች በመሆኗ አምስት የክብር ዲግሪዎችን አግኝታለች፡፡ እነዚህ ለምሳሌ የተጠቀሱ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ክሪስ ማክ ንቨርን የተባሉ ‹‹ዘመቻ ለእውነተኛ ትምህርት›› (Campain for Real Education-CRE) የተባለ ድርጅት መሥራችና ሊቀመንበር እንደተናገሩት፣ ‹‹በእኔ እምነት አንድም አካዴሚያዊና ማኅበራዊ አስተዋጽኦ ለሌላቸው የአርትና የመገናኛ ሰዎች፣ ለእግር ኳስ ተጨዋቾች፣ አሠልጣኞች፣ ወዘተ የክብር ዶክትሬት መስጠት ማለት ሐሰተኛ ሽልማት ለሐሰተኛ ውጤት እንደ መስጠት ነው (Bogus Reward for a Bagus Achievment)፡፡ ስለዚህ የሚሸለሙት ሰዎች በመደበኛ ሥራቸው መሥፈርት የተመረጡ መሆን የለባቸውም፤›› ብለዋል፡፡

ሦስተኛው ሐሳብ ዩኒቨርሲቲዎች ለዝነኛ ሰዎች ዕውቅና ለመስጠት የሚጠቀሙበት አሠራር ‹‹የክብር ዲግሪ›› መሸለም ሳይሆን፣ ሌላ ዓይነትና የሆነ ስያሜ ያለው ለታዋቂ ሰዎች ብቻ የሚሰጥ ለምሳሌ ሜዳሊያ ቢሆን ይመረጣል የሚለው ነው፡፡ የክብር ዶክተር ሊባሉ ግን አይገባቸውም፡፡ የክብር ዶክትሬት መስጠት ለፍተው፣ ደክመው፣ ተምረው በድካማቸው ውጤት ያገኙትን ተማሪዎች የመስደብ ያህል ነው፣ በተማሪዎች ላይ ማፌዝ ነው የሚል አንድምታ ያዘለ ገለጻም ሲነገር ተደምጧል፡፡

ይህንን ሽልማት የማዕረግ ስም አድርጐ መጠቀምንም በተመለከተ ችግር አለ፡፡ በማኅበራዊ ተግባቦት ያለው ግንዛቤ ማንኛውም የክብር ዶክትሬት ተሸላሚ ዶክተር (ዶ/ር) እየተባለ ሊጠራበት፣ ደብዳቤ ሊጻፍለት አይችልም፡፡ ሰጪዎቹ ዩኒቨርሲቲዎችም አብዛኞቹ ‹ዶክተር› የሚለውን ስያሜ ስለመጠቀም የሚከለክል መግለጫ አላቸው፡፡ ይሁን እንጂ ብዙዎች ተሸላሚዎች ‹‹ዶክተር›› የሚለውን መጠሪያ ስለሚፈልጉት፣ በራሳቸው ፈቃድ ‹‹ዶክተር እገሌ›› ነኝ እያሉ ንግግር ያደርጋሉ፣ ይጻጻፋሉ፣ ይፈርማሉ፣ ወዘተ፡፡

ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ በአንድ በኩል የክብር ዶክትሬቱን ያገኙት ከአገሪቱ ሕጋዊ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ስለዚህ በተሰጣቸው የማዕረግ ስም ራሳቸውን ዶክተር የማይሉበት ምክንያት የለም፡፡ አልፈው ተርፈው ‹‹ዶክተር›› የሚለውን ማዕረግ ከስማቸው ፊት አስቀድሞ ላልጠቀሰ አካል፣ ደብዳቤም ሆነ የስብሰባና የግብዣ ጥሪዎች መልስ አይሰጡም፡፡ ‹‹ዶክተር›› ካልተባሉ በምንም ዓይነት ጉዳይ ላይ አይገኙም፡፡ አፍ አውጥተው ‹‹ዶክተር›› በሉኝ ይላሉ (ለነገሩ ከየተራው ድርጅት ተብዬ የሰላም አምባሳደር የሚል ለበጣ እየለጠፉ እንደ ማዕረግ የሚያስነግሩስ ሞልተውን የለ – ልብ ውልቅ!!)፡፡

የአገራችንን ታዳጊነትና የምንገኝበትን ሁኔታ በመረዳት ዩኒቨርሲቲዎች ሥርዓት በተበጀለት መንገድ የክብር ዶክትሬት ይሸልሙ እንበል፡፡ ሽልማቱ ግን አይደለም መላውን ሕዝብ፣ የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብና ተመራቂዎችን እንኳን የማያሳምን እየሆነ ሊቀጥል ግን አይችልም፣ አይገባምም፡፡

እዚህ ላይ አንድ የውጭ ምሳሌ ልጠቀስ፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ ትልቁ የየል ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረበት ጊዜ (1968) በታሪክ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቶ ነበር፡፡ ይህ ተምሮ ያገኘው የትምህርቱ ውጤት ነው፡፡ ነገር ግን ይኸው ዩኒቨርሲቲ እ.ኤ.አ. በ2007 ለጆርጅ ቡሽ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሲሰጠው በዕለቱ ተመራቂ የነበሩ ተማሪዎች፣ ‹‹ቡሽ የክብር ዲግሪ አይገባውም፣ እሱ በሚሸለምበት ሥነ ሥርዓት ላይ እኛ አንመረቅም›› ብለው ምርቃቱን አቋርጠው እስከ መውጣት የደረሱበት ተቃውሞ ታይቶ ነበር፡፡

የእንግሊዟ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርጋሬት ታቸር ምንም እንኳ ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተመረቀች ብትሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበረበችበት ጊዜ ለከፍተኛ ትምህርት የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍ (ፈንድ) እንዲቀነስ በመወሰኗ የተነሳ እ.ኤ.አ. በ1985 ሊሰጣት የነበረውን የክብር ዲግሪ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እንዳታገኝ ወስኖባት ነበር፡፡

እ.ኤ.አ. በ2007 ተቃዋሚዎች የኤደንበርግ ዩኒቨርሲቲ ለፕሬዚዳንት ሙጋቤ በ1984 የሰጠውን የክብር ዲግሪ እንዲመልስ (እንዲሰርዝ) ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡ ሙጋቤ ከ25 ዓመታት በፊት የተሰጠውን የክብር ዲግሪ ለዩኒቨርሲቲው እንዲመልስ ተቃዋሚዎች በግልጽ ጠይቀዋል፡፡

ሙጋቤ በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በፖለቲካ ሙስና የተዘፈቀ ስለሆነ፣ የኤደንበርግ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዲግሪ አይገባውም በማለት በተቀጣጠለው ተቃውሞ የሙጋቤን የክብር ዲግሪ ዩኒቨርሲቲው ሰርዟል፡፡ የሚቺጋን ዩኒቨርሲቲም ለሙጋቤ የሰጠውን የክብር ዲግሪ ውድቅ አድርጓል (በእርግጥ ይህንን ከፖለቲካ ጥላቻ ጋር አያይዘው የሚተቹትም ነበሩ)፡፡

በአጠቃላይ የትምህርት ሚኒስቴር ለክብር ዶክትሬት አሰጣጥና ተዛማጅ ተግባራት ወጥ ሕግ ወይም ስታንዳርድ አውጥቶ በሥሩ ላሉ የአገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለመስጠት ማቀዱ ቢዘገይም መበረታታት ያለበት ነው፡፡ በየትም አገር የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ከአካዴሚክስ ጋር ባልተገናኙ ጉዳዮች ላይ ‹‹የክብር ዶክትሬት›› ለሚባል ሽልማት ያላቸውን ፖሊሲ እንደገና እየመረመሩና እያሻሻሉ በመራመድ ላይ ናቸውና፡፡ የትምህርት ማዕከላቱም ለመመርያው ተፈጻሚነት ከመትጋት ባሻገር ለክብርና አርዓያነት ቢጨነቁ ይገባል፡፡

ሰላም!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...