Wednesday, July 24, 2024

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡ ይታወሳል፡፡ ይኼው የበጀት ዕቅድ ማክሰኞ ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በጀቱ መፅደቁ የሚጠበቅ ቢሆንም ከዚያ ይልቅ ይዞት የመጣው የቁጥር ጭማሪ መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኗል፡፡ አምና ሊባል በቀረበው በተገባደደው የ2016 በጀት ዓመት ሥራ ላይ ከዋለው በጀት አዲሱ ዕቅድ ያለው ብልጫ፣ እንዲሁም ዝርዝር ጉዳዮች ሰፊ ትኩረት አግኝተዋል፡፡

ከሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ባለው አንድ ዓመት መንግሥት በሥራ ላይ ሊያውለው ያቀደው በጀት፣ የተለያዩ ሥራዎችና አገልግሎቶችን ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሏል፡፡

ለአንድ ዓመት በአጠቃላይ 971 ቢሊዮን 200 ሚሊዮን 665 ሺሕ 909 ብር በጀት ነው የቀረበው፡፡ ከዚህ በጀት ውስጥ ደግሞ ከፍተኛውን ወጪ ወይም 451 ቢሊዮን 307 ሚሊዮን 221 ሺሕ 52 ብር የሚወስደው የመደበኛ በጀት መሆኑ ታውቋል፡፡ ደመወዝና መደበኛ አገልግሎት አሁንም ከፍተኛ ፈሰስ የሚወስድ ዘርፍ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የካፒታል ወጪዎች በሚል ለመሠረተ ልማት ግንባታና ለልማት ሥራዎች የቀረበው የበጀት መጠን ሁለተኛው ከፍተኛ መጠን ያለው የበጀት ዓይነት ነው፡፡ ለዚህ ዘርፍ በ2017 ዓ.ም. የተያዘው 283 ቢሊዮን 199 ሚሊዮን 335 ሺሕ 412 ብር መሆኑ ታውቋል፡፡

ለክልሎች የሚከፋፈለው የድጎማ በጀት ደግሞ 222 ቢሊዮን 694 ሚሊዮን 109 ሺሕ 445 ብር ነው ተብሏል፡፡ ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያነት ደግሞ 14 ቢሊዮን ብር በጀት መያዙ ታውቋል፡፡

የመንግሥት ረቂቅ በጀት እንዳመለከተው የፌደራል መንግሥቱ በጀቶች የሚባሉት ሁለቱ የመደበኛ ወጪና የካፒታል ወጪ በጀቶች 734 ቢሊዮን 506 ሚሊዮን 156 ሺሕ 464 ብር በድምሩ ድርሻ ያላቸው ናቸው፡፡

መንግሥት ለክልሎች ብሎ ያቀረበውን 222 ቢሊዮን ብር በጀት ደግሞ ከመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ፣ ከውጭ አገር ብድርና ዕርዳታ ለመሸፈን እንዳቀደ አሳውቋል፡፡ ከመንግሥት ግምጃ ቤት 215 ቢሊዮን፣ ከውጭ አገር ብድር 5.4 ቢሊዮን እንዲሁም ከውጭ አገር ዕርዳታ 1.9 ቢሊዮን ብርን ለማግኘት ማሰቡን አስቀምጧል፡፡

ለክልሎች ከሚከፋፈለው የድጎማ በጀት ውስጥ ደግሞ ኦሮሚያ 74 ቢሊዮን 859 ሚሊዮን 218 ሺሕ 535 ብር በማግኘት ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ አማራ ክልል ደግሞ 46 ቢሊዮን 922 ሚሊዮን 783 ሺሕ 527 ብር በጀት ተመድቦለታል፡፡

ሶማሌ ክልል 21.6 ቢሊዮን ብር በመያዝ በሦስተኛ ደረጃ ተቀምጧል፡፡ አዲሱ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 15.3 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞለት አራተኛ ላይ ተቀምጧል፡፡

ቀጣይ ደረጃ ላይ የሚገኘው ትግራይ ክልል 13 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞለታል፡፡ አዲሱ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 12 ቢሊዮን፣ ሲዳማ 8.9፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ 6.7 ቢሊዮን ብር በጀት ሲያዝላቸው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደግሞ 5.4 ቢሊዮን ብር ቀርቧል፡፡

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 3.9 ቢሊዮን ብር፣ ጋምቤላ 2.8 ቢሊዮን ብር በጀት ሲያዝላቸው፣ ድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር 1.9 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ሐረሪ ክልል 1.6 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞላቸዋል፡፡ ፈደራል መንግሥቱ ከዚህ የድጎማ በጀት በተጨማሪም ለዘላቂ ልማት ማስፈጸሚያ ብሎ የያዘውን የ14 ቢሊዮን ብር በጀት ለሁሉም ክልሎች በቀመሩ መሠረት እንደሚያከፋፍል በረቂቁ በጀቱ ላይ ቀርቧል፡፡

ለመደበኛ በጀት የተመደበውን 451 ቢሊዮን ብር ከፍተኛ በጀት ከ2016 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር ከነበረበት 370 ቢሊዮን ብር፣ 87 ቢሊዮን ብር ወይም 21.93 በመቶ ጨምሮ መመደቡን ረቂቁ ይናገራል፡፡ ይህን የ451 ቢሊዮን ብር ዕቅድ በጀት በተለያዩ ንዑስ ዘርፍች ሲደለድል ደግሞ አስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት 106 ቢሊዮን ብር ወይም 27 በመቶ ድርሻ እንዳለው ይገልጻል፡፡ በ2016 ዓ.ም. ለአስተዳደርና ለጠቅላላ አገልግሎት 80.61 ቢሊዮን ብር መመደቡን በማስታወስ ንዑስ ዘርፉ ጉልህ የበጀት ጭማሪ እንዳለው ያመላክታል፡፡

በመደበኛ በጀት ሥር ከፍተኛ ትኩረት ያገኘው ሌሎች በሚል ንዑስ ዘርፍ የቀረበው ሲሆን፣ ይህም የበጀት ድጋፍን፣ ዕዳ ክፍያንና መጠባበቂያን ይጨምራል፡፡

ለበጀት ድጋፍ 46 ቢሊዮን ብር፣ ለመጠባበቂያ 96 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ዕዳ ክፍያ 139 ቢሊዮን ብር የተያዘላቸው ሲሆን፣ ‹‹ሌሎች›› በሚል የቀረበው የመደበኛ ወጪ ንዑስ በጀት ዕቅድ በድምሩ 267 ቢሊዮን ብር ወይም 59 በመቶውን የዘርፉን በጀት እንደሚያገኝ ተቀምጧል፡፡

በሌላ በኩል ለኢኮኖሚ ጉዳዮች ማስፈጸሚያ 8.4 ቢሊዮን (1.9 በመቶው)፣ ለማኅበራዊ ጉዳዮች ማስፈጸሚያ 68.19 ቢሊዮን (15.1 በመቶ) የመደበኛ በጀቱ እንደተደለደለ ተመላክቷል፡፡

በዚሁ የመደበኛ ወጪ በጀት ሥር በአስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ንዑስ ዘርፉ ሥር የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የፖሊስ፣ የጉምሩክ፣ የውጭ ጉዳይ፣ የማረሚያ ቤቶች፣ የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ፣ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መሥሪያ ቤቶች የበጀት ድልድል ተቀምጧል፡፡

በ2016 የእነዚህን መሥሪያ ቤቶች በጀት ያቀፈው የአስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ዘርፍ 80 ቢሊዮን ብር ተመድቦለት የነበረ ሲሆን፣ በ2017 በጀት ዓመት ግን 26 ቢሊዮን ብር ወይም 32.55 በመቶ አድጎ 106 ቢሊዮን ብር እንደተመደበለት በረቂቁ ተመላክቷል፡፡ ለማኅበራዊ እንዲሁም ለኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ማስፈጸሚያ በሚል የተመደቡት በጀቶች ላይ ከ26 በመቶ እና ከ28 በመቶ የዘለለ ጭማሪ ከአምናው አለመደረጉ፣ እንደ መከላከያና ደኅንነት ለመሳሰሉ ዘርፎች በጀቱ ከፍ ያለ ትኩረት እንደሰጠ ማሳያ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

እነዚህንና ሌሎችም እጅግ በርካታ ዝርዝር ጉዳዮችን አካቶ ያቀረበውና ማክሰኞ ዕለት በፋይናንስ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ አማካይነት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በንባብ የቀረበው ረቂቅ በጀቱ ለውይይት የሚጋብዝ ጉዳዮችም ይዟል፡፡ የበጀት ረቂቁ የማክሮ ኢኮኖሚ ሥርዓት ለማቃናት የሚረዳ ስለመሆኑ ተነግሯል፡፡ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር የአገር ውስጥ ገቢን ማሳደግ፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን ማፋጠን፣ ኢንቨስትመንትን፣ የወጪ ንግድን፣ የኢኮኖሚ አጋርነትን ማጠናከርን ሁሉ ታሳቢ በማድረግ ረቂቁ ስለመቅረቡ ተነግሯል፡፡

ይሁን እንጂ በጀቱ የአገሪቱን ሥር የሰደዱ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ችግሮች ለማቃለል በሚያስችል መንገድ የቀረበ ነው ወይ የሚለው ጥያቄ ያጭራል፡፡ የበጀት ረቂቁ ድህነት ቅነሳን ግብ ያደረገ ወይስ ድህነትና የዋጋ ንረትን አባባሽ የሚለውም ውይይትን ይጋብዛል፡፡ በሌላ በኩል የመንግሥት በጀት አገራዊ የብድርና ዕዳ ጫናን የሚያባብስ ወይስ የሚቀንስ የሚለውም ያከራክራል፡፡ መንግሥት አገሪቱ በፈጣን ሁኔታ እንደምታድግ ታሳቢ በማድረግ ያቀረብኩት ነው ያለው የበጀት ረቂቅ አገሪቱ የተዘፈቀችበትን ግጭት፣ ጦርነት፣ መፈናቀል፣ ድርቅ፣ ረሃብ፣ የአካባቢ ተፅዕኖና ሌሎች ሰብዓዊ ቀውሶችን ያገናዘበ ነው ወይ የሚለውም እያነጋገረ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከተሸከመችው ውስብስብ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች በተጨማሪ የምትገኝበት ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የጂኦ ፖለቲካ ከባቢ አየርም በረቂቅ በጀቱ ታሳቢ ተደርጓል ወይ የሚለው ሐሳብ እየጋበዘ ነው፡፡ መንግሥት አሁን ባለው በአዲስ አበባና በዋና ዋና ከተሞች ዙሪያ ብቻ የተገደበ መዋቅራዊ ጤናማነትን ታሳቢ በማድረግ፣ እንዲሁም በአገሪቱ የሚታየውን ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮና ተንቀሳቅሶ የመነገድ ፈተና ግምት ውስጥ በማስገባት አገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደሩን በአግባቡ ለመምራት እንደሚቸገር የሚገምቱ በርካታ ናቸው፡፡ ይህን መሰል ሥጋት ቢነሳም የበጀቱ ባለቤት መንግሥት ግን ታክስ አሰባሰቡ፣ ኤክስፖርቱ፣ ንግዱ፣ ኢንዱስትሪውና ሌላውም ጤናማ በሆን መንገድ እንደሚያድግ ነው ተስፋውን ሲገልጽ የተደመጠው፡፡

መንግሥት የሚሰበስበውን ገቢ ከ600 ቢሊዮን ብር በላይ የማሳደግ ዕቅድ እንዳለውም አስታውቋል፡፡ ካቻምና ከነበረው የአምናው በጀት ላይ የተጋነነ ጭማሪ ሳይደረግ የታለፈ ቢሆንም፣ ለ2017 በጀት ዓመት ግን ከአምናው በ160 ቢሊዮን ብር የጨመረ በጀት የያዘው የተሻለ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት በአገሪቱ እየተፈጠረ ነው በሚል ዕሳቤ እንደሆነ ገልጿል፡፡  

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ጌታቸው ጳውሎስ ግን ይህን አይስማሙበትም፡፡ ማክሮ ኢኮኖሚው መታመሙን ነው የሚናገሩት፡፡ ለአብነት ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት በአገሪቱ መኖሩ፣ የሥራ አጥነት አኃዝ ከፍተኛ መሆኑ ማሳያ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአመዛኙ በግብርና ላይ ጥገኛ ነው፡፡ የአብዛኛው ሰው የገቢ ምንጭ ግብርና ነው፡፡ አሁን የምናየው ተጨባጭ የአገሪቱ ሁኔታ ግን ለግብርና ሥራ የተመቸ አይደለም፡፡ በአማራም ሆነ በኦሮሚያ ሰላማዊ ሁኔታ የለም፡፡ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያን ጨምሮ የግብርና ግብዓቶች ችግርም ይታያል፡፡ አንድ አገር በጀት የሚይዘው እኮ በመጀመሪያ የሚያገኘውን ገቢ ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አንድ ትሪሊዮን ብር በጀት የሚሸከም አቅም አለው ወይ የሚለው ያጠራጥረኛል፤›› በማለት ነው ያስረዱት፡፡

አቶ ጌታቸው ሲቀጥሉ አሁን ያለው የመንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ይሁን ሌላ ግልጽና የጠራ እንዳልሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹መንግሥት በኢሕአዴግ ዘመን በኢኮኖሚው የራሱን ጣልቃ ገብ ሚና በማሳረፍ፣ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ወደ ግል በመሸጥ (ፕራይቬታይዝ በማድረግ)፣ እንዲሁም ከሕዝብ በሚሰበስበው ቀረጥና ታክስ ነበር ገቢ የሚያመነጨው፡፡ የአሁኑ መንግሥት ያን የማይከተል ከሆነ ግን በቀጥታ በቀረጥና ታክስ ገቢ ላይ የተንጠለጠለ የገቢ ምንጭ ብቻ ነው ያለው ማለት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የሚሰበሰብ ገቢ ደግሞ አስተማማኝ ደረጃ ላይ የደረሰ ባለመሆኑ በጀቱ ከፍተኛ ጉድለት ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ ይህን ጉድለት የሚሞላበት መንገድ ደግሞ የዋጋ ንረት፣ ላይ አባባሽ ተፅዕኖ ያለው ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ካልሆነም ተፅዕኖው የታክስና የቀረጥ ጫና ሕዝቡ ላይ ሊያሳርፍ ይችላል፤›› በማለት ነው ሐሳባቸውን ያከሉት፡፡

በግላቸውም የንግድ ሥራ እንደሚሠሩ ጠቅሰው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከጊዜ ወደ ጊዜ መቀዛቀዝና መኮማተር እንደሚታበት ይገልጻሉ፡፡ አብዛኛው የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድባት ትልቋ ከተማ አዲስ አበባ ብትሆንም፣ በከተማው የሚካሄደው የኮሪደር ልማትና የመናፈሻ ሥራ ያን የንግድ እንቅስቃሴ እንዳቀዘቀዘው ይናገራሉ፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ ከንግዱ ማኅበረሰብ የሚሰበሰበው ገንዘብ እንደሚቀንስ ነው አቶ ጌታቸው ያስረዱት፡፡

‹‹የበጀት ጭማሪው የሚፈስበት የኢኮኖሚ መስክ የድህነት ቅነሳ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል፡፡ ለምሳሌ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ ብዙ ፈሰስ ከዋለ፣ የግብርናውን መስክ የሚያነቃቃ የመስኖ ሥራ ላይ ወይ የግብርና ግብዓት ማምረት ላይ ሰፊ ሀብት ከፈሰሰ፣ ትርጉም ያለው የሥራ አጥነት ቅነሳና የድህነት ቅነሳ ሊኖር ይችላል፤›› በማለት ባለሙያው ሐሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ የኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ዋሲሁን በላይ በበኩላቸው፣ በ2014 ዓ.ም. በጀቱ 40 ከመቶ ቢጨምርም በ2015 ዓ.ም. ግን እጅግ ዝቅተኛ የሚባል ከሁለት ከመቶ በታች መጨመሩን አስታውሰዋል፡፡ ባለፈው ዓመት መንግሥት በበጀት ጉዳይ ላይ እጁን ማሳጠሩና ቆንጠጥ ማለቱ ለዋጋ ግሽበት ዝቅ ማለት አስተዋጽኦ ነበረው በሚል ሲወደስ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

‹‹ዘንድሮ ጥሩ ነገሩ ስህተትን በማመን ነው የበጀት ረቂቁ የቀረበው፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚው መታመሙን፣ የፊሲካል ፖሊሲው ጉድለት ያለበት መሆኑን፣ አጠቃላይ ኢኮኖሚው የገጠሙትን ፈተናዎች በዝርዝር ጠቃቅሶ መጀመሩ ጠቃሚ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር አልተቻለም ብሎ ቃል በቃል ይናገራል፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ያመነውን ችግር ደግሞ በሌላ ጥፋት ሊያጠፋው ይሞክራል፡፡ የዋጋ ንረቱን በግንቦት ወር ከነበረው 27 በመቶ ወደ 12 በመቶ ለመቀነስ ታቅዷል ይልሃል፡፡ ይህ እኮ ከመቶ በመቶ በላይ ቅናሽ ማለት ነው፡፡ ዓመቱን ሙሉ ለፍተህ ያላሳካኸውን በጀት ስታቀርብ መልሰህ አሳካዋለሁ ብለህ ማቀረቡ ዕቅድ አይሆንም፡፡ በየዓመቱ የዋጋ ግሽበትን ወደ አንድ ዲጂት ስለማውረድና ከመቶ በመቶ በላይ ስለመቀነስ ነው የሚወራው፡፡ ነገር ግን ውጤቱ ሲመጣ አይታይም፡፡ የዘንድሮው በጀት ዕቅድ ላይም ይህን መሰል የቁጥር መዳፈርና የቁጥር ጨዋታ ታዝቤያለሁ፤›› በማለት የዕቅዱን አዎንታዊና አሉታዊ ጎኖች ተናግረዋል፡፡

አቶ ዋሲሁን የውጭ ዕርዳታና ብድር መቀነሱ የሚታወቅ ችግር መሆኑን ያወሳሉ፡፡ የዘንድሮው በጀት ረቂቅ ላይም ጉድለቱን በአገር ውስጥ ብድር በዋናነት ለመሸፈን እንደታቀደ መቀመጡን ይጠቅሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ በተቃራኒው ደግሞ ዕዳ ለመክፈል ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያውልም ይናገራል፡፡ ‹‹መንግሥት 70 እና 80 ቢሊዮን ብር ዕዳ ከፍሎ ተመልሶ ደግሞ 150 እና 300 ቢሊዮን ብር የሚበደር ከሆነ ዕዳው ዞሮ ዞሮ ጨመረ እንጂ አልቀነሰም፡፡ በጀቱን ጨምሮ ማቅረቡ መንግሥት ያለበትን የበጀት ጉድለት ብቻ ሳይሆን የብድር ዕዳም የሚያንር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በጀቱ በጥንቃቄ መመርመር ይኖርበታል፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

አቶ ዋሲሁን ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉ፣ ‹‹በጀት ፖለቲካ ነው፡፡ የመንግሥት ወጪ ማለት የመንግሥት ዕቅድና ዓላማ የሚወራበት ነው፡፡ በእኛ አገር እንደ አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ ያሉ ተቋማት ለሚያወጡት የኢኮኖሚ አኃዝ ሪፖርት የመመሰጥን ዝንባሌ እታዘባለሁ፡፡ በዓለም አምስተኛ፣ በአፍሪካ አራተኛ፣ ስድስተኛ ሆናችኋል ለመባል የመጓጓት ነገር ይታያል፡፡ በፖለቲካ ውስጥ ወድቀህ የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ቀዝቅዞ ማክሮ ኢኮኖሚው እየተፈተነ የተጋነነ የኢኮኖሚ አኃዝ መደርደሩ ትርጉም የለውም፡፡ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚፈልጉ ዜጎች ጨምረው ስለጠቅላላ አገራዊ ዕድገቱ ወይም በጀቱ አደገ የምትል ከሆነ ችግር አለ፤›› በማለት ነበር ሐሳባቸውን የደመደሙት፡፡

ዘንድሮ የበጀት ዕቅድ ከመቅረቡ ቀደም ብሎ በየዓመቱ ግንቦት አጋማሽ ይቀርብ የነበረው የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሪፖርት አለመቅረቡ ሌላ መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኗል፡፡ መንግሥት በየዓመቱ የሚመድበው በጀት ምን ላይ እንደዋለ ለማወቅ፣ በአግባቡ ሥራ ላይ የዋለውንና የባከነውን ለመለየት የሚያግዘው የዋና ኦዲተር ሪፖርት አለመቅረቡ፣ የበጀት ረቂቁ ትልቅ ግብዓት የጎደለው ያደርገዋል እየተባለ ነው፡፡

ተጠሪነቱ በቀጥታ ለፓርላማ የሆነውንና ደጋፊ ተቋማት ውስጥ የሚመደበው ዋና ኦዲተር በየዓመቱ የሚያቀርበው ሪፖርት የመንግሥት ተቋማትን ለመቆጣጠርና በሥርዓቱ ለመምራት የማይተካ ሚና ያለው ነው ይባላል፡፡ ዘንድሮ የበጀት ረቂቁ ለፓርላማው ሲቀርብ የብክነትና የሀብት አጠቃቀም ቁጠባ ጉዳይ ተደጋግሞ ሲነሳ ተደምጧል፡፡ ይህን መሰሉን ሥጋትና ሌላም ከበጀት አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚረዳው የዋና ኦዲተር ሪፖርት ከበጀት ረቂቁ ቀድሞ ለፓርላማው አለመቅረቡ በተለያዩ ወገኖች በጉድለትነት ተነስቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -