Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ታሪፍ ሊያሻሽል መሆኑን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ከ367 ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ እንዳለበት ተገልጿል
  • በየዓመቱ በአማካይ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ እያገኘ ቢሆንም 26 ቢሊዮን ብር ኪሳራ እያስተናገደ መሆኑ ተጠቁሟል

በሚያመነጨው ኃይል መጠንና በማመንጫዎቹ ከአፍሪካ የኤሌክትሪክ ኃይል አስተዳዳሪ ተቋማት ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የኢትዩጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ በአሁን ወቅት 367 ቢሊዮን ብር ዕዳ እንዳለበትና የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎችን ለማከናወን በየዓመቱ በአማካይ 29 ቢሊዮን ብር ኪሳራ እየደረሰበት በመሆኑ፣ የታሪፍ ማሻሻያ ማድረግ ወሳኝ የሆነበት ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለጸ።

ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያዘጋጁት ረቂቅ የኃይል ሽያጭ ታሪፍ ክለሳን በተመለከተ፣ ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ.ም. በዓድዋ ሙዚየም የስብሰባ አዳራሽ በጋራ ባዘጋጁት መድረክ ከሚዲያ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ውይይት ሲያደርጉ ነው።

የኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ፕላኒንግ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዱዓለም ሲዓ የተቋሙን ነባራዊ ሁኔታና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ የተቋሙ ካፒታል 672 ቢሊዮን ብር የደረሰ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል 367 ቢሊዮን ብር ዕዳ እንዳለበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ እሱባለው ጤናው ባቀረቡት ገለጻ፣ አገልግሎቱ ኪሳራ ላይ ነው ባይባልም ዓመታዊ የተጣራ ትርፉ ግን አራት ትራንስፎርመሮችን እንኳን መግዛት የማያስችል ነው ብለዋል።

አቶ አንዷለም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢውን እንደ ተቋም፣ እንዲሁም የኃይል አቅርቦት ኢንዱስትሪውን በአጠቃላይና በዘርፉ የሚስተዋሉ ተብለው የተለዩ ችግሮችን በዝርዝር አቅርበዋል።

በዚህም አነስተኛ የአገር ውስጥ የነፍስ ወከፍ የኤሌክትሪክ ፍጆታ፣ ዝቅተኛ የኃይል ተደራሽነትና የማመንጨት አቅም፣ አስተማማኝ ያልሆነ የኃይል አቅርቦት፣ እንዲሁም ያልተቀላጠፈ አሠራር በዋነኝነት ተጠቅሰዋል።

ከተለዩ ችግሮች አንፃር የተለያዩ የመፍትሔ አቅጣጫዎች በመንግሥት ደረጃ ተቀርፀው የተወሰዱ ዕርምጃዎችን ያብራሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ከሪፎርም ሥራዎች ባሻገር በተቋሙ ዕቅድ ውስጥ በማመንጫ ግንባታ እንዲሁም በኃይል ማስተላለፊያ በሚል ሁለት ዘርፎች የተያዙ ዕቅዶችና አፈጻጸሞችን አስረድተዋል።

በ2012 ዓ.ም. 4,460 ሜጋ ዋት የነበረ የማመንጨት አቅምን በ2021 ዓ.ም. ወደ 17,056 ሜጋ ዋት ከፍ የማድረግ ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል።

ይህንን ለማስፈጸም ያግዛሉ የተባሉ ዋና ዋና ግንባታዎች ሥራ አፈጻጸምን በተመለከተ ባቀረቡት ማብራሪያ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 96 በመቶ፣ የኮይሻ የውኃ ኃይል ማመንጫ ግንባታ 66.4 በመቶ፣ የአይሻ ንፋስ ኃይል ማመንጫ 83.41 በመቶ፣ እንዲሁም የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ 52.42 በመቶ የግንባታ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን አስረድተዋል።

በ2023 ዓ.ም. የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን ወደ 36,345 ኪሎ ሜትር፣ እንዲሁም የማከፋፈያ ጣቢያዎችን ብዛት ወደ 323 ከፍ ለማድረግ ዕቅድ መያዙም ተገልጿል።

አቶ እንዷለም የተጀመሩ የማመንጫ ፕሮጀክቶችን ግንባታ ለማጠናቀቅ ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ፣ እንዲሁም የተጀመሩ የማስተላለፊያ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ደግሞ ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት በውኃ ኃይል ላይ ያለ ጥገኝነት በ2012 ዓ.ም. ከነበረው 92 በመቶ፣ በ2021 ዓ.ም. የኃይል አማራጩን በማስፋት ዕቅድ ሥር ከውኃ ኃይል የሚመነጭ ኃይልን ወደ 76 በመቶ ዝቅ ማድረግ፣ የእንፋሎት ኃይልን በ11 በመቶ በመጠቀም፣ ከንፋስ የሚመነጭ ኃይልን ወደ አሥር በመቶ ከፍ በማድረግ ከፀሐይ ኃይል ደግሞ ሦስት በመቶ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ዕቅድ መያዙ ተገልጿል።

ዕቅዱን ከማስፈጸም አንፃር በግንባታ ላይ ያሉ የታላቁ ህዳዴ ግድብ፣ የኮይሻንና የአሰላ የንፋስ ኃይል የማመንጫ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ከሚጠበቀው 6,166 ሜጋ ዋት ኃይል በተጨማሪ፣ ከንፋስ 2,255 ሜጋ ዋት፣ ከውኃ 1,295 ሜጋዋት፣ ከእንፋሎት 1,500 ሜጋ ዋትና ከፀሐይ 975 ሜጋ ዋት ለማመንጨት እየተሠራ መሆኑም ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አሁን ባለው ሁኔታ ከመስመር (Grid) በሚተላለፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ከአጠቃላዩ ሕዝብ ወደ 36 በመቶ የሚሆነውን እንደሚይዝ ሲገለጽ፣ ተቋሙ ያለ ታሪፍ ማሻሻያ የጀመራቸውን የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን ማስቀጠል አዳጋች እየሆነበት መምጣቱንም ኃላፊዎች አብራርተዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳህረላ አብዱላሂ፣ የተቋማቱ የኤሌክትሪክ ታሪፍ አለመሻሻሉ ጥራት ያለው አስተማማኝ አገልግሎትን፣ እንዲሁም ሁሉም አካባቢ ተደራሽነትን ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ውስጥ፣ የዘርፉ ተቋማት አዳዲስ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት አቅም እንዲያጥራቸው፣ የፋይናንስ እጥረቶች እንዲገጥማቸውና ከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ እንዲዘፈቁ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ እያደገ የመጣው የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎትን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማሟላት፣ አስቸኳይ ጥገናዎችን ለማካሄድ፣ በአዳዲስ የኃይል ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ፣ የኃይል አቅርቦት አማራጮችን ለማስፋትና የኤሌክትሪክ የወጪ ንግድ ዘርፍን ለመደገፍ አሁን ባለው ታሪፍ ተመሥርቶ ማሰብ ፈታኝ እየሆነ መጥቷል ሲሉም አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ እሱባለው በበኩላቸው፣ የኃይል ሽያጭ ታሪፉ በ2011 ዓ.ም. ከተሻሻለ በኋላ በየዓመቱ በአማካይ ከ350 ሺሕ በላይ አዳዲስ ደንበኞችን ማፍራት መቻሉን ቢገልጹም፣ አሁን ተግባራዊ እየተደረገ ባለው የኃይል ሽያጭ ታሪፍ ከስምንት ሺሕ አምስት መቶ በላይ ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ እስከ 27 ዓመት ሊወስድ ይችላል ብለዋል።

ከሁለቱ ተቋማት የተውጣጣው የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ ክለሳ የጥናት ቡድን አባልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፋይናንስ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ መንግሥቱ ባቀረቡት ገለጻ መሠረት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለፉት አራት ዓመታት ከሰበሰበው ገቢ ውስጥ በየዓመቱ አማካይ የአምስት ቢሊዮን ብር ገቢ ዕድገት እያሳየ ቢሆንም፣ በሚያከናውናቸው የፕሮጀክት ግንባታ፣ የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎች በየዓመቱ በአማካይ 26 ቢሊዮን ብር ኪሳራ እያስተናገደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አቶ ዓለማየሁ ላለፉት ስድስት ዓመታት በሥራ ላይ የቆየው ታሪፍ የኃይል አቅራቢ ተቋማቱ በፋይናንስ እንዲጠናከሩና የአገልግሎት አሰጣጣቸውን እንዲያሻሽሉ ዕገዛ ቢያደርግም፣ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንዳልተቻለ ገልጸዋል።

የጥናት ቡድኑ አባል የተሻለ አገልግሎት ለመስጠትና ተደራሽነታቸውን ለማሰፋት የታሪፍ ክለሳ ተዘጋጅቶ ለአስተያየት መቅረቡን ሲገልጹ፣ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተሯ በበኩላቸው ባለሥልጣኑ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ፣ በተጠቃሚውና በመንግሥት በኩል ያሉ ፍላጎቶችን በሕግ አግባብና በታሪፍ መገምገሚያ መሥፈርት መሠረት ሚዛናዊ ውሳኔ ያቀርባል ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ የታሪፍ ክለሳ ፕሮፖዛል ሒደትን ለመገምገም በወጣው መመርያ ቁጥር 008/2014 አንቀጽ 54 መሠረት፣ የታሪፍ ውሳኔን አስመልክቶ ባለሥልጣኑ ከሕዝብ የሚነሱ ሥጋቶችንና አስተያየቶችን፣ እንዲሁም የታሪፍ አወጣጥ ሒደቱን አካል አድርጎ እንደሚመለከተው አስረድተዋል።

የታሪፍ ማሻሻያ ዕቅድ ሐሳቡም ለሕዝብ ቀርቦ ተደጋጋሚ ውይይቶች እንደ ሚደረጉበትም ተናግረዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች