Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል አዲስ ረቂቅ መመርያዎችና አዋጅ አዘጋጅቶ ባለድርሻ አካላት እንዲመክሩበት እያደረገ ነው፡፡

ከእነዚህ ረቂቅ መመርያዎችና አዋጅ ጋር ተያያዥ የሆኑ በተለይ የባንክ ፈቃድና ቁጥጥርን የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን የማሻሻል ሥራው የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱም እየተነገረ ነው፡፡

በቅርቡ ፀድቀው ሥራ ላይ ይውላሉ ተብለው የሚጠበቁት ረቂቅ መመርያዎች ከዚህ ቀደም ከነበሩት መመርያዎች ለየት ብለው የቀረቡና አዳዲስ ድንጋጌዎችን የያዙ ስለመሆኑ ታውቋል፡፡ በረቂቁ የባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ውስጥ መግባት የሚችሉበትን አሠራር ጨምሮ፣ ሌሎች አዳዲስ ድንጋጌዎች ታክለውበት የሚወጣ ስለመሆኑ ታውቋል፡፡

አሁን ባለድርሻ አካላት ሐሳብ እየሰጡባቸው ናቸው በተባሉ ረቂቅ መመርያዎች ውስጥም አዳዲስ ድንጋጌዎች ተካትተዋል፡፡ የፋይናንስ ተቋማትን የሚመሩ የቦርድ ዳይሬክተሮች ሥራ አስፈጻሚዎችና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ለሚሰጣቸው የኃላፊነት ቦታ ምን ማሟላት እንደሚገባና አጠቃላይ ኃላፊነታቸውን በዝርዝር ያስቀመጠም ነው፡፡

በተለይ በአንደኛው መመርያ እንደ አዲስ ከተካተቱት ውስጥ የቦርድ ዳይሬክተሮች ውስጥ ገለልተኛ የሚባሉ የቦርድ ዳይሬክተሮች መካተት እንደሚኖርባቸው አመልክቷል፡፡

የፖለቲካ ተሿሚዎች የቦርድ ዳይሬክተር ሆነው ማገልገል እንደማይችሉ የሚጠቅስ አንቀጽ ተካትቶባቸዋል፡፡ በአዲሱ ረቂቅ እንደ አዲስ ከተካተቱ አንቀጾች ውስጥ፣ ገለልተኛ የሚባሉ የቦርድ አባላት በባንክ ቦርድ ውስጥ መካተት እንደሚኖርባቸው ያስገድዳል፡፡ እነዚህ ገለልተኛ የቦርድ ዳይሬክተሮች በባንኩ ውስጥ ምንም ዓይነት የአስተዳደር ኃላፊነት የሌለባቸው የፖለቲካ ወይም የባለቤትነት ተፅዕኖ የማይኖራቸውና የባንኩ ባለአክሲዮን ያልሆኑ ባለሙያዎች እንደሚሆኑ በረቂቁ ተመልክቷል፡፡ ሙያዊ ሥራ የሚሠሩ ስለመሆኑም ኃላፊነታቸውን በተመለከተ በረቂቁ ውስጥ የቀረቡ ዝርዝር ጉዳዮች ያመለክታሉ፡፡  

በረቂቁ መመርያው መሠረት ገለልተኛ የቦርድ ዳይሬክተሮች ከጠቅላላው የቦርድ አባላት ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆነውን መያዝ የሚገባቸው እንደሆነም ተብራርቷል፡፡ እነዚህ ገለልተኛ የቦርድ አባላት የአገር ውስጥ ፖለቲከኞች ለምሳሌ ከንቲባ፣ የፖለቲካ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ የካቢኒ አባል (ሚኒስትር ወይም ሚኒስትር ደኤታ)፣ የፌዴራል ወይም የክልል ፓርላማ አባል የገለልተኛ የቦርድ ዳይሬክተር ሆነው ማገልገል እንደሚችሉ በግልጽ አስቀምጧል፡፡

‹‹ገለልተኛ ዳይሬክተር›› በመባል የሚጠቀሱት ሰዎች በባንኩ ውስጥ ምንም ዓይነት የአስተዳደር ኃላፊነት የሌላቸው በውስጥም ሆነ በውጭ፣ በፖለቲካ ወይም በባለቤትነት ተፅዕኖ ውስጥ የቦርድ አባላትን ተጨባጭ ውሳኔ እንዳይሰጡ ማስደረግ የሚችሉና የቦርድ አባል ያልሆኑ በሚል ገልጿቸዋል፡፡ እነዚህ ገለልተኛ የቦርድ ዳይሬክተሮች በአንድ የፋይናንስ ተቋም ውስጥ ከጠቅላላው የቦርድ አባላት ቢያንስ አንድ ሦስተኛ ሊሆኑ እንደሚገባም ያሳያል፡፡

በአዲሱ መመርያ በባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ውስጥ የሚገባ አንድ ዳይሬክተር ከታወቀ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪና ቢያንስ ሰባት ዓመት ልምድ ያለው መሆን አለበት በሚል የተቀመጠ ሲሆን፣ ከአራት በላይ ድርጅቶች ውስጥ ዳይሬክተር የሆነ ማንኛውም ሰው ደግሞ ከአሁን በኋላ የባንክ የቦርድ ዳይሬክተር አባል መሆን እንደማይችልም በአዲሱ ረቂቅ መመርያ ተካትቷል፡፡

በረቂቁ ገለልተኛ ዳይሬክተር ከባንክ፣ ከሒሳብ አያያዝ፣ ከኦዲቲንግ፣ ከፋይናንስ፣ ከቢዝነስ ማኔጅመንት፣ ከኢኮኖሚክስና ተዛማጅ የፋይናንስ ዘርፎች ጋር በተያያዙ የትምህርት ዘርፎች ከታወቀ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የማስተርስ ዲግሪ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ገለልተኛ ዳይሬክተር በፋይናንሻል ዘርፍ ወይም በፋይናንሻል ዘርፍ የማማከር፣ ወይም የኦዲት ወይም የአደጋ አስተዳደር ወይም ሌሎች ተዛማጅነት ያላቸው የሥራ መስኮች ቢያንስ አሥር ዓመታት ልምድ ሊኖራቸው እንደሚገባም ታውቋል፡፡

‹‹ተፅዕኖ ፈጣሪ›› የሚባሉ ባለአክሲዮኖችና ሌሎች አካላትን በተመለከተ ዝርዝር ድንጋጌዎችን የያዘው ይህ ረቂቅ መመርያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የሚባሉት ከባንኩ አጠቃላይ ካፒታል ሁለት በመቶ ወይም ከዚያ በላይ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ የያዙትን መሆኑን ገልጿል፡፡ ‹‹ከፍተኛ ተፅዕኖ ያላቸው ሰዎች›› ያላቸው ደግሞ ተፅዕኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚና የባንክ ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚዎች፣ ‹‹ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚ›› ማለትም ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሥራ ክፍሎችን የሚያስተዳድርና ተጠሪነቱ ለዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆነ ወይም በቀጥታ ለዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት የሚያደርግና ምክትሎችን የሚያጠቃልል ማንኛውም የባንክ ኦፊሰር መሆኑን አመልክቷል፡፡

የፋይናንስ ተቋማት ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን የሚሰየሙ ተሿሚዎች ሊያሟሉ የሚገባቸውን የትምህርት ዝግጅትና መሥፈርቶችን የሚጠቅሰው አንቀጽ ከታወቀ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ መያዝ ይጠበቅባቸዋል ይላል፡፡

ከዚህም ሌላ በባንክና ወይም በፋይናንሻል ተቋማት ውስጥ ቢያንስ የ12 ዓመታት የሥራ ልምድ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከዚህም ውስጥ ቢያንስ አምስት ዓመታት እንደ ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚ ያሠሩ መሆናቸውን ይደነግጋል።

ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚዎች በሚል የተጠቀሱና የዋና ሥራ አስፈጻሚው ምክትል ሆነው ለሚያገለግሉም ከታወቀ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ መያዝና በባንክና ወይም በፋይናንስ ቢያንስ የአሥር ዓመታት ልምድ ሊኖራቸው እንደሚገባም ያመለክታል፡፡

ከዚህ የሥራ ልምዳቸው ውስጥ ቢያንስ አራት ዓመታት የመምርያ ሥራ አስኪያጅ ወይም ተመሳሳይ ልምድ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ሆኖም የሥራ መደቡ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) ወይም በተዛማጅ ዘርፎች ከሆነ፣ ከIT ጋር በተገናኘ የግድ ከባንክ ጋር ግንኙነት የሌላቸው የሥራ መስኮች ልምድም እንደ አግባብነት ያለው ልምድ ሊቆጠር እንደሚችልም ረቂቁ ያመለክታል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ግን ይህ ሰው የከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚነት ቦታውን ከተረከበ በኋላ በብድር፣ ቁጠባ፣ ዓለም አቀፍ ባንክና ሌሎች ዋና ተግባራት ላይ ቢያንስ ለአምስት ቀናት ሥልጠና መውሰድና የሥልጠና ሰርተፊኬቱ በብሔራዊ ባንክ መመዝገብ እንደሚኖርበት ግዴታ ያስቀምጣል፡፡

እንደ ዋና የውስጥ ኦዲተርና ዋና ሥጋት አስተዳደር ኦፊሰር ያሉ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ያለ አንድ ከፍተኛ የሥራ አስፈጻሚ ለዳይሬክተር ቦርድ ሪፖርት የሚያደርግ ከሆነ፣ ሊያሟላቸው የሚገባቸው መመዘኛዎች የተለዩ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ በእነዚህ ኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለመሥራት ከታወቀ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ መያዝና በባንክ ወይም በፋይናንሻል ቢያንስ የስምንት ዓመት ልምድ ያለው፣ ከዚህም ውስጥ ቢያንስ ሦስት ዓመት በአስተዳደር ቦታ ላይ የሠራ መሆን አለበት ብሏል፡፡ ሌሎች ተያያዥ መሥፈርቶችንም በዝርዝር የቀረበበት ነው፡፡

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ለታቀደው ዋና ሥራ አስፈጻሚና ከፍተኛ የሥራ አስፈጻሚዎች ማመልከቻዎችን ለብሔራዊ ባንክ ሲያቀርብ ተሿሚዎቹ የባንኩን የውስጥ ግምገማ ሒደት ማለፋቸውን ያረጋግጣል። የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ስለዚህ ባንኩ በሰነድ የተደገፈ ብቃትና ትክክለኛ ፖሊሲና አሠራር መኖሩን ማረጋገጥ አለበት።

በዚህ ረቂቅ ሕግ ትልቅ ለውጥ ነው ተብሎ የተጠቀሰው የገለልተኛ ዳይሬክተሮች መካተት ባንኩን ሊያገለግል የሚችል ባለሙያ ቦርድ ውስጥ እንዲካተት የሚያስችል መሆኑን የገለጹት የባንክ ባለሙያዎች እንዲህ ያለው ድንጋጌ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበሩት መመርያዎች በአዳዲሶቹ ረቂቅ ሕጎች ላይ ግን የቦርድ ዳይሬክተሮች ኃላፊነቶች በከፍተኛ ደረጃ መጨመራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡፡

ከበድ ያለ ተጠያቂነትም ያለባቸው ስለመሆኑ በረቂቆቹ በተለያዩ መልኩ ተቀምጠዋል፡፡ አንድ የቦርድ አባል ባንኩ ውስጥ ችግር መኖሩን እያወቀ ችግሩን ለብሔራዊ ባንክ አለማሳወቅ በገንዘብና በእስራት ሊቀጣ እንደሚችል መጠቀሱ እንደ ምሳሌ አንስተውታል፡፡ ሌሎች የባንክ ዳይሬክተሮችን ኃላፊነት ከቀድሞው የበለጠ ስለመሆኑ የሚያሳዩ አንቀጾች የተካተቱ እንደሆነም ታውቋል፡፡ እነዚህ በመሻሻል ላይ ያሉት ረቂቅ መመርያዎች ከኮርፖሬት ገቨርናንስ ጋር በተያያዘ እንደ አዲስ ተካትተዋል ከተባሉ መካከል የኩባንያ ጸሐፊዎች ኃላፊነትን በተመለከተ ተበዳሪዎች የሚሰጡ ብድሮችን በተመለከተ አዲስ ድንጋጌ ዝርዝር ጉዳዮች ቀርቧል፡፡

የኦዲትና መሰል ኮሚቴዎች በዝርዝር መሥራት ያለባቸውን ሥራዎችና ተጠያቂነትን ከዚህ ቀደም ከነበረው በበለጠ ተብራርቶ የቀረበባቸው ሲሆን፣ በተናጠል ያለባቸውን ኃላፊነትም ረቂቁ አመልክቷል፡፡

ይሻሻላሉ ተብለው በሚጠበቁ በእነዚህ መመርያዎች እንደ አዲስና መሠረታዊ ለውጥ ተደርጎ የተጠቀሰው ሌላው ጉዳይ ከብድር አፈቃቀድ ጋር የተያያዙ ድንጋጌዎች ናቸው፡፡

በተለይ ከዚህ ቀደም የሚፈቀዱ ብድሮች በተለያዩ ደረጃዎች ላይ ያሉ ከፍተኛ የሥራ አስፈጻሚዎች ኃላፊነት የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን ብድሮችን ቦርድ ማፅደቅ እንደሚኖርባቸው ተጠቅሷል፡፡ የብድር አሰጣጡም ሒደት በረቂቁ የተመለከተ ሲሆን፣ በአዲሱ አሠራር የባንክ ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎችም የቦርድ አባል መሆን እንደሚችሉ የተደነገገ በመሆኑ ብድር መፍቀድ የጋራ ሥራ እንደሚሆን ከረቂቁ መገንዘብ ተችሏል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ትልልቅ ብድሮችን የሚወስዱ ግለሰቦችና ኩባንያዎች የሚወስዳቸው ብድሮችን በምን መልኩ መሆን እንደሚገባ የሚነግግም አንቀጽ አለ፡፡

ከዚህ ቀደም አንድ ሰው ወደ አንድ ባንክ ሄዶ ብድር መውሰድ ሲፈልግ የባንኩን አጠቃላይ 15 በመቶ በላይ ብድር መውሰድ አይችልም ነበር፡፡

አሁን በተዘጋጀው ረቂቅ ግን ‹‹ሪሌትድ ፓርቲ›› ማለት ግለሰቡ በስሙ ካለው ድርጀት በተጨማሪ እሱ የሚያስተዳድራቸው ተቋማትንና ሌሎች ባለቤትነት የሆነባቸውን ኩባንያዎች አጠቃልሎ የሚይዝ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ግለሰቡ በራሱ በድርጅቱ እንዲሁም 50 እና ከ50 በመቶ በላይ ገቢ የሚገኝባቸው ተቋማት ሁሉ እንደ ሪሌትድ ፓርቲ የሚቆጠሩ መሆኑን ነው፡፡

ስለዚህ ብድር ሲወሰድ የተወሰደው ብድር ምጣኔ የሚለካው በእነዚህ ኩባንያዎች በሙሉ የተወሰዱ ብድሮች ተሠልቶ መሆን እንደሚገባውና በዚህ ድርጅቶች ሁሉ የወሰደው ብድር ተደማምሮ ከባንኩ ካፒታል ከ25 በመቶ በላይ መብለጥ እንደማይኖርበት ረቂቁ አመላክቷል፡፡

ይህ የረቂቁ አንቀጽ አዲስ ከመሆኑም በላይ አንድ ተበዳሪ በራሱ በቤተሰቡና በሌሎች ተቋማት ውስጥ ያለውን የባለቤትነት ድርሻ በሙሉ ፈትሾ ማረጋገጥን የሚጠይቅ ስለመሆኑም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዚህም መሠረት ብድር ከመስጠታቸው በፊት ይህንን ሁሉ ባንኮች የማጣራትና የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባቸው ሲሆን ይህንን ያለ ማድረግም ተጠያቂ ያደርጋቸዋል፡፡

ይህ ድንጋጌ የባንኮችን ብድር የተወሰኑ ሰዎች እየወሰዱ ነው የሚለውን ለማስተካከል ታስቦ የወጣ ስለመሆኑ በረቂቁ ዙሪያ ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ይህ ድንጋጌ ባንኮች ላይ ሥራ ያበዛል ያሉም አሉ፡፡  

የቦርድ ዳይሬክተሮች ማንኛውም ባንክ እንደ የአደጋ አስተዳደር ማዕቀፉ አካል፣ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያላቸውን፣ ብቁ ያልሆኑና ተገቢ ያልሆኑ፣ ለባንኩ የንግድና የፋይናንስ አቋም ሊያስከትሉ የሚችሉ አደጋዎችን በጥንቃቄ መቆጣጠር አለባቸው፡፡ ለዚህም የዳይሬክተሮች ቦርድ ባንኩ በሰነድ የተደገፈና በቦርድ የፀደቀ ተገቢነት ያለውና ተገቢ ፖሊሲ በየጊዜው የሚገመገምና ከባንኩ የንግድ እንቅስቃሴና ከአደጋ ተጋላጭነት የመከላከል ስትራቴጂዎች ጋር የሚጣጣም መሆኑን ማረጋገጥ ጭምር ይኖርባቸዋል፡፡

አንድ ባንክ ላይ ሥጋት ወይም ማጭበርበሮች ካሉ ይህንን ማጋለጥና ሪፖርት የሚደረግበት አሠራር ለመዘርጋት የሚያስችል አሠራር እንዲኖር በረቂቁ የተቀመጠ ሲሆን፣ ያሉ ችግሮችን ሪፖርት ለሚያደርጉም ከለላ የሚሰጥ ስለመሆኑ ይጠቀሳል፡፡

በዚህ ፖሊሲ ማንኛውም ሰው፣ ሠራተኞችን ጨምሮ፣ በቅን ልቦና እንዲህ ያለውን የማጋለጥ ወይም ችግር መኖሩን ሲመለክት ጉዳት እንዳይደርስበት ለመከላከል ሁሉም ምክንያታዊ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ ማድረግ አለበት።

ከፍተኛ ተፅዕኖ ያላቸውን በተመለከተ በረቂቁ የተቀመጠው ሌላው ድንጋጌ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያላቸው ሰዎች ግምገማቸውን በተገቢውና በተገቢው መልኩ ሊለውጡ የሚችሉ ክስተቶችን ለብሔራዊ ባንክ ወዲያውኑ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል። የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ወይም የውጭ ኦዲተሮች ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት፣ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያለው ሰው በዚህ መመርያ ውስጥ የተቀመጡትን መመዘኛዎች ማሟላት ባለመቻሉ ምክንያታዊ ጥርጣሬ ካደረባቸው፣ ወዲያውኑ ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸው በዚህ መመርያ ከተካተቱ ድንጋጌዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ረቂቅ መመርያዎቹ ሌሎች በርካታ አንቀጾችን የያዙ ከመሆኑም በላይ፣ እስካሁን ያለውን የባንክ አሠራር የሚቀይሩ ስለመሆኑም በረቂቆቹ ዙሪያ ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች ጠቁመዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች