Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

ቀን:

በታደሰ ሻንቆ

በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ ነክ ቢጋር፣ ዓላማው የኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ ሲጻፍ በኖረው ላይ ፍርድ መስጠት ወይም ወቀሳ መደርደር አይደለም፡፡ ራስን የታሪክ ጸሐፊ አድርጎ ከመቁጠር ጥግ የተጻፈም አይደለምና ገለልተኛ ለመሆን አይጥርም፡፡ እንደዚያም ሆኖ፣ በኢትዮጵያ የቅርብ ታሪክ አተረጓጎም ረገድ የራሱን ውስን ምልከታዎች ለማበርከት ይሞክራል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ አሁን በእጃችን የገባው ኢትዮጵያን በሕዝቦቿ ፍላጎት መሠረተ ፅኑ አድርጎ የማነፅ ወርቃማ ዕድል፣ በዕውናዊነት አቅሙ ከእስከ ዛሬዎቹ ሁሉ የላቀና ተወዳዳሪ የሌለው መሆኑን ለማሳየትና እንዳይልኮሰኮስ ሐሳብ ለማዋጣት ነው፡፡

 1. ኢትዮጵያ የጥንታዊ ሥልጣኔ ቅርስ የነበራት ብትሆንም፣ ከመዘማመት ወጥታ ሥልጣኔዋን ማራመድ ሳትችል ዘመን አለፈባት፡፡ ከኋላዋ ተነስቶ ዓለምን እያሰሰና በቅኝ ይዞታ እየተስፋፋ በተለያየ የካፒታሊዝም ደረጃዎች ውስጥ ያለፈው አውሮፓ በጥቅሉ ኢንዱስትሪያዊ ጉልበት አበጅቶ አፍሪካን ሊቀራመት በ19ኛው ሁለተኛ አጋማሽ ውስጥ ሲመጣ ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ኢኮኖሚ ውስጥ ከመዳከርና ከጉልታዊ ገባር ሥርዓት አልተነቃነቀችም ነበር፡፡ አፄያዊ አገር የማስፋትና ይዞታ የማርጋት ዘመቻዋ ገና አልተጠናቀቀም ነበር፡፡ የአፄውና የመሣፍንቱ ዘማች ጦር በዘመቻ ጊዜ ገበሬ ላይ እየተሠማራ ጉርሱን ከመሸፈንና ከዘመቻ ድል የምርኮ ሲሳይ ገና አልወጣም ነበር፡፡ መሬት ማግኘትና በባርነት መንዳት የቅጣትና የምርኮ ሲሳይ መገለጫዎች ነበሩና በዘመቻዎች የተያዙት ደቡባዊ ይዞታዎች ውስጥ እንደ አዲስ ነገር ጭሰኝነትና ባሪያ ፍንገላ ደምቆ ነበር፡፡ ሰሜናዊውን የኢትዮጵያ ክፍል በዋና ማኮብኮቢያነት ይዞና ኃይሉን ሰንቆ የጣሊያን ኃይል በአጠቃላይ ቅኝነት ሊውጣት የመጣው ኢትዮጵያ በዚህ አሮጌ ዓውድ ውስጥ ሆና ነበር፡፡

በ1888 ዓ.ም. የዓድዋ ድል የጣሊያንን ወረራ ብታሸንፍም ከሰሜናዊ ክፍሏ (ከኤርትራ) ለመንቀል የሚያስከጅልና የሚያበቃ ሁኔታ ውስጥ አልነበረችም፡፡ ከጦርነት ዕረፍት አግኝቶ አቅም የሚያስገኝ አውሮፓዊ ሥልጣኔ ውስጥ ለመግባት ያደረገችውም ሙከራ (ከምኒልክ እስከ ራስ ተፈሪ/አፄ ኃይለ ሥላሴ ድረስ) ለከፍከፍ ከማድረግ/የአውሮፓውያኑን ኑሮ ከመላመድ የጠለቀ አልነበረም፡፡ ማዕከላዊ ሥልጣንን ከማጥበቅ ሒደት በቀር፣ የገባር-ጭሰኛ ሥሪቷን የቀየረና የዕደ ጥበብ ዕርምጃ ያሳየ መሻሻል ሳታገኝ፣ የጦር አደረጃጀቷን እንኳ ሳታዘምን የጣሊያን ወረራ በአዳዲስ የምድርና የአየር ጦር መሣሪያ ጎልብቶ ነበር በ1928 ዓ.ም. ተመልሶ የመጣባት፡፡

መንግሥቷ ፈርሶ የተማሩ ሰዎቿ በወራሪው ኃይል ጭፍጨፋና በስደት ተመናምነው፣ ዱሩን ቤቴ ባለ የአርበኝነት ተጋድሎ አምስት ዓመታት ተዋግታ፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወሳኝ የኃይል ሚዛን ለውጥ ውስጥ ፋሽስት ወራሪዋን ድል ብትመታም፣ ከስደት ተመልሶ በአፄነት የተተከለው ኃይለ ሥላሴ ኢትዮጵያ ምን ያህል ኋላቀር የመደብና የኢኮኖሚ ግንኙነት ውስጥ እንደሆነች የአምስት ዓመት አውሮፓዊ ስደቱ አላስተማረውም፡፡ ፋሺስት ጣሊያን ራሱ የኢትዮጵያን የሥርዓት ቀርነት ተመርኩዞ ‹‹ሥልጣኔን ይዤ መጣሁ›› ብሎ ለመነገድ ችሎ የነበረ መሆኑ አልጎነተለውም፡፡ እዚያው አሮጌ የገባር-ጭሰኛ ሥሪት ውስጥ ተዘፈቀ፡፡ የአገዛዝ መሻሻል የሚሹ ዱለታዎች በተደጋጋሚ ቢቅቃጡበትም፣ ምክሮች ቢመጡለትም፣ ከ1953ቱ የታኅሳስ መንግሥት ግልበጣ ሙከራ በኋላ እንኳን አዕምሮ ገዝቶ ዘውዳዊ ሥልጣኑን ለሚያላላ፣ በንጉሣዊ-መሣፍንታዊ ቤተሰቦችና በመኳንንቶች የተግበሰበሰውን መሬት ለሚያቀል ማሻሻያ ቸር አልሆነም፡፡ እንዲያውም ምክር አይሰሜነቱና በፍፁማዊ ሥልጣን ሁሉን የመቆጣጠር ስስቱ ብሶ፣ ከፋሺስት ጣሊያን መሄድ በኋላ በብዙ ትግል የተገኘውን የኢትዮጵያና የኤርትራ የፌዴሬሽን ኅብረት በስመ ውህደት በፍፁማዊ ሥልጣኑ ሥር አስገባና የኢትዮ-ኤርትራን ታሪክ፣ ሰላምና ጥቅም የጎዱ መዘዞች ተከለ፡- አካባቢን የለየ የነፃ አውጪነት ታሪክ በኢትዮጵያ ምድር እንዲጀመር ምክንያት ሆነ፡፡ ኑሮን ያማቀቀው የኢትዮ-ኤርትራ የጦርነት ምዕራፍ ተከፈተ፡፡ ከስንት ከበባና አፈና በኋላ በፌዴራል ኅብረት መልክ መልስ የተገኘለት የኢትዮጵያ የቀይ ባህርና የባህር በር ባለድርሻነት፣ የማጣትና ያለማጣት ትግል የሚደረግበት ጉዳይ ሆኖ አረፈ፡፡

 1. የኢትዮጵያ ተማሪዎች ‹‹መሬት ለአራሹ!›› የሚል መፈክር አንግበው ብቅ ያሉበት ዓለም አቀፋዊ፣ አኅጉራዊና አገራዊ ዓውድ፣ እጅግ ውስብስብ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች የነበሩበት ነበር፡፡ ውስብስቦሹን በቅጡ ተረድቶና በፈርጅ በፈርጅ ለይቶ ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ለውጥ ከእነ አካሄዱ መቀየስ፣ በእነሱ የወጣትነት አቅምና የተካበተ የትግል ልምድ ማነስ፣ እጅግ ከባድ ፈተና ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ ከ1966 ዓ.ም. ግብታዊ አብዮት ጋር የተገናኙት የዚያን ጊዜዎቹ ተራማጅ ወጣቶች፣ ወርቃማ ዕድል አግኝተው ነበር ብሎ ከማለት ይልቅ፣ ብዙ የተቃረኑ የሥርዓተ ማኅበርና የርዕዮተ ዓለም ፍትጊያዎች/እንቅስቃሴዎች ባሉበት ዓለምና ተወዝፈው በቆዩ የኢትዮጵያ አሮጌ ጣጣዎች መሀል አጣብቂኝ የገቡበት ከባድ ጊዜ ነበር ቢባል የበለጠ ፍትሐዊ ይሆናል፡፡

በዓለም ገኖ የቆየው በግል ይዞታነት የሚመራው ምዕራባዊ ካፒታሊዝም፣ በኢኮኖሚ አደረጃጀትም፣ በርዕዮተ ዓለምም፣ በፖለቲካም ህልውናውን የተቀናቀነ አዲስ ምሥራቃዊ ጎራ ተፈጥሮበት ነበር፡፡ ይህ ጎራ፣ ራሱን ‹‹የትኛውንም ብዝበዛና ጭቆና የሚቃወም የፍትሕ የእኩልነት፣ የነፃነትና የዕድገት ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴ›› ብሎ የሚገልጽ፣ ምዕራባዊውን ካፒታሊዝም ደግሞ ‹‹ታዳጊነቱን ጨርሶ ያረጀ፣ በኢምፔሪያሊስታዊ ቀጥተኛና ኢቀጥተኛ ቅኝ አገዛዝ የሌሎችን ዕድገት ያነቀ ዓለም አቀፋዊ የብዝበዛና የጭቆና ሥርዓት›› ብሎ ያወገዘ ነበር፡፡ ማውገዝ ብቻ አይደለም፣ የአዲስ መጡ ጎራ ርዕዮተ ዓለም ውስጣዊና ውጫዊ የምዝበራና የጭቆና ሥርዓቶች ላይ እዚህ ቀረሽ የማይባል የቅዋሜና የትግል ፖለቲካ አቀጣጥሎ ነበር፡፡ የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት መገባደጃ ሒደትን ይዞ ይህ አዲስ መጥ ጎራ ከደረጀ ወዲህ፣ በየትኛውም የዓለም ጥግ የተከሰተና የሚከሰት የሓርነት ትግልና ተራማጅ/ አብዮተኛ እንቅስቃሴ አዲሱን ርዕዮተ ዓለም ከማሽተት የሚያመልጥ አልነበረም፡፡ የ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ወጣቶችም ሶሻሊስት ቀመስነት ቅብጠት አመጣሽ አልነበረም፡፡ በዚሁ ርዕዮታዊ ስበት አማካይነት በኩባ፣ በቻይና፣ በቬትናም፣ ወዘተ የታዩት ትጥቅ ነክ ትግሎች የሚኮረኩሩ ነበሩ፡፡ በአፍሪካም ተንቦግቡገው የነበሩ በቀጥተኛ ቅኝ አገዛዝ ላይ የተነሱ የሓርነት ትግሎችና በየጊዜው በ1950ዎችና 60ዎች የሚበሰሩ ድሎቻቸው ‹‹እናንተስ?›› የሚል ቁስቆሳ የሚለቁ ነበሩ፡፡

የኢትዮጵያ ነፃነቷን አስጠብቃ መኖር፣ ይፋ ግንዛቤ ቢሆንም የነበረችበት አሮጌ የምዝበራና የጭቆና ሥርዓት የጊዜውን አብዮተኛ ትግል የሚጋብዝ ነበር፡፡ ይጋብዝ እንጂ የኢትዮጵያ እውነታ በጋራ ትልም አንድ ላይ መሠለፍን ፈተና ውስጥ የሚከትቱና ለተሳሳተ ግንዛቤ የሚያጋልጡ ጉርብጥብጦች ነበሩበት፡፡

በኤርትራ የነበረው የታጠቀ የነፃነት ትግል ፌዴሬሽን ፈርሶ ኤርትራ ከኢትዮጵያ የተቀላቀለችበትን ክንዋኔ የኤርትራ ቅኝ ተገዥነት መቀጠል አድርጎ የተረጎመ ነበረ፡፡ አገር የማስፋቱ ሥራ ሳይጠናቀቅ ዘግይቶ ከአውሮፓውያኑ የቅኝ ሽሚያ ጋር መገጣጠሙ፣ አገር ማስፋፋቱ የአካባቢ ገዥን በውዴታ ካልሆነ በኃይል ዘምቶ የማስገበር ሥልት የነበረው መሆኑ፣ የኃይል ዘመቻው መሬትን የማጣት፣ በባርነት የመነዳትና የመሳሰሉ ጨካኝ ቅጣቶች የነበሩበት መሆኑ፣ ይህም ታሪክ ‹‹የአባቴ አባት…፣ ወዘተ እንደነገሩኝ›› እየተባለ እስከ መወሳት ድረስ ለ1960ዎቹ ትውልድ ቅርብ የነበረ መሆኑ፣ በተዘመተባቸው አካባቢዎች በባለ ርስትነት የተደረገው አካባቢ ገብ መደባዊ መፈላቀቅ ከሲታ መሆኑና በባለ ርስትነት ክምችት ውስጥ መጤ ማየሉ፣ በዚህም ምክንያት ገባር-ጭሰኝነት ማኅበረሰባዊ መልክ መፍጠሩ፣ በዚህ ላይ የአፄው የአገር ይዞታና አገረ መንግሥቱ በፈረንጅ ጸሐፊዎችና በአስተጋቢዎቻቸው የአገር ውስጥ ልሂቃን ዘንድ ‹‹ኢምፓየር››/ ‹‹የአቢሲኒያውያን ኢምፓየር›› እየተባለ መጠራቱ፣ ሌላው ቀርቶ ለ‹ኮሎኒያሊዝም› የተሰጠው የአማርኛ ስያሜ ‹‹ቅኝ ገዥነት›› ከአፄዎቹ ‹አገር ማቅናት› ጋር የተዛመደ መሆኑ የኢትዮጵያን አፄያዊ የአገዛዝ አደረጃጀት በቅኝ ገዥዎቹ ዓይን ለማየት ስህተት የሚያጋልጥ ነበር፡፡ የተሳሳቱም ነበሩ፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በስተ ደቡብ ተጀማምሮ የነበረው ካፒታሊስታዊ (ሰፊ የመኪና) እርሻ የመሣፍንቱና የመኳንንቱ ድንግል መሬት ላይ ከመስፋፋት ፈንታ በጭሰኝነት እህል ቀምሰው የሚያድሩ አራሾችን እስከ ማፈናቀል ድረስ ከመጨረሻ ዝቀተኛ ህልውና ጋር የተላተመና ቅዋሜና አመፅ ያስነሳ ነበር፡፡ ይህ እውነታ በራሱ የጊዜውን ወጣት ልሂቃን በሶሻሊስቱ ጎራ አመለካከትና ጎዳና ለመሳብ አጋዥ ነበር፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ያልተግባቡ ነገሮች የተደረቱባትን ኢትዮጵያንና ውስብስብ የሥርዓትና የርዕዮተ ዓለም ጎራዎች የሚፋተጉባትን ዓለም በደንብ ካስተዋልን በዚያን ጊዜ ውስጥ የተገኙትን የ1960ዎች ለውጠኞች ‹‹አጣብቂኝ/ ከባድ ፈተና ውስጥ የገቡ ወጣቶች›› ብሎ ማለት ስህተት አይሆንም፡፡ ከዓለም አቀፋዊው ማርክሲስት-ሶሻሊስት ሥነ ጽሑፍ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀ ሰው በህሊና-ስሜቱ ላይ የሚታይበትን ለውጥ እዚህ ድረስ ነው ብሎ ለመግለጽ ከባድ ነው፡፡ የእኔን የተስገበገበ ንባብ ተመርኩዤ ተሰምቶኝ የነበረውን ለማስታወስ ብሞክር፡- ፍልስፍናውን፣ የኅብረተሰብ ሥርዓተ ማኅበራዊ ትንታኔውን፣ የለውጥ ፖለቲካውን፣ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ትንታኔውን ሁሉ አነሰም በዛ ሲፈሰፍሱ ሁሉን አወቅሁ ባይ መንፈስ በሁለመና ይሠራጫል፡፡ ንባቡ በጨመረ ቁጥር ለመላው ዓለም፣ በኢንዱስትሪ ለመጠቀው አገርም ሆነ ለኋላቀሩ አገር የሚሆኑ መላዎችን በጀርባው አዝሎ የመዞር ያህል አወቅሁ ባይነት ይንጎማለላል፡፡ በዚያ ላይ ሜዳው ሁሉ የሕዝብ ጥያቄ በጥያቄ የሆነበት ግብታዊ የሕዝብ አብዮት ሲፈነዳ በኢትዮጵያ ታሪክ የ1966ቱ የመጀመሪያ ገጠመኝ ነው፡፡ ሳይዘጋጁ ቀድሞ ብቅ ላለ አብዮት ፈጥኖ ለመድረስ መቻልም ሌላ ፈተና ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ለኢትዮጵያ እውነታ የሚበጀውን መላና መንገድ በደንብ ተረድቶ ሕዝብን ወደ ውጤት የመምራት ጉዳይ በስክነትና በአርቆ አስተዋይነት ብርቱ ለሆኑ አዕምሮዎችም እንኳ ከባድ ሥራ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ከለውጠኞች ፈተና አኳያ በክብደቱ ተቀዳሚ የነበረው የለውጥ አንጓ ይህ ነበር ብል፣ እኔ ለነበርኩበት ዘመን ማዳላት አይመስልብኝም ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህንን ሁሉ የደረደርኩትም ድክመትና ስህተቶቻቸውን ለማድበስበስ ሳይሆን፣ ፍትሐዊ ግምገማ መስጠት የምንችለው የነበሩበትን ከባድ ሁኔታ ስንረዳ ነው በማለት ነው፡፡

ለንፅፅር እንዲረዳን የ20ኛው መባቻ ጊዜን ይዞ ታይቶ የነበረውን ለውጠኝነት ብናነሳ፤ ለለውጠኞቹ በጃፓን መንገድ ለውጥ የማምጣት አቋም ላይ ለመቀራረብ መቻል ቀላል ነበር፡፡ ሊቀል የቻለውም የለውጠኞቹ ምዕራብ ቀመስ ልሂቃዊ አቀራረፅና ፍላጎት ዥንጉርጉር ስላልነበረ ሳይሆን፣ በነበሩበት የጊዜው እውነታ የለውጥ ዕድል የነበረው በገዥው ክፍል ውስጥ የነበረውን ለለውጥ ቅርብ የሆነ ክፍል በመጠጋትና በማገዝ ብቻ ስለነበር ነበር፡፡ ፋሺስት ጣሊያን ከተባረረበት 1933 ዓ.ም. አፍላ የድል ጊዜ እስከ አፄ ኃይለ ሥላሴ መልሶ መንበረ ሥልጣን መቆናጠጥ ድረስ የነበረውም ሁኔታ፣ ፍፁማዊ አገዛዝንና የገባር-ጭሰኛ አሮጌ ሥሪት ዳግም እንዳይደረጅ በይፋ እንቢ ላለ የብዙኃን እንቅስቃሴ የሚመች አልነበረም፡፡ ለዚያ ዓይነት እንቅስቃሴ የሚሆን ልሂቃዊ አቅምን ፋሺስታዊ ጭፍጨፋ ቀደም ብሎ አመናምኖት ነበር፡፡ የአርበኝነት ትግሉም ከሞላ ጎደል በመኳንንቶችና በአፄ ኃይለ ሥላሴ ደጋፊዎች ተፅዕኖ ሥር የወደቀ ነበር፡፡ የብሪታኒያ መንግሥትም አፄውን አቅፎ ከማስገባትና በጊዜው ራሱን በኢትዮጵያ ላይ ዋና አዛዥ አድርጎ ተንኮለኛ ጥቅሙን ከማድራት ባሻገር አሮጌውን የመሬት ሥሪት የሚቀይር አዎንታዊ ሚና ለመጫወት ንፉግ ነበር፡፡ ንጉሡ ሙሉ ሥልጣኑን ካደላደለ በኋላም የማሻሻያ ለውጦች የመምጣታቸው ዕድል፣ የአፄውን በጎ ፈቃድ ከማባበል ውጪ የሚያወላዳ የልሂቅና የማኅበራዊ ንቃት አቅም አልነበረውም፡፡ ያ በጎ ፈቃድ በንጉሡና በመሳፍንቱ ዘንድ ባለመኖሩም ለውጥ ፈላጊዎች በዱለታና በግልበጣ መንገዶች ለውጥ ለማምጣት እስከ 1953ቱ ትልቁ ሙከራ ድረስ ያደረጓቸው መፍጨርጨሮች ምርጫ የለሾች ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡

የ1966 አብዮት ጊዜ ግን እንዲህ ቀላል ጥቅል ድምዳሜዎች ሊሰነዘሩበት የሚችል ዓይነት አልነበረም፡፡ የ1966 የከፋ የወሎ ረሃብና የሰው መርገፍ የአንድዬ ዩኒቨርሲቲያችንን መምህራንንና የዩንቨርሲቲ ተማሪዎችን ለወገን ጥቃት የመድረስና ድምፅ የመሆን እንቅስቃሴን ይዞ መጣ፣ ረሃብና ሞት ያስከተለው ቁጣ ከየካቲት የነዳጅ ዋጋ መጨመርና ከ‹ሴክተር ሪቪው› ቅዋሜ ጋር ተገናኘ፡፡ የካቲት ከወታደር እስከ ሲቪል የብሶትና የጥያቄዎች መድረክ ሆነች፡፡ የአክሊሉ ካቢኔ ለወታደር ደመወዝ በመጨመር፣ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን በማንሳትና በትምህርትና ሥልጠና መስክ የተወጠነውን ማሻሻያ በማገድ መሸንገል ቀላል አልሆነለትም፡፡ ሠራዊቱ ከደመወዝ ጭማሪ ጋር ወደ ካምፑ ፊቱን ቢመልስ ‹‹የራስክን ደመወዝ አስጨመርክና…›› ተባለ፡፡ ከመሬት ለአራሹ፣ ከሃይማኖት እኩልነት፣ ከዴሞክራሲ፣ ወዘተ ጥያቄዎችና ሠልፎች ጋር ‹‹ለወሎው የረሃብ ዕልቂት ምክንያት የሆኑት ይጠየቁ! ለፍርድ ይቅረቡ!›› የሚለው ጥያቄ ደምቆና የአክሊሉ ሀብተ ወልድን ካቢኔ መውረድ እስከ መጠየቅ ተራምዶ ነባሩ ካቢኔ በእንዳልካቸው ካቢኔ ቢተካም፣ የሕዝቡ አብዮት አልረካም፡፡ ‹‹ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥ!›› የጊዜው ዝነኛ (ብዙኃን የተቀባበሉት) ምላሽ ሆነ፡፡

የሕዝቡ አብዮት አልሸነገል ብሎና ወዴትና እንዴት እንደሚጓዝ አውቆ የጋራ ጎዳና ሳይዝ ረዥም ጊዜ ሊቆይ ግን አይችልም ነበር፡፡ የመነጠል ትጥቅ ትግል የሚካሄድበት የኤርትራ ጉዳይ ራሱ የሥልጣን ክፍተትን ቶሎ መሞላት የሚጎተጉት ሁነኛ ሰበዝ ነበር፡፡ ብሶትና ሥጋቱን አንግቦ የሚመራ ኃይልን ሕዝብ ከመቁለጭለጩ አኳያ፣ የወጣቶቹ ለውጠኞች የድርጅታዊ ጥንስስ ታሪክ (በውጭ አገርም ሆነ በአገር ውስጥ በረሃና በከተማ) ፋይዳ የለውም፡፡ ለውጠኞቹ የህቡዕና የሩቅ መትርክርካቸውን ጨርሰው ብቅ እስኪሉ የመሪ ዕጦቱ የሚጠብቅበትም አንዳች ምክንያት አልነበረውም፡፡ በቅድመ የካቲት ትግል ልምድ አማካይነት ሕዝብ ልብና ሙገሳ ውስጥ የገባና ሕዝብ መላ በለኝ የሚለው ዓውራ ከለውጠኞቹ መሀል አልነበረውም፡፡ እናም፣ ለውጠኞቹ በአሰባሳቢ መሪነት ለሕዝቡ አብዮቱ የመድረሳቸው ድፍን ዕድል እንደነበር ሁሉ፣ በአክሊሉ ካቢኔ መውረድ ጊዜ አካባቢ የተሰባሰበ መልክ እያበጀ እንደገና መላወስ በጀመረው የወታደራዊ እንቅስቃሴ ሕዝብ ሊሳብ የሚችልበትም ዕድል አብሮ ነበር፡፡ በእንዳልካቸው መንግሥት ማባበያ የመንከርፈፍና በተልኮሰኮሰ ጥገና የመሸንገል ዕድልም ዝግ አልነበረም፡፡ አመራር ከሚሻ መቁለጭለጭ ጋር ጥያቄና ብሶት ድርደራው፣ ግራ ቀኝ መገላመጡም፣ ሠልፉም፣ የሥራ ማቆም አድማውም እየተባለ ከቆየ በኋላ፣ ብሶትን ተመርኩዞ ሕዝብን የመማረኩን ሚና የወታደሩ ደርጋዊ እንቅስቃሴ ቀድሞ ወሰደው፡፡ ያለማጋነን በተለይ 1966 ዓ.ም. ሚያዝያንና ሰኔን ይዞ፣ ይቅርና ሕዝቡ (ተራማጅ ቀመስ ነኝ የሚለው ጭምር)፣ የደርጎቹን ዕርምጃ ጠባቂና ሐሳብ ጠቋሚ ነበር፡፡ የለውጠኞቹ ሚና የመጣው ከዚያ በኋላ ደርግን ተጠግቶ ወደ ተራማጅነት በመሳብ/በማገዝና በመቃወም መልክ ነው፡፡

 1. በተራማጆቹ ቅራኔ ተጠቅሞና የሥልጣን ተቀናቃኞቹን እያቃለለ ‹‹በሶሻሊስት መሪነት›› በፓርቲ ደረጃም ሆነ በሪፐብሊክ ፕሬዘዳንትነት ኢትዮጵያ ላይ የነገሠው ወታደራዊ አምባገነኑ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ኢትዮጵያ ላይ ያደረሰው ጉዳት በሥልጣን ወዳድነት ከሚለካ ጥፋት በላይ ነበር፡፡ ዝርዝሩን ማተት የዚህ ጽሑፍ ትኩረት አይደለም፡፡ የሰሜኑን ጦርነት አያያዙ ክስርስሩ ወጥቶ፣ ትግራይም ተይዛ፣ የ1981 ዓ.ም. የግንቦት ስምንቱ ዝርክርክ የግልበጣ ሙከራ ከከሸፈ በኋላ ወደ ነበረው ጊዜ እንምጣ፡፡ በመንግሥት ግልበጣው መክሸፍ ቁጭት፣ ተማሪዎች በአደባባይ እነ ጄኔራል መርዕድ ንጉሤንና ጄኔራል ደምሴ ቡልቶን ለለውጥ የተሰዉ አድርገው በአደባባይ ያወደሱበት ተቃውሞ፣ በመላ ኅብረተሰቡ (ሲቪል ከወታደር) ዘንድ የነበረበትን ተቃውሞ ያንፀባረቀ ነበር፡፡ ይህንን ተቃውሞ ማፈንም መሸንገልም ተስኖት ለሰላማዊ መፍትሔ ያለ ቅድመ ሁኔታ በሦስተኛ አደራዳሪ አማካይነት ለመደራደር ዝግጁ ነኝ እስከ ማለት የተንቶሰቶሰው ደርግ ከኢትዮጵያ ሕዝብም የመታረቅ፣ አሜሪካ ከምትመራው ምዕራብም ጋር የመታረቅ ወርቃማ ዕድል ከሰማይ ወርዶለት ነበር፡፡

ለጥገና ለውጥ ዝግጁ መሆኑን የሚያስረዳ ቡድን ወደ አሜሪካ ከመላኩ ባሻገር፣ ነሐሴ 1981 ዓ.ም.፣ በዕርዳታ ተግባር ወደ ደቡብ በአየር ይበር የነበረው አሜሪካዊው ሚኪ ሊላንድ የደረሰበት በጠፋ ጊዜ፣ ከሕዝብ ጋር ፍለጋውን አጧጡፎና የአሜሪካ የአየር ቃኚ ልግባ ቢል ፈቅዶ ለወዳጅነት ዝግጁ መሆኑን አሳየ፡፡ እንድብር አካባቢ የአሜሪካ ሔሊኮፕተር ባረፈ ጊዜ የእንድብር ሕዝብ እልልታ እያቀለጠና አቅፎ እየሳመ አሜሪካ ለምትመራው ምዕራብ ኅብረተሰባችን የነበረውን ናፍቆት ገለጸ፡፡ አሜሪካን ያስደነቀ ትልቅ የሕዝብ ዲፕሎማሲ! በዚህ ላይ ደግሞ መንግሥት የሚኪ ሊላንድ አስከሬንን በወታደራዊ ሠልፍ አጅቦ ያደረገውም የክብር አሸኛኘት ተጨመረበት፡፡ይህ ሁሉ ከአሜሪካ የዲፕሎማሲ ግንኙነትን የማሻሻል በጎ ፍቃድን በደንብ አለምልሞ ነበር፡፡ ከድርድሩ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያን አንድነት እንደምትደግፍ አሜሪካ ገልጻ ነበር፡፡ የጂሚ ካርተርም በገዛ ውዴታው ለአደራዳሪነት ፈቃደኛነቱን መግለጽ የነገሮች መሻሻል ምልክት ነበር፡፡

ሕዝብ አቀፍ ለመምሰል በተሞከረበትና በትግሪኛ፣ በኦሮሚኛ፣ በአፋርኛ ንግግር ማድረግ በታየበት የሃይማኖት መሪዎች ጭምር በተሳተፉበት ጥቅምት 20ዎች፣ 1982 ውስጥ የተካሄደ ብሔራዊ ጉባዔ ላይም ቢያንስ የፖለቲካና መንግሥታዊ መድረኩ ሰፍቶ ለኢትዮጵያ የቆሙ ተቃዋሚዎች ሁሉ እንዲሳተፉ ዕድል እንዲከፈት ተጠይቆ ነበር፡፡ ወደዚህ ያደላ ስምምነትም ታይቶ ነበረ፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ፣ ኅዳር አጋማሽ ላይ የሕወሓቱ ተወካይ በአሜሪካ ሬዲዮ በአስመራና በአዲስ አበባ ሁለት ሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ከሻዕቢያ ጋር ስለመስማማቱ፣ የኤርትራ ነገር ያለቀለት ጉዳይ ስለመሆኑና የላይኛው አፋር ጉዳይ የኤርትራ የውስጥ ጉዳይ ስለመሆኑ ከገለጸ ወዲያ፣ በሰፊ ኅብረትና በአዲስ መንፈስ ከደርግ ጋር ታርቆ ለኢትዮጵያ ጥቅም ለመቆም አገር ወዳድ ሁሉ (ከአገር ውስጥ እስከ ባህር ማዶ) አንድ ላይ ቆሞ ነበር፡፡

መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ከአገር ወዳዶች ጋር ፈጥኖ ተንቀሳቅሶ ቢሆን ኖሮ፣ የሽምቅ ተዋጊዎቹን ግስጋሴ በአዲስ የአርበኝነት ስሜት ገትቶና አስፈግፍጎ የአሰብ ወደብን ከአፋር ሕዝብ ፍላጎት ጋር ለኢትዮጵያ ባደረገ የድርድር ውጤት ከኤርትራ ተዋጊዎች ጋር ያለውን ጦርነት የመደምደም የመጨረሻ ዕድል ከፊት ለፊት ተደቅኖ ነበር፡፡ አራጁና የሥልጣን ስስት የበለጠበት መንግሥቱ ግን በጥፋት ላይ ጥፋት እየሠራ ኢትዮጵያን በሻዕቢያና በሕወሓት የምትያዝበት አፋፍ ላይ አደረሰና በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላሩን ተሸክሞ ፈረጠጠ፡፡ ሻዕቢያና ሕወሓት በአሜሪካ ድጋፍ የኢትዮጵያን ዕጣ እንዳሻቸው ለማድረግ እንዲችሉ ዕድል የሰጣቸው፣ እዚህ ደረጃ ላይ የተሠራ ጥፋት ነበር፡፡ ተቃዋሚዎችን ያሳተፈ የአገር ወዳዶች የኅብረት እንቅስቃሴውም፣ የመንግሥትና የኢኮኖሚ ማሻሻያውም ድርድሩም ከአሜሪካ ጋር ከመግባባት ጋር አንድ ላይ ተዘማምዶ ተካሂዶ ቢሆን ኖሮ፣ የፈለገ ቢሆን ሕወሓት አዲስ አበባ ሰተት የሚልበት ሁኔታ በፍፁም አይኖርም ነበር፡፡ የሕወሓት በአዲስ አበባ መንግሥት የመሳተፍም ጉዳይ ከአድራጊ ፈጣሪነት ውጪ በድርድር የሚገኝ በሆነ ነበር፡፡ በመጨረሻ ሰዓት እንኳ ከሥልጣን ስስቱ ቀንሶ ለኢትዮጵያ ማዋል ያቃተው ሰው፣ ብዙ ትብብርን በሚሻ በዚያ ክፉ ቀን ለሥልጣኑም ለስሙም የማይጠቅመውን ጭፍጨፋ በታሰሩ ጄኔራሎች የፈጸመ ግፈኛ፣ ዛሬ ‹‹መንጌ ሀቀኛ ኢትዮጵያዊ!›› እያሉ የሚያመልኩት ሰዎች ማግኘቱ የሚገርም ነው፡፡

 1. ሀ) ሕወሓት/ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ወደብ ባሳጣ አኳኋን ኤርትራን ከመሸኘት ይበልጥ ኢትዮጵያ ላይ የፈጸመው ጥፋት፣ ብዝኃዊ ጥንቅር አነሰም በዛ የነበረውን አገረ መንግሥታዊ የፀጥታ አውታሯን በትኖ በአንድ ብሔር በተዋጠና ለሕወሓት ታማኝ በሆነ የተጋዳላይ ጥንቅር ማዋቀሩ ነበር፡፡ የወደብ ማጣት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መጉደል ነው፡፡ የአገርን አውታር የአንድ ቡድን ይዞታ አድርጎ ማደራጀት ግን ኢትዮጵያን ራሷን የማፍረስ ያህል (በአንድ ቡድን መዳፍ ውስጥ የማስገባት) ክንዋኔ ነበር፡፡ ጥቅምት 2013 ዓ.ም. ግዙፍ ወረራ ሊከፈትባት የቻለው፣ ከዚህ ግዙፍ ወረራ የመትረፍ ነገርም ከሞት መንጋጋ የማምለጥ ያህል ዕፁብ ሊሆን የቻለው፣1980ዎች ውስጥ በተሠራው የአውታረ መንግሥት አከርካሪ ሰበራ ምክንያት ነበር፡፡

‹‹የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት…›› ሌላው አሳሳች ነው፡፡ በቅድሚያ ይህ ‹‹መብት›› የራስን ዕጣ ፈንታ በራስ ፍላጎት ፈቃድና ውሳኔ መምራት ስለመቻል የሚያወራ አይደለም፡፡ ስለምን እንደሚያወራ በኋላ እንመጣበታለን፡፡ ዕጣ ፈንታን ያለ ጫናና ጣልቃ ገብነት ስለመምራት መብት የሚያወራ ቢሆንስ ኖሮ እንደዚያ ያለ ነባራዊ መብት አለ? የዚህን ተጨባጭነት ከሰው ልጅ ታሪክ ጋር አያይዘን በአጭሩ መቃኘት ይጠቅመናል፡፡

የሰው ልጅ ዕጣ ፈንታ ከሰው ውጪ ከሆኑ ሰበዞች (ለምሳሌ፣ ከፀሐያዊ ሥርዓት ጋርና ከምድሪቱ ሥነ ምኅዳራዊ ለውጦች ጋር ከተያያዙ ክስተቶች) ውጪ ሆኖ አያቅውም፡፡ ከዚያ ሌላ የራሱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችና ዕርምጃዎች የእርስ በርስ ዕጣዎቹን መወሰናቸው ከዘመን ወደ ዘመን እየጨመረ ሲሄድ ነው የታየው፡፡ የጥንታዊ ሥልጣኔዎች/ኢምፓየሮች በመዘማመት መስፋፋት መግነንና መንኮታኮት፣ የአገሮች መጥበብና መስፋት፣ የአገሮች መዋዋጥና የአዳዲስ አገሮች መገንባት፣ ከካፒታሊዝም ማደግና ዓለም አቀፋዊ መስፋፋት ጋር አሰሳ፣ የባሪያ ፍንገላና ማጋዝ መጦፍ፣ የቅኝ ይዞታ መስፋፋት፣ የኢትዮጵያ የውጪ ጥቃትና ከበባ ረዥም ታሪክ፣ የዓድዋ ጦርነት፣ የፋሸስት ጣሊያን ወረራ፣ የሁለቱ ዓለም ጦርነቶች መዘዞች ሒደቶችና ውጤቶች ሁሉ የሚናገሩት የትኛውም አገርና ኅብረተሰብ ዕጣውን በፍላጎቱና በፈቃዱ ብቻ እንደማይወስን ነው፡፡ የአሜሪካና የሶቪዬት ልዕለ ኃያላዊ ጎራዎች በነበሩ ጊዜ የጭፍራ ቀጣናዎች በማስፋት ትግል ኃያላኑ በአገሮች ውስጥ ምን ያህል የመንግሥት ግልበጣዎች፣ አመፆችና የትጥቅ ትግሎች ይወጥኑና ያግዙ እንደነበር ምን ያህል የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎች ይረጩ እንደነበር ማስታወስ ነው፡፡ የምሥራቁ ጎራ መፈረካከስ የውስጣዊ ቀውሶች ውጤት ብቻ አልነበረም፡፡ በአሜሪካ ይመራ የነበረው ምዕራባዊ የተጠራቀመ ፕሮፓጋንዳዊ ግዝገዛና ትኩስ አማሳይነት የነበረበት ነበር፡፡ በ1969 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ላይ ሶማሊያ የከፈተችው ጦርነት ከእሷ ብቻ የመጣና እሷና ኢትዮጵያ ብቻ የተሳተፉበት አልነበረም፡፡ የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም መንግሥት የሶቪዬት ሩሲያ ጥገኛው፣ 1980ዎች ውስጥ የተብረከረከው በውስጥ ጣጣዎች ምክንያት ብቻ አልነበረም፡፡ ከምሥራቁ ጎራ መፈረካከስ ጋር ሩሲያ ቸል ስላለችውም ነበር፡፡ በእነ ሻዕቢያ የትጥቅ ትግል መጎልበትና ድል ውስጥም ሆነ በመንግሥቱ ኃይለ ማርያም መንግሥት የመጨራሻ መጥመልመልና የ‹ቆራጡ መሪ› ፍርጠጣ ውስጥ የውጭ እጅ ነበረበት፡፡

ዛሬስ ቀነሰ? በዛሬ የ‹ግሎባላይዜሽን› ጉዞ ውስጥ በየትኛውም አገር የማኅበራዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ክንዋኔ ውስጥ የውስጥና የውጭ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ሰበዞች (ከሩቅ እስከ አቅራቢያ ድረስ) አሉበት፡፡ ኩባ፣ ቬኑዙዌላ፣ ሄይቲ፣ ሶማሊያ፣ የሙጋቤ ዚምባቡዌ፣ ሱዳን፣ ኮንጎ ኬንሺያሳ፣ ሊቢያ፣ የመን፣ ኢራን፣ ኢራቅ፣ ሶሪያ፣ ሊባኖስ፣ ፍልስጤም፣ ወዘተ እያልን ደጋግመን የምናነሳቸው አገሮች ጣጣና የውጭ አማሽነት ብሶ የጎዳቸው ሆነው እንጂ፣ ጣልቃ ገብነትና ያልፈለገው ጫና የማይጎበኘው አንድም አገር (ትንሽ ነሽ ትልቅ) የለም፡፡ ኢትዮጵያ ከለውጡ አንስቶ እስከዛሬ ድረስ ባሳለፈችው የውስጥ ሰላም ጣጣዎች (የግጭት፣ የታጠቁ ኃይሎች መበራከትና ጦርነት) ጊዜም ሆነ በድርድርና በችግሮች መቅለል ጊዜ ውስጥ ብዙ የውጭ ኃይል ሰበዞችን ማየታችንና እያየን መሆናችን ሊካድ አይችልም፡፡ የዩክሬይን-ሩሲያ ጦርነትም ሆነ ጋዛ ላይ እስራኤል እያካሄደችው ያለው ጦርነት የውስጥ አላዋቂ ጀብደኝነትና የውጭ ጣልቃ ገብነት ሰበዞች ተቀናብረው የወለዱት ነው፡፡ በሒደት የውጭ እጆች የበረከቱባቸው ሁለቱም ጦርነቶች ከራሳቸው አካባቢ በራቀ ደረጃ በዓለም አቀፍ ንግድ አቅርቦት ላይ የእጥረትና የዋጋ ንረት ተፅዕኖ በዚህም ሳቢያ የፖለቲካ አለመረጋጋት እስከ ማሳደር አስከትለዋል፡፡ የዛሬው ጊዜ፣ ‹‹የራስን ዕድል በራስ ፍላጎትና ምርጫ መወሰንና መምራት ይቻላል ወይስ አይቻልም?›› የሚል ክርክር የሚነሳበት ሳይሆን፣ የየትኛውም አገርና ኅብረተሰብ አገነባብና የግስጋሴ ፈተናዎች የውስጥና የውጭ ሰበዞች የሚረካከቡበት መሆኑን ተገንዝቦ አሉታዊ ተራክቦዎችን አዳክሜ አዎንታዊ ተራክቦዎችን እንደምን ላብዛ/ላጎልብት ብሎ የመጠበብ ጉዳይ ነው፡፡ የአገሮችና የመንግሥታቸው ስኬት እዚህ ጥበብ ላይ የተንጠለጠለ ሆኗል፡፡

አገሮች የኅብረተሰባቸውን ግስጋሴና የኢኮኖሚና የሰላም ሁኔታ ብቻቸውን የማይወስኑት ስለመሆኑ ይህን ያህል ከተረዳን፣ ከአገር ወርደን በብሔረሰቦች ደረጃ የራስን የግስጋሴ ዕድል በራስ መወሰን ብሎ ነገር ከከባድም ከባድ የሆነ ምኞታዊነት እንደሆነ ማስተዋል ለፈለገ ቀላል ነው፡፡ በቻርተሩም ሆነ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተቀመጠው ‹የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል ድረስ›› እስካሁን ያወራለትን ዓይነት አይደለም፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 ላይ የተቀመጠው ‹‹የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል›› የፍቺ (ልለይ አልለይ ብሎ የመወሰን) ጉዳይ ስለመሆኑ የዚያው አንቀጽ ቁጥር (4) ይነግረናል፡፡ ‹‹መብቱ ተግባራዊ የሚሆነው…›› በሚል ሐረግ ተነስቶ፣ ከምክር ቤት ውሳኔ አንስቶ እስከ ውሳኔ ሕዝብና ንብረት ክፍያ ያለውን አካሄድ ያስቀምጥልናል፡፡

ይህንን ‹‹መብት›› ከምሥራቅ ቀድቶ በቻርተሩም ሆነ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ሁነኛ ውል እንዲሆን የፈር ቀዳጅነቱን ሚና የተጫወተው ሕወሓት፣ ጥረቱ ሁሉ በጊዜው የመነጠል አጀንዳ (በግልጽም ሆነ በሽፍፍን መልክ) የነበራቸውን ቡድኖች በአንድነት ውስጥ ለማቆየት ታክቲክ ነበር ብለን እናስብ፡፡ በዚህ ላይ የዓለማችን ልምድ የሰጠንን ትምህርት እናክል፡፡ ይህንን አንቀጽ በሕገ መንግሥታቸው ውስጥ ጽፈው የነበሩ አገሮች አንቀጹ ካስማ ሆኗቸው በአንድነት አልዘለቁም፡፡ አንቀጹን ሙጥኝ እንዳሉ መጨረሻቸው መፈረካከስ ሲሆን ታይቷል፡፡ የአንድነት ዋስትናው ወይም ካስማው ዴሞክራሲያዊ ነፃነትን እኩልነትንና ፍትሐዊ ግስጋሴን ይዘቱ ያደረገ የአገር መውደድ መታነፅ ስለመሆኑም ትምህርት ተገኝቷል፡፡ ይህ ባለበትና የመገንጠል መብት በሕገ መንግሥት ባልተቀመጠበት ‹‹ሪፈረንደሞች›› ተካሂደው በአንድነት ውስጥ መቀጠል የብዙኃኑ ምርጫ ሲሆንም ታይቷል፡፡ ሕወሓት ሲመራው በነበረው አገዛዝ ውስጥ ሲሆን የኖረው ከዚህ ልምድ ጋር የተገናዘበ ነበር? ሕወሓት/ኢሕአዴግ የሚያበርረውን አብርሮ፣ የሚያስፈልጉትን ጭፍራ ድርጅቶች አርብቶና የምርጫ ሒደቶችንና ውጤቶችን ተቆጣጥሮ ለመደላደል በሚጥርበትም ጊዜም ሆነ ከተደላደለም በኋላ ያራምዳቸው የነበሩ አስተሳሰቦች ያው ነበሩ፡፡ ትዳር መሥርቶ ልጆችና የጋራ ሀብት እያፈሩ ሳሉ፣ ጥልም በሌለበት፣ ልጆችና ቤተዘመድ በተሰባሰቡባቸው አደባባያዊ አጋጣሚዎች የፍቺ መብትን እንደ ንቃተ ህሊና ማውሳት፣ ‹‹የምንኖረው ትዳሩን እስከ ወደድነው ነው! ሀብት ተካፍሎ እስከ መለያየት ድረስ መብት አለን!›› እያሉ መቀባጠር ከጤና ማጣትና ትዳርን ጤና ከመንሳት የሚቆጠር ነው፡፡ ‹‹የብሔሮች መብት እስከ መገንጠል››ም ይህንኑ ዓይነት ሥራ ሲሠራ ኖሯል፡፡ በእውነተኛ የብሔሮች መከባበር፣ መተሳሰብና ፍትሐዊ ልማት ኢትዮጵያን ከመገንባት ይልቅ፣ አስተውሎትና ወገኔ ባይነት በየክልል፣ ከክልልም በየብሔረሰብ አንሶ እንዲከታተፍ የማኅበረሰቦችም ግንኙነት ባለቤትና ባይተዋር ተባብሎ እንዲመረዝ በዚህም ጭቆና/አድላዊነትና ቅያሜ እንዲባዛ ነው የተደረገው፡፡ እናም ‹‹ሲሻኝ ይዞታዬን ይዤ መገንጠል መብቴ›› እያሉ መጣበብ ታክቲክ ነበር ከማለት ይልቅ፣ በማወቅ የተደረገም ይሁን ባለማወቅ፣ ስትራቴጂያዊ ነበር ብሎ ማለት በኢትዮጵያ ሲሆን የነበረውን እውነት ይናገራል፡፡

ኢትዮጵያ፣ እንዲህ ያለ መከታተፍንም መጠፈርንም አብሮ ባዳበለ አገዛዝ ውስጥ ትውደቅ እንጂ የነበረችበትና አሁንም ያለችበት የዓለም ጉዞ በየሠፈር ማነስና መጣበብን የሚቃረንና የማይበጅ መሆኑን የሚናገር ነው፡፡ የዩጎዝላቪያና የሶቪየት ሩሲያ መፈረከካከስ ማነስን፣ መድከምንና እንዲያም ሲል መናቆርን ነበር ያስከተለው፡፡ የጀርመኖችና የቬትናሞች መቀላቀል ደግሞ ከዓለም የመሰባሰብ ሒደት ጋር ከመጣጣሙም በላይ፣ መተለቅንና መጠንከርን ነበር ያስከተለው፡፡ የኤርትራ መለየት ለኢትዮጵያ መጉደል ነበር፡፡ ለኤርትራ ደግሞ ከመጉደልም በብዙ ነገር ማነስ መሆኑ ቁልጭ ለማለት ጊዜ አልፈጀም፡፡ የሶማሊያ በጎሳ አበጋዞች መከፋፈል የሶማሊያውያንን ሕይወት ብቻ አልነበረም ሲዖል ያወረደው፣ የቀጣናውንም ሰላም ነበር የነሳው፡፡ በዚህ ላይ የኢትዮጵያ መቆራረስ ቢጨመር ውጤቱ የበለጠ አስፈሪ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ዘንድ እዚህ ላይ ቅዠት አልነበረም፡፡ ትርምስ ወለዱ የሶማሌያውያንና የአዲሷ ደቡብ ሱዳን ሰዎች ረሃብ መፈናቀልና ስደት ቤቱ ድረስ የገባ ነበር፡፡ የኤርትራ መነጠልም ዘላቂ ሰላምን እንዳላቀዳጀው ዓይቷል፡፡ ተሳስቦ በጋራ በማደግ ያልተመራው ማጋጣ ግንኙነት በወለደው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ውስጥ ሆ ብሎ የተነቃነቀው፣ ኤርትራውያን ወገኖቹን ጠልቶ ወይም በሕወሓታዊ ጥርነፋ ተገድዶ አልነበረም፣ አገራዊ ህልውናውና ጥቅሙ ቆስቁሶት ነበር፡፡

ለ) ከ1990 እስከ ቅድመ 1992 ምርጫ የነበረው የታሪክ አንጓ፣ ለብቻው መታየት የሚገባው፣ በጋራ ሐዘን ውስጥ ‹‹ተመስጌን›› ያስባለ ደስታ ፍልቅ ያለበት እንቆቅልሻም አንጓ ነው፡፡ በትልቅ የቤተ ዘመድ የመገዳደል ክስረት ውስጥ ሆኖ በቤተሰብ ደረጃ ‹‹ስለማሸነፍ›› ማሰብ ለወሬም የማይመች ነው፡፡ የ1990ው የኢትዮ-ኤርትራ የዘመዳሞች ጦርነት መጀመርም መሰንበትም ያልነበረበት ስለመሆኑ ብዙ ተብሏል፡፡ በዚህ ጦርነት ከሁለት በኩል ብዙ ሺዎች ረግፈዋል፡፡ የሁለቱም አገሮች ኢኮኖሚ አፈር ድሜ በልቷል፡፡ እንደዚያም ሆኖ ያ ጦርነት የለውጥ መልካም ዕድሎችን ሁለቱም ዘንድ ፈንጥቆ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ተወስኜ፣ ከሕወሓት መሰንጠቅ በፊት ስለነበረው ሁኔታ ጥቂት ነገሮችን ላስታውስ፡፡ ያ ጦርነት፣ በጦር ሜዳ ከሚኖር ሞት ባሻገር ከወዲያና ከወዲህ የሚባረሩ ሰዎች ፍዳ የሚቆጠርበት ጊዜ ሆኖ ሳለም የኢትዮጵያውያን አገር ወዳድነት እስከ ምን ድረስ እንደሆነ የተፈተነበትም አንጓ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አገር ወዳድነታቸውን ‹‹የአክሱም ሐውልት ለወላይታ ምኑ ነው!›› ባለ ንግግር አጥብበው አለኩትም፡፡ ከ1983 ዓ.ም. ወደ እዚህ ለሰባት ዓመታት ያህል በተሟሹበት በየሠፈር የተከታተፈ አስተውሎት አልተገደቡም፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግ የደርግ ጨፍጫፊ ሠራዊት ብሎ ያለ ጡረታ ያበረራቸው የቀድሞ ሠራዊት አባላት (በድህነት ከተቆራመዱት አንስቶ ባህር ማዶ ተሻግረው ወፍራም እንጀራ ለመብላት እስከ ተቻላቸው ድረስ) ጉርስ ነፍገው ባበረሯቸው ገዥዎች አዛዥነት ሥር ተዋጉ ሲባሉ ቂም በልጦባቸው እንቢ አላሉም፡፡ ሁሉም በስሜት የተነቃነቀው የካድሬ ደነዝ ስብከትን ጆሮዬ አይስማ እያለ ግን ከአገዛዝ በደል ይልቅ የአገር አላፊነቱና መውደዱ በልጦበት ነበር፡፡

ይህ ጦርነት ባልተደረገ ብለን የምናዝንበትና ከሁለት በኩል የከሰርን ጥቁር ለባሾች የሆንበት ቢሆንም፣ በክስረታችን ውስጥ መልካም ፍሬዎች ያየንበት ነበር፡፡

 • ከኢትዮጵያ አኳያ በጊዜው የተካሄደው የሠራዊት ግንባታ ሕወሓታዊ የዕዝ ሰንሰለትን ባያናጋም ኅብረ ብሔራዊ ስብጥሩን ጉልህ ዕድገት እንዲያሳይ አስችሎ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ የተደረገ የስብጥር ዕርምጃ ከጦርነት በኋላና በሕወሓት መሰንጠቅ ጊዜ ቅነሳና እከላ ተካሂዶበት፣ በ2013 ዓ.ም. የፈተና ጊዜ ኢትዮጵያ የጎደላትን እስክታሟላ የሚቻለውን ያህል ስንቅ ሆኖ አገልግሏታል፡፡
 • ያ ክፉ ወቅት፣ የኢሕአዴግ ገዥዎችንና የቀድሞ ሠራዊትን ይቅር ለመባባል ዕድል ሰጥቷል፡፡ ኢሕአዴግ ከሕዝብም ከተቃዋሚዎቹም ጋር እንዲታረቅ ዕድል ሰጥቷል፡፡ ዕርቁ የአዳራሽ ንግግርና ውሳኔዎች ሳይሻ በተግባር ተጀምሮም ነበር፡፡ ሳይጠማመዱና ሳይኳነኑ ተጋግዞ ለአገር መሥራት እንደሚቻልም ያች አንጓ በተግባር አሳይታ ነበር፡፡ በዚያች የሁለት ዓመታት አካባቢ ጊዜ፣ ሰላይ አለብኝ ሳይሉ ሐሳብን መግለጽ ተችሎ ነበር፡፡ ጋዜጦችና መጽሔቶች ከሾኬ አዙሪት ወጥተው ነበር፡፡ የሕወሓት/ኢሕአዴግ አባላት የግል ጋዜጦችንና መጽሔቶችን፣ ‹‹ተቃዋሚዎችም›› የመንግሥት ኅትመቶችን ይዘው ለመዞርም ሆነ እያነበቡ ሐሳብ ለመለዋወጥ ችለው ነበር፡፡
 • ይህ የተለሳለሰ መስተጋብር ሳይናጩ ለአገር ለመሥራትም ሆነ የአገርን/የሕዝብን ጥቅም ባስቀደመ መተሳሰብና መከባበር ዴሞክራሲን እየተለማመዱ ለመገንባትም እንደሚቻል ቀዳማዊ ትምህርት የሰጠ ነበር፡፡
 • የትናንትናን የተኮሳኮሰ ልምድ ለትናንትና ትቶ አዲሱን ገር ሁኔታ ከተቃዋሚዎቹ ጋር ይዞና ተንከባክቦ ወደፊት ለመራመድ ለኢሕአዴግ ነገሮች በስለውለት ነበር፡፡ በጦርነቱ ከተገኘው ድል ጋር ከተቃዋሚዎች ጋር አብሮ ለአገር በመሥራት የዕርቅ መንፈስ የ1992 ዓ.ም. ምርጫን ቢያስኬደው ኖሮም መሸነፍ የሚያስፈራው አልነበረም፡፡ የተወሰኑ ወንበሮችን ለተቃዋሚዎቹ ለማቋደስ ቸርነት አሳይቶ ቢሆን ኖሮ፣ በተለይም ‹‹ክልላዊ›› አስተዳደር ውስጥ ያለ ቁራጭ መሬትም ሆነ የሕዝብ ህልውና የክልሉ ብቻ እንዳልሆነ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ያስተማረውን ያህል የአመለካከት ዕርማት ለማድረግ ችሎ ‹‹የክልል/የብሔር ሉዓላዊ መብት›› ከሚል ዝባዝንኬ መውጣት ችሎ ቢሆን ኖሮ እንኳ፣ በተቃዋሚዎቹና በኢሕአዴግ መሀል የነበረ ትልቅ ገደል ተቆርሶ ይወድቅ ነበር፡፡ በተሻሻለ ፖለቲካ የጋራ መግባባት ያለበት ብዙ ዘላቂ ነገር መሥራት በተቻለ ነበር፡፡

ኢሕአዴግ ግን ያንን መልካም አጋጥሚ ራሱን ከወጥመድ ማውጫ አድርጎ ብቻ ቆመረበት፡፡ ‹‹አቋምን ለድርድር ማቅረብም ሆነ ሥልጣን በአቋራጭ መፈለግ ዴሞክራሲን የሚጎዳ ነው… አቋማችን የሚታረቅ አይደለም… በምርጫ የቻለ ይግጠመኝ›› ባይ መልቲነቱንና ‹‹ፀረ ሰላም!..›› የሚል ውንጀላውን መልሶ አመጣው፡፡ ያንን የመሰለ ለአገር የሚበጅ በደም የተዋጀ ወርቃማ የዕርቅ ጅምር ለሥልጣን ስስቱ ሰዋው፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ለስላሳ ዕድሎች እየባከኑ ‹‹ወይ ነዶ!›› ያሰኛሉ፡፡ የ1997 ዓ.ም. የምርጫ ጊዜም ወይ ነዶ የሚያሰኝ ነው፡፡ ግን ዕርቃዊ ድባብን ኢትዮጵያውያን በውስጣቸው ከተቃመሱበት የጦርነት ጊዜ ጋር እኩል ሊታይ ከቶም አቅም የሌለው ነው፡፡ የ1997 ዓ.ም. የምርጫ ጊዜ ከሌላው የምርጫ ጊዜ የሚለየው ኢሕአዴግ በዴሞክራሲ ወግ ለማሸነፍ የተዳፈረበትና ከእሱ ይበልጥ ተቃዋሚዎቹ የብልጠት ማነስ ጥፋት የሠሩበት በመሆኑ እንጂ ሁለቱም ተጠማምዶ ከመሽቀዳደም ውጪ አልነበሩም፡፡ ተቃዋሚዎች ኢሕአዴግን ከመዘረር በመለስ ለሚገኝ መለስተኛ የወንበሮች ድል ከእነ ደጋፊያቸው ተዘጋጅተው ቢሆን ኖሮ የዴሞክራሲ ጅምር ብዙ ይጠቀም እንደነበር ተደጋግሞ የተተቸ ስለሆነ የ1997 የምርጫ ጊዜን እንደ አንድ አንጓ ማሰስ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ለስላሳዎቹ ዕድሎች መክነው የንቁሪያ፣ የመደማማት መራር ልምዶች በመስዋዕትነት በእንግልትና በዕንባ ቅጣት የሚያደርሱበት ልምድ ግን ከ1997 የምርጫ ልምድ በኋላም ተከትሏል፡፡ ቤት ውስጥ ከተፈጸሙት ቅጣቶች ባሻገር በእነሊቢያ፣ ኢራቅ፣ ሶሪያና የመን፣ ወዘተ ከጊዜ ጊዜ ሲደርሱ የየቆዩት የትርምስና የጦርነት ሰቆቃዎችም እኛን ያየህ ተማር የሚሉ ነበሩ፡፡

ከዓለማችንና ከዙሪያችን የተገኘውን የተሞክሮ ትምህርት እንደሚከተለው ማጠቃለል ይቻለል፡፡

 • ፍትሐዊ ሥርዓትን/ዴሞክራሲን በትጥቅ ትግልና በመንግሥት ግልበጣ ሴራ እተክላለሁ ብሎ ማሰብ የተሳሳተ፣ እንዲያውም ልዕለ ኃያላን ጥገኛ መንግሥት የሚፈለፍሉባቸው/ የሚኮናተሩባቸው መንገዶች መሆናቸው ለዓለም ገሃድ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡
 • በቅኝ ገዥዎች ላይ የተካሄዱትም የሐርነት ትጥቅ ትግሎች ከቀጥተኛ የባዕድ ተገዥነት ከመላቀቅ ዕርባና ባለፈ ግድ ወደ ኢኮኖሚያዊ-ፖለቲካዊ ሓርነትና ፍትሐዊ ግስጋሴ ለመሄድ ዋስትና እንደማይሆኑ በታሪክ ከተመሰከረ ውሎ አድሯል፡፡
 • በሕዝብ ነፃነት ስምና በዴሞክራሲ ስም በአንድ አገር ውስጥ የሚከፈቱ የትጥቅ ትግሎችም የሕዝብን ሰላምና ኑሮ የሚያማቅቁ በርዝመታቸው ድህነትንና ውድመትን የሚያበራክቱ የተሳሳቱ የትግል ሥልቶች መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ በትጥቅ ትግል ጊዜ ዓላማ ተብለው የተነገቡ የሚያማልሉ ግቦችን ከ‹ድል› በኋላ ወደ ተግባር መለወጥ የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት እንዳላቸውም በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ በአገራችንም በ‹ባለድልነት› የሚጠቀሱት የሕወሓትና የኤርትራ የረዥም ጊዜ ተጋድሎዎች እዚሁ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡
 • የሆነ ሰበብ/ቅራኔ አጡዞ ወደ መነጠል መሄድና ወደ ዴሞክራሲና ግስጋሴ መሄድ መንትዮች እንዳልሆኑ፣ መነጠል (መሸሽ) የዴሞክራሲና የግስገሴ አማጪም እንዳልሆነ፣ የመነጠል ትግል የትግል አቅምን የሚከፋፍል የመነጠል ጥያቄ ያነገበውን ኃይል ለይቶ የሚያስመታና የአፋኝ ገዥዎችን እድሜ የሚያራዝም፣ የአፈና ሥርዓትን ተባብሮ መታገል ግን ዴሞክራሲያዊ-ፍትሐዊ የለውጥ ዕድልን የበለጠ እንደሚያቀርብ ታሪክ ደጋግማ መስክራለች፡፡
 • መነጠልን ለማሳካት ሲባል ቅኝ ተያዝን የሚል በልቦለድ የጦዘ በደል መፍጠርንማ ታሪክ የከሰረ ተረት አድርጋዋለች፣ ያውም ሻዕቢያንና ኦነግን የቁም ምስክር አድርጋ፡፡
 • የተጠማመዱ ጎረቤት አገሮች በ‹ነፃነትና በፍትሐዊ ለውጥ›› ስም የሚተክሏቸው/የሚያግዟቸው መጠቃቂያ የትጥቅ ትግሎች የሁለት በኩል መማቀቂያ (ሁለቱም አገሮች ኅብረተሰባቸውን በድህነት፣ በሰላም ዕጦትና በውድመት ወጥመድ ውስጥ የሚያቆዩበት ወዶገባ ክስረት) መሆኑ ከመረጋገጡ ባሻገር በታሪክ የተሳቀበትና የተናቀ አሮጌ ነገር ሆኗል፡፡ አንዱ ጎረቤት አድብቶ ወረራ ቢከፍት እንኳ ሮጦ ወታደራዊ ግጥሚያ ከመግባት ይልቅ ወረራ የከፈተውን አገር ወደ ውይይታዊና ዕርቃዊ መፍትሔ እንዲመጣ መጣር የፈሪ መላ ሳይሆን ሁለቱንም ጎረቤታሞች የሚበጅ አስተዋይነት መሆኑን የታሪክ ልምድ አስተምሯል፡፡
 • በዚህ እየተጠቃለለ በመጣ ዓለም ውስጥ የውስጥ ጉዳይና የውጪ ጉዳይ ተወራራሽ ሆኗልና የቅርብም የሩቅ ጎረቤት አገር ሥርዓት አልባነት ሁኔታ ውስጥ መግባት የማይሳቅበት/ዝም የማይልበት፣ ጣጣው ተስቧዊ ሆኖ እንዳይባዛ ራስን የማዳን ያህል የተጋገዘ ጥረት ማድረግ የሁሉም (በተለይም የአካባቢው አገሮች) ኃላፊነት የሆነበት ዘመን ውስጥ ተገብቷል፡፡

መጋቢት 2010 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ሰላማዊ መተካካት መልክ የጀመረው የኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ ብቅ ያለው፣ እነዚህን የመሳሰሉ ትምህርት ሰጪ ዓለማዊና ቀጣናዊ ዓውዶች ውስጥ ነበር፡፡ (ይቀጥላል)

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...