Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጠፋ አውሮፕላን ፈልጎ የማዳን ቴክኖሎጂ በልፅጎ ለሥራ ዝግጁ መሆኑ ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የጠፋ አውሮፕላን ፈልጎ የማዳን ቴክኖሎጂ አበልፅጎ ለሥራ ዝግጁ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ አገልግሎት ከሚሰጡ ሁለት ቴክኖሎጂዎች አንደኛው የሆነው ‹‹ኢንሲደንት ኮማንደር ፕሮ ኤይት›› የተሰኘ ቴክኖሎጂ በመግዛት፣ አገር ውስጥ ማስገባቱን የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ገልጿል፡፡ ቴክኖሎጂውን ጥቅም ላይ ለማዋል ሠራተኞች ሥልጠና ማግኘት ስላለባቸው የውጭ ሥልጠና ለማግኘት ሙከራዎች እየተደረጉ እንደሆነ፣ በመጪው ዓመት መጀመሪያ ላይ ሥልጠናው እንደሚሰጥ የባለሥልጣኑ የአየር ትራፊክ ማኔጅመንት ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ አበራ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም አውሮፕላን ከወደቀ በኋላ ይፈለግ እንደነበር፣ አሁን ግን በረራ ላይ እያለ የድንገተኛ ምላሽ የሚሰጥበት አሠራር በዓለም አቀፍ ደረጃ መዘርጋቱን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፈረመቻቸው የሲቪል አቪዬሽን ስምምነቶች መካከል፣ በክልሏ ውስጥ አውሮፕላን ቢጠፋ ፈልጎ የነፍስ አድን ሥራ ማከናወን የሚለው ይገኝበታል፡፡

አውሮፕላን ፈልጎ የማዳን አገልግሎት የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በአዋጅ የተሰጠው ኃላፊነት መሆኑን አቶ ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡

አገሪቱ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ስምምነቶች መሠረት የፈልጎ ማግኘት አገልግሎቱን የመስጠት ግዴታ አለባት ያሉት ዳይሬክተሩ፣ አንድ አውሮፕላን በአገሪቱ የአየር ክልል የሚያልፈው፣ የሚያርፈውና የሚነሳው አገሪቱ የዚህ ስምምነት ፈራሚ በመሆኗ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡

የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዓለም አቀፍ ግዴታ ያለበት ስለሆነ፣ በማቋቋሚያ አዋጁ ላይም ፈልጎ የማዳን አገልግሎት የመስጠት ግዴታ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡

ፈልጎ የማዳን አገልግሎት የሰብዓዊነት ሥራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ አውሮፕላን ሲወድቅ ወይም ሲጠፋ የማዳን ሥራው በአፋጣኝ ካልተካሄደ የሞት ምጣኔው ከፍተኛ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ሲቪል አቪዬሽን ፈልጎ የማዳን ሥራ ማከናወን ባስፈለገበት ወቅት የሚችለውን ሲያካሂድ መቆየቱን፣ አሁን ግን የአውሮፕላኖች ቁጥር በመጨመሩና ዘርፉ እየዘመነ በመምጣቱ ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ማድረግ እንዳስፈለገ አብራርተዋል፡፡

አውሮፕላን ሲጠፋ በመጀመሪያ የት ቦታ ሊጠፋ ይችላል የሚለው ሥራ እንደሚከናወን፣ በዚህ መሠረትም ግምታዊ መረጃዎች እንደሚወሰዱና የአካባቢውን መልክዓ ምድር በመመልከት ፈልጎ የማዳን ሥራ ይከናወናል ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት አሠራሩ ማንዋልና ረዥም ሰዓት የሚወስድ በመሆኑ ለፈልጎ ማዳን ሥራው አዳጋች ያደርገው እንደነበር፣ ይህ ቴክኖሎጂ ሥራ መስጠት ሲጀምር ግን በደቂቃዎች ፍጥነት ፈልጎ የማዳን አገልግሎቱ እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች