Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአገር ውስጥ ቱሪዝም ለአገራዊ መግባባት ምኑ ነው?

የአገር ውስጥ ቱሪዝም ለአገራዊ መግባባት ምኑ ነው?

ቀን:

ኢትዮጵያ ካለፉት ዓመታት ወዲህ እያስተናገደች ያለው ግጭት የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንዲቀንስ አድርጓል፡፡ በተለይ ቀድሞውንም እምብዛም ያልተሠራበትና ትኩረት ያላገኘው የአገር ውስጥ ቱሪዝም እዲመናመን ምክንያት ሆኗል፡፡

የአገር ውስጥ ቱሪዝም ለአገራዊ መግባባት ምኑ ነው? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ቱሪዝም ለአገራዊ መግባባት በሚል የፓናል ውይይት ሲካሄድ (የቱሪዝም
ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት)

የአገር ውስጥ ቱሪዝም መጠናከርና መስፋፋት በአንድ አገር እየኖሩ በወንዝ፣ በቀዬ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በባህልና በልማድ ራሳቸውን አውቀው የሌላውን የማያውቁትን ለማስተሳሰር፣ ለማስተዋወቅ፣ ለማግባት ዓይነተኛ መንገድ ቢሆንም፣ እምብዛም አልተሠራበትም፡፡

የቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ከሰኔ 4 እስከ 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ለ11ኛ ጊዜ ጭብጡን ‹‹ቱሪዝም ለአገራዊ መግባባት›› አድርጎ ባከናወነው የክህሎትና የመስተንግዶ ሳምንት ማጠቃለያ በተዘጋጀ የፓናል ውይይት የተገለጸውም፣ የአገር ውስጥ ቱሪዝም ኢትዮጵያውያን በየአካባቢያቸው ያላቸውን እሴት እርስ በርስ ለማስተዋወቅ ቢያስችልም፣ በዘርፉ አለመሠራቱ ነው፡፡

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ይታሰብ ሥዩም እንደሚሉትም፣ ኢትዮጵያውያን ያሏቸውን በርካታ መገለጫዎች የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ተጠቅሞ በሕዝብ መካከል ትስስርና ይበልጥ መተዋወቅ እንዲፈጠር መሠራት አለበት፡፡

ለዚህ ደግሞ ሰላም ያስፈልጋል ያሉት አቶ ይታሰብ፣ አገር ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ገብቶ 11ኛው የክህሎትና የመስተንግዶ ሳምንት ጭብጥ ‹‹ቱሪዝም ለአገራዊ መግባባት›› የሚል እንዲሆን መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

ችግሩ ዛሬ የተከሰተ ባይሆንም የተረጋጋ ሰላም አጥተናል ያሉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ በበኩላቸው፣ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ለአገራዊ መግባባት ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል፡፡

ቱሪዝም ለአገራዊ መግባባት ያለው ፋይዳ ምንድነው? በሚል በተደረገው ውይይት የተሳተፉት የቱሪዝም ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች አማካሪ ጌታነህ አዲስ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ በዘመናት ያፈራቻቸውን እሴቶች መጠቀም ያልተቻለው በየጊዜው በሚፈጠሩ ፖለቲካዊ አለመግባባቶች ነው፡፡ ይህ እሴቶችን ለመግባቢያነት እንዳንጠቀምባቸው፣ ለጥቅም እንዳይውሉ አድርጓል፡፡

እንደ ማስጎብኘት ሥራ ላይ የተሰማሩት የቱሪዝም ባለሙያ አቶ ዳንኤል ተስፋዬ ደግሞ፣ ቱሪዝምን ለአገራዊ መግባባት እንዳንጠቀምበት ያደረገን ስለአገራችንና ራሳችን አለማወቃችን ነው፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ብዙ መስኮቶች ያሏትና ታይታ የማትጨረስ ናት›› ያሉት ባለሙያው፣ የሌላው ባህል የራሳችን እንደሆነ አለማወቅ፣ የመሬት አቀማመጣችን በወንዞች፣ በስምጥ ሸለቆና በሌሎችም የተከፋፈለ መሆኑ ኅብረተሰቡ እርስ በርሱ እንዳይተዋወቅ ማድረጉ፣ ቅኝ ባንገዛም ያጋጠሙን ታሪካዊ ክስተቶችና የአስተዳደር መዋቅራችን ሰዎች የሁሉም ባህልና ታሪክ ባህሌና ታሪኬ ነው ብለው እንዳይቀበሉ አድርጓል ብለዋል፡፡

‹‹ዜጎች የማያውቁትን አገር አይለውጡም›› ሲል አስተያየት የሰጠው ተጓዡ ጋዜጠኛ ሔኖክ ሥዩም፣ ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ሕዝብ፣ ባህል፣ አኗኗርና እሴት ካወቁ ይግባባሉ፣ አገራቸውን ይቀይራሉ፣ ለዚህ ደግሞ የአገር ውስጥ ቱሪዝም ለአገራዊ መግባባት ያግዛል ብሏል፡፡

በኢትዮጵያ አለመግባባት ያለው በሕዝቡ ውስጥ ሳይሆን በፖለቲከኞች ዘንድ ነው፣ ስለሆነም ከላይ ጀምሮ ያሉ ፖለቲከኞች አገራቸውን፣ ሕዝባቸውን፣ ባህላቸውንና እሴቶቻቸውን በደንብ ይጎብኙ፣ ይወቁ ይህ ሲሆን አንዱ ያንዱን መቀበልና መግባባት ይችላል የሚል አስተያየት ከመድረኩ ተነስቷል፡፡

ለዚህ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ማስፋፋትና ማጠናከር፣ በአብዛኛው በውጭ ቱሪስቶች ላይ ትኩረት የሚሰጡ የዘርፉ ተቋማትና ባለሙያዎች የአገር ውስጥ ቱሪዝም ፓኬጅ እንዲያዘጋጁ ከመድረክ አስተያየት ተሰጥቷል፡፡

ሕዝቡ የአገሩን እምቅ ያልተነካ የቱሪዝም ሀብት፣ የሰውን አኗኗርና ባህልና እሴት እያወቀና እየተረዳ በሄደ ቁጥር፣ ችግርና ሥጋት የሚመስሉ ነገሮች ሁሉ እየተቀረፉ እንደሚሄዱ፣ ለዚህ ግን በዘርፉ የተሰማሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት መሥራት እንደሚገባቸውም አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡

የአገር ውስጥ ቱሪዝም ኢኮኖሚውን ከማገዝ ባለፈ ለሰላምና ለመግባባት ያግዛል ያሉት ጌታነህ (ዶ/ር)፣ ሚኒስቴራቸው ከ2015 ዓ.ም. እስከ 2019 ዓ.ም. የሚቆይ የአገር ውስጥ ቱሪዝም ትራቴጂ መቅረፁን፣ ሆኖም፣ ባለው ሁኔታ ምክንያት ወደ ሥራ እንዳልተገባ ገልጸዋል፡፡

ስትራቴጂው ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን እንዲያውቁ፣ እርስ በርስ እንዲግባቡ በአገር ውስጥ ቱሪዝም በኩል ያሉ ክፍተቶች እንዲሞሉ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

spot_img
Previous article
Next article
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...