Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ይጠቅማሉ የተባሉ አዋጆችንና የገበያ ዕድሎችን በአግባቡ እናስተዋውቅ!

ኢትዮጵያ ለውጭ ዜጎች ዘግታቸው የነበሩ የቢዝነስ ዘርፎች እንዲከፈቱ አዋጆችንና የተለያዩ ድንጋጌዎችን አውጥታለች፡፡ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ተብለው በሕግ ተገድበው የነበሩ የቢዝነስ ዘርፎችን ሳይቀር የሚችል ይሥራው ተብሎ ለሁሉም እንዲከፈቱ ፈቅዳለች፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ዘርፎች የውጭ ኩባንያዎች በተበጣጠሰ ሁኔታም ቢሆን ገብተው እንዲሠሩ ሲፈቀድ የነበረ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አይነኬ ሲባሉ የነበሩና ከአገሬው ሌላ የውጭ ኩባንያዎች መሳተፍ እንደሚችሉባቸው ይገለጹ የነበሩ የቢዝነስ ዘርፎች አሁን ክልክላው ተነስቶላቸዋል፡፡ በቴሌኮም፣ በባንክና በመሳሰሉት ዘርፎች ላይ የውጭ ኩባንያዎች እንዲገቡ ተፈቅዷል፡፡ የካፒታል ገበያ ለመጀመር እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችም የውጭ ኩባንያዎችን ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው፡፡ ገበያው ለአገሬው ብቻ የተተወ አይደለም፡፡ 

የውጭ ኩባንያዎች እንዲገቡባቸው ከተፈቀዱ ዘርፎች ውስጥ በቴሌኮም ዘርፍ አንድም ቢሆን የኢትዮጵያን ገበያ ተቀላቅሏል፡፡ በቅርቡም በገቢና በወጪ ንግድ እንዲሁም በጅምላና በችርቻሮ ንግድ የውጭ ኩባንያዎች እንዲሳተፉበት የሚፈቅደው አዋጅም ለአገሬው ተብሎ የሚተው የቢዝነስ ሥራ እያበቃ መሆኑን ያሳያል፡፡  ከዚህ ጎን ለጎን የውጭ ኩባንያዎች ይሳተፉበታል የተባለው የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅም ቢሆን ከዚህ ቀደም የነበሩ ክልከላዎችን በማንሳት በነፃ የገበያ ሥርዓት አገልግሎት እንዲሰጥ ተፈቅዷል፡፡ 

የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንቶች ላይ ተሳትፏቸው እንዲጎላ ያስችላሉ የተባሉ የተለያዩ አዳዲስ ድንጋጌዎች በልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅ ውስጥ እንዲካተት መደረጉ በራሱ ትልቅ የለውጥ ሒደት ነው፡፡ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ ተብለው የታመነባቸው እነዚህ አዳዲስ ሕግጋት ጨከን ተብሎባቸው እንዲወጡና እንዲተገበሩ የተፈለገበት ዋነኛውና አንዱ ምክንያት የአገሪቱን ኢኮኖሚን ለመደገፍ ነው፡፡ 

በነፃ ገበያ ተወዳዳሪዎችን በማብዛት በዚያ ውድድር ሸማችና ተገልጋይ በተሻለ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በመታመኑ የተወሰደ ዕርምጃ ተደርጎ ሊወሰድም ይችላል፣ ደግም ነው፡፡ የውጭ ኩባንያዎችን በሚጋብዙት በእያንዳንዱ አዋጅና መመርያዎች መግቢያ ላይ የውጭ ኩባንያዎች በተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች ላይ መሳተፋቸው አስፈላጊነትን በተመለከቱ በዝርዝር የቀረበው ማብራሪያም ይህንን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ለምሳሌ የጅምላና የችርቻሮ ንግድ ውስጥ የውጭ ኩባንያዎች ይግቡ ሲባል ገበያን ለማረጋጋት ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ 

በተለይ የዘፈቀደ የትርፍ ሕዳግ በማስቀመጥ የሚታየውን ያልተገባ ተግባር ለማከምና አጠቃላይ የኢትዮጵያን የግብይት ሥርዓት መስመር ለማስያዝ በዚህ ቢዝነስ የውጭ ኩባንያዎችን ማስገባት አንድ አማራጭ ነው፡፡ የውጭ የፋይናንስ ተቋማትም እንዲገቡ የተዘጋባቸው በር ይከፈት ሲባል የሚፈጠረው ውድድር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተገልጋዩ የተሻለ ተጠቃሚ ስለሚያደርገው ነው፡፡  

ለዚህ ደግሞ በቴሌኮም ዘርፍ የውጭ ኩባንያዎች እንዲገቡ መፈቀዱ ኢትዮ ቴሌኮም በገበያው አሸናፊ ለመሆን ያሳየው ጠንካራ ትጋት የተገልጋዩን ምን ያህል እንደተጠቀመ መጥቀስ ብቻ በቂ ነው፡፡ ስለዚህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወጡ ሕግጋት ውድድር ያለበት ገበያን በመፍጠር ሸማችና ተገልጋዩን የተሻለ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል የሚለውን እምነት ያጠናክራል፡፡ ያለ ጠንካራ ተወዳዳሪ ለዘመናት የዘለቁ አገር በቀል ኩባንያዎቻችንም ቢሆን ጠንከር ያለ ውድድር እንዲመጣባቸው ስለሚረዱ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ እንዲተጉ ያበረታቸዋል፡፡ ለዚህም አሁንም ኢትዮ ቴሌኮም ምሳሌ ነው፡፡ እየወጡ ያሉ ሕጎች እውነተኛ ፉክክር በመጣ ቁጥር ለአገራችን ኩባንያዎች እንዲጠነክሩ የማድረግ መልካም ዕድል ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ 

በአጭሩ እነዚህ ድንጋጌዎች የሚሰጡት ጠቀሜታ ከፍ ብሎ ይታያል፡፡ እውነታው ይህ ከሆነ የእነዚህ ድንጋጌዎች አስፈላጊነታቸው ታምኖ፣ እዚህ ደረጃ እንዲደርሱ የመደረጉን ያህል ለተግባራዊነታቸው ካልተሠራ ግን ትርጉም አይኖራቸውም፡፡

አዋጆቹን ማውጣት ብቻ ስኬት አይደለም፣ ወይም የሚፈለገውን ግብ አይመታም፡፡ የውጭ ኩባንያዎች በተለያዩ ቢዝነሶች ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ ተገቢ መሆኑን አምኖ ሕግ ማውጣት እስከተቻለ ድረስ፣ ይህንን ብዙ የተባለለትን ጉዳይ በተጨባጭ መሬት ላይ ማዋል ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ውሳኔ ላይ የደረሰችባቸውን አዳዲስ አሠራሮችና ሕጎች በሚገባ ማስተዋወቅ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ እንዲህ ያለ ጠቃሚ ሕግ ስለማውጣቷ እነማን አውቀውልናል? አሁን ላይ መሠረታዊ ጥያቄ መሆን ያለበት ይህ ነው፡፡ አዋጁ የሚመለከታቸውን የውጭ ኩባንያዎች በማፈላለግ መረጃውን መስጠትና የማግባባት ሥራ ካልተሠራ የመመርያና የአዋጆች ተከታትሎ መውጣት ግብ አይሆንም፡፡  

በኢትዮጵያ የቢዝነስ ሥራ ውስጥ ሥር ነቀል የሚባል ለውጥ ስለመደረጉ የሚያመለክቱት እነዚህ ድንጋጌዎች ይዘት የውጭ ኩባንያዎችን ለመሳብ የሚችሉ በመሆኑ፣ በቀላሉ ሊገዙት የሚችሉት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ዕውን የሚሆነው ግን ኢትዮጵያ በእነዚህ ቢዝነሶች የውጭ ኩባንያዎች እንዲሠሩ ስለመፍቀዷና እነሱም ከመጡ የሚደረግላቸው ድጋፍ ሁሉ በየአገሩ በግንባር ጭምር በመሄድ ሕጎቻችንን ስንሸጥ ነው፡፡

ቢያንስ ኤምባሲዎቻችን በያሉበት አገር ይህንን የማድረግ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን በግዴታም ሊሠሩበት የሚገባ ቀዳሚ አጀንዳቸው ሊሆን ይገባል፡፡ በየቢዝነስ ዘርፉ አንቱ ለተባሉ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያለውን መልካም ዕድል አስተዋውቀው የምንፈልጋቸውን የውጭ ኩባንያዎች እንዲመጡ ካላደረጉ አዋጅና መመርያ በመውጣታቸው ብቻ ተንደርድሮ የሚመጣ እንደማይኖር ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ቀርቶ እዚህ ካሉ ኤምባሲዎቻችን የውጭ ኩባያዎችን ስለሚጋብዙ ስለድንጋጌዎቻችንን ምን ሠርተዋል? በአጠቃላይ  ከልምድ እንደምንረዳው ከኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግሮች መካከል አንዱ አገርን በሚገባ አለማስተዋወቅ ስለሆነ አሁንም ይህ ችግር እየተስተዋለ ስለመሆኑ ያስገንዝበናል፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን መልካም ዕድል በቀጥታ ለሚመለከተው አካል የመግለጽ ችግራችን አልተፈተሸም፡፡

በእጃችን ያሉ የቱሪዝምም ሆነ የወጪ ንግድ ምርቶቻችንን በአግባቡ አስተዋውቆ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል የተደራጀና የተናበበ የማስተዋወቅ ልምድ የለም፡፡ ይህ የኢትዮጵያ የዘመናት ችግር ነው፡፡ አሁን የውጭ ኩባንያዎችን እንዲገቡ የሚፈቅዱ ሕጎቻችንንም በአግባቡ ካላስተዋወቅን ተመሳሳይ ችግር ይገጥመናል ብለን የምንሠጋው ለዚህ ነው፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች ተከትሎ ይገኛሉ የተባሉ ጥቅሞች ሊገኙ የሚችሉት እነዚህን ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ በአግባቡ መሸጥ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ 

ከዚህ አንፃር ያለው ክፍተት ብዙ ነገር እያሳጣንም ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተገነቡ ያሉ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች የተሠሩት ለእኛ ብቻ አይደለም፡፡ አዎ ያማምራሉ ደረጃቸውንም የጠበቁ ናቸው፡፡ እነዚህን የሚያማምሩ ሥራዎች ሌሎች መጥተው እንዲጎበኙልን ካላደረግን ጥቅም የላቸውም፡፡ ሌሎች ሊጎበኙ የሚችሉት ሀብቶቻችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ የምናስተዋውቅበትን መንገድ ማበጀት ግድ ይላል፡፡ የውጭ ቸርቻሪዎችን እንዲገቡ የፈቀድነው ዋጋ እንዲያረጋጉ ከሆነና ይህ ጥቅም እንዳለው ካመንን፣ ኩባንያዎቹ የሚመጡት ደጃፋቸው ድረስ ተሄዶ በር በማንኳኳትና ዕድሉ የጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስለመሆኑ ስንገልጽ ነው፡፡  

የቱሪስት ቦታ የምንገነባው ለኢኮኖሚ ዕድገት ከሆነ እንደ አገር ራሳችንን የምንሸጥበት መንገድ ከሌለና ስለመዳረሻዎቹ በቂ ግንዛቤ ካልተሰጠ ነገሩ ሁሉ ‹‹አለን›› ከማለት ውጪ ገንዘብ ሊሆኑን እንደማይችሉ መተማመን ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በሁሉም ዘርፍ ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ ራሱን የቻለ ፖሊሲና ተቋም ያስፈልጋል፡፡ 

ዛሬ እኮ ከኋላችን በብዙ ርቀት ላይ የነበሩ እንደ ሩዋንዳ ያሉ አገሮች በአጭር ጊዜ ከተሞቻቸውን አሰማምረው ዓለም እንዲጎበኛቸው እያደረጉ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በተጠና መልኩ ለዓለም ራሳቸውን ለማስተዋወቅ እየተጠቀሙበት ያለው ዘዴ ጠቅሟቸዋል፡፡ በዓለም ላይ የቢሊዮኖች ዓይኖች የሚያርፍባቸው የእግር ኳስ ጨዋታዎች በሚካሄዱባቸው ትልልቅ ስታዲዮሞች ውስጥ ሳይቀር ራሳቸውን እያስተዋወቁ ነው፡፡ ኑና ጎብኙን እያሉ ነው፡፡ ይህ ዕርምጃቸው ዶላርን እያመጣላቸው ነው፡፡ እኛም ራሳችንን የምናስተዋውቅበት አዲስ ዘዴ ያስፈልገናል፡፡ ይጠቅማሉ የተባሉ አዋጆችንና የገበያ ዕድሎችን በአግባቡ እናስተዋውቅ፡፡ የምንገነባቸው ለጎብኚዎች የተመቻቹ ሥፍራዎቻችንን በአግባቡ እንሽጥ፡፡ ገበያ ያረጋጋሉ የተባሉ ብዙ የተደከመባቸው አዋጆቻችንም ተተግብረው ለአገርም ለሸማችም ድጋፍ የሚሆኑት ራሳችንን በአግባቡ ስንገልጽና ስንሸጥ ነው፡፡. 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት