Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት ባዮሎጂና የብዝኃ ሕይወት ተመራማሪ

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400 የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም. ወርኃ ሰኔ የተወለደው ሉዶልፍ፣ ከመምህሩ አባ ጎርጎርዮስ ካሰባሰበው መረጃ በመነሳትና በጥንታዊ ብራናዎች ላይ ባደረገው ጥናት፣ 17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ስለ ኢትዮጵያ የሚናገሩ መጻሕፍትን አሳትሟል፡፡ ከነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ታሪክ (Historia Aethiopica) የግእዝ ሰዋስው (Grammatica Aethiopica)፣ የላቲንና አማርኛ (Amharico-Latinum) መዝገበ ቃላት ይገኙበታል፡፡ አዲስ አበባ የሚገኘው የጎተ ኢንስቲትዩት የልደቱ 400 ዓመት አስመልክቶ ስለ ሂዮብ ሉዶልፍና አባ ጎርጎርዮስ ሥራዎች የሚዘክር ሲምፖዚየም በቅርቡ አካሂዶ ነበር፡፡ በመድረኩ ጥናታዊ ሥራቸውን ያቀረቡት የታሪክ ተመራማሪው ሽፈራው በቀለ (ፕሮፌሰር)፣ የፊሎሎጂ ባለሙያው አባ ዳንኤል አሰፋ (ዶ/ር) እና የዕፀዋት ሳይንቲስቱ ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር) ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር ሰብስቤ  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት ባዮሎጂና የብዝኃ ሕይወት አስተዳደር ዕውቅ ሳይንቲስት ናቸው። 1970ዎቹ መጀመርያ ጀምሮ በማስተማርና በድኅረ ምረቃ ሥልጠና እንዲሁም በብዝኃ ሕይወት፣ በኤትኖቦታኒ፣ በሥነ ምኅዳር (ኢኮሎጂ) በተያያዥ መስኮች በምርምር ላይ ተሳትፈዋል። ከሰባት ያላነሱ መጽሐፎችና ከሁለት መቶ በላይ ሳይንሳዊ ጽሑፎችን አሳትመዋል። በኢትዮጵያ የሚገኙ ዕፀዋት መልከዓ ምድራዊ ሥርጭት፣ ዓይነትና መጠንን በጥልቀት የሚፈትሽ ጥናት የከወኑት ፕሮፌሰሩ በግላቸውና በጋራ ከሠሯቸው ከብዝኃ ሕይወት ጋር የተያያዙ የምርምር መጻሕፍት መካከል ‹‹Aloes and Other Lilies of Ethiopia and Eritrea›› ‹‹Aromatic Plants of Ethiopia›› ‹‹Atlas of the Potential Vegetation of Ethiopia›› ‹‹Ethiopian Orchids›› ‹‹Field Guide to Ethiopian Orchids›› ይገኙበታል፡፡  በምርምራቸው ስኬቶችን በመጎናፀፋቸው የተከበሩ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ከእንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ጣሊያን፣ እንዲሁም ከሌሎች ተቀብለዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ በሆኑ በዴንማርክ የሳይንስ አካዴሚ (2000) የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚና የእንግሊዝ ሮያል ሶሳይቲ (2010) አባል በመሆን ይሠራሉ። አባ ጎርጎርዮስንና ሂዮብ (ኢዮብ) ሉዶልፍን በዘከረው መድረክ ላይ ስላቀረቡት ጥናት ሔኖክ ያሬድ በቢሮአቸው በመገኘት አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያን በተመለከተ አባ ጎርጎርዮስና ሂዮብ ሉዶልፍ ያበረከቱት ነገር ምንድን ነው?

ፕሮፌሰር ሰብስቤ፡- ጀርመናዊው ሂዮብ ሉዶልፍ የኢትዮጵያዊውን ሊቅ የአባ ጎርጎርዮስን ዕውቀትና ግንዛቤ፣ ሐሳብና አስተያየት በጽሑፎቹ ውስጥ በማካተትና በአውሮፓ ተደራሽ በማድረግ በኢትዮጵያ ጥናት ውስጥ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ባበረከቱት አስተዋጽኦ ምክንያት የኢትዮጵያ ጥናት መሥራች በአውሮፓ በማለት ይጠሯቸዋል። ምክንያቱም ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ታሪክና ቋንቋዎች በጀርመን አገር ሆነው ኢትዮጵያ ሳይመጡ ከኢትዮጵያው ሊቅ አባ ጎርጎርዮስ ጋር ሆነው አጥንተዋል፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ብዝኃ ሕይወት፣ ሥርዓተ መንግሥታት ሁሉ የያዘ መጽሐፍም ጽፈዋል፡፡ የእሳቸው 400ኛ ዓመት ሲከበር በመጽሐፋቸው ስለጻፉት ስለ ዕፀዋትና ስለእንስሳት ዝርያዎች ዳሰሳዬን እንዳቀርብ በተጋበዝኩት መሠረት ነው ያቀረብኩት፡፡ ሉዶልፍ በመጽሐፉ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ የመንግሥታት ታሪክ፣ የአፈርና የብዝኃ ሕይወቱን ገጽታ ምን እንደሚመስል ለምነቱና ያለውን ሀብት ጽፈዋል፡፡ በእንስሳት በኩል ትልልቅ የዱር እንስሳት፣ ከውኃ ውስጥ የሚወጡ አራዊት፣ የእባብ ዝርያዎችና ወፎችንም ከሥዕላዊ መግለጫዎች ጋር አካተው አቅርበዋል፡፡ አሁን ስናነበው ዕውን እንዲህ ነበረ የሚል ሐሳብ የሚያጭር እናገኝበታለን፡፡ ለምሳሌ ከዕፀዋት ከአዝርዕት ጤፍን፣ ስንዴን ገብስን፣ አጃን፣ ሙዝ፣ እንሰት፣ ሩዝ የወይን ፍሬዎች ጠቅሰዋል፡፡ የዕፀዋት መድኃኒቶችንም ዘርዝረዋል፡፡ ይህን በሚዘረዝሩበት ጊዜ አንዳንድ ለመቀበል  የሚያስቸግሩ አሉ፡፡ በወቅቱ እውነት የሆኑ ሊሆኑ ይችላል፡፡ ጥቃቅን የዘር ፍሬ ያለው ጤፍ ለምግብነት እንደሚውል ሲገልጹ፣ ስለገብስ ሲገልጹ ግን አብዛኛውን ጊዜ ለፈረስ ምግብነት የሚውል ነው ብለው ጠቅሰዋል፡፡

ሌላው የጠቀሱት በአገሪቱ ብዙ የወይን ፍሬ አለ፣ ይተከላል ይበቅላል ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ወይን አያመርቱም፣ ወይ ዕውቀቱ የላቸውም በተለያየ ጊዜ ስለማያፈራና የሚጎመራበት ጊዜ የተለየ ስለሆነ አያደርጉትም ይላሉ፡፡ ሌላው ከአጃ ይልቅ ሩዝ ይወዳሉ የሚለው አባባላቸው በጣም የገረመኝ ነው፡፡ ሩዝ የምሥራቅ አገሮች የእነ ህንድ፣ ቻይና ምግብ ሆኖ ሳለ እንዴት ሩዝን ይመርጣሉ ያሉት በምን አግባብ ነው? ክትትል የሚያስፈልገው ነው፡፡ በአሁን ወቅት ሩዝ ምን ያህል ተስፋፍቷል፣ በተወሰነ ቦታ ይበቅላል፡፡ ከ400 ዓመት በፊት እንዴት ነው እንደዚያ የነበረው የሚል ጥያቄ የሚያስነሱ ነገሮች አሉ፡፡ ከእሱ በተጨማሪ ደግሞ ትኩረቴን የሳበው አንድ ዕፅ ነው፡፡ ‹‹አሳዞ›› የሁሉ ነገር ፈውስ ነው ይሉታል፡፡ በተለይም የአገሬው ሰው አሳዞን በኪሱ ከያዘ እባብ አጠገቡ ካለ ይሸሻል፡፡ አኝኮ ቢውጠው አጠገቡ አይደርስም ይላል፡፡ የሉዶልፍ አስተማሪ የሆኑት አባ ጎርጎርዮስ ከሰሜኑ የአገራችን ክፍል የሄዱ በመሆኑ ‹‹አሳዞ›› የሚለው ቃል በአማርኛም ሆነ በትግርኛ እንዳለ ብፈልግ አላገኘሁም፡፡ ወደፊት ይገኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የሚባለው ነገር እውነት ከሆነ ጥናት የሚያስፈልገው በመሆኑ በሰሜን በኩል ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችን አጣርተው ትክክለኛ የሳይንስ ስሙ ቢታወቅ ይጠቅማል፡፡

ሪፖርተር፡- በግእዝ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ስለ ልዩ ልዩ መድኃኒቶች የሚገልጽ ‹‹ዕፀ ደብዳቤ›› የሚባል ብራና አለ፡፡  ሉዶልፍ በዚያን ጊዜ ከአስተማሪው፣ ከታሪክ ነጋሪው አባ ጎርጎርዮስ ካገኘው መረጃ በተጨማሪ ከግብፅ ከሄዱት ብራናዎች ውስጥ ዕፀ ደብዳቤን አግኝቶ ተጠቅሞስ ከሆነ?

ፕሮፌሰር ሰብስቤ፡- ሂዮብ ሉዶልፍ በጣም የታወቀ የታሪክ ሰው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ባይመጣም ግእዝን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ዓረቢኛና ላቲንም ይችላል፡፡ አማርኛም ይሞክራል፡፡ እዚህ ሳይመጣ ብዙ ዕውቀት አለው፡፡ ከኢትዮጵያ የሄዱትን መጻሕፍትን አጥንቷል፡፡ በተለይ በግብፅ በኩል የተሰነዱትን መርምሯል፡፡ አባ ጎርጎርዮስን ከማግኘቱ በፊት መጻሕፍትን መርምሯል፡፡ ካገኛቸው መረጃዎች ላይ ጥያቄዎችን አውጥቶ ከሳቸው ምላሽ አግኝቷል፡፡ ሥራው የሁለቱም ነው፡፡ አሳዞ የተባለው ዕፅ፣ በዕፀ ደብዳቤም ሆነ በሌላ ይገኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ አዲስ ነገር ያገኘሁት ስለ ሙዝና እንሰት ነው፡፡ አባ ጎርጎርዮስ ከሰሜኑ የአገራችን ክፍል የሄዱ ስለሆነ በወሎም ሆነ በትግራይ ያኔ የሙዝ ብዝኃነት ነበረ ወይ ብዬ እንድጠይቅ አድርጎኛል፡፡ በመጽሐፉ በሥዕል ጭምር ተደግፎ የቀረበው ሐተታ እንሰት በሰሜኑ ክፍል ከ400 ዓመት በፊት እንደነበረ ነው፡፡ እንሰት በአሁኑ ጊዜ በደቡብና በምዕራቡ አካባቢ በብዛት የሚታይ ነው፡፡ አባ ጎርጎርዮስ በነገሩትና በጻፈው መሠረት እንሰቱን በጣም የሚገርም ትልቅ ዛፍ ብሎ ነው የጠቀሰው፡፡ አገላለጹ ዛሬ ከምናውቀው የእንሰት አጠቃቀም ይለያል፡፡ ዛፉን (እንሰቱን) ከላይ ጀምረህ ከመሃል ሰንጥቀህ ወደ ሥር ብትደርስ እንሰቶችን ታገኛለህ፡፡ የሚበላም ነው ይላል፡፡ የዛሬ 400 ዓመት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል እንሰት ይበላ እንደነበር ያሳያል፡፡ የእንሰት ሥዕል ለመጀመርያ ጊዜ የተሣለው ጀምስ ብሩስ የዓባይን ምንጭ ሊፈልግ ሲመጣ አብሮት በመጣው ሠዓሊ ነው፡፡ እንሰት በሰሜን ስለመበላቱ ሰነድ አላገኘሁም፡፡ ሂዮብ ሉዶልፍና አባ ጎርጎርዮስ የጻፉት ላይ ግን ኅብረተሰቡ ይመገበው እንደነበር ተገልጿል፡፡

ሪፖርተር፡- እንስሳትን በተመለከተስ መጽሐፉ ምን ይዟል?

ፕሮፌሰር ሰብስቤ፡- እንስሳትን በሦስት/አራት ቦታዎች ነው የመደባቸው፡፡ የዱርና የቤት እንስሳትን ዘርዝሯል፣ አስፈሪ አራት እግር ያላቸው የዱር አራዊት ውስጥ አንበሳ፣ ነብር፣ ጅብ፣ በሌላ በኩል የተለያዩ ዓይነት ጦጣዎችን ከነሥዕላቸው አቅርቧል፡፡ በአሁን ጊዜ የማይታወቁ ጭራ የሌላቸው ጦጣዎችም ይታያሉ፡፡ ከሌላ አገር ቀላቅለው ነው ወይስ ነበሩ የሚለው እንደገና መፈተሽ አለበት፡፡ የእንስሳቱን ስም በአማርኛ በግእዝ፣ በእንግሊዝኛ አድርገው ጽፈውታል፡፡ የሜዳ አህያ፣ ቀጭኔ፣ ወፎችና ነፍሳት ውኃን መኖሪያቸው ያደረጉ ፍጥረታትንም ይዟል፡፡ ሁለተኛው የእንስሳ ክፍል ከውኃ ውስጥ የሚወጡ አራዊት አሉ ብለው ከጠቀሷቸው ጉማሬ ይገኝበታል፡፡ ጉማሬ ከውኃ ውስጥ ወጥቶ ሳር ይበላል፡፡ እሳቸው ያሣሉት ግን አንበሳን የሚመስል ጥርስ ያለውና ተናካሽ እንደሆነ አድርገው ሲያቀርቡ፣ አባ ጎርጎርዮስ ጣና አካባቢ ያየሁትን ጉማሬ አይመስልም እንዴት እንደሣልከው አላውቅም የሚሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ ‹ታይገር› እንዳለም ተጠቅሷል፡፡ ነብሩን ነው ታይገር ያሉት፡፡ የአጻጻፍ ስህተት ነው፡፡ ስለመጠጥ ጠላን በስም ባይጠቅሱም የሚጠቀሙበት አለ ብለው አውሮፓውያኑ ለቢራ የሚጠቀሙበትን ‹‹ሆፕ››› ጠቅሰዋል፡፡ ሆፕ ያሉት ጌሾውን ነው፡፡ ጌሾው ለጠላ የሚረዳ ነው ሲላቸው እነሱ በሚያውቁት ሆፕ ብለውታል፡፡ እንሰትና ሙዝን ‹‹የህንድ ዛፍ›› ነበር ያሉት የስም ግድፈቶች ይታየሉ፡፡

ሪፖርተር፡- አውሮፓውያኑ ኢትዮጵያን ለምን ለማጥናት ፈለጉ?

ፕሮፌሰር ሰብስቤ፡- አውሮፓውያኑ በኢትዮጵያ ላይ ያተኮሩት አንደኛው መንግሥቱ የክርስቲያን መንግሥት ነው ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡ በመጽሐፉ ላይ እንደተጠቀሰው ‹‹የፕሬስተር ጆን አገር›› (የንጉሡ የካህኑ ዮሐንስ አገር) የሚል አመለካከት መፍጠራቸው ነው፡፡ ከሱ ሌላ በዓለም ደረጃ ጥሩ ቦታ የሚባሉ እህሎች የሚመረቱባቸው ወይም የተለመዱባቸው ቦታዎች ተብለው ከሚጠቀሱት ኢትዮጵያ በዓለም ካሉት ስምንቱ አንዷ ነች፡፡ ከእኛ ውጪ በሜዲትራኒያን አካባቢ ያሉ ግብፅ ኢራን፣ ቱርክን ጨምሮ ብዙ የምግብነት ዕፀዋት የተፈጠረባቸው/የተላመደባቸው ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን ደግሞ ሲያውቁ ብዙ የተላመዱ የእህል የሰብል ዝርያዎች የእንሰት፣ የጤፍ፣ ገብስ፣ ስንዴ ስላሉ ከሌሎቹ የሜዲትራኒያን አካባቢ አገሮች የማያንስ መሆኑ መረዳታቸው ነው፡፡ የእርሻ አስተራረስ ከበሬው ጀምሮ ከሌላው የተለየ ነው፡፡ ሕዝቡም የተለየ ዕውቀት የሥልጣኔ መነሻ አለው ብለው ማሰባቸው ነው ኢትዮጵያን ለማጥናት የፈለጉት፡፡ ኢትዮጵያ የብዝኃ ሕይወት ማዕከል በመሆኗ፣ የግብርና አመራረቷ በጣም የተለየ ስለሆነና ከሌሎች አገሮች ጋር የምትወዳደር በመሆኗ ትኩረት ስባለች፡፡

ሪፖርተር፡- የሂዮብ ሉዶልፍ መጻሕፍት ለዚህ ዘመን ያላቸው ጠቀሜታ እንዴት ይገለጻል?

ፕሮፌሰር ሰብስቤ፡- የሉዶልፍ መጻሕፈት የተቀናጁ ናቸው አንድ መጽሐፍ ይምሰል እንጂ አራት ክፍሎች አሉት፡፡ የዛሬ 400 ዓመት የተጻፈው መጽሐፍ እንዴት ነው የምናየው? ከአራቱ ክፍሎች የመጀመርያውና ‹መጽሐፍ 1› እየተባለ የሚጠራው በአባ ጎርጎርዮስ ትረካ ላይ የተመሠረተ የዕፀዋትና የእንስሳት መረጃዎችን ያካተተ ነው፡፡ በተለይ መድኃኒቶቹ ጥልቅ ምርመራ ያስፈልጋቸዋል፡፡ መግለጫዎቹ የበለጠ ጥንቃቄ የተሞላበት ምርመራ የሚያስፈልጋቸው ግን ጠቃሚ የሚሆኑ ናቸው፡፡ ከዚህም ባለፈ በኢትዮጵያ የነበሩ የተያዩ ንጉሦች ስለነበሯቸው ምልክቶችና ማኅተሞች ታሪክንም የያዘ ነው፡፡ ሁለቱም አባ ጎርጎርዮስም ሆኑ ሂዮብ ሉዶልፍ ለኢትዮጵያ ጥናት መጀመር ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ሊመሠገኑም ሊዘከሩም ይገባል፡፡ በበርካታ ወራት ውስጥ ሉዶልፍና አባ ጎርጎርዮስ መዝገበ ቃላትን በጋራ አዘጋጅተው ሰፊ ውይይት አድርገዋል፣ በኢትዮጵያ ስላለው ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሁኔታ ዝርዝር መግለጫ ሰጥተዋል፣ በዚህም በኢትዮጵያ ላይ ለሚደረገው ጥናት አስፈላጊ መሠረት ጥለዋል።

ለመሆኑ እኛስ በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው? ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አድርገናል መጠየቅ ያለበት ነው፡፡ ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ ምድር ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ ገጽ ያለው ትልቅ መጽሐፍ እውን ያስደረጉ ስለሆነ ክብር ይገባቸዋል፡፡

 የሉዶልፍ ምርምርና ኅትመቶች ያለ ሊቁ አባ ጎርጎርዮስ ዕርዳታና ድጋፍ እውን ሊሆን አይችልም። ሉዶልፍ ስለ ኢትዮጵያ ያሉትን መጽሐፎችና ዘገባዎች በማጥናት ብቻ ሳይሆን በታዋቂው ጎታ ቤተመጻሕፍት ስብስቦች ውስጥ ያገኙትን መጽሐፎች በጥልቀት የተገነዘቡት በአባ ጎርጎርዮስ አማካይነት ነው፡፡ ጀርመኖቹም አባ ጎርጎርዮስ ከሉዶልፍ ጋር ባንድነት የሚወሱበት ምልክትም በሉዶልፍ ማዕከል ውስጥ ቢቀመጥ ጥሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጀርመኖች ለዘመናዊ መድኃኒት ቅመማ ከባህላዊው ውርስ መጠቀማቸው ይታመናል፡፡ በግእዝ፣ ከዓረቢኛ፣ ከሱርስት (ሶርያ)፣ ዕብራይስጥ ቋንቋዎች ከተጻፉ መድኃኒት ተኮር መጻሕፍት ተጠቅመዋል ይባላል፡፡ እኛስ ምን ያህል ዕፀ ደብዳቤን የመሰሉ መጻሕፍትን ተጠቅመንባቸዋል?

ፕሮፌሰር ሰብስቤ፡- በእኛ የማይታወቅ ነገር የለም፡፡ ነገሩ ግን ጥቅም ላይ እንዴት እናውለው የሚለው ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባህላዊ ዕውቀቶቻችን ተመዝግበው የሕግ ከለላ ማግኘት አለባቸው፡፡ ብዙ አገሮች ለምሳሌ ህንዶች ባህላዊ ዕውቀቶቻቸውን በመመዝገብና በመጠቀም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በእኛ የተጀመሩ ጉዳዮች አሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ባህላዊ ዕውቀታችን በደንብ ተሰንዶ መቀመጥ አለበት፡፡ ለምሳሌ የጤፍ እንጀራ አሠራር በሚል የኔዘርላንድስ ዩኒቨርሲቲና ካምፓኒ መብቱን ወስደው ተጠቅመውበታል፣ እየሸጡም ነው፡፡ ዘፋኞቻችንና አንዳንድ ነገር የሚፈጥሩም የቅጂና የፓተንት መብቶቻቸውን እያስከበሩና ባለቤትነትን እያገኙ ነው፡፡ ይህ ለባህላዊ ዕውቀትም መደረግ አለበት፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ለምሳሌ የዴንሾ ቆሎ፣ የደብረ ብርሃን ቆሎ ዕውቅናን አግኝተዋል፡፡ ይህ ጥሩ አጀማመር ነው፡፡ ባህላዊ ዕውቀቶቻችን በተመለከተ ከዕፀዋቱም ሆነ ከእንስሳቱ ጋር በተያያዘ ተመዝግበው የሕግ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እንዲያው ተነስተን በቃላችን ይኼ ይኼ ቢደረግ፣ እንዲህ ያለ ዕውቀት አለን ብንል በቂ አይመስለኝም፡፡ የሕግ ከለላ ያስፈልገዋል፡፡ ነገ አንዱ ተነስቶ ጤፍ የኔ ነው ቢል የለም ያንተ አይደለም፣ ምክንያቱም ብለን የምንቋቋምበት ከለላ ያስፈልገናል፡፡

ሪፖርተር፡- አገራዊ የሆኑ ዕፀዋትን፣ አዝርዕትን ከማስተዋወቅ አንፃር ሉዶልፍ እንደጻፈው መጽሐፍ ዓይነትም ሆነ በሌላ መንገድ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ፕሮፌሰር ሰብስቤ፡- በመረጃ ደረጃ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ25 እስከ 30 ዓመታት በፕሮጀክት የተሠሩትን የምርምር ውጤቶችን ከዓመታት በፊት በመጽሐፍ አውጥቷል፡፡ ስድስት ሺሕ ያህል ዕፀዋት እንዳሉ፣ ከእነዚህም ውስጥ 600ዎቹ አገር በቀል እንደሆኑ የሚያሳይ መሠረታዊ መረጃ አለ፡፡ የዕፀዋቱ ስም በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛና በሌሎችም ቋንቋዎች ተሰንደው ተቀምጠዋል፡፡ ሁሉም ዕፀዋት ጠቃሚ ቢሆኑም የተለዩትን ደግሞ አንጥሮ ከዚያ ውስጥ ጨምቆ አውጥቶ በጣም መጠበቅ ያለባቸውን፣ ሊጠፉ የደረሱትን ዕፀዋት እነሱን አጉልተን ኅብረተሰቡ እንዴት ይጠብቃቸው? የሚለው መታየት አለበት፡፡ ለምሳሌ በማዕከላዊውም ሆነ በምሥራቃዊው የአገራችን ክፍሎች ብቻ የሚገኙ ዕፀዋትን ለይተን አውጥተን ተማሪዎቻችንን በማስተማር እንዲንከባከቡት፣ እንዳይጠፉ የሚሆኑበትን መንገድ መፍጠር አለብን፡፡ እኔ ለፒኤችዲ የተማርኩት ስዊድን አገር ነው፡፡ መጀመሪያ እንደሄድኩ የመስክ ጉብኝት እያደረግን ሳለ አንድ የሚያምር ዕፅ አየሁና ጎንበስ አልሁ፡፡ የአስተማሪዬ ልጅ አጠገቤ ነበረች፡፡ ‹‹ይሄ እኮ የማይነካ ነው፤›› አለችኝ፡፡ ለምንድነው የማይነካው ስላት፣ ‹‹የክፍለ አገሩ መጠሪያ ዕፅ ነው›› አለችኝ፡፡ ልጅቱ የአፀደ ሕፃናት ተማሪ ናት፡፡ አንደኛ ደረጃ እንኳን አልገባችም፡፡ ልጆቹ ሲጫወቱ የዚህ ክፍለ አገር ዕፅ ነው ሲባሉ የመጠበቅ ስሜት ይፈጠርባቸዋል፡፡ ፡ በአገራችን ተመሳሳይ ነገር ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ ስለ ብዝኃ ሕይወት ተማሪዎቻችንን ከታችኛው ክፍል ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ ማስተማር አለብን፡፡ ሁሉን መጠበቅ ያስፈልጋል ግን ለምሳሌ የተወሰኑትን፣ መጠበቅ ያለባቸውን – መድኃኒት ሊሆን ይችላል፣ የሚያምር አበባ ዓደይ አበባ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲጠብቋቸው ማስገንዘብ ይኖርብናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከስምንት ዓመታት በፊት ከእንግሊዝ ሮያል ቦታኒክ ጋርደን በተሸለሙ ጊዜ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በቀጣይ ከሚሠሯቸው ምርምሮች በተጓዳኝ፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ ዕፀዋት፣ በድረ ገጽ ለማስተዋወቅ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በቅንጅት ለመሥራት ፍላጎት እንዳለዎት ገልጸው ነበር፡፡ ከምን ደረሰ?

ፕሮፌሰር ሰብስቤ፡- በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዕፀዋት አስተዳደር (ማኔጅመንት) የትምህርት ክፍል ውስጥ ብዙ ጥናቶች ይካሄዳሉ፡፡ በእኛ ክፍል ብርቅዬ ዕፀዋት የሚሆኑት አብዛኛዎቹ ተለይተዋል፡፡ ዕፀዋቱ በአገራችን ክፍል ውስጥ ምን ያህል ተጋላጭ ናቸው? የሸፈኑት ቦታስ ምን ያህል ነው? የሚለው ተጠንቷል፡፡ እንዴት በማኅበራዊ ገጽ፣ በበይነ መረብ ይገለጽ? ታትሞ እንዴት ይውጣ? የሚለውንም አሁንም እየሠራን ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ዝም ብሎ ማውጣት አይደለም፡፡ ሥርዓት ባለው ሁኔታ የሚጠቀምበት ያስፈልጋል፡፡ ሊጠቀምበት የሚፈልግ ሰው ማን ነው? ምንድነው የሚያደርገው? የሚለውን የአይሲቲ ባለሙያዎች ተካተውበት፣ ዩኒቨርሲቲው ወደፊት ኃላፊነቱን ወስዶ ያደርገዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚቀጥለው ዓመት ምናልባት ወደ ተሟላ ራስ ገዝነት ሲገባ ብዙ ነገር ያደርጋል ብለን እንገምታለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ሻሸመኔ ከተማ ማደጋቸውንና መማራቸውን፣ በአግሮ ሜካኒክስ በዲፕሎማ...

‹‹የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሥራቸውን በነፃነት ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ እንዲያከናውኑ ዋስትና የሚሰጣቸው ሕግ የለም›› አቶ አመሐ መኮንን፣ የሕግ ባለሙያና የመብት ተሟጋች

ለበርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በፍርድ ቤት በመሟገት የሚታወቁት የሕግ ባለሙያ፣ ጠበቃና የመብት ተሟጋቹ አቶ አመሐ መኮንን የፈረንሣይና  የጀርመን መንግሥታት በጋራ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የላቀ...

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም....